Pages

Sunday, November 5, 2017

ተቃዋሚዎች ከራሳቸው ይልቅ ኢሕአዴግን ያምኑ ይሆን?

ከዓመታት በፊት አንድነት ፓርቲ በሕይወት ሳለ፣ የቀድሞዎቹ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት አቶ ስዬ ኣብርሓ እና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፓርቲውን ሊቀላቀሉ ሲሉ ትልቅ ፌሽታ ሆኖ ነበር። እንዲያውም ‘መርሕ ይከበር’ በሚል የተገነጠለው ቡድን፣ እነርሱን ለመቀበል የተዘጋጀውን ድግስ በአመፅ እስከማደናቀፍ ደርሷል(?)። ቅራኔው “እነርሱ የተለየ አቀባበል የሚደረግላቸው የገዢው ፓርቲ የቀድሞ አባል ስለሆኑ ነወይ?" የሚል ነበር። ተቃዋሚው የቀድሞ የኢሕአዴግ አባል ለቅቆ ሲወጣ ማግነን ያውቅበታል። በአንድ በኩል ሳስበው፣ መቃወማቸው ትክክል መሆኑን የገዢው አባላት መልቀቅ ለተቃዋሚዎቹ ስለሚያረጋግጥላቸው ይመስለኛል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከጥቅም ባሕር ውስጥ መውጣት ስለሚከብድ ያንን እያሰቡ ይመስለኛል። የኋለኛውን እንዳላምን እንደ ዶ/ር ነጋሶ፣ ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ ተገፍተው ነው ከገዢው የሚወጡት።

የሆነ ሆኖ፣ አናንያ ሶሪ በስላቅ እንደተናገረው፣ ‘ብለን ብለን ኦሕዴድ እና ብአዴን ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ዛሚ እና ENN ነጻ ሚድያዎች የሆኑበት ዘመን ላይ ደርሰናል’። ለማንኛውም በምናገባኝ ነገሩን ከመታዘብ ይልቅ የኦሕዴድ (እንዲሁም የብአዴን) የሰሞኑ እምቢተኝነት እውነት ወይስ የሕወሓት ሴራ? ተቃዋሚው (በፓርቲ የታቀፈውም ያልታቀፈውም) ጉዳዩን እንዴት ነው ማስተናገድ ያለበት? የሚሉትን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክር።

የጠላቴ ጠላት ለኔ ምኔ?

በተቃዋሚዎች ዘንድ "የሕወሓት የበላይነት" መኖሩ እምብዛም አጠራጣሪ አይደለም። ማኅበራዊ ሚድያ አሁን (ከተዳራሽነቱ በላይ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሐሳብ አቅጣጫ አስማሪ እንደመሆኑ ይህንን እምነት የበለጠ በማስረፅም ሆነ በመታገል ረገድ የጉዞ ካርታ (road map) አስቀማጭ ነው። ይህንን ብዙዎች መረዳታቸው ሽሚያ ፈጥሯል። መጀመሪያ ታሪክን፣ ከዚያ ድልን፣ አሁን ደግሞ ሟችና ገዳይን መሻማት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በዚህ መሐል የሕወሓት ደጋፊ/ካድሬዎችም የራሳቸውን ትርክት ይፈጥራሉ። ተቃዋሚው ደግሞ እነርሱ የወደዱትን መጥላት፣ እነርሱ የጠሉትን መውደድን እንደ ምላሽ ይገብራል። አንዳንዴ ሳስበው የሕወሓት ካድሬዎች ተቃዋሚው የሚፈልጉትን እንዲያደርግላቸው ከፈለጉ፣ ያንን ነገር እንዳያደርገው መቀስቀስ ብቻ የሚበቃቸው ይመስለኛል። "ገዱን የምወደው ሕወሓት ስለምትጠላው ነው” የሚል መፈክር ሰምቻለሁ። አቶ ገዱ በሕወሓት ካድሬዎች ፌስቡክ ላይ ከመተቸታቸው በቀር ፓርቲያቸው (ብአዴን) በሕወሓት እልቅና የሚተዳደረው ኢሕአዴግ አባል ነው። የኦሕዴድ የሰሞኑ ነገርም ያው ነው። ይህ ዓይነቱ ምክንያት ለብአዴንም ይሁን ለኦሕዴድ የድጋፍ መሠረት ሊሆኑ አይችሉም።

ኦሕዴድ እና ብአዴን እውን ሕወሓት ላይ አምፀዋል?

ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በፊት ፌዴራል ፖሊስ የኦሮምያ ከተሞችን መናኻሪያው ሲያደርገው፣ በአማራ ከተሞች ግን (ቢያንስ ተቃውሞዎችን ለመበተን) አልገባም ነበር። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በታወጀበት ወቅት የሚበዙት እስረኞች የታፈሱት ከኦሮሚያ አካባቢ ነበር። ሌላው ደግሞ እነ ኮሎኔል ደመቀን ለፌዴራል መንግሥቱ አሳልፎ ባለመስጠቱ፣ በዚያ ላይ ብአዴን በላዕላይ ደረጃ ሹም ሽረት ባለማድረጉ፣ በተወሰነ ደረጃ ብአዴን የክልሉን ነጻነት (autonomy) እያስከበረ ነው ማለት ነው በሚል ወስጄው ነበር። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ወቅት የክልሉን ነዋሪዎች ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ በፌዴራሉ የፀጥታ ኃይሎች በዝምታ እንደተሠራ ሰማሁ። እንዲሁም ከክልሉ ታፍሰው መቐለ፣ ባዶ ሽድሽት ታስረው የተፈቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባሎች አግኝቼ የክልሉ ነጻነት (ወይም የአቶ ገዱ እና ፓርቲያቸው እምቢተኝነት) ላይ ያለኝ የማመን ዝንባሌ ቀስ በቀስ ተገፈፈ። በርግጥም አሁን፣ የሕወሓት ካድሬዎች ስሞታቸውን ከብአዴን ላይ አንስተው ወደ ኦሕዴድ አዙረዋል። ኦሕዴድም በተራው ደጋፊ እየጎረፈለት ነው።

ኦሕዴድ በተቃዋሚዎች ዘንድ ሳይቀር ተአማኒነት እንዲያገኝ ያደረገው በኦሮሚያ ሶማሊ ክልሎች ድንበር ነዋሪዎች ዘንድ በተደረገው ግጭት ላይ፣ የክልሉ መንግሥት ባሳየው ለክልሉ ነዋሪዎች ያደላ ተቆርቋሪነት ነው። በዚህ ላይ የሶማሊ ክልል መንግሥት ያንፀባረቀው ብስለት የጎደለው ምላሽ ግጭቱን በማባባስ፣ የኦሕዴድን ተቀባይነት ጨምሮታል። የሶማሊ ክልል ገዢ ፓርቲ (መንግሥት) የ2008ቱን ሕዝባዊ አመፅ ከመቃወም ጀምሮ፣ ያሳየው ዝንባሌ በሕወሓት ወዳጅነት አስፈርጆታል።
ስለዚህ ከሶማሊ መንግሥት ጋር የኦሮሚያ መንግሥት መጋጨቱ፣ ኦሕዴድ ሕወሓትን እንደደፈረ ተደርጎ ተተርጉሟል። በተለይ እኔ ራሴ ቢሾፍቱ ተገኝቼ ባየሁት የኢሬቻ በዓል ላይ እና ከዚያ በኋላ በተካሔዱ ተቃውሞዎች ላይ የክልሉ ፖሊስ አንድም እርምጃ አለመውሰዱ፣ ቀድሞም እነጃዋር “ገዳያችን አግኣዚ ነው” የሚሉትን ተአማኒ አድርጎታል። ለኦሕዴድም ግርማ አላብሶታል።

የኢሕአዴግ አባሎች እንቢታ ምን ፋይዳ አለው?

"የሕወሓት የበላይነት" በፌዴራል መንግሥቱ ብቻ ሳይሆን በኢሕአዴግ ውስጥም አለ። ይህ የሚጀምረው ከአመሠራረታቸው ነው። የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች፣ በሕወሓት ፍላጎትና ርዕዮተዓለም ተጠርበው፣ ለሕወሓት በኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ ክልሎች ቅቡልነት ለማስገኘት የተፈጠሩ ቡድኖች ናቸው። ‘እነዚህ የግንባሩ አባላት የሚያደርጉት ‘መፈንቅለ ሕወሓት’ ተረኛ ጨቋኝ ከማምጣት ውጪ ምን ያመጣሉ?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

አምባገነን ገዢን ለመጣል የሚደረገው ትግል ብዙ ፈርጅ አለው። አንዱ አማራጭ ቡድን አቅርቦ ሕዝቡ እንዲመርጠው ማድረግ ነው። ሌላው፣ ገዢው ፓርቲን ሕዝቡ እንዳይቀበለው ማድረግ  ነው። ኢሕአዴግ አማራጭ ኃይሎችን በሚችለው መንገድ ሁሉ ያዳክማል። ተቃዋሚዎች ግን የማዳከም ዕድሉን ለማግኘት እንኳን ሲሞክሩ አይታዩም። በ2008ቱ የኦሮሞ ሕዝብ አመፅ ወቅት ግን የኦሮሞ አክቲቪስቶች ለደረሰው ጥፋት ሁሉ የክልሉን መንግሥት በመውቀስ ፈንታ አግኣዚ እና ሕወሓትን ላይ በማሳበብ በስተመጨረሻ፣ በከፊልም ቢሆን የታችኛው የኦሕዴድ ካድሬዎችን ልብ ከሕወሓት መነጠል ችለዋል። ኦሕዴድን ከሕወሓት መነጠል፣ ወይም ውስጣዊ ነጻነቱን እንዲያስከብር መቻል ለተቃዋሚው የራሱን ዕድል ይሰጣል። ስለዚህ ተቃዋሚው ከዶግማዊ ተቃውሞ ወይም ድጋፍ ይልቅ፣ ስልታዊ ድጋፍ እና ተቃውሞ ማድረግ ለድል ያበቃዋል የሚል እምነት አለኝ። ጥያቄው መሆን ያለበት፣ ‘ድጋፉ ከስልት አልፎ ሙሉ እምነት ዕድሜ ልካቸውን ሲጨቁኑ ወይም ለጨቋኝ አሳልፈው ሲሰጡ የነበሩት ላይ መጣል ደረጃ ተደርሷል ወይ?’ የሚለው መሆን አለበት።

በፌስቡክና ትዊተር ላይ ለኦሕዴድ የቀረበለትን ድጋፍ እየተመለከትኩ ነበር። ለድጋፍ የሚቀርቡትን ምክንያቶች እንደሚከተለው አዋቅሬያቸዋለሁ፦

፩ኛ፣ ኦሕዴድ በአሁን ይዞታው የኦሮሞን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቁ ነው በሚል፤
፪ኛ፣ የግንባሩ ውስጥ-ለውስጥ ትግል ኢሕአዴግን ያፈርሰዋል/ያዳክመዋል (በዚህም ተቃዋሚው የመጠናከር ዕድል ያገኛል) በሚል፤
፫ኛ፣ በፓርቲ ውስጥ ያለው የሕወሓት የበላይነት መቀረፍ፣ በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ ያለውን የበላይነትም ይቀርፈዋል በሚል፤
፬ኛ፣ ታሪካዊ ብሶት የሌለበት አናሳ ቡድን ከሚጨቁነኝ፣ ታሪካዊ ብሶት ያለበት ብዙኃን ቡድን ቢጨቁነኝ ይሻላል በሚል፤
፭ኛ፣ ኦሕዴድ "የኛው" (የኦሮሞዎች) ስለሆነ ከቀናው ተረኛ መሪ እንዲሆን ዕድሉን እንስጠው በሚል፤
፮ኛ፣ ሌሎች…

በተመሳሳይ፣ የኦሕዴድን ማፈንገጥ (ያፈነገጠ መምሰል) ያልተቀበሉት፦

፩ኛ፣ የኦሕዴድ (የብአዴንም ሊሆን ይችላል) ‘ያፈነገጠ መምሰል’ የሕወሓት የፖለቲካ ሴራ ነው ብለው ያመኑ፤
፪ኛ፣ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በተፈጥሯቸው ሊለወጡ የማይችሉ ናቸው የሚሉ፣
፫ኛ፣ የግንባሩ አባላት የፈለገ ቢለወጡ ምንም ዓይነት ይቅርታ ሊደረግላቸው አይገባም የሚሉ፣
፬ኛ፣ ሕወሓት በመከላከያ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ያለው ቁጥጥር የእነኦሕዴድን መፍጨርጨር የትም አያደርሰውም እና ጉልበት እነርሱ ላይ ማባከን አያስፈልግም የሚሉ፤ እና፣
፭ኛ፣ የተለያየ ምክንያቶች የሚሰጡ ናቸው።

አፈንጋጭ የተባሉትን ምንም ዕድል ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆኑት በፖለቲካ ዓለም ቋሚ ወዳጅ ወይም ቋሚ ጠላት የሚባል እንደሌለ የዘነጉ ይመስላሉ። ግዚያዊ ወዳጅነቶች/ጠላትነቶች ለሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ካለው ፋይዳ አንፃር ነው መገምገም የሚኖርባቸው። ሁሉን ነገር የሕወሓት ሴራ ነው ብሎ ማሰብ ሕወሓት የገዘፈ ብልሐተኛ የማድረግ አባዜ ይመስለኛል። ኢሕአዴግ ብልሕ እየሆነ ከሆነም ከሱ በላይ ብልሕ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል። ይህ ሕወሓትን የተወሳሰበ የፖለቲካ ጫወታ ባለቤት ማድረግም ይሁን የገዢው ፓርቲ አባላትን ሲለቅቁ እልል ብሎ መቀበል፣ ከራስ ይልቅ ለኢሕአዴግ ያለን የተደበቀ እምነት አሳባቂ ይመስላል።

ሕወሓት ለምን ዝም አለ?

ብአዴን ሲተብት፣ ኦሕዴድ ሲያፈነግጥ - አለቃ ተብዬው ሕወሓት ለምን ዝም አለ? እስኪ ማን ማን እንደሚያፈነግጥ ልያቸው እና ለቃቅሜ ልክ አስገባቸዋለሁ ብሎ ነው? ወይስ፣ የራሱ ሴራ ስለሆነ (በዚህ አጋጣሚ ተቃውሞው ስለታገሰለት፤ እንዲሁም ዳያስፖራው ከጫወታ ውጪ ስለሆነ) ደስ ብሎት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች በአሻጥር ትንተና ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃዎች መገምግም ያስፈልጋል። በመልሱ ላይ ተመሥርቶ ስልታዊ ድጋፍ/ተቃውሞ ማድረግ ይከተላል። የአሁኑ ግን ጭፍንነት ይበዛዋል ባይ ነኝ።

የኦሕዴድ ኅብረ ዝማሬ ምንጩ ምንድን ነው?

የኦሮሞ ፖለቲከኞች ‘በአንድነት ኃይሎች’ በጠባብነት እና በተገንጣይነት የመፈረጃቸው ነገር ያደባባይ ምሥጢር ነው። ነገር ግን የምር ኢሕአዴግ ውስጥ ሕወሓትን ለመቀናቀን ከፈለጉ አንድ አጋር ያስፈልጋቸዋል። ፈዛዛው ደኢሕዴን የሕወሓት ካርድነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ስለዚህ ከብአዴን ጋር መተባበሩ የግድ ነው። ኦሕዴዶች ጉባኤያቸው ላይ ባሳለፉት አቋም፣ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ለኢትዮጵያዊ ኅብረት ያላቸው ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ መግባት እንደሌለበት በመሐላ እያረጋገጡ ነው። 7ኛ መደበኛ ጉባዔያቸው ላይ አቋም ከወሰዱባቸው ነጥቦች አንዱ “የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም እና የኢትዮጵያውያንን ኅብረት ጉዳይ የማይደራደሩበት” መሆኑን ገልጸዋል። የጥቅምት 25-27ቱ የምክክር መድረክ ዓላማም ይኸው ይመስለኛል። (ከታች ሶልያና ሽመልስ በትዊተር ላይ የኦሕዴድ-ብአዴንን የሰሞኑን ኅብረት የሚደግፉት ሰዎች ለምን እንደሚደግፉት የጠየቀችበትን ፖል ውጤት አስቀምጣለሁ፤ ብዙዎቹ “ለኢትዮጵያ አንድነት ይጠቅማል” በሚል ተስፋ ነው ድጋፋቸውን የሰጡት።)
ብዙዎቹ መልስ ሰጪዎች የሁለቱን ድርጅቶች
ኅብረት የሚደግፉት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ተስፋ
አድርገው ነው። የኦሮምኛ እና እንግሊዝኛው
ፖልም ተመሳሳይ ውጤት ነው ያላቸው።

ከመደምደሜ በፊት ግን የኦሕዴድ-ብአዴን ጥምረትን ለሚደግፉ ሁለት ማስጠንቀቂያዎችን አኖራለሁ፦ አንደኛ፣ የሁለቱ ቡድኖች ጥምረት ከሠመረ ዴሞክራሲ ሊያመጣ የሚችል የመሆኑን ያክል፣ የብዙኃን ገነንነት (majority dictatorship) ሊያመጣ የሚችል እንደሆነ እንዲያስቡበት፤ ሁለተኛ፣ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ወይም ተቃውሟቸው ሙሉ ለሙሉ በሁለቱ ፓርቲዎች ላይ ጥገኛ አድርጎ እንዳያስቀራቸው እና መርሕ-መር መሆን እንደሚኖርበት ሁሌ ራሳቸውን ማስታወስ እንዳይዘነጉ ነው።

ከሁሉም በላይ ግን ይህ በሕዝብ አመፅ የተገኘ ዕድል ለኦሕዴድ እና ብአዴን የሥልጣን መወጣጫ እርካብ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር መትጋት ያስፈልጋል።

1 comment: