Monday, January 9, 2012

ገመና 2፣ ሰው ለሰው፣ ጀግንነትና ኢትዮጵያ


የገመና 2፣ እና የሰው ለሰው ድራማዎች (ሶጵ ኦጴራዎች?) ሁለቱም ተወዳጅ ጀግና ከመፍጠሩ ይልቅ፣ የሚጠላ ጀግና የመፍጠሩ ሙከራ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ ዘመነኞቹ የሶጵ ኦጴራ ደራሲዎች መጥፎ እና ጥሩ ሰዎችን እየፈጠሩ ከማባላት የድሮ የታሪክ አወቃቀር ስልት እየወጡ፣ ከሕይወት ውጣ ውረድ ጋር ታግለው የሚያሸንፉ ጀግኖችን በመፍጠር ላይ አተኩረዋል፡፡ የኛዎቹ ደራሲዎች የሚፈጥሯቸው ጀግኖች ግን የሚፈተኑት ለእኩይ ተግባር የተፈጠሩ በሚመስሉ ሰዎች ነውና በዚያው አካሔድ እያነሳን እንጥላቸዋለን፡፡

Monday, January 2, 2012

እስኪ ስለዋጋ - ቆም ብለን እናውጋ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን ቆሞ የማይጠብቀን ነገር ቢኖር ዋጋ ነው፡፡ የሌላው፣ የሌላው ነገር ቀርቶ የአንበሳ አውቶቡስ ዋጋ እንኳን በተሳፈርንበት ዋጋ መመለስ እስከማንችል ድረስ በፍጥነት ነው የሚለዋወጠው፡፡ (“ማርያምን” አላጋነንኩትም!) ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጥቼ መሃል አዲሳባ መዋል ከጀመርኩ ወዲህ በዋጋ ጉዳይ እንደሳሙና እያደር እያለቅኩ፣ አሁን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፡፡

በሃገራችን ዋጋ የሚጨምሩባቸው በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኞቹ ግን የታክስ እና የትርፍ ጭማሪ ፍላጎት ናቸው፡፡ በጥቅሉ በሽታው መንግስት አመጣሽ ወይም ነጋዴ አመጣሽ ተብሎ ሊከፈል ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ ዛሬ፣ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የትርፍ ጭማሪ ፍላጎት ላይ ብስጭቱን እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡

Saturday, December 17, 2011

ጨርቆስና ቦሌ - ሕይወትን እኛ እንደኖርነው!


ጨርቆስና ቦሌን ምን አገናኛቸው? በርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም ጨርቆስና ቦሌ ተለያይተው አያውቁም - በቀልድም በድንበርም፡፡ በኑሮ መቀለድ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የኑሮአችን አካል ነው፡፡ የጨርቆስ እና የቦሌ ጉርብትናም በኢትዮጵያ እየሰፋ ለመጣው የኑሮ ደረጃ ልዩነት በርካታ አዳዲስ ቀልዶችን አበርክቷል፡፡ ምንም እንኳን የጫወታዬ ዓላማ ቀልዶቹን ለአደባባይ ማብቃት ባይሆንም አንድ ስሜቴን የነካ ቀልድ ግን ሳላስታውስ ማለፍ አይቻለኝም፡፡ ቀልዱ የተነገረው ወንድማማቾቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ መንግስታችን በወቅቱ ‹‹ፈንጂ ማክሸፊያ›› ወጣቶች ያስፈልጉት ነበርና‹ወዶ ዘማች› የሚለው ቃል ወረት ሆኖ ነበር፡፡ እናም የሃገራቸው መወረር ያስቆጣቸው የቦሌ ልጆች ገንዘብ አዋጥተው ለጨርቆስ ሰፈር ‹ወዶ ዘማቾች› ደሞዝ እንዲከፈል አበረከቱ ተብሎ ተቀለደ፡፡

ከዚህ ቀልድ በኋላ ግን አንድ ጥያቄ በጭንቅላቴ ሲጉላላ ከረመ፡፡ ‹‹የሃብታምና የድሃ ሕይወት የዋጋ ልዩነት ስንት ነው?››

Saturday, December 3, 2011

የዳዊት ከበደ እና የተመስገን ደሳለኝ ወጎች


“Every newspaper that's rented instead of being sold is a further challenge for those few trying to survive in the tough Ethiopian media environment,” ይህን የተናገረው የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ለሲኤንኤን ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የጋዜጣ ኪራይን በተመለከተ ነበር፤ የጋዜጣ ኪራይ በአዲስ አበባ ቀድሞ ለታመመው የግሉ ሚዲያ ተጨማሪ ተግዳሮት መሆኑን ሲገልፅ፡፡ (የጋዜጣ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢዎችን›› ዳዊት እንዴት እንደማይወዳቸው ይታያችሁ! እኔ ግን አታስዋሹኝ እወዳቸዋለሁ፡፡ እስኪ አስቡት ሳምንት ሙሉ የሚታተሙትን ጋዜጦች እየገዛሁ ባነብ ደሞዜ ይበቃኛል? ጋዜጣ በልቼ፣ በጋዜጣ ተሳፍሬ፣ በጋዜጣ የቤት ኪራይ ከፍዬ፣ በጋዜጣ ሁሉን ነገር አድርጌ መኖር ይቻለኛል?)

ዳዊት ከበደ አሁን ዋሽንግተን፣ አሜሪካ ነው ያለው፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንግስት ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ‹‹በይቅርታ›› መፈታቱ ይታወሳል፡፡ እንግዴህ ያ ‹‹ይቅርታ›› እንደሰኞ ሊሰረዝ እሱ ቅዳሜ ወደአሜሪካ በርሯል፡፡ ይመስለኛል፤ ዳዊት ይቅርታው እንደሚሰረዝ ከመስማቱ በፊት ገምቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአሜሪካ ቪዛ የማግኘቱ ጉዳይ ቀላል ባለመሆኑ ቀድሞ መጀመርን ይጠይቃልና እሱም ይህንኑ ቀድሞ ማሳካት ችሎ ነበር ማለት ነው፡፡

Saturday, November 26, 2011

“ኢትዮጵያውያን፣ ኢትዮጵያ እያለች ሃገር የላቸውም”


“በዓለም አንደኛ ነው፤” በሚል በገዛ ጓደኞቼ ተጠቁሜ፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ ገብቼ ያየሁት “ዘመቻ ድንግልን ፍለጋ” የተሰኘ ፊልም አንደኝነቱን ለደረጃ አጣሪ ኮሚቴ ሰጥቼና እምባዬን ወደሰማይ ረጭቼ ከውስጡ ያገኘሁትን ዓረፍተ ነገር ለወጌ ርዕስነት መርጬዋለሁ፡፡ ዓረፍተ ነገሩ “7ተኛው ሰው” የተባለ ሌላ “በዓለም አንደኛ” ፊልም አስታወሰኝ፡፡ ሰባተኛው ሰው ወደአሜሪካ ለዎርክሾፕ ከሄዱት ሰባት ሰዎች መካከል ወደሃገሩ ተመልሶ የመጣው እና በፊልሙ ዓለም ውስጥ በነበሩ ምሁራን፣ ተቃዋሚ እና ገዢ ፖለቲከኞች ብሎም በቤተሰቦቹ ሳይቀር የመገለል ዕጣ የደረሰበት ነበር፡፡ ለምን ተመለስክ በሚል፡፡

እዚህ ፊልም ላይ የታየው ታሪክ እንዳልተጋነነ ለማወቅ ከፈለጋችሁ አንድ የእውነተኛ ታሪክ ልጨምርላችሁ፡፡ ፋንታሁን ሸዋንቆጨኝ በብሔራዊ ቲያትር አንጋፋ ድምፃዊ ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በባለሙያዎች የተወደሰ አልበም አውጥቶ ብዙም አድማጭ አላገኘም ነበር፡፡ በርግጥ ዜማዎቹ ለአሸሸ ገዳሜ የማይመቹ ስለሆኑ፣ የዘመኑን መስፈርት አያሟሉም ነበር፡፡ ብዙዎቻችሁ ከጂጂ ጋር በማሲንቆ ያዜማቸውን እና ከሸገር ሬዲዮ በቀር በሌላ ሬዲዮ ጣቢያ እምብዛም በማይደመጡት ዜማዎቹ ታውቁታላችሁ፡፡ ስለርሱ ነው የምነግራችሁ፡፡

Tuesday, November 22, 2011

የኢሕአዴግ ‹‹ትርፍ›› እና ኪሳራ


ኢሕአዴግን ፀሃዩ መንግስት እያለ በሽሙጥ የሚያንቆለጳጵሰው አበበ ቶላ በካድሬዎች ሽንቆጣ ብዛት ኮበለለ፣ የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተርና የ2010 CPJ ፕሬስ ነፃነት ተሸላሚው ዳዊት ከበደም እያሻቀበ በመጣበት ትንኮሳና (እንደራሱ ገለፃ ‹‹ማክሰኞ፤ ሕዳር 12፤ 2004›› ሊታሰር ስለነበር) ወደ ሃገረ አሜሪካ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ የምንወዳቸው፣ ጽሁፎቻቸውን የምንናፍቅላቸው ጋዜጠኞች በሙሉ ከፊሎቹ ተሰደዱ፣ ከፊሎቹ አቋማቸውን አለዘቡ፣ ከፊሎቹ ብዕራቸውን ሰቀሉ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ታሰሩ፡፡ ‹‹ሂስ ቀረበብን ብለው ሃገር ጥለው ፈረጠጡ›› በሚል በጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተተቹት እነ ዐቢይ ተክለማርያም እና መስፍን ነጋሽ በአሸባሪነት በሌሉበት በተከሰሱበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት የሃገራችን የፕሬስ ነጻነት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ አቶ በረከት ስምዖንን፣ ሚሚ ስብሃቱን፣ ሳምሶን ማሞን ወይም የኢቴቪ ሚዲያ ዳሰሳ አዘጋጆችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡

በተቃራኒው WorldPress Freedom Index 2010 የኢትዮጵያን የፕሬስ ነፃነት ‹‹አስቸጋሪ ሁኔታ›› (ለመጨረሻ ሩብ ጉዳይ) ላይ እንዳለ ይነግረናል፡፡ የ2011 ውጤት ሲታወቅ ደግሞ ‹‹በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ›› (የመጨረሻ ደረጃ ላይ) ነው ብሎ እንደሚፈርጀው መገመት አይከብድም፡፡ በFreedom of the Press Global Status ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ‹‹ነፃ ያልሆነች›› ተብላለች፡፡ ጋዜጠኞችንም በማሰር ቢሆን ኢትዮጵያን ከኤርትራ በቀር የሚበልጣት እንደሌለ chartsbin.com በዝርዝር ያስነብበናል፡፡ እኛ ማንን እንመን? በመንግስት ቲፎዞነታቸው የምናውቃቸውን እኒያን ግለሰቦች ወይስ በጥናት ላይ ተመርኩዘው የሚነግሩንን እኒህ ኃላፊነት የሚሰማቸውን ድርጅቶች? ግዴለም የምናየውን እንመን፤ የታሰሩትንና እየተሰደዱ ያሉትን ጋዜጠኞች አይተን እንፍረድ፡፡

Thursday, November 10, 2011

“Every nation deserves its government” - ኦቶ ቮን ቢስማርክ

ሠላም ሰፍኗል፡፡ ሠላም የሚያሰፍን ግን አንዳችም ነገር የለም፡፡ የኑሮ ዋጋ ከሕይወት ዋጋ በልጧል፣ በቂ ቀርቶ ግማሽ ነፃነት የለም፤ ሕዝቡ ግን አይበሳጭም ወይም ብስጭቱን አፍኖ ተቀምጧል፡፡ ‹‹የባሰ አታምጣ›› እያለ የምድራዊውን ገዢ በደል ‹‹በሰማያዊው›› ላይ ያሳብባል (‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› መባሉ ተዘንግቷል!) - የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢሕአዴግን መንግስት እንደሚጠላው እና እንደተማረረበት ቢታወቅም - ‹በቃኸኝ› ሊለው ግን አልፈለገም ወይም አልደፈረም፡፡

ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ኢትዮጵያውያን ለአብዮት የሚያበቃ ብስጭት ላይ ደርሰዋል? ባሉት ጽሁፋቸው ላይ ‹‹ሕዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ የመነሳት ዕድሉ በብዙሐኑ ስነልቦናዊ ዝግጅት ላይ የተመረኮዘ ነው›› በማለት የስነልቡናው ዝግጅት አናሳ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመጽ፣ በቅርቡ ይቀሰቀሳል ብሎ መጠበቅ እንደማያዋጣ አመልክተዋል፡፡

ሕዝባዊ አመጽ ያስጠላል፡፡ ሁሉም ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ይወዳል፡፡ ነገር ግን ከጊዜያዊ ሰላም ይልቅ ዘላቂ ለውጥ ይበልጥ አስፈላጊ ነው፡፡ የማንበላ መብላት፣ የታረዝን መልበስ፣ የታሰርን መፈታት ያምረናል፡፡ እንዳምና ካቻምናው ሁሉ ከመሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ጋር ተጣብቀነ በምግብ ራስን ስለመቻል እና የነፃነት አየር ስለመተንፈስ ማውራት ያሰለቻል፤ እንደሌሎች ሃገራት ስለዓለም ዓቀፍ ገበያ፣ ስለኅዋ ሳይንስ እና ስለሁለተኛ ፍላጎቶቻችን የማውራት ወግ ያምረናል፡፡ አምሮታችንን ለመወጣት ደግሞ እንቅፋት ከፊት ለፊታችን ተደቅኖ ይታየናል - ለውጡ ባይመጣስ ብለን እንፈራለን ወይም ደግሞ የለውጥ ሒደቱን ከወዲሁ ስናስበው ይደክመናል፡፡

Transforming Ethiopia’s Exclusionary Constitution into an Inclusive One

Before introducing my proposal, I would like to explain my motivation for writing this now. One of the outcomes of the National Dialogue o...