Pages

Saturday, January 18, 2014

የአዲስ ዘመን “አዝማሚያ ጥናት” አዝማሚያ


አዲስ ዘመን ጋዜጣ (በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና በሕግ ይፍረስ ተብሎ ያልፈረሰው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ትብብር ተሰርቷል ያለውን) ጥናት፣ በፊት ገፁ ላይ፣ ባለፈው ረቡዕ ይዞ ወጥቶነበር፡፡ ጥናቱ፣ እንደአዲስ ዘመን አገላለጽ ‹‹የአዝማሚያ ጥናት›› ነው፡፡ ከዚህ በፊት የአዝማሚያ ጥናት የሚባል ነገር ሰምቼ አላውቅም፡፡ በእንግሊዝኛም ፈልጌ ስላጣሁት አገር በቀል የጥናት ዓይነት ሊሆን ይችላል ብዬ በደንብ አነበብኩት፡፡ ከአነበብኩት የተረዳሁት ነገር ቢኖር ‹የመጽሔቶቹ ጽሑፍ አዝማሚያ ምንድን ነው?› የሚለውን ለማጣራት የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ነው፤ እናም እኔም በበኩሌ የጥናቱን (ጥናት ከሆነ) አዝማሚያ ምን እንደሚሆን ለመመርመር ደግሜ አነበብኩት፡፡

የዜናው የመጀመሪያው አንቀጽ እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹በኢትዮጵያ ከሚታተሙት መጽሔቶች መካከል ሰባቱ ‹በብዙ ባሕሪያቸው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳን መሆናቸው፣ በተሳሳቱ መረጃዎች ይዘት ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ ዘገባዎች ይቀርባሉ› ሲል አንድ የአዝማሚያ ጥናት አመለከተ፡፡…››

‹‹ጽንፈኛ›› ተብለው የተመረጡት ሰባቱ ከነማን ጋር ተወዳድረው እንደሆነ አይገልጽም፤ ሰባቱ ግን አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ ዕንቁና ሊያ ናቸው፡፡ ‹‹ጥናቱ›› ከመስከረም 1/2006 እስከ ኅዳር 30/2006 ለሦስት ወር ዘልቋል ይላል፡፡ ‹‹የአዝማሚያ ትንታኔ›› እያለ የሚጠራው ትንታኔ ግን ጋዜጣው መጽሔቶቹን በገዢው ፓርቲ መነጽሩ ዓይቶ ከመዳኘቱ በስተቀር በቅጡ ለሦስት ቀን ታስቦበት የተጻፈ አይመስልም፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ መመዘኛ ተብለው የቀረቡት 6 ነጥቦች (ጥያቄዎች) ውስጥ፣ በስድስቱም ሰባቱ መጽሔቶች ብቻ ትልልቅ ነጥብ አስቆጥረው ነው ‹‹የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ›› ሆነው የተመረጡት ወይስ እንዲሁ በአዲስ ዘመን የተሰጣቸው ሽልማት ነው? ምክንያቱም፣ ትንታኔውን በሚያብራራው የአዲስ ዘመን ዜና ውስጥ ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ የተጠቀሰ አንድም መጽሔት የለም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያውኑ እነዚህ ሰባት መጽሔቶች ብቻ ተመርጠው ከሆነ ጥናቱ የተጀመረው ድምዳሜውም ይታወቅ ነበር ማለት ነው፡፡

ሌላው፣ በተነሱት የግምገማ ነጥቦች ጥሩ ያስመዘገቡት እነማን ናቸው? ጥሩ ያስመዘገቡ የሉም? ከሌሉና የሁሉም አጻጻፎች ከተመሳሰሉ፣ መሬት ላይ ያለው እውነታ እነዚያን ጽሑፎች ብቻ እንዲጽፉ አስገድዷቸዋል ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ጥናቱ ወይም መጠይቁ/መመዘኛው የተሳሳተ ነበር ማለት ነው፡፡

የተፈተሸበትን ይዘት (ጥያቄዎቹን) ደግሞ እንመልከታቸው፡-
  1. የመንግሥትን ኃላፊዎች የግል ስብዕና የሚነኩ፣
  2. የአመጽ ጥሪዎችን የሚጠሩ፣
  3. ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ፣
  4. የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ፣
  5. የኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚክዱ፣
  6. ሕገ መንግሥቱን የሚያጣጥሉ፣
‹‹የአዝማሚያ ጥናቱ›› ዜና እንደሚጠቁመው ከሆነ መጽሔቶቹ በእነዚህ ነጥቦች ተመዝነው ወደቁ እንጂ፣ ሙሉ ይዘታቸው ተፈትሾ በነዚህ ላይ ሲያተኩሩ አልተገኙም፡፡ መጽሔቶቹ መንግሥትን መጠ’የቅ ባለበት ቦታ ላይ የጠየቁበትን ጽሑፍ እንዲሁ አላግባብ (ወይም እንደዜናው አገላለጽ ‹‹መረጃዎችን አዛብቶ በማቅረብ›› እና ‹‹የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ››) መሆኑን ጥናቱ የጠቆመበት መንገድ የለም፡፡ ለምሳሌ፣ በሦስቱ ወራት ውስጥ ቆንጆ 80 ጊዜ፣ ሎሚ 66 ጊዜ፣  አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት እና ጃኖ እያንዳንዳቸው 55 ጊዜ፣ ሊያ 35 ጊዜ እና ዕንቁ 30 ጊዜ ‹‹የአመጽ ጥሪዎችን የሚጠሩ›› ጽሑፎችን አትመዋል ተብሏል፡፡ በድምሩ 376 የአመጽ ጥሪዎች ተጽፈዋል ማለት ነው፡፡ የሚገርመው ነገር፣ በሦስት ወራት ውስጥ የተጠሩት የነዚህ ሁሉ የአመጽ ጥሪዎች ውጤት ምንድን ነበር? መንግሥትስ ምን ያህል ሆደ ሰፊ ቢሆን ነው ሕገ-ወጥ የአመጽ ጥሪ እያየ የሚያልፈው?

በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአንድ ሕትመት ብቻ ተደጋግመው ተጽፈዋል ያሏቸውን ጽሑፎች ቁጥር ሲያስቀምጡ፣ መጽሔቶቹ በሦስት ወራት ውስጥ በወጡት እትሞቻቸው በሙሉ በየሳምንቱ/በየ15ቀኑ ዕኩል ጊዜ ያንን ነገር ጽፈዋል ማለት ነው? ወይስ አማካዩ ነው የተቀመጠልን? ወይስ በአንድ እትም በብዛት የጻፉበት? ለምሳሌ አዲስ ጉዳይ መጽሔት ‹‹የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ›› 7 ጽሑፎችን ጽፏል ሲባል ምን ማለት ነው? በሦስት ወራት ውስጥ 77 ጽፏል ከተባለ፣ በሦስት ወራት ውስጥ በወጡት 11 እትሞቹ ያወጣቸው አማካይ ነው ወይስ በየሳምንቱ ሰባት፣ ሰባት የፖለቲካ ስርዓቱን የሚያጨልሙ ታሪኮች ይጽፋል ማለታቸው ነው? አማካይ ከሆነ ለሁሉም ድፍን አማካይ (even) ቁጥር የሚመጣበት ጥናት ምን ዓይነት ነው? ግኝት ተብለው የተጠቀሱት ቁጥሮች በሙሉ እንዴት ተካፋይ ሆኑ፣ ለዜና አቀራረቡ እንዲመች ወይስ እውነትም ተጠንቶ የተገኘ?

መጽሔቶቹ ‹‹የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ደምጽ›› ናቸው ተብለዋል፡፡ ጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲ የሚለው አንድን ነጠላ ፓርቲ የሚመለከት አይመስልም፤ ይልቁንም የተለየ ባሕሪ ያለው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ናቸው ይላል በጥቅሉ፡፡ ለመሆኑ ጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባለው ብያኔው ምንድን ነው? ፓርቲዎቹስ የየትኛው የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ናቸው? የትንታኔው ዜና በዚያው ሲቀጥል የዜና ምንጮቹ የታወቁ ናቸው ይልና፤ ኒዮ-ሊበራሎችን እና በሽብርተኝነት የተፈረደባቸው ግለሰቦችና ቡድኖችን በድፍኑ ይጠቅሳል፡፡ ኒዮ-ሊበራሎችን እንደዜና ምንጭ መጠቀም በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ዕኩል በወንጀልነት የተቀመጠበት አግባብ፣ ሙሉ የጥናቱን መመዘኛ የተንሸዋረረ ዓይን ያጋልጣል፡፡

አዲስ ዘመን፣ በዚህ በጥናት ስም መጽሔቶቹን በወንጀለኝነት በፈረጀበት ጽሑፉ ያሳበቀው እውነት ቢኖር ምርጫ ከመቃረቡ በፊት የገዢው ፓርቲ ሊወስዳቸው የሚፈልጋቸውን እርምጃዎች ነው፡፡ መጽሔቶቹ ‹‹የቀለም አብዮት ባስተናገዱ አገሮች የታየው ቅኝት የሚከተሉ ሆነው ይታያሉ›› የሚለው ዓረፍተ ነገር የጥናቱን ዓላማ አጠያያቂ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም የቀለም አብዮት በመባል የሚታወሱት የአመፅ-አልባ አብዮቶች፣ ብዙዎቹም ምርጫዎች ፍትሐዊና ሚዛናዊ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጫና ማሳደር የቻሉ እና በውጤታቸውም ዴሞክራሲን ያጎናፀፉ አብዮቶች ናቸው፡፡ እነ አዲስ ዘመን ግን በገዢው ፓርቲ ሕሊና በማሰብ የቀለም አብዮት አዝማሚያ በማለት ለፍትሕ እና ሚዛናዊነት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የፊት ገጻቸውን ሞልተው መጡ፡፡ እነሆ መንግሥትን መተቸት ጽንፈኝነት ሆኖ ተበየነ።

እንደመደመደሚያ ምክር፣ አዲስ ዘመን ይህንን የፍረጃ አዝማሚያውን ትቶ የገዛ ይዘቱን ጥራት ለማሻሻል ጥረት ቢያደርግ ከጨረታና ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ማተሚያ ብሎም ከመጠቅለያነት ተራ ወጥቶ ለመነበብ የሚበቃ የሕዝብ ንብረት ለመሆን ይበቃ ነበር፡፡ 
---

ይህ ጽሑፍ በዛሬው የአዲስ ጉዳይ መጽሔት እትም ላይ የታተመ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment