Pages

Friday, September 30, 2011

የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ለተቃዋሚዎች


መጀመሪያ ጭብጨባ

አንድነት ፓርቲ በቅርቡ ተቃዋሚዎች/የተቃዋሚ ደጋፊዎች በቂ የመረጃ ምንጭ የላቸውም በማለት በየሣምንቱ ማክሰኞ፣ በ5 ብር ገበያ ላይ የምትውል ‹‹ፍኖተ ነፃነት›› የተሰኘች ጋዜጣ ማሳተም ጀምሯል፡፡ አንዱአለም አራጌ ሲናገር እንደሰማሁት ‹‹በጋዜጣዋ ላይ የኢሕአዴግ ደጋፊና አባላትም ቢሆኑ መጻፍ ይፈቀድላቸዋል፤ አንድነት እንደ ኢሕአዴግ የመናገር ነፃነትን የማፈን ፍላጎት የለውም፡፡››

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው በየሣምንቱ እሁድ ማለዳ በተጋባዥ ምሁራን ጽሁፍ አቅራቢነትና በተሳታፊዎች መካከል የሚካሔድ የውይይት ፕሮግራም ጀምሮ ነበር፡፡ (የእነ አቶ አንዱአለም በ‹‹አሸባሪነት›› ተጠርጥሮ መታሰር ይህንን ጠቃሚ ልምድ እስከወዲያኛው ያስቀረው ይሆን?)

በሌላ በኩል (የኔ favorite ባይሆንም እንኳን) ኢዴፓ የዓለም ሊበራል ፓርቲዎችን ጉባኤ በ2004ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያካሒድ ጎንበስ ቀና እያለ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው፡፡ እንዲህ ሰበብ እየፈለግን የምናቆለጳጵሳቸው ተቃዋሚዎች ግን በደመስማሳው ስንመለከታቸው መንግስት አንድ ውሳኔ ባሳለፈ ቁጥር የፕሮፓጋንዳ መግለጫ ከመስጠት ባሻገር (ያውም ከሰጡ) ባለፈው ምርጫ ካየናቸው በኋላ የት እንደገቡ ጠፍተዋል፡፡


ተቃዋሚዎች እና “ተቃዋሚዎች”
የተቃዋሚዎችን ትክክለኛ ቁጥር እንኳን እኔ የምርጫ ቦርድ ራሱ የሚያውቀው አይመስለኝም ነበር፡፡ ሆኖም የምርጫ ቦርድ ድረዓምባ (ከተጻፈ ቢሰነብትም) በሃገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 79 ፓርቲዎችን እንደመዘገበ ነግሮናል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በሁለት ይከፈላሉ፤ ተቃዋሚዎች እና “ተቃዋሚዎች” ተብለው፡፡ ነገር ቶሎ ለማይገባችሁ ሰዎች፤ “ተቃዋሚዎች” የሚባሉት እነሱ ተቃዋሚዎች ነን ስላሉ እና ምርጫ ቦርድም ፓርቲ ናቸው ብሎ ስለመዘገባቸው ነው፡፡

“ተቃዋሚዎች” የምርጫ ሰሞን ብቻ አለሁ የሚሉና በእኔ እምነት የተለየ አላማ ያላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ገዢው ፓርቲ የተቃዋሚዎችን ድምጽ በመበታተን ለማሳነስ የሚፈጥራቸው ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ በቤተሰብ እና በአካባቢያቸው ሙገሳ የሃገር መሪ የመሆን ምኞት ያደረባቸው ግለሰቦች የፈጠሯቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡

ደግነቱ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አጀንዳ “ተቃዋሚዎች” ሳይሆኑ ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን ከዚያ በፊት Naming and Shaming የሚገባቸው የተቃዋሚ መሪ አሉ፡፡

Naming and Shaming
መኢብን ሲባል ሰምታችሁ ታውቁ ይሆናል፡፡ መላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚባለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡ መሪው አቶ መሳፍንት ሽፈራው ይባላሉ፡፡ ሰውየውን በፊት የምታውቋቸው ሰዎች ካላችሁ አቶ መስፍን ሽፈራሁ ነበር ስማቸው፡፡ አንዴ ለአውራምባ ታይምስ በሰጡት ቃለ ምልልስ አንድ መስፍን ሽፈራሁ የተባለ ሰውዬ በታክስ ማጭበርበር ስሙ በቴሌቪዥን ስለተጠራ ደጋፊዎቻቸው ግራ እንዳይጋቡ ሲሉ ስማቸውን እንደቀየሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ መሳፍንትን ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ደጋግሞ የሚንቀሳቀስ ሰው አያጣቸውም፡፡ እኔም ደጋግሜ አገኛቸዋለሁ፡፡ አንድ ቀን ግን ያገኘሁዋቸውን ዓይነት አገኛኘት ባላገኛቸው ይሻለኝ ነበር፡፡ እኔ ከቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ወደ አራትኪሎ ስወርድ እሳቸው እያሻቀቡ ተገጣጠምን፡፡ ማለዳ ነበር፤ እርሳቸው ደግሞ የስፖርት ትጥቅ የሚመስል ታጥቀዋል፡፡ ጥድፍ፣ ጥድፍ እያሉ የነበረ ቢሆንም ለስፖርት አልነበረም፡፡ ከፊታቸው ያለች አንዲት በእሳቸው ዕድሜ ክልል ያለችን ሴት ‹‹እየለከፉ›› ነበር፡፡ ዓይኔን ተጠራጥሬው ቆም አልኩ፡፡ ሁኔታቸው አረጋገጠልኝ፡፡ ሴቲቷ ጥላቸው ወደ ቤተክርስቲያኑ ስትገባ እርሳቸው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ (አሁን ይሄ በስም አጥፊነት ያስከስሰኝ ይሆን? ለኢሕአዴግማ ጥሩ ሰበብ ነው፡፡)

ከሰሞኑ ከወጡ ጋዜጦች አንዱ ደግሞ የሚያስደምም ርዕስ ይዞ ነበር፡፡ “ተቃዋሚዎች” እና ኢሕአዴግ በአንድ መድረክ ሊመክሩ ሲያውጠነጥኑ መክረማቸው ይታወቃል፡፡ ታዲያ ጋዜጣው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ መኢብን ፕሮግራሙን እንዳላቀረበ ተናግሯል፡፡ በርዕሱ መኢብን ከኢሕአዴግ ጋር ተመሳሳይ ፕሮግራም ስላለው አጀንዳ አልያስያዘም ብሎን እርፍ፡፡ ታዲያ መኢብን የተለየ ፕሮግራም ከሌለው ለምን የኢሕአዴግ አባል አይሆንም፡፡ ኢሕአዴግ እስካሁን ብሔር ተኮር ፓርቲዎችን ያሰባሰበ ፓርቲ አይደል? ምናለ ታዲያ ሕብረብሔራዊ የሆነውን መኢብንንም ቢያቅፈው?

ይሄ ዜና ግን አንድ ነገር ሳያስታውሰኝ አላለፈም፡፡ የመኢብን ሊቀመንበር፣ አቶ መሳፍንት በምርጫ 97 በግል ተወዳድረው ነበር (አዲስ አበባ፤ ወረዳ 12/13) ምን ዋጋ አለው ያኔ ያዲሳባ ሕዝብ ቀልቡ ከቅንጅት ጋር ሸፍቶ ስለነበር ያስታወሳቸው የለም፡፡ ነገር ግን ያኔም ቢሆን ኢሕአዴግ በጣት የሚቆጠሩ ታማኞች ነበሩት፡፡ ከታማኞቹ መካከል አንድ እኔ የማውቀውን የኢሕአዴግ ታማኝ፣ ገና ምርጫ 97 በተጠናቀቀ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቶ መሳፍንት ፓርቲያቸውን ሲመሰርቱ አባል ያስፈልጋቸው ስለነበር ለመኢብን መፈረሙን ነግሮኛል፡፡ አሁን ሲገባኝ እሱም የፈረመላቸው ለካ በፕሮግራማቸው መካከል ያለውን መመሳሰል አገናዝቦ ነበር?

ይህንን ርዕስ የተዋስኩት የፍትህ ጋዜጣው ተመስገን ደሳለኝ በነሐሴ 20፤ 2003ዓ.ም. እትሙ ‹‹ፓርቲዎቹ [ተቃዋሚዎች] በህዝብ ዘንድ ካላቸው ታዋቂነት ይልቅ አመራሮቹ (በተለይ ሊቃነመናብርቱ) ያላቸው ታዋቂነት በብዙ እጥፍ በልጦ መገኘቱ››ን ከአተተበት ጽሁፉ ነው፡፡ አባባሉ ትክክል የሚሆነው በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ገንነው የወጡትን ፖለቲከኞች አመለካከት ከፓርቲያቸው ፕሮግራም የበለጠ የምናውቃቸው በመሆኑ ነው፡፡

አቶ ልደቱ ቅንጅትን በማተራመስና በቁርጥ ቀናት (ምርጫ ሲመጣ) ኢሕአዴግን በማሞካሸት እናውቃቸዋለን፡፡ ሆኖም ፓርቲያቸው ፕሮግራሙ ምን እንደሆነ የምናውቅ ሰዎች መኖራችን አጠራጣሪ ነው፡፡ እነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል፣ እነ ዶ/ር መረራ፣ እነ ፕ/ር በየነ ከፓርቲያቸው ይልቅ የራሳቸውን ስምና ዝና ገንብተዋል ነው የሚለን ተመስገን፡፡

እኔ ደግሞ እላለሁ፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሶሻሊስት ናቸው፡፡ ከኢሕአዴግ ፈንቅሎ ያስወጣቸውም ሶሻሊዝምን በነጭ ካፒታሊዝም ለመተካት የማሰቡ ነገር ነው፡፡ አሁን የት ናቸው? የካፒታሊዝም አቀንቃኝ የሆነው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 39 ‹‹በመርሕ ደረጃ›› ይቀበላሉ፤ ፓርቲው ይቃወመዋል፣ መሬት የመንግስት መሆኑን ይቀበላሉ፣ ይህንንም ፓርቲው ይቃወመዋል፡፡ እነዚህን ዐቢይ ልዩነቶች እንዴት አቻቻሉት?

በርግጥ ፓርቲዎች በአስተሳሰብ አንድ የሆኑ ሮቦቶች ስብስብ እንዲሆኑ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን እንታገልለታለን የሚሉት ዐቢይ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች ካቀፉ ሕልውናቸው አጠራጣሪ ነው፡፡

ከዚህም በላይ ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ ግን ሌላ ምክንያት አለ፡፡ ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ተቃዋሚዎች ለመቃወም ከመቃወም ሌላ ምን አጀንዳ አላቸው?

የአማራጭ ነገር
‹‹መንግስት ነጋዴውን እያዋከበ ነው፣ ነጋዴውን ከሕብረተሰቡ ጋር ለማጣላት ፈልጎ ነው፡፡›› እያሉ ሲነግሩን የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠርና የአቅርቦቱን ነገር ለማሻሻል ምን መደረግ አለበት እያሉ ነው? የታክስ አሰባሰቡ ስርአት የተበላሸ እንደሆነ ሲነግሩን ነጋዴው ታክስ መክፈል የለበትም፣ ዝቅተኛ ነው መክፈል ያለበት፣ የሚያጭበረብር ነጋዴ የለም እያሉ ነው ወይስ ምን? በሌሎችም ዐብይ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲቃወሙ አማራጫቸው ምን እንደሆነ ለምን አይነግሩንም? ነው ወይስ ኢሕአዴግ ፕሮግራሜን ይሰርቀኛል የሚል ‹የኮፒ ራይት› ስጋት አለባቸው?

በእኔ እይታ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ተማርሯል፣ የገጠሩ ሕዝብ በረሃብ ከተሜውም በኑሮ ውድነት ውሎ ማደርን እንደስኬት እየቆጠረው ነው፡፡ በኢሕዴግ ለውጥ ያላመጣ የሩብ ምዕተ ዓመት የስልጣን ጉዞ ተሰላችቷል፣ በነፃነት እጦትና በፍርሃት ተወጥሯል፣ በአድሎአዊ አስተዳደር ውስጡ በግኗል፡፡ ግን ደፍሮ አይናገርም፡፡ ስለዚህ ደፍረው የሚናገሩትን ተቃዋሚዎች በትክክለኛው መንገድ ባይናገሩለትም ያወድሳቸዋል - የብሶቱ ተጋሪ ስለሚመስሉት ብቻ ይመርጣቸዋል፡፡ ከበጣም ክፉ ክፉ ይሻለኛል ዓይነት፡፡ ስለዚህ ተበዳዩ ሕዝብ በድፍረታቸው ተደንቆ የተቀበላቸው ተቃዋሚዎች በሙሉ እኛ ነን ለሕዝቡ የምናስፈልገው የሚል ትምክህት ላይ እንዳይደርሱ እፈራለሁ፡፡ መጀመሪያ እጃቸው ከምን? በኢሕአዴግ የተማረርንባቸውን ነገሮች እንዴት እንደሚቀርፉ አሁኑኑ ይንገሩን፡፡

የቁጥር ጫወታ
ኢሕአዴግ የፖለቲካ ምሕዳሩን አጥብቦታል፡፡ የፖለቲካ ምሕዳሩን ማጥበቡ የተጫዋጮችን ቁጥር ይቀንሰዋል ወይ ስንል ‹‹አይሆንም›› ነው መልሱ፡፡ አሁንም ሰዉ በልቡ ተቃዋሚ ነው፡፡ ችግሩ ተሰባስቦ የሚያሰባስብ ቁርጠኛ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ነው ወይስ አሁንም ተቃዋሚዎች የአባላት ቁጥርን የማሳደግ ፋይዳ አልተገለጸላቸውም? ተቃዋሚዎች የአባላት ቁጥር ለማሳደግ የሚያደርጉት ምንም ጥረት የለም፡፡ እንዲያውም አሁን፣ አሁን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ቁጥር ይልቅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር የሚበዛ ይመስለኛል፡፡

የሕብረት ጫወታ
በነገራችን ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቁጥር ብዙ ያደረገው ተቀራርበው መነጋገር አለመቻላቸው፣ ሁሉም የፓርቲዎቹ መስራቾች መሪ መሆን ስለሚፈልጉ እና የተቃውሞ አባዜ ስለተጠናወታቸው እንጂ ፕሮግራማቸውን ቢናበቡ በአብዛኛው ልዩነት የለውም፡፡ በመድረክ ስር የተጠለሉትን ብሔር ተኮር እና ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ስንመለከት እውነታውን ማረጋገጥ አንችላለን፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ሕብረት መፍጠር በመቻላቸው ያለምን ዝግጅት፣ ምሕዳሩ በጣም በጠበበት የምርጫ 2002 ወቅት የተሻለ ድምጽ ማግኘት ችለው ነበር፡፡

ለዚህ ነው እነዚህን ቅሬታዎቻቸንን የሚያሟሉ ተቃዋሚዎች ለማግኘት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ማውጣት የሚያስፈልገው፡፡

እናም ይህችን እስከ ቀጣዩ ምርጫ መዳረሻ ያለችውን ጊዜ ተቃዋሚዎች የአባላቶቻቸውን ቁጥር በማሳደግ እና እርስ በእርሳቸውም በመዋሃድ ትልቅ የተቃዋሚ ስብስብ መፍጠር ይችሉ ነበር፡፡ ከዚያም ኢሕአዴግ አጠበብኩት የሚለውን ምሕዳር ጥቅጥቅ ብለንበት፣ የማጭበርበሪያ መንገድ አሳጥተነው፣ ያለሁካታ ምርጫችንን እናሸንፍ ነበር፡፡ ያሸነፍነውን አልሰጣችሁም ካለን ያኔ ነፍጣችንን አንግተን ጫካ ለመግባት ከአሁን የተሻለ ምክንያት አገኘን ማለት አይደለም? ችግሩ ይሄንን መጣጥፍ ማን ወስዶ ለተቃዋሚዎች ይሰጥልኛል?

No comments:

Post a Comment