Pages

Saturday, June 9, 2012

“አሸባሪ” ፊልምም ይታገድ ጀመር

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ከዚህ ቀደም ‹የባሕር በር› በሚል ርዕስ በጥላሁን ጉግሳ የተሰራው የአማርኛ ፊልም በኢቴቪ ማስታወቂያው እንዳይታይ ታግዶ የአንድ ሰሞን አወዛጋቢ አጀንዳ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የፊልሙ ዋና ገጸ ባሕሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ‹‹በእኔ እምነት፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ቀን መልሰው አንድ ይሆናሉ፡፡›› ብለው መናገራቸው ነው፡፡ ያለምንም ማጋነን መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንድ ሆነው ከሚያዩ ከሚና ሕንጻ ላይ ዓይናቸው እያየ ቁልቁል ቢወረወሩ ይመርጣሉ፡፡ የሻዕቢያን የጫካ ውለታን ኤርትራን እንደተገነጠለች በማስቀረት ነው የሚያረጋግጡት፡፡ እንዴያውም አንዳንዴ ሳስበው መለስ ከስልጣን መውረድ የማይፈልጉት ለሻዕቢያ እንደርሳቸው ታማኝ የሚሆን ኢትዮጵያዊ መተካት ስለሚከብዳቸው ይመስለኛል፡፡

ወደቀደመው ነገራችን ስንመለስ ትላንት አርብ፣ በኤድናሞል ማቲ መልቲፕሌክስ ሲኒማ መታየት የጀመረው ‘The Dictator’ የተሰኘ ፊልም እንዳይታይ ታገደ የሚል ዜና አነበብኩ፡፡ መውጣቱን ከሰማሁ ጀምሮ በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ይህ እምባና ሳቅ ያዘለ (comedy satire) ፊልም ሦስት ቀን እንኳን እንዳይታይ በመደረጉ ለእሁዴ ሳይደርስልኝ ቀርቷል፡፡ ግን ለምን የሚለው ጥያቄ አጭር ግምቴን እንደሚከተለው አስቀምጣለሁ፡፡  

በባሮን ኮኸን በገዛ ፊልሙ መሪ ተዋናይ የሆነበት ይህ ስላቃዊ ፊልም የጋዳፊ እና የሳዳም ሁሴን ድቅያ የሆነ አምባገነነዋ ገዢ ሆኖ የሚጫወት ገጸ ባሕሪ ፈጥሯል፡፡ ከፊልሙ ቅኝቶች ላይ ለማንበብ እንደሞከርኩት በርካታ የአምባገነኖች ባሕርያት የተሰገሰጉበት ይህ ፊልም፣ ከአንድ ወዳጄ እንደሰማሁት ደግሞ የኛውን ‹መለስ› ዜናዊን ቁልጭ የሚመስሉ በርካታ ትዕይንቶች አሉት፡፡ እናም የፊልሙ መታገድ ዋነኛ ምክንያት ከዚህ ውጪ ምን ሊሆን ይችላል?

በርካታ ጋዜጦች ታገዱ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ታገደ፣ በመንግስት ያልተወደዱ ዘፈኖች በመንግስት ይዞታ ስር ባሉ ሬዲዮ ጣቢያዎች እንዳይተላለፉ ታገዱ፣ አንዳንድ መጽሃፍቶች ሜጋ መጽሃፍት ማከፋፈያ ውስጥ እንዳይገቡ ታገዱ፣ የተቃዋሚ ድረገጾችና ጦማሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበቡ ታገዱ፣ የጀርመንና የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሰሙ ታገዱ፣ …. ታገዱ፣ ታገዱ፡፡

እነዚህ ሁሉ ነገሮች መታገዳቸው የሚነግረን አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ራሳቸውን ከነሞቡቱ፣ ሙአመር… (The ‘M’ Dictators) ሳይሆን ከነማንዴላ (The Democrats) ጋር ማመሳሰል ሲመኙ የነበሩት መለስ ዜናዊ፣ ሕዝባቸውን ነፃ ለማውጣት ትምህርታቸውን አቋርጠው “የነፃ አውጪ ትግል” የጀመሩት መለስ ዜናዊ፣ አምባገነንነታቸው ከተረጋገጠላቸውና የአምባገነንን መጨረሻ ከቀመሱት ሳዳም ሁሴን እና ሙአመር ጋዳፊ እንዳንዱ መሆናቸውን እርሳቸው ራሳቸውም ሆኑ የማገዱን ሥራ እየተከታተሉ የሚፈጽሙላቸው ተከታዮቻቸው ማመናቸውን ያረጋግጣል፡፡

1 comment:

  1. Highlight of the Dictator from you tube
    http://www.youtube.com/watch?v=E-2PVh-Ht3U

    ReplyDelete