Pages

Saturday, September 3, 2011

የሁለት እምነቶች ጦርነት… [ወግ አጥባቂዎች እንዲያነቡት የማይመከር - ክፍል ሦስት]

ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ ጦር ሜዳው ሕሊና፣ ጦረኞቹ አማኞች እና ኢ-አማኒዎች ናቸው፡፡ በኔ ጦማር ኢ-አማኒዎች ምክንያተኞች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ለዚህም ነው፣ ስለ ኢ-አማኒዎች በተናገርኩ ቁጥር ከአማኒዎች ጋር ማወዳደር የሚቀናኝ፡፡ እንግዲህ በክፍል ሁለት ጽሁፌ ለማመልከት እንደታገልኩት አማኒዎች ከኢ-አማኒዎች አንፃር (ወይም አንግል) ሲታዩ ፈሪዎች፣ ጠባቦችና አምላካችን ብለው በሚጠሩት አካል ላይ ጨካኞች መሆናቸውን ገልጬ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል›› (መዝ. 14፥1) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱሰ ጥቅስ ተንተርሼ ሙግቴን እቀጥላለሁ፡፡ ~ ‹ጎበዝ በይፋ ፈጣሪ የለም ይላል› ወደማለቱ ነኝ፡፡

ኢ-አማኒዎች (atheists) ሞራል የሌላቸውና ማስተዋል የተሳናቸው ተደርገው በአማኒዎች ይሳላሉ፡፡ ኢ-አማኒዎች ከአማኒዎች ይልቅ የሞራል (የሕሊና) ጥያቄን ከግምት ውስጥ ማስገባት የሚችሉና ዓለምን ለመቀየር የሚያስችል አስተውሎት ያላቸው ስለመሆናቸው ጥናቶች ሳይቀሩ ያረጋግጣሉ፡፡


ኢ-አማኒዎችና ወንጀል
ሃይማኖተኞች በፈሪሃ እግዚአብሔር ከወንጀል እንደሚቆጠቡና የኢ-አማኒነት መስፋፋት ወንጀልን ሊያስፋፋ እንደሚችል አልፎ፣ አልፎ የሚከሰቱ የስነ ልቦና ተመራማሪዎች ሳይቀሩ ይገምታሉ፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ወፍ ዘራሽ ምሁራን ናቸው፡፡ በምርምርና አመክንዮ ያልተደገፈ ግምት ሰንዛሪዎች፡፡ ይሁንና እውነታው ምን ይመስላል፡፡ በተገኘው መረጃ እንመልከተው፡፡

የአሜሪካው Federal Bureau of Prisoners ባሳተመው አንድ መረጃ እ.ኤ.አ. በ1997 – 75% አሜሪካውያን ክርስቲያን ሲሆኑ 10% ብቻ ያክሉ ደግሞ ኢ-አማኒዎች ነበሩ፡፡ ሆኖም በወቅቱ ከነበሩት ወንጀለኛ ታራሚዎች/እስረኞች መካከል 75% ክርስቲያኖች ሲሆኑ 0.02% የሚሆኑት ደግሞ ኢ-አማኒዎች ነበሩ፡፡ ይህ መረጃ ምን ዓይነት እውነት ይነግረናል? እውን ከአማኒዎች ይልቅ ኢ-አማኒዎች ሕሊና ቢሶች ናቸውን?

ኢ-አማኒዎችና አስተዋይነት
ይሄ ጉራ የሚመስላቸው በርካቶች ሊኖሩ ቢችሉም እውነት ነው፡፡ ሰዎች ወደኢ-አማኒነት ለመሸጋገር ከፍተኛ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያሻቸዋል፡፡ ሁሉም ኢ-አማኒዎች ከፍተኛ አስተውሎት (ወይም ደግሞ በቁጥር ለመለካት እንደሚሞክሩት ከፍተኛ IQ) ባይኖራቸውም፣ ከሃይማኖተኞች በሚበልጥ ንጽጽሮሽ አብዛኛዎቹ ኢ-አማኒዎች አርቆ አሳቢዎች፣ ዓለምን ለመቀየር የሚያበቃ ክህሎት ያላቸው መሆናቸው በጥናቶች ሳይቀር ተረጋግጧል፡፡

ለዚህ ወጋችን ግብዓት ይሆኑ ዘንድ ሁለት ጥናቶችን መርጬላችኋለሁ፡፡ አንደኛው Intelligence and religious belief within nations በሚል ከሦስት የአውሮፓ ዩንቨርስቲ የተውጣጡ ምሁራን በ127 ሃገራት ያደረጉት ጥናት ነው፡፡ ሌላኛው በኖርዝ ካሮሊና ቻርሎቲ ዩንቨርስቲ የተካሄደ A state level investigation of the associations among intellectual capital, religiosity and reproductive health የተሰኘ ጥናት ነው፡፡ ሁለቱም ጥናቶች ስለኢ-አማኒዎች አርቆ የማሰብ ችሎታ ይመሰክራሉ፡፡

በመጀመሪያው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ኢ-አማኒዎች በሚበዙባቸው አገሮች ዜጎች ከፍተኛ IQ እንዳላቸው ተመላክቷል፡፡ (IQ ~ Intelligent Quotient በመባል የሚታወቀው የቀለም ጉብዝና መለኪያ ነው፡፡) 0.05 በመቶ ኢትዮጵያውያን ብቻ ኢ-አማኒዎች ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያውያን አማካይ IQ 64 ብቻ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ ለምሳሌ ጃፓኖች ግን በአማካይ 105 IQ ሲያስመዘግቡ፣ 65 በመቶ ሕዝባቸው ኢ-አማኒ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ 14,277 ሰዎችን ባካተተ መጠይቅ ‹ኢ-አማኒ ነኝ› ብለው የተናገሩት መላሾች አማካይ IQ 103.09 ሲሆን ‹በጣም አማኝ ነኝ› ያሉት ደግሞ 97.14 ነው፡፡

Intelligence (ወይም ጉብዝና) የቀለም ትምህርት ደረጃ ሲጨምር፣ ዕድሜ ሲጨምር፣ እና ከተሜነት ሲስፋፋ እንደሚጨምር ሁሉ ኢ-አማኒነትም እንዲሁ ነው ይለናል ጥናቱ፡፡ በአገራችን አማኞች ግን ይህ ‹‹ስልጣኔ ስይጣኔነትን ሲያመጣ›› የሚል ባጅ ይለጠፍበታል፡፡

በሁለተኛው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ደግሞ ምንም እንኳን ጥናቱ በአሜሪካ ስቴቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ቢሆንም፤ ከመጀመሪያው ጥናት የተለየ ውጤት አይነግረንም፡፡ Intelligence–religiosity associations በሚል የአማኒነትና ጉብዝናን ዝምድና ሲገልፀው lower IQ individuals are less likely to have the capacity for critical abstract thought and thus subscribe to religious orthodoxy as a means to find “uncontested and uncontestable answers” (ዝቅተኛ IQ ያላቸው ሰዎች ጠጣር አመክንዮአዊ ሐሳቦችን ለመመርመር አቅሙ ስለማይኖራቸው በሃይማኖታዊ ድርቅና በመቁረብ ‹‹የማይገዳደሩት ምላሽ›› እንዳገኙ ይቆጥሩታል፡፡) በድምሩ በጣም ሃይማኖተኛ ሃገራት ድሆች፣ ከተሜነት ያልተስፋፋባቸውና ትምህርት ያልተዳረሰባቸው ሃገራት ናቸው – ሙሉ ተስፋቸውን በምናባዊ አምላክ ላይ የጣሉ እንደማለት፡፡

የዓለም ሕዝቦች የቀለም እውቀት እና ከተሜነት እየተስፋፋ እና እየተመነደገ እየመጣ እንደመሆኑ መጠን፣ ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ፣ አሁን ኢ-አማኒነት እብድነት እንደሆነው ሁሉ አማኒነት እብድነት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው (ሉቃስ 23፡34)
ይሄ ጽሁፍ መደምመደም አለበት፤ ከዚያ በፊት ግን እርቀ-እምነት ያስፈልጋል፡፡ ላለመስማማት መስማማትም ቢሆን እርቅ ነው፡፡ አማኒዎች (በተለይም የክርስትና እምነት ተከታዮች ኢየሱስ ሲሰቀል ለሰቃዮቹ የለመነላቸውን ይቅርታ በማስታወስ) ኢ-አማኒዎችን ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ሲሉ ወደአምላካቸው ይለማመናሉ፡፡ ኢ-አማኒዎችም ቢሆኑ አማኒዎች ያለመጠየቅ ያምናሉና ለአማኒዎች ይቅርታ መለመን ይፈልጉ ነበር፤ ግን አይችሉም፡፡ ምክንያቱም ይቅርታ ሰጪ አለ ብለው አያምኑም፤ ይቅርታ ሰጪም ተቀባይም እኛው ነን፡፡ እኛ (አማኒዎችና ኢ-አማኒዎች) ደግሞ በአመለካከት ተቆራቆዝን እንጂ ጠብመንጃ የሚያማዝዝ በደል አንዳችን ባንዳችን ላይ አልሰራንም፡፡ ነገር ግን ኢ-አማኒዎችም በበኩላቸው አማኒዎች ‹የሚያምኑትን አያውቁምና ያስቡበት› ብለው ይመክራሉ፡፡

1 comment:

  1. አጻጻፍህ ደስ ይላል፡፡ልኩ ባይታወቅም! እግዚአብሔርን እና ተከታዬቹን ልክ ልካቸውን ነገርካቸው፡፡እነርሱን ‹ማሸነፍ› ቀላል የሆነልህን ያህል ግን ያደክበትን ሃይማኖታዊ ባሕል እና የተቀረጽክበትን የአስተሳሰብ መንገድ መለወጥ ቀላል አይመስለኝም፡፡ ጽሑፍህ ቢያልቅም! በውስጥህ ያለው ውጊያ ግን ተፋፍሞ እንደሚቀጥል እገምታለሁ፡፡ My advise is 'try to stay away from both extremes and just be normal citizen'. ለማመን መሞከር እና ላለማመን መሞከር-እንደ Action and Reaction-ተመጣጣኝ ጉልበት ይፈልጉብሃልና፡፡

    ReplyDelete