እስኪ የዛሬውን ወጋችንን ብዙ በተደመጠ ቀልድ እንጀምረው፡፡ አንዲት ተማሪ ለፈተና ተቀምጣለች፡፡ ጥያቄዎቹን አየቻቸው ‹እውነት› ወይም ‹ሐሰት› ነው መልሳቸው፡፡ ምንም ባለማጥናቷ የቱ እውነት፣ የቱ ሐሰት እንደሆነ አታውቅም፡፡ የመጣላት አማራጭ ሳንቲም ከኪሷ አውጥታ ‹አንበሳ› ሲሆን ‹እውነት›፣ ተቃራኒ ሲሆን ደግሞ ‹ሐሰት› እያለች መመለስ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ፈተናዋን ሰርታ ስትጨርስ በጣም ብዙ ጊዜ ተረፋት ስለዚህ የሰራችው ትክክል መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ፈለገች፡፡ ግን ደግሞ ማረጋገጫ መንገድ የላትም፤ ስለዚህ በጀመረችው መንገድ እንደገና ሳንቲም እየወረወረች አንበሳን ለእውነት፣ ጀርባውን ለሐሰት እየመደበች መልሷን ታረጋግጥ ጀመር፡፡
በእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ውስጥ ሁለት መልስ ብቻ በመኖሩ፥ ያለሳንቲምም ቢሆን ሞክሮ መሳሳት፣ ሞክሮ ለመማር ነው፡፡ (በፈረንጅ አፍ Trial and Error Learning ይባላል፡፡ በአማርኛ ልተረጉመው ፈልጌ ነበር፤ ከበደኝ እንጂ! ‹ሞክሮ በመሳሳት መማር› ብለው ትክክል ነው እንዴ?) ግን ደግሞ በሕይወት ዓለም እልፍ መንገዶች አሉ፤ የትኛው መጨረሻው እንደሚያምር ለማወቅ ወይ በሁሉም መንገዶች ተራ፣ በተራ መሄድ አሊያም [ወደኋላ የምንመካከርበትን ጉዳይ ማድረግ] ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም መንገዶች እየሄድን መጨረሻቸውን እንይ እንዳንል ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ አንዱ፡- ለሙከራ የጀመርነው መንገድ መጨረሻው ባያምርስ? እሺ፡- መጨረሻው ሰላም ሆኖ መድረሻውን ስላልወደድነው ብቻ መመለስ ብንፈልግ የምንመለሰው እንዴት ነው? ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ሁሉንም መንገዶች ለመሞከሪያ በቂ ጊዜ የለንም፤ ሕይወት አጭር ናት፡፡
ዓላማቸው ግልጽ ባልሆነ የሐሳብ ድሪቶዎች ይህንን ያህል ካደከምኳችሁ ይበቃል፡፡ የዚህን ጽሁፍ ዓላማ ለማብራራት ግን አሁንም አንድ አንቀፅ ያስፈልገኛል፡፡ ከሰው ጋር ተግባብቶ ለመኖር እየሞከሩ፣ መሳሳት፤ እየተሳሳቱ፣ መማር ይቻል ይሆናል፡፡ በሰዎች ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ግን እየሞከሩ መሳሳት፣ እየተሳሳቱ መታረም አይቻልም፡፡ ዕጣ ፈንታ መዳረሻ በመሆኑ ማጣፊያ (undo) የለውም፡፡ በሃገራችን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚወጡ መመሪያዎች እና ውጤታቸው ግራ ቢያጋቡኝ ይህንን መጻፍ ጀመርኩ፡፡
ብስጭተ መንስኤ
የዛሬው የብስጭት መንስኤዬ በርግጥ የታክሲ ታሪፍ ድንገተኛ ጭማሪ ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ከዚያም በላይ ስር የሰደደ ነው፡፡ የታክሲዎች በየቀጠናው መሰማራት ሲታወጅ የመጀመሪያ ተጠቂ የሆንኩት እኔ ነኝ፡፡ ወደመስሪያ ቤቴ የሚወስደኝ አንድ መስመር ታፔላ ሳይሰራለት ቀረ፡፡ (ከአራት ኪሎ በብሔራዊ ሜክሲኮ) በዚህ ደንግጬ ሳለሁ ታፔላ በስህተት ያልተሰራላቸው ቀጠናዎች አሥራ አራት ገደማ እንደሆኑ ሰማሁ፡፡ ‹‹ለዓመታት ተጠንቶ›› የተባለው፥ አሥራ አራት ቀጠና ለመዘንጋት ነው ወይ ብዬ ሳልጨርስ፤ ከ‹‹ሙከራው›› ተምረው ነው መሰለኝ በሰሞኑ ዜና ታክሲዎች ከቀኑ 3፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት ድረስ በየታክሲ ማሕበራቱ ምድብ አካባቢ ውስጥ ያለታፔላ እንዲሰሩ ተፈቀደላቸው ተባለ፡፡ ሌላም የተባለ ነገር አለ፤ የታክሲ ታሪፍ ባልተለመደ ሁኔታ 15፣ 20 እና 30 ሣንቲም ጭማሪ ተደረገበት (ለወትሮው - ያውም በነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ሳቢያ - 5፣ 10 እና 15 ሣንቲም ነበር የሚጨመረው፡፡) ለምን ሲባል፤ ባለታክሲዎች ‹‹ለተጠቃሚው ጥቅም›› ሲሰማሩ ‹‹ገቢያቸው ቀነሰ፡፡››
የዋጋ ጭማሪውን የሰማሁት በዋዜማው ስለነበር የተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ የነበረውን ረዳት ጠየቅኩት፡፡ ‹‹እውን ገቢያችሁ ቀንሷል?›› ረዳቱ በፈገግታ ‹‹እኔ በበኩሌ፤ ታፔላ ከተጀመረ ወዲህ ከ100 ብር በታች ይዤ ወርጄ አላውቅም›› አለኝ፡፡ ‹‹በፊት ግን….›› (ረዳቱ ‹እኔ በበኩሌ› ያለኝ እሱ የተሰማራበት መስመር ገበያ ስላለው ሳይሆን አይቀርም ብዬ ገምቻለሁ፡፡)
ቢሆንም ግን መንግስት የሚነግረን ሕዝባዊ ተጠቃሚነት የታለ? የባለንብረቶች እና የታክሲ ሰራተኞች ተጎጂነትስ? ነው ወይስ እያመፁበት ከሚያስቸግሩት ባለታክሲዎች ጋር መወዳጀት አማረው? መልሱን ባውቀው አልደብቃችሁም ነበር፡፡
በመጀመሪያ
የታክሲ ስምሪቱ ከሁለት ዓመታት በላይ ተጠንቷል ሲሉ ለማመን አልቸገረኝም ነበር፡፡ ምክንያቱም ስለጉዳዩ ሲወራ ከሁለት ዓመታት በላይ ሁኖታል፡፡ የገረመኝ ነገር ሁለቱ ዓመት የጠፋው በጥናት ከሆነ
የተጠናው ‹እንዴት እናሰማራ?› የሚለው እንጂ ‹ለትራንስፖርት እጥረቱ የሚበጀው መፍትሄ ቀጠናዊ ስምሪት ነው ወይ?› የሚለውን ለመመለስ አይደለም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ ከጥናቱ መጀመሪያ ጀምሮ ‹‹ስምሪትን ለመተግበር›› የሚባል ቋንቋ አይወራም ነበር፡፡ ስለዚህ ጥናቱ ከጅምሩ ጎዶሎ ነው፡፡ በተራ መላምት ‹‹መፍትሄ›› ያሉትን ለመተግበር የሚያስችላቸውን አካሔድ አጠኑ (ሊያውም ያልተሟላ ጥናት) እንጂ ችግሩን አጥንተው ወደመፍትሄው አልመጡም፡፡
በመጨረሻ
መፍትሄ ብለው ያመጡት ነገር፤ እንኳን የትራንስፖርት እጥረቱን ሊያቃልል የራሱ የሆነ ችግር ወለደ፡፡ ሲጀመር ጥቂት ጠቃሚ መሳይ ነገሮች ቢታዩበትም በድምሩ ግን ከምሬት አላተረፈንም፤ ሲቀጥል እኛ የታክሲ ስምሪት ይደረግልን ብለን ሰላማዊ ሰልፍ አልወጣንም፡፡ መንግስ በራሱ ፍላጎት የተገበረው ስምሪት ላመጣው ችግር ተጠያቂ የምንሆንበት ምክንያትም መኖር አልነበረበትም፤ ግን ኖረ፡፡ ይኸው የታክሲ ስምሪቱ ‹‹ላከሰራቸው›› ሰዎች ጥቅም ሲባል፣ ምንም የማያውቀው ብዙሐኑ ተጠቃሚ ተጨማሪ ይክፈል ተባለ፡፡
‹‹ነገርን ነገር ያመጣዋል››
የኢሕአዴግ መንግስት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች በሙሉ እንደተጠጠኑ ይነገረናል፡፡ ሲተገበሩ ችግር ያመጣሉ፡፡ ፖሊሲ አውጪዎቹ ለፈጠሩት ችግር መፍትሄ ያበጁለታል፤ ለመፍትሄው እኛ እንከፍላለን፡፡ ይህ ጉዳይ እስከዛሬ የኖርንበት ዘይቤ መሆኑን ማስተዋል የሚሳነው ያለ አይመስለኝም፡፡ ኢሕአዴግ በአፍላ ዕድሜው ከኤርትራ ጋር ፈርሞ የሸጠው ወደባችን አሁን በጎረቤት ወደብ ኪራይ ከዚችው ዓመታዊ በጀታችን ላይ የማይናቅ ጉርሻ ይወስዳል፡፡ ባለፈው ዓመት ‹‹በጥናት›› የተተገበረው የዋጋ ተመን የሰወራቸው የዘይት እና ስኳር ነጋዴዎች እና ምርቶች ዘንድሮም እንደወጡ አልተመለሱም፡፡ በትምህርት ፖሊሲው የችኮላ ለውጥ ላይም ተመሳሳይ ‹‹ጥናት›› ተደርጎ ነበር፡፡ ኋላ ከረፈደ ደግሞ ጥራት ጎደለ ተብሎ ዩንቨርስቲዎች አምነውባቸው ያስመረቋቸውን ተማሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በመስጠት የጎደለውን ለመሙላት ሩጫ ተጀመረ፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ጉዳይ አዳዲስ ‹‹ጥናት›› የወለዳቸው ነገሮች ማከታተሉን አላቆመም፡፡ ከየት እንደመጣ የማይታወቀው የ70/30 የተፈጥሮና ማሕበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ቅበላ መመሪያም፣ ኢሕአዴግ ራሱ የፈጠራቸውን የግል ከፍተኛ ተቋማት መቃብር እየማሰ ይገኛል፤ የመንግስቶቹስ በመንግስት ፈቃድ ይኖራሉ፡፡
No comments:
Post a Comment