Pages

Monday, September 2, 2019

የእምነት ነጻነት ወይስ አስተዳደራዊ ጥያቄ?

በፍቃዱ ኃይሉ

ሰሞኑን "የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት አደራጅ ኮሚቴ" ያነሳው ጥያቄ የውዝግብ መንስዔ ሆኗል። ጉዳዩ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ስለሆነም፣ ምናልባት ደግሞ ለከፍተኛ ግጭት መንስዔ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። ይህንን መጣጥፍ የምጽፈውም፣ ከዚህ በፊት ስለማውቃቸው መሰል ውዝግቦች እና ድርድሮች የማውቀውን (የማስታውሰውን ያክል) ለማካፈል ነው። በስተመጨረሻ በወቅታዊው ውዝግብ ውስጥ የዴሞክራሲ እና የመብት ተሟጋቾች ጉዳዩን እንዴት መመልከት አለባቸው የሚለው ላይ የራሴን ነጥብ አስቀምጣለሁ። ይህንን የምጽፍበት ምክንያት የጥያቄውን ምንነት፣ የአቀራረቡን ሁኔታ፣ የቤተ ክርስቲያኗን አቋም እና የምዕመኑን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ማስገባት ለመብት ተቆርቋሪዎች ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ ነው።

በዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ የሒደቱ መገምገሚያ መሥፈርቶቻችን 1ኛ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ መግባት የለበትም፤ 2ኛ፣ ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም፤ 3ኛ፣ በውዝግቡ ግጭት እንዳይነሳ እና ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግሥት የመከላከል ኀላፊነት እና ተወዛጋቢ አካላትም ይህንን የማስወገድ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ነው። 

የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ ጉዳይ

ያደግኩበት ሰፈር “ራስ ካሣ ሰፈር” ይባላል። የራስ ካሣ መኖሪያ ጊቢ ፊት ለፊት አንቀፀ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አለ። ቤተ ክርስቲያኑ “ጭቁኑ ሚካኤል” በሚል ሥም ነው የሚታወቀው። ይህንን ሥያሜ ያገኘው ከቤተ ክሕነት ጋር በነበረው ውዝግብ ነው። በወቅቱ እዚያው እኛ ሰፈር የሚገኘው የገነተ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሥር ነበር ሚካኤል ቤተ ክርስትያንም የሚተዳደረው። እናም ባንድ ወቅት የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች (ቀሳውስቱ እና ዲያቆናቱ) በገነተ እየሱስ አስተዳደር ሥር መሆኑ ቤተ ክርስቲያኑን ጎድቶታል ብለው ተቃውሞ አሰሙ። የራሳችን አስተዳዳሪ ይሾምልን ብለው ቢጠይቁም የቤተ ክሕነት ኀላፊዎች አልተባበሯቸውም። ስለሆነም ፀብ ውስጥ ገቡ።
 
በዚህ መሐል የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች “ነጻነታቸውን አወጁ” - ማለትም “በገነተ እየሱስ አስተዳደር አንመራም” አሉ። በዚህ ወቅት ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ አግኝተው ነበር። ስለሆነም ምዕመኑ በሚሰጠው ሙዳየ ምፅዋት “ጭቁኑ ሚካኤል” ራሱን ማስተዳደር ጀመረ። በወቅቱ በቤተ ክሕነት ቁጥጥር ሥር ባሉ ቤተ ክርስቲያኖች እንዳያስተምሩ ተከልክለው የነበሩት አባ ገብረመስቀልም ሚካኤልን የተከታዮቻቸው ማሰባሰቢያ እና ማስተማሪያ ደብራቸው አድርገውት እንደነበር አስታውሳለሁ። አንዳንዴ የቤተ ክሕነት ሰዎች የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በማስወጣት እና በሌሎች በመተካት ችግሩን ለመፍታት ሲሞክሩ፣ ምዕመኑ እምቢ በማለት ተከላክሎላቸዋል። በስተመጨረሻ ግን ቤተ ክሕነት የደብሩን ጥያቄ በመቀበል ለሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ራሱን የቻለ አስተዳደር በመመደብ ውዝግቡ ተፈትቷል።

ጭብጥ አንድ፤ ቤተ ክሕነት እና የአስተዳደር ጉዳይ በርካታ ውዝግቦች ያሉበት፣ እና ወደ ፊትም የሚኖርበት ውስጣዊ ጉዳይ ነው።

ቤተ መቅደስ እና ቤተ ክሕነት

ብዙዎች እንደ አንድ ቢመለከቷቸውም በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ሁለት ዓይነት መዋቅሮች አሉ። በርግጥ ተመጋጋቢ ናቸው። አንዱ መዋቅር መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጠው ቤተ መቅደስ ሲሆን፥ ሌላኛው አስተዳደራዊ አገልግሎት የሚሰጠው ቤተ ክሕነት ነው። መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጠው ቤተ መቅደሱ ሲሆን፥ አስተዳደራዊ አገልግሎቱን (የሀብት፣ የሰው ኃይል እና መሰል ቁጥጥር እና አስተዳደር) የሚሰጠው ደግሞ ቤተ ክሕነት የሚባለው ነው። በቤተ ክርስትያን ውስጥ ሥር የሰደደ ሙሰኝነት እና ጥቅመኝነት ተንሰራፍቷል የሚባለው በቤተ ክሕነቱ ውስጥ በሚሠራው ሥራ ነው። የሙስናው ደረጃ ዲቁናና ቅስና ለመቀበል ከሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም ጀምሮ እስኩ ደብር እና አስተዳደራዊ ክፍሎች ውስጥ ባሉ እርከኖች በሙሉ የሚስተዋል እንደሆነ በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ አገልግሎት መዋቅሮች ውስጥ የመጨረሻው የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶሱ ነው። ከሥሩ የሲኖዶሱ አባል [እና ሰብሳቢ] የሆኑት ፓትርያርኩ አሉ። በሦስተኝነት ጠቅላይ ቤተ ክሕነት አለ። ከቤተ ክሕነቱ ሥር ሀገረ ስብከቶች አሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ 53 ሀገረ ስብከቶች ያሉ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ውጪ 12 ሀገረ ስብከቶች አሉ። ከእነዚህ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ አንዳቸውም በክልል ሥም አልተጠሩም።

በቀሲስ በላይ መኮንን የሚመራው “የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት ጽ/ቤት አደራጅ ኮሚቴ” ማቋቋም የፈለገው የአስተዳደራዊ መዋቅሩን ነው። ከውስጥ አዋቂዎች ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ ቀሲስ በላይ በቤተ ክሕነት የተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል። ከነዚህም መካከል የጠቅላይ ቤተ ክሕነቱ ምክትል ኀላፊ ሆነው አገልግለዋል። ከ53ቱ ሀገረ ስብከቶች አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኀላፊ ነበሩ።  የጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲንም ነበሩ።

ቀሲስ በላይ መኮንን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ካድሬያዊ ሚና ሲጫወቱ ከነበሩ ሰዎችም መካከል ይመደባሉ። በተለያዩ የፖለቲካ ተሳትፏቸው የሚታወቁ ከመሆናቸውም ባሻገር በመርጋ በቃና ጊዜ የምርጫ ቦርድ አባል ነበሩ። በመንፈሳዊ እምነታቸው ግን ጥያቄ ተነስቶባቸው እንደማያውቅ የሚያውቋቸው ሰዎች ነግረውኛል። ኢሬቻ በዓል የዋቄፈና እምነት አካል እንደመሆኑ ‘ከኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ጋር አይጋጭም’ ያሉት በአማኞቹ ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ናቸው።

ጭብጥ ሁለት፤ ቤተ ክሕነት ሙስናና ሌሎችም ብልሹ አሠራሮች ያሉበት ከመንፈሳዊ አገልግሎት የተለየ የቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር ክፍል ዘርፍ ነው።


የቤተ ክሕነት የሥራ ቋንቋ

ቤተ ክርስቲያኗ የምትተዳደርባቸው ሕገ ቤተ ክርስቲያን (ሕገ መንግሥት እንደማለት) የሚባል እና ቃለ ዐዋዲ የሚባሉ መመሪያዎች አሏት። አብዛኛዎቹ አሠራሮች የሚወሰኑት በነዚህ ሕግጋት እና መመሪያዎች ነው። በዚህ መሠረት የቤተ ክሕነት የሥራ ቋንቋ አማርኛ፣ የቅዳሴ (መንፈሳዊ አገልግሎት) ቋንቋ ደግሞ ግዕዝ እንደሆነ ቢገለጽም፥ በሌሎች ቋንቋዎች የአስተዳደር ሥራ መሥራትም ሆነ ቅዳሴ መቀደስ ስለማይከለክል እየተተገበረ ይገኛል። እንደ ውስጥ አዋቂዎቹ ከሆነ ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ሀገረ ስብከቶች ደብዳቤ የሚጻጻፉት በትግርኛ ነው። በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ብዙ ቤተ ክርስትያኖች በኦሮምኛ የቅዳሴ እና የስብከተ ወንጌል አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ሆኖም “በቂ ኦሮምኛ መናገር የሚችሉ ቀሳውስት እና ዲያቆናት ባለመኖራቸው ምክንያት” በኦሮምኛ የሚቀደስባቸው እና የሚሰበክባቸው ቤተ ክርስትያናት ቁጥር በቂ አለመሆኑን የቤተ ክሕነት ሰዎች ያምናሉ።

ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ያናገርኳቸው የምሥራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉድሩ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በርሳቸው አገረ ስብከት ውስጥ ባሉ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖች በሙሉ “በኦሮምኛም፣ በግዕዝም፣ በአማርኛም ይቀደሳል፣ ይሰበካል፣ ይዘመራል” በማለት በኩራት ነግረውኛል። ሆኖም “ኦሮምኛ ቋንቋ የሚናገሩ አገልጋዮች እጥረት ያለብን መሆኑ በፍፁም የማይካድ ነው” ብለዋል።

የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት ጽ/ቤት አደራጅ ኮሚቴ አባላት በኦሮምኛ ባለመሰበኩ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ ምዕመኗን እያጣች ነው በማለት ትላንት ሐምሌ 26፣ 2011 ባወጡት መግለጫ ተናግረል። የቤተ ክሕነት ጽ/ቤቱን መመሥረት አስፈላጊ የሆነውም በዚህ የምዕመናኑን ወደ ውጪ መፍለስ ለመግታት እንደሆነ አመልክተዋል። ሆኖም ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ - “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ከተማ ናት በግዕዝ፣ አማርኛ እና ኦሮምኛ እንደሚቀደሰው፣ በኦሮምኛም ይቀደሳል” በማለት ከመንፈሳዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ጥያቄ መሆኑን የሚያሳዩ ዓ/ነገሮችን ተናግረዋል፤ ይህም ጥርጣሬውን አባብሶታል። በአዲስ አበባ በኦሮምኛ መቀደስ ችግር ባይኖረውም፣ የአዲስ አበባ ምዕመናን ጥያቄ ነው የሚያስችል ሁኔታ የለም። ሌላኛው ቀሲስ ግን “ብዙ የኦሮሞ ቀሳውስቶች ከመጡ ምን ይሆናል የሚለውን ካልኩሌሽን ሠርተው የሚፈሩ ሰዎች እንዳሉ ይገባናል” በማለት ጥርጣሬውን ሊያጣጥሉት ሞክረዋል።

ነገር ግን ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሆነው “በአንድ ወር ውስጥ ምላሽ ካልተሰጠን የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን” የሚለው የመግለጫው አካል ነው።

ጭብጥ ሦስት፤ ቤተ ክሕነት የሥራ ቋንቋዋ አማርኛ ሲሆን የመንፈሳዊ አገልግሎት ቋንቋዋ ግዕዝ  ነው። ቤተ ክርስትያኖች በሌሎችም ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ነገር ግን የአገልጋዮች እጥረት አለባቸው። በችግሩ ላይ መሥማማት ቢኖርም በመፍትሔ አማራጩ ላይ ግን ልዩነት አለ።

ፖለቲካዊ ቁርሾ

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት - ለትክክለኛ ጥያቄ የተሳሳተ መልሥ” በሚል ርዕስ በጻፈው መጣጥፍ የቀሳውስቱ ጥያቄ ትክክለኛ፣ የጠያቂዎቹ ፍላጎትም ቀና መሆኑን ተናግሮ የመፍትሔ ሐሳባቸው ግን የተሳሳተ መሆኑን አመሏክቷል። እኔ ግን የቀሳውስቱ ጥያቄ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው ብዬ እከራከራለሁ።

በዘውዳዊው ስርዓት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ‘ሲሦ ላራሽ፣ ሲሦ ለቀዳሽ፣ ሲሦ ለተኳሽ’ በሚል መርሕ ሲሦ የኢትዮጵያ መሬት ባለይዞታ እንደነበረች ይታወቃል። እስከ 1966 ድረስ መንግሥታዊ ሃይማኖትም ነበረች (የቀ.ኃ.ሥ. ሕገ መንግሥትም ይህንኑ አጠናክሮታል)። በዚህ ወቅት ብዙ አገር በቀል ሃይማኖተኞችንም ይሁን እስልምናን በማጣጣልም ይሁን አማኞቹን በኀይል ወደ ክርስትና በመቀየር የነገሥታቱን ኀይል ለመስፋፊያነት ተጠቅማለች። በምላሹ የነገሥታቱ ጨቋኝ ስርዓት ተቀባይነት እንዲያገኝም ቡራኬ ስትሰጥ ኖራለች። በዚህ የነገሥታቱ እና የቤተ ክርስትያናቱ ግንኙነት ቤተ ክርስትያኑም ነገሥታቱም ተጠቃሚ ነበሩ፤ ሁለቱም ተስፋፍተዋል።

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ቀደምት ታሪክ ላይ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የጭቆና ተባባሪ በመሆኗ የታሪክ ቁርሾ ተፈጥሮባቸዋል። ቂም ይዘውባታል፤ አሁንም ድረስ የአንድን ማኅበረሰብ የበላይነት የማስቀጠያ መሣሪያ ናት ብለው ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪም ቤተ ክርስትያኗ ነባሩን ታሪካዊ ጭቆና በውስጥ ለውስጥ እያስቀጠለች ነው ብለው ይተቿታል። የዚህ ትርክት ዋነኛ አራማጆች የሆኑት የኦሮሞ ብሔርተኞች ናቸው። የኦሮሞ ብሔርተኝነት አራማጆች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም የበለጠ መንግሥታዊ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉበት ጊዜ ላይ ናቸው። የአሁኑ የአምልኮ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተነሳው ጥያቄም ይህ የፖለቲካ ተፅዕኖ ያበረታታው የቂም በቀል ውጤት ሊሆን ይችላል የሚለው ብዙዎችን ስጋት ውስጥ የከተተው ጉዳይ ነው።

ጭብጥ አራት፤ ቤተ ክርስቲያኗ ታሪካዊ ስህተቶች ሠርታለች፤ በወቅቱ ታሪካዊ ስህተቶቿ ለመስፋፋት ቢጠቅማትም፣ የኋላ ኋላ ግን ለወቀሳ እና መፍረስ አለባት እስከሚል የሚዘልቅ ተቃውሞ ዒላማነት ዳርጓታል።

የነጻነት ትግል እና ሃይማኖት
‘ኢትዮጵያኒዝም’ እና የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት

ቤተ እምነቶችን ከፖለቲካ የነጻ ታሪክ አልነበራቸውም። የሴኩላሪዝም (ቤተ ክርስትያንን እና ቤተ መንግሥትን የመነጠል) ጥያቄ ጎልቶ የወጣውም በዚህ ሳቢያ ነው። በአሜሪካ ጥቁሮች ምዕመን እንጂ አገልጋይ መሆን አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ነገር ግን በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ጥቁሮች በቤተ ክርስቲያናቸው እንደሚቀድሱ ሰምተዋል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ በተዳጋጋሚ ኢትዮጵያ መጠቀሷን በመጥቀስ  የአቢሲኒያ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያንን እ.ኤ.አ. በ1808 በማቋቋም ጥቁሮች አገልጋይ የሆኑበት ቸርች አቋቁመዋል። ከዚያ በኋላ እንቅስቃሴው ‘ኢትዮጵያኒዝም’ ተብሏል። አፓርታይድ ከመውደቁ በፊት በደቡብ አፍሪካ 37 ሺሕ የሚደርሱ “የኢትዮጵያ” የሚባሉ ጥቁር አገልጋይ የሆነባቸው ቸርቾች ነበሯቸው።

‘ኢትዮጵያኒዝም’ በነጭ ማኅበረሰብ ጭቆና ውስጥ ላለፉ ጥቁሮች፣ የጭቆና መሣሪያ ሆኖ የመጣባቸውን ሃይማኖት በራሱ ዘዴ የተዋጉበት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ እንደነ ማልኮም ኤክስ ያሉት ‘ኔሽን ኦፍ ኢስላም’ የሚባል ተቋም በመመሥረት፣ ክርስትናን መቃወምን ጨቋኞቻቸውን የመቃወሚያ መሥፈርት አድርገው ብዙ ተጉዘዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የአገረ መንግሥት ምሥረታውን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ከነገሥታቱ ጋር ሆና አራምዳለች። የአገረ መንግሥት ምሥረታው ጨቁኖናል ለሚሉት ወገኖች ግን የጭቆና መሣሪያ ሆናለች ማለት ነው። ስለሆነም ብዙ ምዕመኖቿ ሸሽተዋታል። ከኦሮሙማ (ኦሮሞነት) ንቅናቄ ውስጥ አንዱ ወደ ራስ ሃይማኖት መመለስ ነበር፤ ወደ ዋቄፈና። ይህ በእንዲህ እያለ ግን፣ የለም እምነታችንን በቋንቋችን እንተገብራለን የሚሉ ደግሞ ለዚሁ ተግተዋል። የሆነ ሆኖ ብሔርተኞች (በተለይ የኦሮሞ ብሔርተኞች) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ተቀናቃኝ የሆነውን የኦሮሞ ብሔርተኝነት ታደናቅፋለች ብለው ስለሚያስቡ በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወሟታል። ምንም እንኳን አማኞች ባይሆኑም በተለይ ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ መገንጠሏን እንደ ብቸኛ የፖለቲካ መፍትሔ የሚወስዱት ብሔርተኞች፣ የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክህነትን መመሥረት ለፖለቲካ ግባቸው ጠቃሚ ነው በሚል ሲደግፉት እና ሲያበረታቱት ይታያሉ፤ የትግላቸውም አካል አስመስለውታል።

ጭብጥ አምስት፤ የኦሮሚያ ቤተ ክሕነት ጽ/ቤት ጉዳይን የሚያራግቡት ሰዎች የምዕመኑን ጥያቄ ማዕከል ከማድረግ ይልቅ የብሔርተኝነት ጥያቄዎችን ማዕከል ያደረጉ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ናቸው።

መደምደሚያ

የእምነት ነጻነት ሕገ መንግሥታዊም ተፈጥሯዊም ነው። አሁን የምናየው ውዝግብ ግን የእምነት ሳይሆን የአምልኮ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ነው። ይህ አስተዳደራዊ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ጉዳይ ነው። ችግሩን በመለየት ደረጃ በኦሮምኛ ቋንቋ አገልግሎቱን መስጠትን በተመለከተ በአካባቢ ቋንቋዎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ድክመት እንዳለባቸው የጠቅላይ ቤተ ክሕነት ኀላፊዎችም አልካዱም። ልዩነታቸው የአስተዳደር መዋቅሩ ላይ ነው። “የኦሮምያ ቤተ ክሕነት ጽ/ቤት አደራጅ ኮሚቴው” ችግሩን ለመቅረፍ ክልላዊ የቤተ ክሕነት ጽ/ቤት ማቋቋም መፍትሔ ነው ብለው እየተናገሩ ነው፤ የእነርሱን እርምጃ የሚቃወሙት የቤተ ክሕነት ሰዎች ግን ይህ አካሔድ ችግሩን አይፈታውም፣ ፖለቲካዊ ያደርገዋል እንጂ ባይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እያለ፣ በቤተ ክሕነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ርዕሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ ዓርብ ዕለት (ነሐሴ 24፣ 2011) ትላንት የተሰጠውን መግለጫ እንዳይካሔድ፣ መንግሥት እንዲያስቆመው ጥሪ አድርገው ነበር። መንግሥት ምላሽ አልሰጠም፤ መግለጫው የኦሮሚያ ክልል መሥተዳደር በሚያስተዳድረው የኦሮሞ ባሕል ማዕከል ተደርጓል፡ በመግለጫው ላይ የኮሚቴው አባላት ለጠቅላይ ቤተ ክሕነቱ የራሳቸውን እርምጃ ለመውሰድ አንድ ወር መስጠታቸው ግርታን የሚፈጥር ሆኗል። በአንድ ወር ውስጥ ምላሽ ካላገኙ ምንድን ነው የሚያደርጉት? የራሳቸውን ቤተ ክሕነት አቋቁመው፣ የራሳቸውን ቤተ ክርስትያናት በመመሥረት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ሊያስኮበልሉ ከሆነ፣ መብታቸው ነው። የለም፣ በኦሮምያ ያሉ ቤተ ክርስትያናትን እኛ ነን ማስተዳደር ያለብን የሚል የኀይል እርምጃ ከወሰዱ ከሕግ ተጠያቂነት አይተርፉም። ሌላው ደግሞ ከላይ አንቀፀ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን ቀሳውስት እንዳደረጉት ቀሳውስቱ እና ምዕመኑ እስከፈቀዱላቸው ድረስ አንገዛም ለማለት ዕቅድ ካላቸውም የውስጥ ጉዳይ ይሆናል። ችግሩ ግን የመጨረሻዎቹን ሁለቱን እናደርጋለን ካሉ፥ ይህንን ከሚቃወሙት ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡ በዚህ መሐል ተጎጂዎች ንፁኃን ምዕመናን/ዜጎች ናቸው።

ለመብት ተሟጓቾች

የመብቶች ተሟጋቾች 1ኛ፣ ጥያቄው የእምነት ነጻነት ሳይሆን የአገልግሎት አሰጣጥ (አስተዳደራዊ) መሆኑን መረዳት፣ 2ኛ፣ ችግሩ ላይ (በቋንቋ የእምነት አገልግሎት ማግኘት ጉዳይ ላይ) መግባባት ቢኖርም የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ በአማኞቹ ዘንድ ልዩነት መኖሩን መረዳት፣ እና 3ኛ) የችግሩ አፈታት ላይ ያለው ልዩነት ወደ ግጭት ሊያመራ እና የዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችልበት ዕድል እንዳለ መረዳት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን የፖለቲካ ኀይሎች አሰላለፍ፣ የኀይል ሚዛን፣ የብሔርተኞቹ ከሌሎች ብሔር አባላት ጋር ያላቸው ፉክክር እና ጥላቻ እንዲሁም ብሔር ተኮር የመለያየት መፍትሔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ማስታወስ ያስፈልጋል።

በችግሩ አፈታት ዙሪያም፣ 1ኛ፣ መንግሥት የትኛውንም ወገን ይህን አድርግ ወይም አታድርግ የማለት መብት የለውም። 2ኛ፣ የትኛውም ወገን መንግሥትን እንዲህ አድርግ ወይም እንዲህ አታድርግ የማለት መብት የለውም። ስለሆነም ምዕመናንን ለግጭት የሚጋብዝ ማንኛውንም አካሔድ መከታተል፣ ቀድሞ ሥጋቶችን ማሳወቅ እና መከላከል ይገባል። ምክንያቱም ብሔርን ብሎም ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ከዚህ በፊት እንዳየናቸው በቀላሉ ሊዘነጉ የሚችሉ የመንግሥት እና የሕዝብ ግጭት ሳይሆኑ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ነው የሚሆኑት። በቀላሉ ለማረጋጋት እና ዘላቂ መፍትሔ ለማውረድ ይቸግራል። በተጨማሪም ከላይ የተጠቀሱትን ታሪካዊ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቁጣ እና ግጭት የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን ከማስተላለፍ መቆጠብ ያስፈልጋል።

1 comment:

  1. በፍቄ፣
    ይህን ሊንክ አስቱ ልካልኝ ሼር ላርግ ብዬ ነው። ብዙ ጠቃሚ ጽሑፎችን አግኝቼበታለሁ። ሌሎች ድረገጾች ላይ ሊስት ተደርጎ እንደሆነ ፈልጌ አላገኘሁም። እንዲህ የመሳሰሉትን ገጾች አሰባስበህ መለጠፍ ብትችል ይጠቅማል። በአሳብ ነጻነት የምታምኑ ከአንተ ጋር ጥቂቶች ናችሁ። ብዙዎች አሳባቸውን የሚደግፍ ካልሆነ አያትሙም። ቻዎ፣ አዲስ። https://bit.ly/2piuNyp

    ReplyDelete