Skip to main content

የዐቢይ አሕመድኹለት ዓመታት!

ከወር በፊት፣ ከጓደኞቼ ጋር የሆነ ኮንሰርት ልንገባ በር ላይ ስንደርስ ከኛ የቀደሙት ትኬታቸውን ሊያስመልሱ ሲከራከሩ ደረስን። በር ላይ ያለው ሰውዬ ለማግባባት በማሰብ ትኬት ይመለስልን የሚሉትን ወጣቶች "የኛ የመጀመሪያው ኪሳራችን እናንተን ማስከፋታችን ነው" አለ። አንዱ ጎረምሳ ከአፉ ነጥቆ "ባክይ ዐቢይ አሕመድ አትሁንብኝ" ብሎ ሁላችንንም በሳቅ አፈረሰን።

እዚሁ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "ቅቤው" እያሉ ሲጠሯቸው እሰማለሁ፤ በአራዳ ልጆች አነጋገር "ፎጋሪው" እንደማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያረጋገጧቸው ነገሮች ቢኖሩ በንግግራቸው አባባይ መሆናቸውን ነው።

ንግግራቸው ታዲያ ብዙዎችን ያስደስት እንጂ፥ የኔ ቢጤዎችን ግን ብዙ ጊዜ ያበሽቃል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንግግሮች ከፕሮቴስታንት አስተምህሮ፣ ከመንፈስ ማነቃቂያ መጽሐፍት ምክሮች እና ከሳይንሳ ለበስ ግምቶች አያልፉም። ዐቢይ ለጆሮ የማይረብጥ ነገር የሚያወሩት ስለ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲያወሩ ብቻ ነው ባይ ነኝ

"አዳኝም መንገድም"

ዐብይ አሕመድ የኖሩበት የፕሮቴስታንት ባሕል ሳይጫናቸው የቀረ አይመስለኝም፥ ችግሮችን ሁሉ በስብከት እና በምክር እንዲሁም በመተቃቀፍ መፍታት የሚቻል ይመስላቸዋል። ብዙ ንግግሮቻቸው በምክር የተሞሉ ናቸው። ብዙዎቹ መግለጫዎቻቸው እና ንግግሮቻቸው ውስጥ የአማካሪያቸው ሙዓዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት የረዥም ዓመታት የተረታ ተረት ዘይቤዎች ይስተዋላሉ። (አንድ ጊዜ "እየወጋች ምትጠቅመው መርፌ" መስለው ያወጡት መግለጫ ሥር "እናመሰግናለን ዳንኤል ክብረት" የሚል አስተያየት አይቼ እስከዛሬ ያስቀኛል።) ይህ ዘይቤ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ከሥነ ምግባር ጦት የመነጨ ነው ከሚል የሚመነጭ ስለሆነ፥ እንዲህ ብትሆኑ እና ብታደርጉ ኖሮ እንዲህ አትሆኑም የሚሉ ናቸው። በዚህም ምክንያት መንግሥት የሥነ ምግባር አስተማሪ፣ መካሪ ወላጅ ወይም አሳዳጊ (paternalistic) ሚና ለራሱ ሰጥቷል። በዚህ አሠራር ሕዝብ ታዳጊና አጥፊ ሕፃን ነው ማለት ነው። ለዚህ ነው መንግሥት በቲቪ የምታዩትን ማስታወቂያ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የምታነቡትን መረጃ እኔ እመርጥላችኋለሁ ማለት እየቃጣው ያለው።

ዐቢይ አሕመድ በፓርቲ ውስጣዊ የሥልጣን ትግል የተዋጣላቸው መሆኑ ግልጽ ነው፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብልፅግና ፓርቲን በገዛ ፍላጎታቸው ልክ ለመመሥረት የፓርቲ አጋሮቻቸውን ሁሉ ያስገበሩበት መንገድ ለዚህ እማኝ ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረ የእኩያሞች ትግል ለማጧጧፊያነት ተጠቅመውበታል። በዚህም የኢትዮጵያን የሥልጣን ቁንጮ ተቆናጠዋል። ነገር ግን ዘላቂ የዴሞክራሲ፣ የብልፅግና እና የሰላም ፍኖተ ካርታ ማውጣት ላይ በተግባር ራሳቸውን ማስመስከር አልቻሉም። በሥልጣናቸው አፍላ ጀንበር ሰሞን ከተቃዋሚዎች ጋር የነበራቸው ወዳጅነትም ይሁን ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበራቸው የፍቅር ግንኙነት የጋራ ጠላታቸውን ሕወሓትን ለማጥቂያና ሥልጣን ማደላደያነት ከመዋሉ በቀር ዘላቂ ሥምምነት እና ሰላም ማስፈኚያ ሲያደርጉት አላየንም። ይልቁንም በዚህ አደራ የተሰጣቸውን የሰላም ኖቤል ሽልማት የብፁዕነታቸው መለኪያ አድርገው ወስደውታል ብዬ መጠርጠር ጀምሬያለሁ። በቅርብ የማግኘትና የማነጋገር ዕድሉ የገጠማቸው አንድ ሰው ዐቢይ አሁን ያሉበትን ሁኔታ የገለጹልኝ፥ "Arrogant and Ignorant" ሆነዋል በሚል ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዓለም ዐቀፍ ሜዳዎች ጎልቶ መውጣት እንደ ዓላማ አንግበዋል፤ በኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድሮች ውስጥ ያለውን ኩርፊያ ቸል ብለው፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት እየሞከሩ ነው። ሙከራው አይከፋም፣ በራሳቸው ንግግር ‘እኛ በሰላም እንድናድር፣ ገረቤቶቻችን ሰላም ማደር አለባቸው’። በቅርቡ በሶማሊያ እና ሱማሌላንድ አመራሮች መካከል ዕርቅ ለመፍጠር መሞከራቸው ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን ከአካላዊ መተቃቀፍ ተጨማሪ ነገር መያዝ እንዳለባቸው አማካሪዎቻቸው ሊያስታውሷቸው ይገባል። ባለፈው ዓመት ደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የሆኑትን ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻርን በግፊት ሊያስተቃቅፉ የሞከሩበት መንገድ አሳፋሪ ትዕይንት ነበር።

ዐቢይ አሕመድ "የቄሳርን ለቄሳር" የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክርም ዘንግተዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት መንግሥትን እንደ ወላጅ አሳዳጊ፣ ሕዝብን እንደ ታዳጊ ልጅ የሚመለከት አቀራረባቸው በፖሊሲ እና ሕግ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን እንዲያወጡ አድርጓቸዋል። የሞራል አባትነቱ ደግሞ ሃይማኖታዊ ይመስላል። ባለፈው ከአፍሪካ ኅብረት ጥቂት መሪዎች ጋር በጋራ ፀሎት ካደረጉ በኋላ "Jesus Christ is the ultimate solution for African problems” ማለታቸውን ሰምቼ ጥርጣሬዬን አረጋግጦልኛል፤ መቼም መሪዎች የፈጠሩትን ችግር እግዜር ይፈታልናል ብለው እንደመጠበቃቸው ያለ አስደንጋጭ ዜና የለም።

ዐቢይ በቤተ መንግሥት

ዐቢይ "ደሞዜ 4 መቶ ዶላር ብቻ ነው" ብለው ያማረሩበት መድረክ አለ። እዚያው መድረክ ላይ "ሁሉም የከፈለኝ ይመስል ይጨቀጭቀኛል"ም ብለዋል። የምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ትልቅ ሙዚየም (‘አንድነት ፓርክ’ ብለው የሰየሙትን) አስገንብተዋል። ፓርኩን የጎበኙት ሰዎች ሁሉ አድንቀውላቸዋል። አፈፃፀሙንም የእርሳቸውን የዕቅድ አተገባበር ብቃት ማሳያ አድርገው ወስደውታል። እርሳቸውም በሁሉም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይህንኑ የደሰኮሩበት ጊዜ አለ። የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርኩ እየተገነባ ሳለ ላገኟቸው ሰዎች "ቤተ መንግሥቱን ለማሠራት ከመንግሥት ሰባራ ሳንቲም አልወሰድኩም" ብለዋል። አሁንም ለብልፅግና ፓርቲ የገቢ ማሰባሰቢያ የመንግሥት ሥልጣኔን አልተጠቀምኩም እንደሚሉ አልጠራጠርም። የሆነ ሆኖ ደሞዛቸው፣ በየወሩ ከሚከፈላቸው እጅግ በብዙ እጥፍ የበለጠው ጥቅማ ጥቅማቸው እንደሆነ እናውቃለን። የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራም የሚሠራው ስለደሞዙ አይደለም። በሌላ በኩል ፓርኩን ለማስገንባትም ገንዘብ የሚሰጧቸው የውጭ አገራት ወዳጆቻቸው በግል እርሳቸውን ወደው አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ሥም ነው። እነዚህን ሐቆች መዘንጋት የመጀመሪያው የመንግሥት መሪ ሀጢያት ነው።

ዐቢይ አሕመድ በውጭ

ዐቢይ አሕመድ ብልጭ ድርግም ከሚል ትችት በቀር በውጭ አገራት ብዙኃን መገናኛዎች በጥቅሉ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ መልካም ሥም አፍርተዋል። ሥማቸው ሲነሳ አብሮ የሚነሳው የኖቤል የሰላም ሽልማት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሪፎርም ማምጣታቸው፣ ሴቶችን ወደ አመራርነት ከፍ ከፍ ማድረጋቸው እና የዛፍ ተከላ አብዮት መጀመራቸው ናቸው። በእርግጥ እነዚህ ነገሮች ላይ አስተዋፅዖ አልነበራቸውም ብሎ መካድ አይቻልም። ከኤርትራ ጋር መዝለቁን ባናውቅም ሰላም አስፍነዋል፣ ራሳቸውንና ፓርቲያቸውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ባይሆንላቸውም፥ ለዴሞክራሲ ሪፎርም የሚበጁ ለውጦችንም ጀማምረዋል፣ ተተኪ ሴቶችን በእየርከኑ ማዘጋጀቱ፣ እንዲሁም በንግግራቸው Gender-sensitive መሆን ባይሳካላቸውም፥ ካቢኔያቸውን በፆታ ውክልና አመጣጥነዋል፣ የተባለውን ያህል ቁጥር ማስተከላቸው ባይዋጥልኝም፣ ችግኝ ተከላን እንደፋሽን ማስመሰላቸው ይደነቅላቸዋል።

በነዚህ ሁሉ መሐል ግን የኢትዮጵያውያን የረዥም ጊዜ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚችል ስርዓተ ማኅበር ግንባታ ቸል ተብሏል። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ የገጽታ ግንባታ ላይ ተጠምዷል። ከፖሊሲ ይልቅ ማባበያ ንግግርን መርጧል፤ እናም፣ በዚህ ሰዓት፣ ከምንጊዜውም በላይ ወቃሽ ያስፈልገዋል።

Comments

  1. Who shall tell you about your arrogance

    ReplyDelete
  2. ቅቤው ማለት አፈ ቀላጤ እንደ ማለት ነው! Not ፎጋሪ!
    ሌላው አሪፍ እይታ ነው!

    ReplyDelete
  3. It has good points as i belive criticise any government will be good for peoples benefit but who is lacking policy ? Abiy or his oppositions, and as a leader preaching good things will not be a problem i think

    ReplyDelete

Post a Comment

Popular posts from this blog

The "Corridor Development" is a Façade of the Prosperity Party

Befekadu Hailu I have seen a news report claiming that 40% of central Addis Ababa will be demolished for the corridor development; I am not able to confirm the validity of the news but it sounds real to me given the size of massive operations in the demolition of old neighborhoods and construction of bike lanes, green areas, and glittering street lights. I like to see some beauty added to my city but cannot help mourning the slow death of it too. Addis Ababa was already in a huge crisis of housing and the demolition of houses is exacerbating it. Apparently, Prime Minister Abiy Ahmed is eager to showcase his vision of prosperity by demonstrating how fast his administration can do magic by beautifying the front sides of the streets with lights, new pavements, and painted fences ("to fake it until he makes it" in my friend's words). Therefore, he and his party do not care about the miserable human stories behind the scenes and they will harass you if you tell it (Azeb Woku...

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል። “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።” (ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ) ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን ...

የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ

በፍቃዱ ዘ . ኃይሉ “የአዲስ አበባ ብሔርተኝነት” ቢኖር ኖሮ መሪው ልጅ ሚካኤል ይሆን ነበር። አሁን አሁን እሱ ስለ አዲስ አበባ የዘፈናቸውን ዘፈኖች ቁጥር ራሱ በትክክል መቁጠር ይቸግረኛል። ለአዲስ አበባ ከተዘፈኑ ዘፈኖቹ ውጪም በየዘፈኑ ውስጥ የሚጨማምራቸው መልዕክቶች በራሳቸው መወድሰ አዲስ አበባ ናቸው። ለምሳሌ፣ በቅርቡ በለቀቀው ‘አዲስ አራዳ’ በተሰኘው አልበሙ ውስጥ ‘የድሬ ልጅ’ የሚል ዘፈን አለው። ዘፈኑ የተዘጋጀው ያው የአዲስ አበባ እህት ተደርጋ የምትቆጠረውን ድሬ ዳዋን ለማወደስ ነበር። ልጅ ሚካኤል ግን የአዲስ አበባ ፍቅሩ ያመልጠውና የሚከተለውን ያቀነቅናል፦ “መጣልሽ በሏት፣ ድሬ ድረስ፣  ከአዱ ገነት፣ ከሸገር፣ ከአዲስ ደረሰ፣... የሸገር ልጅ አራዳ ነው፣ ሰው አክባሪ፣ ሰው ወዳዱ፣ ቀላጅና ተረበኛ፣ ፍቅር ይዞ የሚተኛ፣ ‘አለው’ የለ፣ ‘የለው’ የለ፣ ከሁሉ ጋ፣ ግባ ጀባ...፤” ፤ ልጅ ሚካኤል በዚህ አልበሙ ብቻ አዲስ አበባን የሚያውድሰባቸው ሌሎችም ዘፈኖች አሉ፤ ‘ አዲስ አራዳ ’ የሚለው የአልበሙ መጠሪያ እና ‘ሸገር’ የሚሉት ዘፈኖቹ ዋነኞቹ ናቸው። ታዲያ እንዲህ በአዲስ አበባ ፍቅር የሚቃጠለው ልጅ ሚካኤል "ሊነግረን የሚፈልገው ምንድን ነው?" የሚለው ጥያቄ ደጋግሞ ይመጣብኛል። ይህ የልጅ ሚካኤል አዲስ አበባ ምንነትን ለመረዳት የሚጥር ፖለቲካዊ መጣጥፍ ነው። ‘አዲሱ አራዳ’ ማነው? በዚህ ዘፈኑ በብዙዎቻችን ዕድሜ የትዝታ ማኅደር ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በአዲስ አበባ ልማት ሥም የፈረሱ እና እየተረሱ ያሉ ሰፈሮችን ሥም ያነሳሳል። ዘፈኑ በግጥሙም በዜማውም፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ያለበት ነው። ምሳሌ እንውሰድ፦ “ጨርሰሽ ስትወጪ ከቡፌ ዳ’ላጋ፣ ጠብቂኝ እንዳልል፣ ቆመሽ መሐሙድ’ጋ፣ አገር ...