Skip to main content

የዳዊት ከበደ እና የተመስገን ደሳለኝ ወጎች


“Every newspaper that's rented instead of being sold is a further challenge for those few trying to survive in the tough Ethiopian media environment,” ይህን የተናገረው የአውራምባ ታይምሱ ዳዊት ከበደ ለሲኤንኤን ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የጋዜጣ ኪራይን በተመለከተ ነበር፤ የጋዜጣ ኪራይ በአዲስ አበባ ቀድሞ ለታመመው የግሉ ሚዲያ ተጨማሪ ተግዳሮት መሆኑን ሲገልፅ፡፡ (የጋዜጣ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢዎችን›› ዳዊት እንዴት እንደማይወዳቸው ይታያችሁ! እኔ ግን አታስዋሹኝ እወዳቸዋለሁ፡፡ እስኪ አስቡት ሳምንት ሙሉ የሚታተሙትን ጋዜጦች እየገዛሁ ባነብ ደሞዜ ይበቃኛል? ጋዜጣ በልቼ፣ በጋዜጣ ተሳፍሬ፣ በጋዜጣ የቤት ኪራይ ከፍዬ፣ በጋዜጣ ሁሉን ነገር አድርጌ መኖር ይቻለኛል?)

ዳዊት ከበደ አሁን ዋሽንግተን፣ አሜሪካ ነው ያለው፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ መንግስት ዕድሜ ልክ ተፈርዶበት ‹‹በይቅርታ›› መፈታቱ ይታወሳል፡፡ እንግዴህ ያ ‹‹ይቅርታ›› እንደሰኞ ሊሰረዝ እሱ ቅዳሜ ወደአሜሪካ በርሯል፡፡ ይመስለኛል፤ ዳዊት ይቅርታው እንደሚሰረዝ ከመስማቱ በፊት ገምቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአሜሪካ ቪዛ የማግኘቱ ጉዳይ ቀላል ባለመሆኑ ቀድሞ መጀመርን ይጠይቃልና እሱም ይህንኑ ቀድሞ ማሳካት ችሎ ነበር ማለት ነው፡፡

የመንግስት አፍ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል፤ ዳዊት ከበደ የጋዜጣው ዋጋ በማሽቆልቆሉ ይሆናል እንጂ ማንም እሱን በሽብር ሊያስር የተዘጋጀ የለም፣ ይቅርታውም አይነሳም ነበር ብለው ነበር፡፡ በርግጥ አቶ ሽመልስ ‹‹ልናስረው እንደተዘጋጀን ምስጢር ሾልኮ ስለደረሰው፤ አመለጠን›› ሊሉ አይችሉም፡፡ በዚያ ላይ የኢትዮጵያ ጋዜጣ ገበያ ከመጀመሪያውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ በማስታወቂያ ካልተደጎመ በቀር፡፡ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ደግሞ እምብዛም ሸማች እንዳልነበረው እኔ ራሴ እማኝ ነኝ፤ ማስታወቂያም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሻሻልም ያን ያክል አጥጋቢ አልነበረም፡፡

አውራምባ ታይምስ ከማክሰኞ ወደቅዳሜ ዘልሎ የመጣው በአዲስ ነገር ጋዜጣ እግር ተተክቶ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ፍትሕ ጋዜጣም ከአርብ ወደቅዳሜ ይመጣል ብዬ እያሰብኩ ነው፡፡ በርግጥም ወደቅዳሜ ቢመጣ የእረፍት ቀን እንደመሆኑ የአንባቢው ቁጥር ይጨምርለታል የሚል እምነት አለኝ፡፡) አዲስ ነገር ጋዜጣ ሲዘጋ እና አዘጋጆቹ ሲኮበልሉ መጀመሪያ ሐዘን፣ ኋላ ጥርጣሬ በመጨረሻም እምነት ተፈራርቀውብኛል፡፡

እውነቱን ለመናገር አዲስ ነገር ጋዜጣ ብቻ አይመስለኝም ነበር - ልክ እንደ ሎተሪ በጉጉት ነበር በየሳምንቱ የምጠብቀው፡፡ ለሕትመት ከበቃበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው እየተሻሻለ (በፅሁፍ ቅርፀትም ሆነ በይዘት) መምጣቱ ከዚያ በፊት አቻ ያላገኘንለትን አዲስ አድማስን አስንቆን ነበር፡፡ አዲስ ነገር ጋዜጣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ተጎናጽፎ የነበረው በይፋ ተቃውሞው ብቻ ሳይሆን፣ በመረጃዎቹ ጥንካሬና በክርክሮቹ አምክኖአዊነት ነው፡፡ እናም የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ተሰደዱ ሲባል በጣም ነበር ያዘንኩት አንድም ለራሴ፣ አንድም ለነሱ፡፡ በኋላ ላይ ግን (ሐሳቡ የቂል ቢመስልም) እነዚህ ሰዎች በዚህ አጋጣሚ ባገኙት ዕውቅና ጥገኝነት ሊጠይቁ ጥለውን ሄዱ ማለት ነው ብዬ ተጠራጥሬ ነበር፡፡ ምክንያቱም ያኔ በአሸባሪነት የተፈረጀ አካል አልነበረም፤ ድጋፍ አደረጋችሁለት ሊሉ አይችሉም፡፡ (እዚህጋ ሰዎቹ የፈለጉትን ሊሉ የሚችሉ መሆኑ ተዘንግቶኝ አይደለም) ለዚህ እርግጠኛ መልስ ማግኘት አንችልም፡፡ ነገር ግን መንግስት ያኔ የቋጠራትን ቂም አሁን በተሰደዱበት 23ኛና 24ኛ ተከሳሾች ዐብይ ተክለማርያምና መስፍን ነጋሽ ብሎ ሲያሰፍር ተጋለጠ፡፡ መለስ በወቅቱ ‹‹ሂስ ተሰነዘረ ብለው የኮበለሉ›› ሲሉ የተቿቸው ሐሰት ሆነ፡፡

አሁን ደግሞ ተረኛው አውራምባ ታይምስ ሆኗል፡፡ የአውራምባ ታይምስ የገፅ ዲዛይኑም ሆነ የጽሁፉ ይዘት አንጀት አርስ ነበር ማለት ይከብዳል፡፡ ይሁን እንጂ እኔ በግሌ መንግስትን የሚተቹ እና የመንግስትን ምስጢር የሚያጋልጡ ጋዜጦችን ማንበብ ስለምመርጥ ያለመታከት እገዛው ነበር፡፡ ምናልባትም ከዚህ ጎራ የቀረው ፍትሕ ጋዜጣ ስለሆነ ቀጣዩ እሱ እንደሚሆን ሁላችንም እየገመትን ነው፡፡ ለፍትሕ ጋዜጣ ያለኝም አመለካከት ከአውራምባ ታይምስ የተሻገረ አይደለም፡፡ በርግጥ የፍትሕ ጋዜጣ ትችት ከአውራምባ ይጠነክራል፣ ፍትሕ ማስታወቂያ የለውም ቢባል ይመረጣል፣ ፍትሕ የገፅ ዲዛይኑ ማራኪ አይደለም (አንብቡኝ፣ አንብቡኝ አይልም) ነገር ግን አቦይ ስብሐት ፍትሕ ላይ ከጻፉ ወዲህ ገበያው ደርቷል፣ ዋጋውም ጨምሯል፡፡ ፍትሕ ጋዜጣ የጋዜጣው ስም የሚፃፍበት ቀለም፣ ትርጉሙ እና በጀርባው ገጽ የሚያሰፍረው ሃይማኖታዊ ቅብ ፖለቲካው በምርጫ 97 ሰሞን ብቅ ብሎ የጠፋውን ‹‹ነፃነት›› ጋዜጣ ያስታውሰኛል፡፡

የፍትሕ ጋዜጣ ፊታውራሪ ተመስገን ደሳለኝ ነው፡፡ ደሳለኝ ብዕሩን በተለይ በመለስ ዜናዊ ወንበር ላይ ያነጣጠረ ቁርጠኛ ጸሃፊ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደጋግሞ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በመጠየቅ የሚወዳደረው የለም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ሳስበው መለስ ራሳቸው ‹‹ይሄ ሰውዬ እኔ ወንበር ላይ ያየው ነገር አለ እንዴ?›› የሚሉ ይመስለኛል፡፡ እጅግ ያልሰማናቸውን በርካታ ምስጢሮችንም አውጥቷል፡፡ ተመስገን ከዳዊት የሚለየው ከአገር መውጣት ባለመፈለጉ ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን ተመስገን የሚፈልገው ነገር የለም ማለት አይደለም፤ የሚፈልገው ነገር በሚቀጥለው ንዑስ ርዕስ ውስጥ ይገመታል፡፡

‹‹መውጣትና መግባት››
ንዑስ ርዕሱን ከበውቀቱ ስዩም የወግ መጽሃፍ አይደለም የተዋስኩት፡፡ ከቀድሞው የአውራምባ ታይምስና ፍትሕ ስላቅ አምደኛ አበበ ቶላ ነው፡፡ አቤ ቶክቾው ከአዲስ ነገር ኦንላይን ጋር መሰደዱን አስመልክቶ ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ፤ ‹‹ከምገባ ብዬ ወጣሁ›› ነው ያለው፡፡

ብዙዎቹ ጋዜጠኞች (አቤ ቶክቾን ጨምሮ) የሚኮበልሉት፣ ‹‹ውጣ አትበለው፤ እንዲወጣ አድርገው›› በሚባለው ዘዴ መሆኑን ሰምተናል፡፡ በዚህ መንገድ የሚሰደዱት ብዙዎቹ መረጃውን የሚያገኙት ከመንግስት ካድሬዎች እንደሆነ ሰምተናል፡፡ በርግጥ ኢሕአዴግ ያለደረጃቸው የተሾሙ እና ለሹመታቸው ቀናተኛ፣ በርካታ ታማኞች እንዳሉት ቢታወቅም ፈርተውት፣ አብረውት የሚኖሩት ካድሬዎች ምስጢር አያሾልኩም ማለት አይቻልም፡፡ ቢሆንም ግን የኛ ጋዜጠኞች እነዚያን ካድሬዎች ለማመን ምን ዋስትና አላቸው? እነዚህ ብዕረኛ ተዋጊዎች ከሃገር እንዲወጡ ይፈልጋል፣ ምክንያቱም ለኢሕአዴግም ቢሆን ፍርድቤት የሚገትራቸው ሰዎች ቁጥር መብዛት ለስሙ አይፈልገውም፡፡ 

እናም አንዳንዴ፣ የካድሬዎቹን የውሸት ይሁን የእውነት የማይታወቅ ‹‹ልትታሰሩ ነው›› የሚባል ነገር ሰማን እያሉ መውጣት ትክክለኛ ውሳኔ ላይሆን ይችላል፡፡ ዳዊት ከበደ ላለፉት ሦስት ወራት ከሃገር እንዲወጣ ጫና እየተደረገበት እንደሆነ በመግለጽ ሥራ ተጠምዶ ነበር፡፡ ጽሁፎቹን ሳነብ መቼ ይሆን የሚወጣው እያልኩ ነው የቆየሁት፡፡ በተለይ ዛሚ ኤፍ ኤም ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ እነዳዊት ከበደ ከሃገር መውጣት አለባቸው አሉ ካለ በኋላ፡፡ በርግጥ የአዲስ ዘመን ‹‹አጀንዳ›› ዘመቻም ቀላል እንዳልነበር እናስታውሰዋለን፡፡ የሁለቱ ሚዲያዎች ትልቅ ሚና ግን እነዚህን የነፃ ሚዲያ ሰዎች ማሳጣት መሆነኑን መዘንጋት መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡

ዳዊት ከበደ ስለመውጣት አስቦ በወጣበት ሰዓት ተመስገን ደሳለኝ ስለመግባት እያሰበ ነው፡፡ በየሳምነቱ ‹‹ካልታሰርኩ እንገናኛለን›› እያለ መሰናበቱን ተያይዞታል፡፡ ቃሉ ያሳዝናል፣ ጋዜጠኞች ካልታሰርኩ እያሉ የሚሰጉበት ሃገር ውስጥ እንደምንኖር ያስታውሰናል! የእርሱንም ከሃገር ላለመውጣት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡ ቢሆንም ግን ‹‹ፍርሃት የመንዛት›› ሚናም አለው፡፡ በየሳምንቱ ያቺን ሐረግ ባነበብኩ ቁጥር፤ ‹አሁንስ እነዚህ ሰዎች ተመስገንን አጓጉተው ሊያስቀሩት ነው እንዴ፤ ምናለ አስረው በገላገሉት› ዓይነት ቀልድ እቀልዳለሁ፡፡ ለምን እንደዚህ አሰብክ ብላችሁ የሐሳብ ሳንሱር እንዳታስቀምጡብኝ እንጂ እንዲያውም አንዳንዴ ሳስበው ‹‹ተመስገን ካልታሰርክ ፕሮፋይልህ አያድግም›› የተባለ ሁሉ ይመስለኛል፡፡

We're the ones who made you
ይህችኛዋን ንዑስ ርዕስ የተዋስኩት ደግሞ ከኤሚነም አንድ ዜማ ላይ ነው፡፡ በንዑስ ርዕሱ ውስጥ ያለነው እኛ፤ ብዙሐኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነን፡፡ እኛ የምንፈራው ሁሉንም ወገን ነው፡፡ እኛ በኑሮ ዱብዱብ እየተሸበርን ባለንበት ሰዓት መንግስት ያገኘውን ሰው ሁሉ እያሰረ ‹‹አሸባሪ›› ናቸው ሲል፤ አስተያየት መስጠት ብንፈልግም ‹‹ተባባሪዎች›› እንዳንባል ፈርተን ዝም እንደምንለው ሁሉ ተቃዋሚዎች እና ከተቃዋሚው ጎራ አሉ ብለን የምናስባቸው ሰዎች ያጠፉ ሲመስለንም አስተያየት ለመሰንዘር ስንፈልግ ‹‹የመንግስት ቅጥረኛ›› ብንባልስ ብለን እንፈራለን፡፡

በመሠረቱ ጋዜጠኞች ፖለቲከኞች አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ጋዜጠኞች ልታሰር እችላለሁ ብለው ፈርተው ሲሸሹ ይቅርታ የምናደርግላቸው፡፡ ነገር ግን በነባራዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከፖለቲከኞቻችን ይልቅ፣ ጋዜጠኞቻችን የተሻለ ታጋዮች ናቸው፡፡ እኛም የምንሰጣቸው ቦታ የነፃ አውጪ ታጋይ እንጂ የተራ ጋዜጠኛ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች ብዙዎችን ለመብት ትግል የማነሳሳት ብቻ ሳይሆን በትግሉ ተስፋ የማስቆረጥ ሚናም አላቸው፡፡ የምሬታችንን ያህል ኢሕአዴግን እስካሁን መጣል ያልቻልነው በፓርቲው ጥንካሬ ሳይሆን በእኛ ድክመት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለድክመታችን ደግሞ የተደገፍናቸው ጋዜጠኞችና ዐቢይ ተቃዋሚዎች መንሸራተት ዋነኛው መንስኤ ነው፡፡ እኛ የምንሰጣቸውን ስም እና ዝና ተጠቅመው መሸጋገሪያ የሚያደርጉን ከሆነ ደግሞ እምነት በሊታነታቸው ማንንም እንዳናምን ያደርገናል፡፡ ለዚህም ነው ይሄንን አመፃዊ ጽሁፍ በታላላቆቹ ዳዊትና ተመስገን ስም ለመጻፍ የተነሳሳሁት፡፡

በስደት ከሃገር የወጡ ፖለቲከኞቻችን፣ ትክክለኛ የስደታቸውን መንስኤ (ሃገር ቤት ይጋለጣል ብለው የሚያስቡት ሰው ካለ ምስጢሩን እንደሸሸጉ) ለሕዝብ መዳረስ በሚችል መንገድ ይፋ ያድርጉልን፡፡ አለበለዚያ እምነታችን ከጥርጣሬ አይነፃም፡፡

Comments

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...