ሰሞኑን በሞት
ስልጣናቸውን ስለለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ያለኝን ትዝታ ‹የመለስ ሁለት መልክ› በሚል
ጽፌው ነበር፡፡ ጽሑፉ ውስጥ የመለስ አስተዳደር በተለይ የተመቻቸው የብሔር አባላት እንዳሉ በስም በመጥቀሴ ‹‹ዘረኛ ነህ›› የሚል
ብዙ አስተያየት ተሰንዝሮብኛል፡፡ እነሆ ይህ አስተያየትም ይህን ጽሑፍ ወልዷል፡፡ ነውርን ማን ፈጠረው? በመጀመሪያም፡-
ነፃነት እና ልቅነት
ሐሳብን የመግለጽ
ነፃነት ለድርድር የማይቀመጡለት አጀንዳ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ሰው ሐሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴ በሕግ ተደንግጓል ወይም ተፈጥሮ
ያጎናፀፈኝ ነው በማለት እንዳሻው አይናገርም፡፡ በተለይም ሐሳቡ የሚቀርብበት ሚዲየም ሰፊ ሲሆንና ብዙ ተደራሲዎች ሲኖሩት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ጥንቃቄ የሚያስፈልግበት በርካታ ምክንያቶች
አሉ፤ ከነዚህም ውስጥ የሕዝብን አቅጣጫ ላለማሳት፣ መረንነትን ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት እና አሁን ስለሆነው ሳይሆን ነገ እንዲሆን
ስለምንፈልገው በመሳሳት (ሳ ላልቶ ይነበብ) ነው፡፡ ሁሉንም በሒደት ወደታች አብራራቸዋለሁ፡፡
‹የሕዝብን
አቅጣጫ ላለማሳት› ያልኩት ሐሳባችንን የምንገልጽበት አገባብ (context) ተደራሲያኑ ጋር ሲደርስ ሌላ አንድምታ እንዳይኖረው
የሚለውን ነው፡፡ ምናልባትም ያለፈው ጽሑፍ ውስጥ ‹ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥ ከተሰሩ ሕንፃዎች መካከል አብዛኛዎቹ
የትግራይ ልጆች ንብረት ናቸው› ማለቴ በአንባቢው ዘንድ የትግራይ ልጆች ሁሉ በኢሕአዴግ ስርዓት ተጠቅሟል የሚል ትርጉም ከሰጠ አቅጣጫ
አስቷል ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እኔ በፃፍኩበት መንፈስ የትግራይ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንፃር ካላቸው ድርሻ (proportion)
ጋር ሲወዳደር በስልጣን እና በከተማ ሃብት ይዞታ ላይ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው የሚል ነው፡፡
ይሄንን እውነታ
እንዳላነሳ የሚያስገድደኝ አካል ሊኖር አይችልም፤ የአገላለፁ አቀራረብ ላይ ውይይት ሊደረግ ግን እንደሚችል አልደራደርም፡፡ ይልቁንም
ይህንን ጉዳይ የማይወራ ‹‹ነውር›› ነው የሚሉት (የሚያነውሩት) የስርዓቱ ፈጣሪዎች ወይም ተጠቃሚዎች ራሳቸው እንደሆኑም ይሰማኛል፡፡
‹መረንነትን
ወይም ልቅነትን ላለማስፋፋት› ያልኩትን በወሲብ እና ወሲብ ነክ ጉዳዮች ብገልፀው ይበልጥ ይብራራልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በባሕላችን፣
መወሻሸምም ሆነ ወሲባዊ ውስልትናዎች
ዝነኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን በጥቅሉ ስለወሲብ ነክ ጉዳዮች በአደባባይ ማውራት ነውር ነው፤ ስለዚህ ስለመፍትሄዎቹ እንኳን ማውራት
አልተቻለም፡፡ በመሰረቱ በኔ ሐሳብ፣ ከድርጊቱ የከፋ ወሬ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገር ግን የድርጊቱ ፈፃሚዎች እንዲነውር አድርገው
ስር አሰድደውታል ስለዚህ አይወራም፡፡ ለምን የሚል ጥያቄ ሲነሳ የሚሰጠው ዘመናዊ ተብዬ መልስ በዚህ ጉዳይ የሚወሩ ጉዳዮች ልቅነትን
ወይም መረንነትን ያስከትላሉ ነው፡፡ እንዲህ አድርጉ ሌሎችም እንዲህ እያደረጉ ነው ካላሉ ወይም አደራረጉን የሚያስተዋውቅ ማስታወቂያ
ካላወጡ ነውሩ ምኑ ላይ ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ባደባባይ ላይ እንዳይውል የሚታገሉት የድርጊቱ ባለቤቶች እና ለውጡ እንዳይመጣ የሚፈልጉት
ነውረኞች ራሳቸው ናቸው፡፡
ስለዚህ አስተሳሰቡ
ራሱ የተሳሳተ ከሆነ (ከሕዝቦች ሕሊና ውስጥ መኖሩ እሙን ስለሆነ) በትክክለኛው ለማረም፣ አልያም ካልተሳሳተ መፍትሔ ሐሳቦችን ለማፍለቅ
ሐሳብን በአግባቡ መግለፅ ሊያስፈርጅ ፈፅሞ አይገባም፡፡
እያስመሰሉ መኖር
ዛሬ የሆነውን
እንዳልሆነ እያስመሰሉ መኖር ሕይወታችን ነው - ስለነገ ሲባል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ስርዓቱ በፓርቲ ቁጥጥር ስር እንደሆነ
ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ ያይናችንን ቀለም ካልወደደው፣ አንዱን የሽብር፣ ወይም የወንጀለኛ አንቀፅ መዝዞ፣ በራሱ ትርጓሜ
ተርጉሞ አሊያም ካስፈለገ አዲስ አዋጅ አውጥቶ መቀመቅ ሊያወርደን ይችላል፣ እያደረገውም ነው፡፡ ነገር ግን ነገ ኢትዮጵያ እንዲህ
ሆና ትቀጥላለች ብለን አናስብም፡፡ የሕግ የበላይነት ስለሚሰፍንባት የነገዋ ኢትዮጵያ ብለን ሕግ አክብረን እንንቀሳቀሳለን፣ አዋጅ
ወይም መመሪያ ሲወጣ እንደማይቀየር እያወቅን ይህ መስተካከል አለበት እያልን እንፅፋለን፣ ምርጫዎች እንደሚጭበረበሩ እያወቅን እንመርጣለን…
ሁሉም ዛሬ ስላለው ውሸት ሳይሆን ነገ እውን ትሆናለች ብለን ስለምናስባት ኢትዮጵያ ተብሎ የሚደረግ ማስመሰል ነው፡፡
በጎሳ ጉዳይም
ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ እኔ በግሌ በቅጡ የማውቀው ብሔር እንኳን የለኝም፡፡ ነገር ግን በዚህ ስርዓት ውስጥ ግን የየትኛው ብሔር
ተወላጆች ፈላጭ ቆራጮች እንደሆኑ አውቃለሁ፣ ማንም ያውቃል፡፡ ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ የኃይል እና የሀብት ክፍፍል አገሪቱን እየጎዳት
እንደሆነ እያወቅኩ እንኳን ብዙ ጊዜ ዝም ብያለሁ፣ ነገ የማስባት ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል እንጂ ‹‹አንዳንዶች የበለጠ እኩል የሚሆኑባት››
አይደለችም፣ ስለዚህ ስለነገዋ ኢትዮጵያዬ ስል የዛሬውን ባልፈው ነገ ይረሳል በሚል ነው፡፡
ይህ ማስመሰል
በጎ ቢሆንም፣ እውነቱ መነገሩ ግን ክፉ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አልደረስኩም፡፡ መወራት አለበት፤ ካላወራነውማ የዛሬው ሲቀየር የነገ
ባለተራ ደግሞ የራሱን ዓይነት ‹‹ዛሬ›› ሊደግም የማይችለው እንዴት ነው?
No comments:
Post a Comment