ጎበዝ! ወሩ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን ጉዳይ ካምናው የተሻለ የሚያሰኘው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ከሰሞኑ ሮይተርስ የኢትዮጵያ ስታትስተክስ ኤጀንሲን ጠቅሶ ያስነበበን ዜና እንደሚነግረን ከሆነ የገንዘብ ውድቀቱ ከአምናው ነሐሴ ጋር ሲነፃፀር ባለፈው ወር 40.6 በመቶ አሻቅቧል፡፡ ማለትም የዘንድሮ መቶ ብር መግዛት የሚችለው የአምናው 60 ብር መግዛት የሚችለውን ያክል ብቻ ነው፡፡ ገንዘብን ባንክ በማጠራቀም 40በመቶ ማትረፍ አይቻልም፤ በመነገድም ይህን ያህል ትርፍ ማግኘት ይቻል እንደሆነ እጠራጠራለሁ፡፡ ስለዚህ በደሞዝ ጭማሪ መርካት አይቻልም፤ ጊዜው ራስን የማዳን ነው፡፡ መንግስት ያተመውን ገንዘብ በቦንድ ግዢም አለ በሌላ ሰብስቦ ሊጨርሰው ስላልቻለ የኑሮ ውድነቱ በቅርቡ ላያባራ ይችላል፡፡
ስለሆነም ለኑሮ ዘይቤ ለውጥ ጊዜው ዛሬ ነው፡፡ የኑሮ ውድነትን ማሸነፍ የሚቻለው በኑሮ ዘይቤ ነው፡፡ (5/11 ወይም ቁምሳ ምናምን የተሰኙ የኑሮ ዘይቤዎች እዚህ ቦታ የላቸውም፡፡ ለጸሎት ካልሆነ በቀር እየጾምን ሳይሆን ሳንጾም መኖር መጀመር አለብን)
ዐቢይ ለውጥ
ኑሮ ከዕለት ዕለት ዋጋው ቢያሻቅብም ካፌ፣ ሬስቶራንቶች እና ባሮች ግን ሰው ቸግሯቸው አያውቅም፡፡ ካፌ አትግቡ ሊለን ነው ደግሞ ካላችሁ፤ አልተሳሳታችሁም፡፡ ግን ምናለበት?
በአዲስ አበባ፣ አንድ ማኪያቶ ከ2 ብር ከ50 እስከ 10 ብር ድረስ ይጠጣል፡፡ አንድ አዲስ አበቤ ደግሞ በቀን ከአንድ እስከ አምስት ማኪያቶ ሊጠጣ ይችላል፡፡ አንድ ማኪያቶ የማዘጋጃ አማካይ ዋጋ ከ1 ብር አይበልጥም፡፡ ስለዚህ በ10 ብር ቤተሰብ ሙሉ ማኪያቶ ማጠጣት እየተቻለ ለምን በዚህ በተወደደ ኑሮ እና በስንት አበሳ በሚገኝ ገንዘብ እንቀልዳለን? ለምን ከቤት ኪራያችን በተጨማሪ የካፌ ኪራይ እንከፍላለን፣ ለምን ከገቢ ታክስ በተጨማሪ የካፌ ቫት እንከፍላለን፣ ለምን የአገልግሎት ቅብጥርሶ ተጨማሪ ወጪ እናወጣለን? ለምን የቤት ልጅ አንሆንም?
የማኪያቶን እንደምሳሌ አመጣሁት እንጂ የምግብ ዋጋም አይቀመሴ እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ወንደላጤዎችም፣ ሴተላጤዎችም፣ ቤተሰብ ተደጋፊዎችም፣ ቤተሰብ መሪዎችም - ሁላችንም ምግብ ማብሰል ለመማር አሁን ትክክለኛው ሰዓት ነው፡፡ ይህ ወጪን በአራት እጅ የመቀነሻ ሁነኛ እርምጃ ነው፡፡
ፖስተኝነት
ከኑሮ ውድነት ጋር ተግባብቶ ለመኖር አንዱ መንገድ ወጪን ማቀድ ነው፡፡ ብዙ ወጪን ማስተካከያ እና መቆጣጠሪያ መንገዶች አሉ፡፡ ወጪያችንን ስናስተካክል የመጀመሪያው ደረጃ አላስፈላጊ ወጪን መቀነስ ነው፡፡ አላስፈላጊ (ያልታቀደ) ወጪን የመቀነሻው የመጀመሪያው ደረጃ ደግሞ እንደፍላጎት ሳይሆን እንደአቅም ለመኖር መወሰን ነው፡፡ የወር ገቢን የሚመጥን ቤት መከራየት፣ ልብስ መልበስና ምግብ መብላት… ወዘተ፡፡
የወር ወጪን ማቀድ ወጪን ለመቆጣጠር ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ የፖስታ መንገድ የሚሏት መንገድ ደግሞ ከሁሉም የበለጠ ወጪን ለመቆጣጠር ሁነኛ መንገድ ነች፡፡ ፖስተኝነት ብያታለሁ፡፡
ፖስተኝነት ልክ ደሞዝ የተቀበልን ዕለት አራት ወይም አምስት ፖስታዎችን እናዘጋጃለን፡፡ እያንዳንዱ ፖስታ ላይ የቤት ኪራይ፣ የምግብ አስቤዛ፣ የትራንስፖርት፣ የተለያዩ ክፍያዎች፣ የመዝናኛ… ምናምን ብለን እንጽፍበታለን፡፡ ከዚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በማስቀደም በያንዳንዱ ፖስታ ውስጥ የሚበቃውን ያህል ገንዘብ እናስቀምጣለን፡፡ ከዚያም የተረፈውን መጠባበቂያ፣ ተቀማጭ… እናደርገዋለን፡፡ በዚህ መንገድ ያለ ቀውስ ወሩን ገቢያችንን በሚመጥን መንገድ መምራት እንችላለን፡፡
የትርፍ ሰዓት ሥራ
እንዲህ ዓይነት ምክር ኢትዮጵያው ውስጥ ማስተላለፍ እንደመሳለቅ ይቆጠራል፡፡ አብዛኛው ሰው የመደበኛ ሰዓት ሥራ ባላገኘበት አገር የትርፍ ሰዓት ሥራ መመኘት እንደ ቅንጦት ሊቆጠርም ይችላል፡፡ የሆነ ሁኖ ከኑሮ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባት ወይም ከመሰደድ (ወይም በብድር ከመሳደድ) የማይሻል ነገር የለምና ዕድልን መሞከር ያስፈልጋል፡፡ የትርፍ ሰዓት ሥራዎች ግዴታ በሙያችን ላይሆኑ ይችላሉ፣ እንደየዝንባሌያችን፣ አቅማችን እና ዕውቀታችን ምንም ሥራ ብንሰራ ነውር አይኖረውም፡፡
የትርፍ ሥራ ስናስብ ስለደረጃችን መጨነቅ ማቆምም ሊኖርብን ይችላል፡፡ የካፍቴሪያ አስተናጋጅነት፣ የእጅሥራዎች፣ አነስተኛ ንግድ፣ ድለላ ወይም ሌላ መሞከር ሊኖርብን ይችላል፡፡
‹‹ምክር እና ቡጢ ለሰጪው ቀላል ነው››
ከላይ የተናገርከውን ነገር ትተገብረዋለህ ወይ ብላችሁ ብትጠይቁኝ ‹‹ልተገብረው እፈልጋለሁ›› ከሚል የተሻለ መልስ አልሰጣችሁም፡፡ በርግጥ ከሻይ ማፍላት የበለጠ የኩሽና ሙያ የለኝም፣ ገንዘብ አወጣጥም ላይ ቢሆን እጄን ኪሴ ውስጥ እየከተትኩ እንዳሻኝና ኪሴ እስከፈቀደው ከማውጣት የበለጠ ልምድ የለኝም፡፡ ግን እንዲህ እየሆንኩ የዘንድሮን ኑሮ መግፋት እንደማልችል አውቀዋለሁ፡፡ ብወድም፤ ባልወድም፣ ብችልም፤ ባልችልም መኖር መጀመር አለብኝ፡፡ ስለዚህ ምክሩ ለአንባቢ ብቻ ቢሆን ይቀለኝ ነበር፣ ስለዚህ ቡጢው ለኔም ነው፡፡ ለኑሮ ጥያቄ ደግሞ ‹እፈልጋለሁ› መልስ አይሆንም፡፡ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡
ደስ የሚል ቁም ነገር ነው፡፡ እኔ በወጣትነቴ ላጤነት እና የኢኮኖሚ ድቀት የተጫወተብኝ ዘመን ነበር፡፡ ውጤታማ ሆኖ ያገኘሁት ግን አንድ ነገር ነው፡፡ ማግባት፡፡ ነገሩ የደሃ ኢኮኖሚክስ ቢመስልም፤ አንዳንድ ሚስቶች ለመኖር የሚበቃ ሲሳይ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ከትዳር ጥቅም እንደ አንዱ በገሃድ አልተነገረም እንጂ፤ ትዳር ለኢኮኖሚም ይጠቅማል፡፡ ጥሩ ከተገኘ ማለቴ ነው፡፡
ReplyDelete