እስኪ የዛሬውን ወጋችንን ብዙ በተደመጠ ቀልድ እንጀምረው፡፡ አንዲት ተማሪ ለፈተና ተቀምጣለች፡፡ ጥያቄዎቹን አየቻቸው ‹እውነት› ወይም ‹ሐሰት› ነው መልሳቸው፡፡ ምንም ባለማጥናቷ የቱ እውነት፣ የቱ ሐሰት እንደሆነ አታውቅም፡፡ የመጣላት አማራጭ ሳንቲም ከኪሷ አውጥታ ‹አንበሳ› ሲሆን ‹እውነት›፣ ተቃራኒ ሲሆን ደግሞ ‹ሐሰት› እያለች መመለስ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ፈተናዋን ሰርታ ስትጨርስ በጣም ብዙ ጊዜ ተረፋት ስለዚህ የሰራችው ትክክል መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ፈለገች፡፡ ግን ደግሞ ማረጋገጫ መንገድ የላትም፤ ስለዚህ በጀመረችው መንገድ እንደገና ሳንቲም እየወረወረች አንበሳን ለእውነት፣ ጀርባውን ለሐሰት እየመደበች መልሷን ታረጋግጥ ጀመር፡፡
በእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ውስጥ ሁለት መልስ ብቻ በመኖሩ፥ ያለሳንቲምም ቢሆን ሞክሮ መሳሳት፣ ሞክሮ ለመማር ነው፡፡ (በፈረንጅ አፍ Trial and Error Learning ይባላል፡፡ በአማርኛ ልተረጉመው ፈልጌ ነበር፤ ከበደኝ እንጂ! ‹ሞክሮ በመሳሳት መማር› ብለው ትክክል ነው እንዴ?) ግን ደግሞ በሕይወት ዓለም እልፍ መንገዶች አሉ፤ የትኛው መጨረሻው እንደሚያምር ለማወቅ ወይ በሁሉም መንገዶች ተራ፣ በተራ መሄድ አሊያም [ወደኋላ የምንመካከርበትን ጉዳይ ማድረግ] ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም መንገዶች እየሄድን መጨረሻቸውን እንይ እንዳንል ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ አንዱ፡- ለሙከራ የጀመርነው መንገድ መጨረሻው ባያምርስ? እሺ፡- መጨረሻው ሰላም ሆኖ መድረሻውን ስላልወደድነው ብቻ መመለስ ብንፈልግ የምንመለሰው እንዴት ነው? ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ሁሉንም መንገዶች ለመሞከሪያ በቂ ጊዜ የለንም፤ ሕይወት አጭር ናት፡፡
ዓላማቸው ግልጽ ባልሆነ የሐሳብ ድሪቶዎች ይህንን ያህል ካደከምኳችሁ ይበቃል፡፡ የዚህን ጽሁፍ ዓላማ ለማብራራት ግን አሁንም አንድ አንቀፅ ያስፈልገኛል፡፡ ከሰው ጋር ተግባብቶ ለመኖር እየሞከሩ፣ መሳሳት፤ እየተሳሳቱ፣ መማር ይቻል ይሆናል፡፡ በሰዎች ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ግን እየሞከሩ መሳሳት፣ እየተሳሳቱ መታረም አይቻልም፡፡ ዕጣ ፈንታ መዳረሻ በመሆኑ ማጣፊያ (undo) የለውም፡፡ በሃገራችን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ መመሪያዎች እና ውጤታቸው ግራ ቢያጋቡኝ ይህንን መጻፍ ጀመርኩ፡፡