Pages

Thursday, February 13, 2014

የፖለቲከኞቻችን ሰው ፊት አቀራረብ (Presentability)

ፖለቲካ ጥበብ ነው፤ አንዳንዶች 'የማመቻመች ጥበብ'፣ አንዳንዶች 'የማጭበርበር ጥበብ'፣ ሌሎች 'art of possible' ይሉታል። አንዳንዴ እውነተኛ የሕዝብ ተቆርቋሪዎች እያሉ አስመሳዮች ያሸንፋሉ፤ ሐሳብ አፍላቂዎቹ እያሉ ሰራቂዎቹ ይመሰገናሉ። ሌሎች ፖለቲካ ጫወታ (game) ነው ይሉታል። ለብዙዎች የጨቀየ ጫወታ ነው፤ ለጥቂቶች ግን ጥበብም ጫወታም ነው። ተጫዋቾቹ ደግሞ በጨዋታው ሕግ (rule of the game) መሠረት መጫወት አለባቸው።

በእኛ አገር 'ፖለቲካ' እና 'ፖለቲከኝነት' ዛሬም አፍላ ነው። እስከዛሬ ጉልቤው ገዢ ነው፣ ገዢው ወሳኝ ነው። ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ጥበብ የሚጠይቅ የፖለቲካ ፉክቻ የለም። በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድሜ 40 አይሞላም። በጠብ መንጃ ተነድቶ ሥልጣን ላይ የወጣ እንጂ በፖለቲካ ፉክክር ተንጓሎ የወጣ ፓርቲ የለም።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃዋሚ እና ገዢ ተብለው ፉክክር ውስጥ የገቡት በኢሕአዴግ ዘመን ነው። ሆኖም ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ በዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረጉ ፓርቲዎች ትግሉን ከዜሮ እንዲጀምሩ አስገድዷቸዋል፤ ያውም በጠበበ ምኅዳር።
ከምርጫ 97 ወዲህ በተደረጉ የፖለቲካ ሽኩቻዎች ውስጥ ኢሕአዴግ በዝረራ ያሸነፈባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ለዚህ መንስኤው ከኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ንፉግነት ባሻገር የተቃዋሚዎቹም ድክመት ተጠቃሽ ነው። ተቃዋሚዎች ፕሮግራሞቻቸውን በማስተዋወቅ እና ደጋፊ በማበርከት ረገድ ጉልህ ችግር አለባቸው። ሕዝቡ ተቃዋሚ መሆናቸውን አውቆ እንዲሁ እንዲመርጣቸው ይፈልጋሉ እንጂ የሚመርጥበትን ምክንያት ሊያስረዱት አይከጅሉም። ስለተቃዋሚዎች ድክመት ብዙ ተብሏል፤ እኔም አሁን አንዱን ነቅሼ ላወራ ነው - ሰው ፊት አቀራረብ (presentability)።


የተቃዋሚ አመራሮች ለፖለቲካ ክርክር፣ ለጋዜጣዊ መግለጫ ወይም ለቃለ ምልልስ ሕዝብ/ካሜራ ፊት ሲቀርቡ የሚኖራቸው አለባበስ፣ ንቃተ-ፊት እና አነጋገር ዝርክርክነት ሰዎች "ሲሪዬስሊ" እንዳይወስዷቸው ከሚያደርጉ  እንቅፋቶች አንዱ ነው። እዚህጋ ሁለት ትችቶች ሊነሱ ይችላሉ፤ አንደኛው 'ፖለቲከኞች ማስመሰል አለባቸው ወይ?' የሚለው ነው። የጫወታው ሕግ የሚጠይቅ ከሆነ አዎ! ሰዎች መጀመሪያ በሚያዩት ነገር ተማርከው ጆሮ ይሰጣሉ፣ አነጋገሩን አድምጠው ነገሩን ያጤናሉ። የመጀመሪያውን ፈተና ያላለፈ ቀጣዩን የመደመጥ ዕድል አያገኝም፣ ያንን ዕድል ያገኘ አነጋገሩን ካላሳመረ ነገሩን ገዢ አያገኝም። ሦስተኛው ደረጃ ላይ ያለው የመጨረሻው እና ወሳኙ ፈተና ነው።

'የለም፤ ይህንን መጽሐፉን በሽፋኑ የሚዳኙትንም ጭምር መታገል አለብኝ' የሚል ፖለቲከኛ፣ ፖለቲከኛ ሳይሆን አራማጅ (ለውጥ አማጭ) ነው መሆን የሚችለው።

ሮብ ያንግ የተባለ "Power Dressing" የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲ ከፎርብስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ፖለቲካን በሚያህል የአገር ዕጣ ፈንታ በሚወሰንበት ጉዳይ ስለአለባበስ ማውራት ብዙ ሰዎችን ያሳፍራቸዋል፣ ግን አማራጭ የለም ብሏል። "Politics wants to present itself as a serious institution about substantive issues, rather than a popularity contest based on what the contenders look like. But the fact is that fashion… can be mighty powerful political currency."

አንዱና ትልቁ ችግር ፖለቲከኞች ራሳቸውንና ሕዝቡን ከአለባበሱ እና አቀራረቡ አልፈው ለመመልከት ቢሞክሩም ሕዝቡ የእነሱን አለባበስና አቀራረብ አስቀድሞ መገምገሙን አለማቆሙ ነው። ስለዚህ በጥቃቅን የአቀራረብ (presentability) ሳቢያ ትልቁ ቁምነገር ሰሚ ከሚያጣ፣ ትንሽ ዋጋ መክፈል ያዋጣል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በተለይ ተቃዋሚዎች ይህንን ጉዳይ በቅጡ ያጤኑት አይመስልም። አቶ ይልቃል (ኢ/ር) ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው የሰጧቸው ቃለምልልሶች ላይ የወጡ ፎቶዎቻቸው በሙሉ ጉስቁልቁል ያሉና ኮታቸው ተዛንፎ ወይም ከትከሻቸው የሰፋ መስሎ ነው። ዛሬ (የካቲት 6/2006) መግለጫ ሲሰጡ ያየኋቸው የሁለት ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላት፣ ጠረጴዛው ኋላ ሳያቸው ለአቀራረባቸው እንዳልተጨነቁ ያሳብቅባቸዋል። አለባበሳቸው የአዘቦት ዓይነት ነው፤ 'ፎርማል' በሚባል ሁኔታ እንኳን አልለበሱም። አንዱ ሲናገር ሌለኞቹ አንዱ አገጩን ተደግፎ፣ ሌላኛው በዚህንኛው ንግግር ያልተደሰት በሚመስል አኩርፎ፣ አንደኛውም ጉስቁል ባለ መልኩ ተቀምጠው ያደምጡታል። በኔ እምነት፣ አንዱ ሲናገር ሌላኛው በተቻለ መጠን የፊት ገጽታውን ሳያዘባርቅ፣ ቀጥ ብሎ ቢቀመጥ ሌላው ቢቀር የታዳሚዎችን ሐሳብ ከተናጋሪው አይሰርቅም።

ሌላው ጉዳይ የንግግር ዘዬ ጉዳይ ነው። በፖለቲካ አምባ፣ አንደበተ ርቱዕነት ወሳኝ ቁም ነገር ነው። እነ ልደቱ አያሌው፣ ብርሀኑ ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ሀብታሙ አያሌው የዚህ አንደበተ ርቱዕነት ማሳያ ናቸው። ይህ የሚያውቁትን አሳምሮ፣ የማያውቁትን አድበስብሶ የማሳለፊያ ጥበብ ለፖለቲከኞች ቁልፍ በመሆኑ ሌላው ዓለም ሥልጠና ሳይቀር ይወስዱበታል። የመጨባበጥ ሒደት፣ የእንግዶች /ካሜራ/ ፊት እንቅስቃሴ፣ የእጅ ውዝዋዜ ሳይቀሩ ይጠናሉ። ግለሰቦችን በአንቱታ እና ትክክለኛ ማዕረጋቸውን ሳያዛንፉ መጥራትም ራሱን የቻለ በልምምድ የሚገኝ ጥበብ ይጠይቃል፤ ትርፍም አለው።
የእኛ ፖለቲከኞች ለዚህ ቁብ አይሰጡትም። መወዳደሪያ እሴት ነው ብለው የሚያስቡም አይመስሉም። በመንግሥት በጀት ፕሮቶኮል የሚቀጠርላቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሳይቀሩ በኔልሰን ማንዴላ ቀብር ላይ ከሰው ሁሉ የተለየ አለባበስ ለብሰው የታዩት፣ እዚህ ግባ የማይባል ንግግር ያደረጉት በዚሁ ሳቢያ ነው። አነዚህ የአቀራረብ ቅንብሮች ተደማምረው ነው አንድን መሪ ሞገስ ያለው (charismatic) ነው፣ አይደለም የሚያስብሉት። ሰዎቹ፣ ብንወዳቸውም ብንጠላቸው አገራችንን ወክለው ሲቀርቡ ሞገስ ቢኖራቸው መልካም ነው።

በጥቅሉ ሲታይ ግን ተቃዋሚዎች ከገዢው አንፃር የመሪ-ሞገስ አልባ ናቸው ማለት ይቻላል። ገፅታ አይቶ በሚዳኝ ሕዝብ ውስጥ እየኖሮ ለአቀራረብ አለመንጠንቀቅ ዋጋ ያስከፍላል። ያንን ዋጋ ደግሞ ተቃዋሚዎች አይችሉትም።

No comments:

Post a Comment