#EthioElection2020: What to Expect When You're Expecting Ethiopian Election!
ወቅቱን የጠበቀ፣ ፉክክር ያለበት፣ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ጎጆ ውስጥ የመሐል ዋልታ ነው። ይሁን እንጂ ዴሞክራሲ ማለት በየአራት፣ አምስት ዓመቱ የሚመጣ ምርጫ ብቻ አይደለም፤ በኹለት ምርጫዎች መካከል ያለ የዜጎች ተሳትፎም የሚረጋገጥበት ስርዓት ነው። ለዚህ ነው ዴሞክራሲ መንገድ እንጂ መዳረሻ አይደለም የሚባለው። ነገር ግን በምርጫ መካከል የዜጎች ተሳትፎ (በተለይም በነጻ ሚዲያ እና ሲቪል ድርጅቶች አማካይነት የሚደረግ የዜጎች ተሳትፎ) የሌለው ዴሞክራሲ የይስሙላ ዴሞክራሲ ነው። ወቅቱን የጠበቀ (periodic) ምርጫ የሌለው ዴሞክራሲ ግን ከናካቴው የይስሙላ ዴሞክራሲ እንኳን ሊባል አይችልም። ለዚህ ነው ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አዋጭ ስርዓት ነው ብለን የምናምን ሰዎች፥ በጥቅሉ ምርጫን፣ በተለይ ደግሞ የዘንድሮውን የኢትዮጵያን ምርጫ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና የወል ትብብር መከታተልና ማድረግ የሚኖርብን።
ባለፉት ኹለት ዓመታት የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ወዲህ የተዘጋውን የፖለቲካ ምኅዳር ለመክፈት ከበፊቱ የተሻለ ተነሳሽነት ታይቷል። የሲቪክ እና የፖለቲካ ምኅዳሩን ያጠበቡትን ሕጋዊ ማዕቀቦችን ለማሻሻል ጥሩ የሚባል ጥረት ተደርጓል። የመንግሥት ተቋማትን ተአማኒ እና "ነጻ" ለማድረግ ቃል ተገብቷል፣ ጥቂት የተቋማት ጥገናዊ ለውጥም ተደርጓል። ይኼ ሁሉ የተሐድሶ ሙከራ ግን በፉክክር በደመቀ፣ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ ካልታጀበ "እቃቃው ፈረሰ፣ ዳቦው ተቆረሰ" መሆኑ ነው።
First Things First
ምርጫ ቦርድ ይታመናል?
ይኼንን ጥያቄ ለመመለስ ነገሩን ከበርካታ አቅጣጫዎች መመልከት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ተአማኒ መኾን ያልቻለበትን ምክንያት እናስታውስ። ዋነኛው ምክንያት የገዢው ፓርቲ መሣሪያ በመሆኑ ነው።
ምርጫ ቦርድ የገዢው ፓርቲ መሣሪያ ነበር ስንል ከመገለጫዎቹ አንዱ የፓርቲዎችን ጠብ የሚገላግልበት መንገድ ነበር። በተለይ ትልልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጣዊ ውዝግብ ሲኖራቸው (አንዳንዶች እንዲያውም የውዝግቡ ለኳሾች ራሱ ገዢው ፓርቲ አስርጎ የሚያስገባቸው ሰዎች ናቸው ብለው ያምናሉ)፣ የመፍትሔ ውሳኔው ብዙ ጊዜ ፓርቲዎቹን የሚያሽመደምድና የተፎካካሪነት ቁመና የሚያሳጣ ነበር። በሌላ በኩል፣ ትልልቆቹን ፓርቲዎች ለመሰንጠቅ ካለው ቁርጠኝነት ውጪ ትንንሾቹን እና ሕጋዊ መሥፈርቶችን የማያሟሉ የይስሙላ ፓርቲዎችን ዕውቅና ሰጥቶ እያባበለ ማቆየቱ ደግሞ ሌላው የቦርዱ ሐሳዊነት መገለጫ ነበር። በአጭሩ ገዢው ፓርቲን እንደ ቤተኛ፣ ለአቅመ ፉክክር የደረሱትን ተቃዋሚዎች ደግሞ እንደ ባዕድ ሲያስተናግድ ከርሟል። ከዚህ በተረፈ ያለው ምርጫ ቦርድን አያገባውም፤ ኢሕአዴግ ሌላውን የጫወታ ሜዳ (ሚዲያዎችን እና ሲቪል ድርጅቶችን በማዳከም ወይም ወደ ራሱ ተለጣፊ በማድረግ ሜዳውን) እንዲያጋድል በማድረግ ራሱ ተጫውቶ፣ ራሱ ሲያሸንፍ ከርሟል።
የአሁኑ ምርጫ ቦርድ ብርቱካን ሚደቅሳን ሰብሳቢ አድርጎ ሲሾም ከፍተኛ የእምነት ካባ እንደደረበ ብዙዎች ይስማማሉ። ብርቱካን በእሳት ተፈትነው የከበሩ ወርቅ ናቸው። ነገር ግን አንድ እርሳቸው ብቻቸውን ተቋሙን ተአማኒ አያደርጉትም። የሕግ ማሻሻያ ከጎበኛቸው ተቋማት መካከል የምርጫ ቦርድን ያክል ብዙ አዋጆች ያስከለሰ ተቋም የለም። የቦርዱ መልሶ ማቋቋሚያ አዋጅ የቦርድ አባላትን ቋሚ ሠራተኞች እንዲሆኑ አድርጓል። ሰብሳቢዋን ጨምሮ ውብሸት አየለ፣ ብዙወርቅ ከተተ፣ ጌታሁን ካሣ (ዶ/ር) እና አበራ ደገፉ አሁን የቦርዱ አባል እና ቋሚ ሠራተኞች ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በመለጠፍ ታምተው የሚያውቁ ሰዎች አይደሉም። ሆኖም የሕግ ክለሳውን እና ተቋማዊ መልሶ ማዋቀሮችን እንደምክንያት በመጥቀስ የመዘግየት ችግሮችን አሳይተዋል። የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ አንደኛውና ዋነኛው ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተብለው ያለአግባብ የሚዘረዘሩትን ከመቶ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ቡድኖች እና ግለሰቦች፥ እስከዛሬ ድረስ በሕጋዊ መንገድ አጣርቶ ዜጎች ሐቀኞቹን ከሐሳዊዎቹ እንዲለዩ ማድረግ መዘግየታቸው ሌላው ጉዳይ ነው።
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ተሞክሮ የአሁኑን ምርጫ ቦርድ አቋም እና ቁመና መገምገሚያ ይሆናል። ሕዝበ ውሳኔው ቢዘገይም ተካሒዷል። ምርጫ ቦርድ ማድረግ የሚችለው እና የማይችለውም የታየበት አጋጣሚ ነበር። በሕዝበ ውሳኔው የታየው ትልቁ ጉድለት የአፈፃፀም ነው። ለምሳሌ የመጨረሻው ውጤት ሲታወጅ ከ1,862 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ውስጥ የ166ቱ ውጤት ውድቅ ተደርጓል። ምርጫ ቦርድ ይህንን ያደረገበት ምክንያት፥ በነዚህ ጣቢያዎች ውስጥ የመራጮቹ ቁጥር ለመምረጥ ከተመዘገቡት ሰዎች ቁጥር በልጦ በመገኘቱ ነው። ቦርዱ ይኼንን በማድረጉ፥ በአንድ በኩል ለመራጮች ድምፅ ዋጋ እንደሚሰጥ ቢያሳይም፥ የአፈፃፀም አቅም ችግር እንዳለበት ግን አሳይቷል። የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የረባ ፉክክር ስለሌለው የነዚህ ጣቢያዎች ውጤት መሠረዙ ውጤቱን አያስተጓጉለውም። ፉክክር በሚበዛበት የአገር ዐቀፉ ምርጫ ግን ይህ ችግር በቸልታ ለማለፍ የማይቻል ነው የሚሆነው። ዳግም ምርጫ እንዲካሔድም ሊያስገድድ ይችላል። ከዚህ በተረፈ ቦርዱ ሕዝበ ውሳኔውን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ የሲቪል ድርጅት ታዛቢዎች ካወጡት የተሻለ ጠንካራ ነበር ማለት ይቻላል። ስለዚህ ቦርዱ የአፈፃፀም አቅም ችግር ሊኖርበት ይችላል። ነገር ግን ለአንድ ወገን የመወገን እና የመራጭ ተመራጮችን እምነት የማጉደል ችግር ግን ይኖርበታል ለማለት የሚያስችል ውኃ የሚቋጥር መከራከሪያ የለም። የአፈፃፀም ችግሩ የመራጮችን ድምፅ ካባከነ ግን እምነት መጉደሉ አይቀሬ ነው።
ይኼንን ጽሑፍ ስጽፍ ግብዓት ይኾነኛል በማለት ትዊተር ላይ አስተያየት እየሰበሰብኩ ነበር። "የአሁኑን ምርጫ ቦርድ ምን ያህል ታምኑታላችሁ?" ብዬ ጥር 10 እና 11 በሰበስኩት ድምፅ መሠረት መልስ ከሰጡ 1208 ተጠቃሚዎች ውስጥ 21.4% "እጅግ በጣም"፣ 25.9% "በጣም"፣ 27.7% "በጥቂቱ" እና 25% "አላምነውም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። "አላምነውም" ያሉት ሩብ ያክሉ ብቻ መሆናቸው ካለፈው ሪከርዱ አንፃር እመርታ ነው። ምርጫው በተቃረበ ቁጥር ግን ጥርጣሬው ስለሚበረታ ተዓማኒነትን ለመገንባት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።
ሆኖም የማኅበራዊ ሚዲያ ድምፆች/አስተያየት መሰብሰቢያ ዘዴዎች መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይወክሉም። ሌላው ቀርቶ ትዊተር ላይ ያለውን እውነታ እንኳን በቅጡ ላይወክሉ ይችላሉ። የኔ የትዊተር ተከታዮች የተወሰነ ብዝኀነት ቢኖራቸውም በብዛት የመንግሥት ተቺዎች ናቸው። በብዛት ወንዶች ናቸው። ሴቶች በመራጭነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሳተፉ ልብ ይሏል! በጥቅሉ ይኽ ድምፅ በመጠኑ የተማሩ፣ ወይም በስደት ያሉ፣ መንግሥትን በጥርጣሬ ዓይን የሚለከቱ፣ ወንዶች እና ጥቂት ሴት ከተሜዎች ድምፅ ነው። ሆኖም ይህ ድምፅ የተፅዕኖ ፈጣሪዎች እና አጀንዳ ቀራጮችም ድምፅ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። አስተያየታቸውን እንደጠቃሚ ግብዓት መውሰድ ያስፈልጋል። ቦርዱ ተዓማኒነት ላይ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አመለካከት እንደሌለው ያስረዳናል።
የፀጥታ ሁኔታ፦ የምርጫ ነውጥ ይከሰት ይሆን?
አዲሱ አመራር ከመምጣቱ በፊት ሕዝቦች መንግሥትን ሲቃወሙ፥ በምላሹ መንግሥት የሚያደርሰው በነፍጥ የታገዘ ነውጥ ነበር የኢትዮጵያውያን ራስ ምታት። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን የጎንዮሽ ነውጡ በርትቶ ታይቷል። በቀላል አማርኛ መንግሥታዊው ነውጥ መንግሥታዊ ባልሆኑ ኀይሎች ተተክቷል። በርግጥ ተተክቷል የሚለው ቃል ሊያሳስት ይችላል። አሁንም ቢሆን ከፍተኛ የነውጥ ኀይል (force of violence) በመንግሥት እጅ ነው።
ባለፉት ኹለት ዓመታት ሚሊዮኖች የተፈናቀሉት እና የደቦ ፍርዶች የተፈፀሙት በዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ነውጠኞች መፈርጠም ሳቢያ ነው። በርግጥ ይህንን ከውስጥ ለውስጥ የፖለቲካ ልኂቃን የሥልጣን እና የአጀንዳ ሽኩቻ ነጥሎ ማየት ለስህተት ይዳርጋል። የሆነ ሆኖ እነዚህ የጎንዮሽ ነውጦች አሁንም የሚታዩ ቢሆንም እያሽቆለቆሉ መምጣታቸውም መካድ የለበትም። ጥያቄው ግን "የምርጫ ፉክክር እየጎነ ሲሔድ የጎንዮሽ ነውጡ እንደገና ያንሰራራ ይሆን?" የሚለው ጥያቄ ነው።
በግሌ ከዓመት በፊት የነበረኝ ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ነገር ግን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በነበርኩበት ጊዜም ምርጫውን ማራዘም የበለጠ ቀውስ ያስከትላል ብለው ከሚሰጉት ወገን ነበርኩ። ዞሮ ዞሮ አሁን ለነውጡ ስጋት መቀነሻ ኹለት መተማመኛዎች አሉኝ። አንደኛው የፀጥታ ኃይሉ እንደሚፈራው የተከፋፈለ አለመሆኑ ነው። የፖለቲከኞቹ መከፋፈል የፀጥታ ኃይሉ ጋር በሚያሳስብ ደረጃ ስለመድረሱ ምንም ምልክት የለም። ኹለተኛው ምርጫው የሚካሔድበት ወቅት ክረምት መሆኑ ለአመፅ አስቸጋሪ የሚያደርገው መሆኑ ነው። በርግጥ ይህ የምርጫውን ድምቀት እና አሳታፊነትም ይቀንሰዋል። ነገር ግን ኹለት ወዶ አይሆንም። አሁንም ቢሆን የደኅንነት ክንፉ ደካማነት እና ግጭቶችን ከመከሰታቸው በፊት የመከላከልና ከተከሰቱ በኋላ እንዳይሰራጩ የመቆጣጠር አቅም አያስተማምንም።
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ እስካሁን ያላባራ ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ምዕራብ ወለጋ በመንግሥት እና ተቃዋሚ ኃይሎች የነፍጥ ትግል ውስጥ ነው የከረመው። በዚህ ቦታ እና አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ከናካቴው ላይታሰብ ይችላል።
ስለሆነም፣ ከዚህ በታች ያለው ግምት አመፅ ሳይኖር፣ ምርጫ ቦርድ በነጻ መንፈስ ያዘጋጀዋል በሚል ቅድመ ግምት የተሰናዳ ነው።
እነማን ያሸንፋሉ?
ይኼ ጥያቄ "የሚሊዮን ብር ጥያቄ" የሚባል ዓይነት ነው። ማንም ምርጫው ተካሔዶ ውጤቱ እስኪታወጅ እርግጡን መገመት አይችልም። ግን ግምቶችን ከነምክንያታቸው ማስቀመጥ የዴሞክራሲያዊ ባሕል መገለጫ ነው። እኔ የበኩሌን ግምት ለማስቀመጥ የሚከተሉትን ድምር ሁኔታዎች ተጠቅሜያለሁ፦ በየክልሉ ተቀባይነት ወይም ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ያላቸውን ድርጅቶች መለየት፣ ያላቸውን መዋቅራዊ አደረጃጀት እና ዝግጅት እንዲሁም ውስጣዊ ጥንካሬ እና ስምምነት መገምገም ብሎም የሰዎችን አስተያየት ትዊተር ላይ መሰብሰብ ይጨምራል። (የትዊተር ድምፅ መሰብሰቢያዎች ያላቸውን ውሱንነት ቀደም ብዬ አስምጫለሁ። ነገር ግን እዚያው ትዊተር ላይ በጽሑፍ የተሰጡ አስተያየቶችንም እንደማጠናከሪያ ግብዓት አክያቸዋለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ፖሉን ያደረግኩት ለግምቴ ማመሳከሪያ ቁጥር ስለሚሰጡኝ ነው።)
"እነማን ያሸንፋሉ?" ብዬ ስጠይቅ፥ የየክልላቸውን ምክር ቤቶች ሳይሆን ክልላቸውን ወክለው በሚያገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ብዛት ነው። በዚህ መሠረት ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልል ብቻቸውን ከ547 የምክር ቤቱ ወንበሮች 439ኙን ይወስዳሉ። ስለዚህ እነዚህ ሦስቱ ጋር ጥሩ መዋቅር ያለውና ጥሩ ቅቡልነት ያለው ድርጅት መንግሥት መመሥረት አይቸግረውም። የትግራይ ክልል 38 መቀመጫዎች ከሕወሓት የመትረፍ ዕድል ያላቸው አይመስሉም። የሶማሊ ክልል 24 መቀመጫዎች በኦብነግ እና በብልፅግና የሶማሊ ክንፍ መካከል እኩል፣ እኩል ሊሔዱ ይችላሉ። ቀሪዎቹን የአፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረሪ እና ድሬዳዋ ድምር 26 ድምፆች ብልፅግና የመውሰድ ዕድሉ ሰፊ ነው፤ ግን ለግምቱ ማጠናከሪያ ከፊሎቹን ለተቃዋሚ መስጠት እንችላለን።
ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎቹ የሚለየው ገዢ ፓርቲ በመሆኑና አሁንም የመንግሥት መዋቅሮችን እንደልቡ ማሾር የሚችል በመሆኑ ነው። ምርጫ ቦርድ እጁ ባይጠመዘዝለት እንኳን (መሞከሩ አይቀርም) ሀብቱን ለመቀስቀሻም፣ ለመደለያም ይጠቀምበታል። መዋቅር አለው (ምናልባት ከትግራይ በቀር) በሁሉም ክልሎች ያሉ የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ ለክልልም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶችም ሙሉ ዕጩ ማቅረብ የሚችል ብቸኛው ድርጅት ነው። የፀጥታ ስጋቱ ብልፅግና ፓርቲን ያን ያህል አያሰጋውም፤ የኀይል ባለቤት ነው።
ተቃዋሚዎች በተቃራኒው በቅጡ ያልተደራጁ እና ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት የሌላቸው ናቸው። ለድክመታቸው አገዛዙ ራሱ ሲያደርስባቸው የነበረው ተፅዕኖ እና ልክ እንደምርጫ ቦርድ ሁሉ፣ ያውም አንዳንዶቹ ከዜሮ ጀምሮ ለመደራጀት የነበራቸው ጊዜ 1 ዓመት ከ6 ወር ገደማ ብቻ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው። እዚህ ጋር ማስተዋል የሚኖርብን በገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ መካከል እጅግ ከፍተኛ መበላለጥ (asymmetry) አለ። አንዱ ከምርጫው መጠበቅ የሌለብን ነገር ፍትሐዊነት የሚሆነው፣ ዐሥር ዓመት እና ከዚያ በላይ ካልተሰጣቸው በቀር ተቃዋሚዎች ተመጣጣኝ አቅም ማዳበር የማይችሉ መሆኑን ነው። የሆነው ሆኖ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተሻለ አደረጃጀትና መዋቅር ያለው ኢዜማ ቢሆንም፥ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ከፍተኛ የማጥላላት ዘመቻ እየተደረገበት ነው። በደቡብ ክልልም የክልልነት ጥያቄ የሚያራምዱ ብሔርተኞች በየዞኑ ከፍተኛ ተቋቁሞ (resistance) ፈጥረውበታል። ኢዜማ፣ ከሌሎቹ የተቃዋሚ ፖለተካ ድርጅቶች በሙሉ የበለጠ የፖሊሲ ግልጽነት ቢኖረውም፥ በጦዘ የብሔርተኝነት ፖለቲካ ውስጥ ባይተዋር ተደርጓል፤ ከሁሉም ያልሆነ ምናልባትም የከተሞች ብቻ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሊሆን ይችላል።
በኦሮሚያ ከፍተኛ ተቀባይነት ይኖረዋል የተባለው ቅንጅት ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም (Coalition for Democratic Federalism) የተባለው የኦፌኮ፣ ኦነግ እና ኦብፓ ጥምር ፓርቲ ነው። ስለዚህ ቅንጅት ከሚታወቀው የማይታወቀው ቢበዛም ቅሉ፥ የኦሮሚያን የተቃዋሚ ድምፅ በፉክክር ይከፋፍለዋል የሚለውን ስጋት ይቀርፋል። የሆነ ሆኖ ከጊዜ ጋር ያለበት ፉክክር ከፍተኛ ስለሚሆን የብልፅግናን የኦሮሚያ ክንፍ በቀላሉ ይረታዋል ብሎ መገመት የዋህነት ይሆናል።
በአማራ ክልል አብን መነሻው ላይ የነበረው ፍጥነት እና ብርታት ከአማራ ክልል መሪዎች መገዳደል ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልሶ መነቃቃት ቢያሳይም ውስጣዊ አንድነቱን አጥቶ መክረሙ የአደባባይ ምሥጢር ነው። በዚያ ላይ የብልፅግና የአማራ ክልል ክንፍ ክፉኛ ይሞግተዋል። ከኢዜማም ጋር ድምፅ መቀማማቱ አይቀርም።
እነዚህን ግምገማዎች ይዤ የትዊተር ሰዎች ምን እንደሚያስቡ ጠየቅኩ። በየተራ እነማን አብላጫ ድምፅ የሚያገኙ ይመስላችኋል ብዬ ስጠይቅ የተገኘው ምላሽ በአዲስ አበባ ኢዜማ፣ በኦሮሚያ ቅንጅት ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም፣ በአማራ አብን፣ እና በደቡብ ክልል ደግሞ ብልፅግና የሚሉ መልሶች ተገኙ። መልሶቹን እንመልከት እና ምን ትርጉም እንደሚሰጡ ቀጥለን እንነጋገራለን።
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እነማን የሚያሸንፉ ይመስላችኋል? (2145 መላሾች)
☞ 50% ቅንጅት ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም
☞ 40% ብልፅግና
☞ 7% ኢዜማ
☞ 3% ሌሎች ፓርቲዎች
አማራ ክልል ውስጥ እነማን የሚያሸንፉ ይመስላችኋል? (1674 መላሾች)
☞ 46.8% አብን
☞ 35.8% ብልፅግና
☞ 11.6% ኢዜማ
☞ 5.7% ሌሎች ፓርቲዎች
ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ውስጥ እነማን የሚያሸንፉ ይመስላችኋል? (924 መላሾች)
☞ 47% ብልፅግና
☞ 29% የክልልነት ጥያቄ የሚያነሱ የዞን ፓርቲዎች
☞ 19% ኢዜማ
☞ 4 % ሌሎች ፓርቲዎች
አዲስ አበባ ውስጥ እነማን የሚያሸንፉ ይመስላችኋል? (1526 መላሾች)
☞ 36% ኢዜማ
☞ 33% ብልፅግና
☞ 22% ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ
☞ 9% ሌሎች
የትዊተር መላሾች የሚሰጧቸው መልሶች አንዳንዴ ምኞታቸውን፣ አንዳንዴ ደግሞ ግምታቸውን ነው። ችግሩ አብዛኛዎቹ የራሳቸው ወጥነት (homogeneity) አላቸው። በየቀበሌው እና በየወረዳው ያሉ ልዩነቶችን እና ውስብስብ እውነታዎችን ይደፈጥጣሉ። የመዋቅርን አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ ላያስገቡ ይችላሉ። ነገር ግን ከፊሎቹ የማኅበረሰቡ አካል፣ ከፊሎቹ ፖለቲካዊ ሒደቱን በቅርብ የሚከታተሉ እና ተፅዕኖም አሳዳሪዎች ናቸው። ግምታቸውን ከላይ ከሰጠነው ትንታኔ ጋር በማመሳከር ጠንከር ያለ ግምት ማሳለፍ እንችላለን። ነገር ግን ቀድሜ እንዳልኩት የላይኛውን ትንታኔ ቁጥር ስለሚያለብሱልኝ ነው የምፈልጋቸው።
ቁጥሮቹን በታትነን ስንመለከታቸው፣ ከ547 የምክር ቤት ወንበሮች 84.5% (462ቱን) በሦስቱ ክልሎች እና አዲስ አበባ መውሰድ ይችላል። ብልፅግና ምንም እንኳን ከደቡብ በቀር ኹለተኛ ቢሆንም በድምሩ 186ቱን ይወስዳል። ቅንጅት ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም፣ አብን እና ኢዜማ 89፣ 65 እና 59 መቀመጫዎችን እንደቅደም ተከተላቸው በመውሰድ ኹለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ብዛት ያላቸውን መቀመጫዎች ይወስዳሉ። ሕወሓት በርግጠኝነት የትግራይን 38 ወንበሮች ያለተሻሚ ይወስዳል፤ ተሻሚ ቢመጣበት እንኳን ከክልሉ አዲስ ብሔርተኛ ቡድኖች አያልፍም። ነገር ግን ቀሪዎቹን 47 የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሐራሪ እና የድሬዳዋ ከተማ ድምር መቀመጫዎች የማሸነፍ ሰፊ ዕድል ያለው ብልፅግና ቢሆንም፥ በግማሽ የሚካፈሉት ቡድኖች ቢመጡ ብለን ብንቀንስበት በድምሩ 209 ዘጠኝ ወንበሮች ይወስዳል ማለት ነው። ይህ መንግሥት ለመመሥረት ከሚያስፈልገው 274 በ65 ያንሳል። ስለዚህ ብልፅግና ከኦሮሞ ድርጅቶቹ ቅንጅት ወይም ከአብን አንዳቸው ጋር በመጣመር መንግሥት መመሥረት ይችላል። ምናልባት ደግሞ በእውነተኛው ውጤት ቁጥሩ ከዚህ ስለሚለይ ከኢዜማ ጋር የመጣመር ዕድል ሊኖረው ይችላል። ይህ እውን ቢሆን የትኞቹን ይመርጣል የሚለው አጓጊ ድራማ ይሆን ነበር። ነገር ግን ይህ ተራ ግምት ነው። ምናልባት ግምቱን ጠንካራ ለማድረግ በየምርጫ ወረዳዎቹ ያለውን እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ጥናት እና ግምት (projection) መደረግ አለበት። ይህ በኔ ሌጣ የትርፍ ጊዜ አቅም የተዘጋጀ እንደመሆኑ ብዙ ውስኖች አሉበት። ለነገሩ ሒሳዊ አንባቢያን (critical readers) ይህ አይጠፋቸውም።
አንድ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በልበ ሙሉነት መገመት እንችላለን። ብልፅግና ፓርቲ ብቸኛው የማሸነፍ ዕድል ያለው ፓርቲ ነው። ብቻውን መንግሥት መመሥረት የሚያስችል መቀመጫ ማግኘት ባይችል እንኳን ጥምር መንግሥት ለመመሥረት መራጭ እንጂ ተመራጭ አይሆንም።
ቅድመ ምርጫ እና ድኅረ ምርጫ ተግዳሮቶች
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ደግመን እንጥቀስ። ሕዝበ ውሳኔው ፉክክር አልነበረበትም። ስለዚህ በዚህ ረገድ ምሳሌ አይሆንም። እንዲያም ኾኖ ሒደቱ ውስጥ የዞኑ ተፅዕኖ ከፍተኛ ጥላ አጥልቶበታል። ትንሽም ቢሆኑ ከክልልነት በተቃራኒው የሚፈልጉ መራጮች በነጻነት ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ ታፍነው ነበር። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ተዋናዮቹ ዞኑ እና በዞኑ ውስጥ በኢመደበኛ መንገድ የተደራጁ ወጣቶች የፈጠሩት ሥጋት ነው። ይህንን ነጻ እና ገለልተኛ የፀጥታ አካላት ሊቆጣጠሩት በተገባ ነበር፤ አልሆነም። ከነሐሴው ምርጫ አስቀድሞ በየክልሉ አመራሮች እና በጎን በሚደግፏቸው ኢመደበኛ እና ሞገደኛ ወጣቶች ቡድን በየክልሉ፣ ዞኑ እና የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ "ያልተፈለጉ" ተወዳዳሪዎች ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ፣ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ እና መራጮቻቸውም መረጃ እንዳያገኙ፣ በነጻነትም እንዳይመርጡ ሊያደርጉ ይችላሉ። እዚህ ላይ የመንግሥት ቁርጠኝነት እስከታችኛው እርከን ድረስ ወርዶ ካልታየ በቀር ሌላ መፍትሔ የለውም። በየእርከኑ ያሉ ግጭቶች እና ዕቀባዎች በሙሉ በእየርከኑ ያሉ አስተዳደሮች ቡራኬ ካልሰጧቸው እንደማይከሰቱ ባለፉት ጊዜያት ከተከሰቱ ግጭቶች እና ክልከላዎች መረዳት ይቻላል።
ድኅረ ምርጫው የሚገጥመው ትልቁ ተግዳሮት ተፎካካሪዎቹ (በተለይ ተሸናፊዎቹ) ውጤቱን አንቀበልም የሚሉ ከሆነ ነው። ቅድመ ሒደቱን በጣም ግልጽነት የተሞላበት እና ሕጋዊነቱን የጠበቀ ማድረግ የሚያስፈልገው ድኅረ ምርጫ ሥምምነት ለመፍጠር ስለሚጠቅምም ጭምር ነው።
መውጪያ
ይህ የአንድ ሰው ግምት ነው። ግምቱ ምርጫው ከ200 በላይ ቀናት ስለሚቀረው በሒደት ሊታረም ወይም ሊጠናከር ይችላል። ገና የሚፈርሱ ፓርቲዎችና ጥምረቶች አሉ። ጎልተው የሚወጡም እንደዚሁ። አስፈላጊው ነገር በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ምርጫ የዴሞክራሲ ጎጆ ውስጥ የመሐል ዋልታ መሆኑን ማስታወስ ነው። የልኂቃን ሥምምነት መመሥረት በሚቸግርባት ኢትዮጵያ፥ የምርጫ ሥምምነት ግን ገላጋይ ሊሆን ይችላል። እናም የሚገባውን ትኩረት መስጠትና ጥንቃቄ የተመላበት ንቁ ተሳትፎ ማድረግም ያስፈልጋል። ይህ መጣጥፍ የዚህ አስፈላጊ ንቁ ተሳትፎ አንድ ጥረት ማሳያ ነው።
No comments:
Post a Comment