☞ የአዲስ አበባን የውሃ ፍላጎት ይቀርፋል የተባለ ፕሮጀክት በተዋወቀ ማግስት የኦሮሚያ መንግሥት አልተማከረም ነበር ተብሎ ተሰረዘ (ምክንያቱም ጃዋር ተቃውሞል)
☞ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ወጥቶ በኅትመት እንዳይሰራጭ የመስተዳድሩ ጋዜጣ (አዲስ ልሳን) ላይ መታተም ከተጀመረ በኋላ እንዲቋረጥ ተደረገ (ምክንያቱም ጃዋር ተቃውሟል)
***
☞ ጃዋር "ኹለት መንግሥት አለ" ብሎ ነበር፤ "ኹለተኛው መንግሥት" የተባለው ሥራ በማጣት ምሬት በሕዝባዊ አመፅ ሕይወቱን አደጋ ላይ እስከመጣል ሊደርስ የተዘጋጀ ወጣት ነው።
☞ ጃዋር "አዲስ አበባን ቀለበት ውስጥ አስገብተን" ያሻንን ማድረግ እንችላለን ብሎ ነበር፤ ለዚህም "ኹለተኛው መንግሥት የጦር መሣሪያ ነው።
ለመኾኑ ኦሮሚያን እያስተዳደረ ያለው ማነው? አዲስ አበባስ ምን ታድርግ?
ኢትዮጵያ ውስጥ 'የማንነት ጥያቄ' አለ። ግን ብቸኛው ጥያቄ አይደለም፤ መፍትሔውም ብሔርተኝነት ወይም ደግሞ ብሔረ መንግሥት (nation state) መመሥረት አይደለም። እንደውም ከችግርቹ አንዱ ይኸው ብሔርተኝነት እና ብሔረ-መንግሥት ለመመሥረት ታስቦ የሚሠራው ሥራ ነው። ይኹን እንጂ ብሔርተኝነትን በማጦዝ አንዱ ፖለቲካዊ ተፈላጊነቱን (political relevance) ለመጨመር፣ ሌላው ፖለቲካዊ ታማኝነቱን ለማረጋገጥ፣ ቀሪው ደግሞ በአጋጣሚው ሥልጣን ለመንጠቅ ወይም ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ርብርብ ከሚበጀው ይልቅ የሚፈጀው እየበዛ ነው። እውነተኛ የሕዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማዕከል የኾነችውን አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿን እንደታጋች ቆጥሮ በላይዋ ላይ የውክልና (proxy) ጦርነት እየተካሔደባት ነው። በዚህ ሁሉ ትግል ውስጥ ለሥራ አጥ የኦሮሞ ወጣቶችም ይሁን ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለመስዋዕትነት ከሚያማልላቸው ውጪ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይኼ ነው የሚባል ተስፋ የሚሰጣቸው ወገን እስካሁን የለም።
የአዲስ አበባ ተጎራባች ገበሬዎች ችግር ምንድን ነው?
የአዲስ አበባ ተጎራባች ገበሬዎች ችግር አዲስ አበባ እንደ አውራ ከተማነቷ የአገሬውን ቀልብ ሁሉ መሳቧና አለቅጥ መለጠጧ ነው። ችግሩ አለቅጥ መለጠጧ ብቻ ሳይሆን ስትለጠጥ እና የልማት አገልግሎት ስትሻ የምታፈናቅላቸው መኾኑ ነው። በተጨማሪም አዲስ አበባ ከተማ እንደመኾኗ የተጎራባቾቿን ማንነት እያቀለጠች የምትውጥ መኾኗ እሙን ነው። ይኹንና የከተሞች መስፋፋት የወደፊቱ አይቀሬ ዕጣ ፈንታ ነው። አዲስ አበባም ትሁን ሌሎቹ ከተሞች በዙሪያቸው ያሉ ገበሬዎችን እያከተሙ መዋጣቸው አይቀሬ ነው። የትኞቹም የገበሬ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ከተሜ ቢኾኑላቸው አይጠሉም፤ የተሻለ የሕይወት ጣዕም የሚገኘው ከተማው ውስጥ ነውና። ገበሬዎቹ የሚጠሉት ከተሞቹ ሲስፋፉ እነሱንም የከተማው አካል እያደረጉ አለመስፋፋታቸውም ነው። ይኽ እንዳይሆን በኢትዮጵያ ቢያንስ ኹለት ዋና እንቅፋቶች አሉ።
አንደኛው እንቅፋት ገበሬዎችም ይሁኑ ሌሎች በመሬታቸው ላይ የመወሰን ሥልጣን የሌላቸው መኾኑ ነው፤ 'ገበሬዎች መሬት የመሸጥ የመለወጥ ሥልጣን ከተሰጣቸው ከበርቴዎች ገበሬዎቹን በገንዘብ ደልለው መሬት አልባ ያደርጓቸዋል' የሚል ሰበብ የሚሰጠው መንግሥት እና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የገበሬዎቹን መሬት በሊዝና በትንንሽ ካሣ (አንዳንዴ ካሣውም ሳይከፈል ይቀራል) እያፈናቀሉ የገበሬዎቹን ቤተሰቦች መንገድ ላይ መበተናቸው አለመቅረቱ ነው። ሌላኛው እንቅፋት የፅንፈኞች ጦርነት ነው። በዚህ ጉዳይ ፅንፈኞች የምላቸው "አዲስ አበባን አካታች ማድረግ ያስፈልጋል" የሚለውን የሚቃወሙ በአንድ ወገን እና "አዲስ አበባን የአንድ ብሔረ-መንግሥት አካል" ማድረግ ያስፈልጋል በሚል እዚያ እና እዚህ ወጥረው የያዟት ፖለቲከኞች ችግር በሌላ ወገን ነው።
በሌላ በኩል፣ ፖለቲከኞቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያገኙትን በሙሉ በሥጦታ ወይም በዝርፊያ ያገኙት በማሥመሰል ሥራ ተጠምደዋል። በዚህ ፕሮፓጋንዳም ለዒላማቸው ግብ አጎራባቾቿ ከተማዋን 'ሳቦታጅ' እንዲያደርጉ እየገፋፏቸው ነው። በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ግንኙነቶች በገዢና ሻጭ መካከል ያሉ 'ትራንዛክሽኖች' ናቸው። የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ግንባታንም ኾነ የለገዳዲ የውሃ ግድብ ግንባታን የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ሳያውቅ የአዲስ አበባ አስተዳደር ግንባታ ውስጥ ይገባል ብዬ አላምንም። እንደዚያም ከኾነ ችግሩ የአስተዳደሮቹ ስለኾነ አስተዳደሮቹ አለመቻላቸውን አምነው ለሚችሉ ይልቀቁ፤ አለበለዚያ የሥልጣን እና የጥቅማ ጥቅም አጀንዳቸውን ለማሳካት የከተማዋን እና አጎራባች ነዋሪዎች የግጭት ውጥረት ውስጥ መክተት አደገኛ ቁማር ስለኾነ አቁመው በነጻ ውድድር አሸናፊውን ወገን ሕዝብ የመምረጥ ዕድል ይሰጠው።
የአዲሳባ ችግር ምንድን ነው?
አዲስ አበባ ብዙ ችግሮች ሊኖሩባት ይችላሉ። ከነዚህ ችግሮቿ ውስጥ የአካታችነት ችግር አንዱ ነው ብዬ አምናለሁ። ምንም እንኳን ነዋሪዎቿ ቅይጥ በመኾናቸው እንደ ወጥ መመልከቱ (homogenizing) ስህተት ቢሆንም፥ አንዳንድ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ክፍሎችን እና ፖለቲካቸውን በጥርጣሬ ማየት ከጥቅል ድክመቶቿ አንዱ ነው፤ ማኅበራዊ ንቃት ላይ ብዙ መሥራት ያሻል። እንዲያም ኾኖ ግን ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ የተሻለ አካታች የምትባለው ራሷ አዲስ አበባ ነች። ላልተሟላው አካታችነቷ ተጠያቂው ግን በተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት ሽሚያ ዒላማ ተደርጎ የታነፀው ሕዝብ አይደለም። የፖለቲካ ስርዓቶቹ ናቸው። የፖለቲካ ስርዓቶቹ አዲስ አበባ ሁሉንም ወካይ ለማድረግ ትዕምርታዊ መገለጫዎችን ማኖር፣ የኢትዮጵያውያንን የተለያዩ ባሕሎች እና ቋንቋዎችን ማስተዋወቅ እና ማበረታታት የመሣሠሉ ሥራዎችን መሥራት ነበረባቸው።
ከነዚህ ውጪ የፖለቲካ ስርዓቶቹ እና ፖለቲከኞቹ የማንነትን ጥያቄዎችን ከብሔርተኝነት ጋር በማቆራኘት የፈጠሩት ምሥል እና የተረኛ ጨቋኝነት ፍላጎት አባዜ በከተማዋ እና አጎራባቾቿ መገፋፋቱን ተባብሶ እንዲቀጥል አድርጎታል። ይሁን እንጂ በከተማዋ መስፋፋት ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ማድረግ የሚችሉት ምንም ነገር የለም፤ ጉዳዩ አስተዳደራዊ መፍትሔ የሚፈልግ የሥልጣኔ ሒደት ነው። ምክንያቱም ይኽ በማደግ ላይ ያሉ አገራት፣ ከተሞች ሁሉ እውነታ ነው። ለዚህም ነው ንፁኀን ነወሪዎች የፖለቲካ ውክልና ጦር ሜዳ ሰለባ መደረግ የማይኖርባቸው።
የኦሮሚያ መንግሥት ገጽታ…
እንደተናጋሪው ፍላጎት የብሔር ወይም የብዝኀ ብሔር እየተባለ የሚጠራው ፌዴራሊዝም ዘውገኝነትን ተቋማዊ በማድረጉ የሚታማ መኾኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ክልሎች ምንም እንኳን የብዙ ዘውግ ቡድን አባላት የሚኖሩባቸው ቢኾንም የተወሰኑ ብሔሮች ንብረት ተደርገው ነው የሚቆጠሩት። ይህ ለብሔረ መንግሥት አስተሳሰብ ቦታ ሰጥቷል። የዜጎች መንግሥት እንጂ የብሔር መንግሥት አስተሳሰብ ከዓለም እንዲጠፋ ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ጊዜ፥ በኢትዮጵያ ግን ዜጎች በተለያዩ "የብሔር" ክልሎች ውስጥ በኹለተኛ ዜግነት ማዕረግ እንዲመደቡ ተገድደዋል።
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ገጽታም በዚሁ መሠረት የተገነባ ነው። በርካታ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ያልኾኑ ዜጎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ውስጥ ኦሮሞ ያልኾኑ የኢትዮጵያ ዜጎች የመንግሥት ሥራ አካላ መኾን የማይችሉበት አሠረር በክልሉ ተዘርግቷል። ይኽ ችግር የአዲስ አበባን ተጠሪነት ወደ ኦሮሚያ ለማድረግ የሚጠይቁ ኦሮሞዎችን ጥያቄ እንኳን እንደ አንድ የፖለቲካ ወይም አስተዳደር ጥያቄ ብቻ መመልከት እንዳይቻል አድርጓል። ጉዳዩ እየታየ ያለው የብሔረ መንግሥት ማነፁ ጥረት አንድ አካል ተደርጎ ነው። ስለዚህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች (ምንም እንኳን አሁንም በቂ ወይም ቅቡልነት ያለው አስተዳደራዊ ውክልና ባይኖራቸውም) የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ጥያቄ በጥርጣሬ የሚመለከቱበት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ይኸው ነው።
'ባላደራ' እስከ ምርጫ…
በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው የባልደራሱ ቡድን 'ብቸኛው ሕዝባዊ ውክልና ያለን [ባላደራ] እኛ ብቻ ነኝ' እያለ ነው። በዴሞክራሲያዊ መርሕ ውክልና የሚሰጠው በቂ መረጃ ባለው መራጭ፣ የተለያዩ አማራጮች ቀርበውለት፣ በነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ በተካሔደ የተመረጠ አካል ነው። ይኽንን የባልደራሱ ቡድን አያሟላም። ስለዚህ እኔ 'ብቸኛ' ወይም 'ወኪል' የሚሉትን ባልቀበላቸውም ግን በአሁኑ ሰዓት ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ሥጋት ውስጥ የገቡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ 'ይወክሉኛል' የሚላቸው ሊኖር ይችላል የሚለውን እቀበላለሁ። ነገር ግን በመርሓችን መሠረት የታከለ ዑማ አስተዳደርም ይህንን ባያሟላም፥ 'ይወክለኛል' የሚለው የአዲስ አበባ ነዋሪም መኖሩ አይቀርም። ይልቁንም የታከለን አስተዳደር እንደ ባላደራ መቁጠሩ ሊበጅ ይችላል ብዬ አምናለሁ፤ ምክትል ከንቲባቸውም የራሳቸውን ሚና እንደዛ ቢቆጥሩ የሚበጅ ይመስለኛል።
እንደምናየው የታከለ ዑማ አስተዳደር ሊወስን የሚሞክረውን የኦሮሚያ ክልል እያስቆመው ነው። ኾኖም አዲስ አበባን የመወከል ሕጋዊ ኀላፊነት አንፃራዊ የተሻለ ተቀባይነት ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ተሰጥቶታል። ስለሆነም ይህንን ኀላፊነት 'እንደ ባላደራነት' በመጠቀም የከተማዋ ነዋሪዎች "በርግጥም ይወክለኛል"፣ "እኔን ወክሎ ይከራከርልኛል" የሚሉትን አስተዳደር እንዲመርጡ መራጮች በቂ መረጃ አግኝተው የሚካሔድ ነጻ እና ርትዓዊ ምርጫ እንዲዘጋጅ ኹኔታዎችን ያመቻቹ። ምርጫ ቦርድም ይኽንን ለማስፈፀም ታጥቆ ይነሳ። የባልደራሱ ቡድንም ከዚህ የተለየ የሚጠይቀው ነገር ያለ አይመስለኝም።
No comments:
Post a Comment