Pages

Wednesday, September 7, 2016

EthiopiaProtests: ‘የበሰለው ፍሬ’

ሐምሌ 2006 ከማዕከላዊ ወደ ቂሊንጦ ስዛወር፣ ዞን ሁለት ነበር የተመደብኩት። በወቅቱ በሽብር የተከሰሱ ብዙ ጎንደሬዎች ነበሩ። አልጋው ሥር "ደቦቃ" በማስተኛት ያስተናገደኝም ቢራራ የተባለ ጎንደሬ ነበር። ከዚያ በፊት ከሥሙ በስተቀር የማላውቀውን ፋሲል ደሞዝን አንድ ዘፈን ያስተዋወቀኝ እሱ ነው። ዘፈኑን እስከዛሬ ባልሰማውም ሁለቱን ስንኞች ግን በቃሌ ይዣቸዋለሁ። "አረሱትን አልሰማኸውም?" አለኝ ድጋሚ 'አልሰማሁትም' አልኩት ባለማወቄ ሲገረም አይቼ እያፈርኩ፤ ስንኞቹን ነገረኝ።

"አረሱት ይሉኛል የመተማን መሬት፣
ያውም የኛን ዕጣ
እነሱ ምን ያርጉ ከኛ ሰው ሲታጣ።"

ሰሞኑን 17 ያህል አርቲስቶች ለአዲስ ዓመት ዋዜማ አቅደውት የነበረውን የሙዚቃ ድግስ በሐዘናችን ምክንያት መሰረዛቸውን ሰማሁ። አርቲስቶቻችን ሰው እየወጣቸው ነው ማለት ነው የሚል ስሜት ተሰማኝ። እኛው ያከበርናቸው አርቲስቶች የሕዝባችንን ሐዘን ማክበር ከጀመሩ ትግላችንንም የሚቀላቀሉበት ግዜ ሩቅ አይሆንም፣ እኛም 'አርቲስት' የሚለውን ቃል ስድብ ከማድረግ እንቆጠባለን እያልኩ ሳስብ ሳልሰማቸው ያመለጡኝ ብዙ የትግል ዘፈኖች እንዳሉ ተረዳሁ።

የኦሮምኛ ዘፋኞች ዘፈንን የትግል መሣሪያ ማድረግ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ሁሉም ዕኩል መደመጥ አልቻሉም እንጂ ባለፈው አንድ ዓመት በአማካይ በቀን አንድ የትግል ዘፈን እየለቀቁ ነበር። ከሁሉም ግን በጣም ተወዳጅ የሆነውና ቋንቋውን የማታውቁትን ሳይቀር የሚወዘውዘው የሀጫሉ 'ማለን ጅራ' ነበር፤ ስለዚህ ዘፈንም መጀመሪያ የሰማሁት እዚያው ቂሊንጦ በመጣ ወሬ ነው።

ኪነ ጥበብ ትግሉን ሲቀላቀል የትግሉን መብሰል የሚያሳይ ምልክት አድርጌ ነው የማየው። በአዲስ አበባ መንግሥትን በገደምዳሜ የሚወርፉ ትያትሮች ከሌሎቹ የበለጠ ብዙ ተመልካች አላቸው፣ የመግቢያ ዋጋቸውም ውድ ነው። ምክንያቱም የሕዝቡን ዝምታ ይናገራሉና። አሁንም፣ አርቲስቶቻችን የትግል ዘፈኖችን ሲዘፍኑ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያላቸው ዋጋ ይጨምራል።

ስለፋሲል ደሞዝ እነዚያ ስንኞች ሳወራ ወንድሜ "‹እንቆቅልሽ› የሚለውን አታውቀውም?" አለኝ። አላውቀውም ነበር። ይገርማል ፋሲልን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዘፈኑ ሰማሁት፣ አየሁት። ክሊፑ ላይ፣ ሴቲቱ እንቆቅልሽ ትጠይቀውና መልሱን ባለማወቁ "አገር ስጠኝ" ትለዋለች፣ እሱ ግን እንዲህ ይላታል።

"እንቆቅልሽ፣
በሰም ለበስ ቅኔ፣
አሁን ገና፣ መጣሽብኝ ባይኔ።"

ፋሲል "በይ ደስም አላልሽኝ ጨዋታ ቀይሪ" እያለ ሲያንጎራጉር የሆነ ልብን የሚኮረኩር ኃይል አለው። ወንድሜ "ይሄ ይገርምሃል እንዴ?" አለኝና የይሁኔ በላይ አዲሱን ዘፈን አስደመጠኝ። ለወትሮው፣ ይሁኔን ከፍቼ የማዳምጠው ዘፋኝ አልነበረም። ይሄንን 'ሰከን' የሚለውን ዘፈኑን ስሰማው ግን የማላውቀው ስሜት ልቤን አተራመሰው።

"…ሰከን በል፣
ሰከን ማለት፣
ነው ጨዋነት
ሰከን ማለት፣
ነው ጀግንነት
ወታደሩ፣ ሰከን በል
አፈሙዙን ሰከን አርገው፣
ቃታህንም እንዳትስበው፣
ባዶ እጁን ነው፣ የሚጮኸው፣
ሠላማዊ፣ ወንድምህ ነው፣
ሰከን በሉ፣ ሕዝቤን ተዉት
ድምፁን ስሙት፣ አትግደሉት…"

በማለት የመንግሥትን ሀጢያት "…ውጉዝ ከመአርዮስ" ብሎ በማውገዝ፣ ስለኅብረት ሲባል፣ "በወላጁ ጥፋት፣ አይወቀስ ልጁ" እያለ መስከንን ይመክራል።

ናቲ ማን ቀጠለ። ናቲ ደግሞ በኦሮምኛ ስልተ ምት "አሁን ተነካሁ" እያለ፣ እሽክም፣ እሽክም አስባለኝ።

"ኦሮሞን፣ ኦሮሞን ሲከፋው
አሁን ተነካሁ
አማራን፣ አማራን ሲከፋው
አሁን ተነካሁ…"

ከዚያ ደግሞ የመስፍን በቀለ ዜማ ቀጠለ። በቀረርቶ የሚጀምረው የመስፍን "ሠላም ለኢትዮጵያ" አዲስ ትውልድ መጥቷል ይላል። ወራደሩንም እንዲህ ይለዋል፦

"ወታደሩ ጓዴ፣ አንተ ያገሬ ሰው፣
ወንድምክን አትግደል፣ ብረትክን መልሰው።…"

ሌንሴ ለሜሳ ደግሞ ጆሮ በሚለሰልስ ድምፅዋ፣ "ተነቃንቋል" ትላለች፣

"ተነቃንቋል ጥርሱ ይነቀል፣
ይነቀል፣
ይነቀል ይውለቅ
የአሉላ የጆቴን ትከሉበት ወርቅ፣
ክፍተቱ እንዲሞላ ውበቱ እንዲደምቅ።…"

መክፈቻዬ ላይ የጠቀስኩትን ፋሲል ደሞዝን መዝጊያም ላድርገው። በቅርቡ በለቀቀው ዘፈኑ እንዲህ ይላል፣

"…ኧረግ ወዲያልኝ (ወዲያልኝ)
ኧረግ ወዲያልኝ (ወዲያልኝ)
በቃ ሒድልኝ (ሒድልኝ)
25 ዓመት አላገጥክብኝ።…"

ክብር ለእነዚህ አርቲስቶች ይሁን!
አሜን።

No comments:

Post a Comment