Pages

Monday, August 8, 2016

ቋንቋችንን እንታዘበው

በፍቃዱ ኃይሉ

፩. Independence, Freedom, Liberty (ነጻነት የቱ ነው? የቱስ አይደለም?)

"ነጻነት ውስብስብ ነው" ብዬ ልጀምር።ነጻነትየሚለውን የአማርኛ ቃል በተለምዶ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ሦስቱንም የእንግሊዝኛ ቃላት ለመተርጎም እንጠቀምበታለን። ትርጉሙ ግን ሁሌም አጥጋቢ አይሆንም።

ቃላት ባብዛኛው ደረቅ አይደሉም ፅንሰ-ሐሳብ (concept) ያዝላሉ። የሆነ ፅንሰ-ሐሳብን የሚወክሉ ቃላቶች በሆነ ቋንቋ ውስጥ የሉም ማለት የዚያ ፅንሰ-ሐሳብ በቋንቋው ተናጋሪው ማኅበረሰብ ዘንድ እምብዛም አይታወቅም እንደ ማለት ነው። ፅንሰ-ሐሳቡን በቃላት ቀንብቦ ማስቀመጥ መቻልና ብዙኃን በየለት ንግራቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ መቻል ቃሉን ከነፅንሰ-ሐሳቡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ማስረፅ ማለት ነው። ይህንን ለማስረዳት ቀላሉ መንገድ የአየር ሁኔታን መግለጽ ነው። በረዶ (Ice) እና snow (የበረዶ ብናኝ እንበለው) ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ በአማርኛ ግን የሚጠሩት በአንድ ሥም - በረዶ - ተብለው ነው። Frost (snow ወይም የበረዶ ብናኝ የለበሰ ተራራ) አመዳይ ይባላል። በአገራችን የሌለ በመሆኑ ሥሙ የውሰት እና እምብዛም የማይታወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ (መዝ 147: 16) ከመገኘቱ በቀር ቃሉም፣ ሐሳቡም በማኅበረሰቦቻችን ዘንድ የሌለ ነገር ነው። Tornado የሚለው ቃል የአማርኛ አቻ የለውም፤ ምክንያቱም በሐሳብ ደረጃም እምብዛም አይታወቅም። ሩቅ ምሥራቃውያን በየጊዜው ለሚያጠቃቸው የነፋስ እና የማዕበል ዓይነት (ነፋስን ከነፋስ፣ ማዕበልን ከማዕበል) የሚለዩባቸው እልፍ ቃላት አሏቸው። የቃላት እና ሐሳብ ቁርኝት እንዲህ ይገለጻል።

ኢትዮጵያ ውስጥነጻነትየሚለው ቃል እና ፅንሰ-ሐሳብ በአማርኛ ተናጋሪው ዘንድ እንዴት ነው እየታየ ያለው? መነባንቡ (rhetoric) ብቻ ነው ወይስ ግንዛቤውም አብሮት አለ? አብረን እንፈትሽ።

ምሳሌ ፩፦

A) Ethiopia is an independent country.
B) Zone 9 is an independent blogosphere.
C) She is an independent woman.

በሚሉት ሦስት /ነገሮች ውስጥ ‘independent’ የሚለው ቃል ሦስት ተለምዷዊ ትርጉሞች አሉት፣

) ኢትዮጵያ "ነጻ" አገር ናት።
) ዞን ነጻየጡመራ መድረክ ነው።
) እሷነጻሴት ናት።

ሦስቱ ቃላቶች በዐውድ (context) የተለያዩ ቢመስሉም በመሠረታቸው አንድ ናቸው። ሁሉም፣ማንም ላይ ጥገኛ ያልሆነ/ወይምራሱ/ሷን የቻለ/የሚለውን ሐሳብ ያዘሉ ናቸው። ነገርዬው በራስ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ወይም በሌሎች ጉዳይ ላይ አቋም ለመያዝ የማንም ተፅዕኖ የሌለበት እንደማለት ነው። መቶ በመቶ ራስን መቻል ወይም ከሌሎች ተፅዕኖ መላቀቅ የሚባል ነገር አለ ብዬ ባላምንም የሌሎችን በራስ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት በእጅጉ መቀነስ መቻልንራስን መቻልብለን ብንጠራው አይከፋኝም። በላይኞቹ ምሳሌዎች ላይ ‘independence’ ራስን መቻል ወይም ገለልተኛ የሚሉት ቃላቶች ሊተኩት ይችላሉ።


ምሳሌ ፪፦

Eritrea became an independent country since 1991.

በተለምዶ ሲተረጎም፣

ኤርትራ 1983 ጀምሮ ነጻ ወጥታለች (ነጻ አገር ሆናለች)

ከላይ ያለው አተረጓጎም አስተዳደራዊ መገንጠልን (secession) እንደ ነጻነት መቁጠር ነው። ጎረቤቶቻችንን እየወሰድን ብንነጋገር እንኳ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ እንደራሱን የቻለአገር የደረሱበት ደረጃ ከነጻነት በስተቀር በሌላ ሥም ሊጠራ ይችላል። ነጻ ወጥቷል የሚለው ቃል ‹independent› የሚለውን ቃል አይገልጸውም ማለት ነው። በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያኢንዲፔንደንትሆና ቆይታ ሊሆን ይችላል። ይህንን ግንነጻቆይታ ነበር ብሎ መተርጎም አሳሳች ይሆናል፤ አሊያም የአገሪቷን መንግሥት የመወሰን ነጻነት ብቻ ይወክላል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁሉ፣ የነጻነት ትርጉም የተዛባ እንዲሆን ያደርግብናል።

ነጻነት (freedom) ~ ያለምንም ክልከላ ወይም ዕቀባ የሚፈልጉትን የማድረግ፣ የመናገር ሥልጣን ወይም መብት ነው። Independence (“ራስንመቻል”) ግን ለነጻነት ቅድመ ሁኔታ እንጂ ነጻነት ራሱ አይደለም። ኤርትራውያን የ‹ሪፈረንደሙ› ጊዜነጻነትወይስባርነትየሚል ምርጫ ነበር የተሰጣቸው። ትክክለኛው ምርጫመገንጠልወይስአለመገንጠልብቻ ነበር ~ ራሱን የቻለ የራስ ገዝ አስተዳደር መፍጠር ወይም አለመፍጠር።

በአማርኛችን በጣም የተበደለው እና በባሕላችን እምብዛም የማይታወቀው፣ ቢታወቅም በወግ አጥባቂነታችን ተቀባይነት የማያገኝ የሚመስለኝ ቃል ደግሞ ‹liberty› ነው። የጉግል ተርጓሚ ሦስቱን ቃላቶች እንዲህ ይፈታቸዋል፦

Independence (ሦስት ተቀራራቢ ትርጉሞች አሉት) ~ the fact of being,
(1) free from outside control; not depending on another's authority. (ከውጭ አካል ቁጥጥር ነጻ መሆን፤ በሌሎች ትዕዛዝ ሥር አለመሆን፤ራስ-ገዝነትእንበለው።)

(2) not depending on another for livelihood or subsistence. (ለኑሮ ሌሎች ላይ ጥገኛ አለመሆን፤ራስን-መቻልእንበለው።)

(3) not connected with another or with each other; separate. (ከማንም ጋር ያልተነካካ፣ የተነጠለ፤ገለልተኝነትእንበለው።) በዚህ መንገድ የቃላት አጠቃቀሙን ባበዛነው ቁጥር ፅንሰ-ሐሳቡን በውስጣችን የማስረፅ ዕድል ይኖረናል።

Freedom ~
the power or right to act, speak, or think as one wants without hindrance or restraint. (ያለምንም ክልከላ ወይም ዕቀባ የሚፈልጉትን የማድረግ፣ የመናገር ሥልጣን ወይም መብት፤ነጻነትእንበለው።)

Liberty ~
(1) the state of being free within society from oppressive restrictions imposed by authority on one's way of life, behavior, or political views. (በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥልጣን ባለው አካል ተጭኖ በግለሰብ የኑሮ ዘዬ፣ ባሕሪ ወይም ፖለቲካዊ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩዕቀባዎች ነጻ መሆን፤ግላዊ-ነጻነትእንበለው። /አንዳንዶች ‹አርነት› የሚለው ይተካዋል ይላሉ፡፡)

(3) the power or scope to act as one pleases. (የአንድ ሰው እንደፈለገው የመሆን ልክ፤ግለኝነትእንበለው።)

ሦስቱን የእንግሊዝኛ ቃላት በኦሮምኛ ከአማርኛ በተሻለ መረዳት ይቻል እንደሆነ ለማጣራት ሞክሬ ነበር። ነገር ግን ኦሮምኛችንም ልክ እንዳማርኛችንነጻነት›ን የመረዳት ገደብ አለበት። ከነዚህ ትርጉም እጥረቶች የምንረዳው ነገር ቢኖር ብዙ ኢትዮጵያውያን ነጻነትን በቅጡ ተረድተነው የማናነበንበው መሆኑን ነው። እንዲሁ ሥሙ ደስ ስለሚል ብቻነጻነት’-‘ነጻነትእንላለን።


፪. Government, State (የቱ መንግሥት ነው? የትኛው አይደለም?)

ስለመብቶች እናውራ። በተለይ ደግሞ ስለሰብኣዊ መብቶች። ሰብኣዊ መብቶች በማንም የሚሰጡን አይደሉም። በተፈጥሮ የምናገኛቸው ናቸው። ይህንን መንግሥታት በሕግ ለማስከበር ቃል ይገባሉ። መንግሥታት ይህንን ቃልኪዳናቸውን የሚገቡት መብቶቻችንን ሊጠብቁ እና ሊያስጠብቁ ነው፤ እኛ [ዜጎች] ደግሞ በምላሹ በሹመት ኃላፊነቶችን እንሰጣቸዋለን። አምባገነኖች ግን ይህን መሠረታዊ የመንግሥት እና ዜጎች የግንኙነት መሥፈርት ስተው ራሳቸውን የመብት ሰጪ እና ነሺ አስመስለው ያቀርባሉ። ይህንን ተገዢዎችም ሳይታወቃቸው ይቀበሉታል።መንግሥት የሰጠኝን መብቴን…” ሲባል እንሰማለን። ዜጎች መብታቸውን መንግሥት እንደሰጣቸው ካሰቡ አለቀ፣ ደቀቀ። ሊቀማቸው እንደሚችልም ያስባሉ። ስጦታውን እንዳይቀማቸው በመፍራት ሰጥ-ለጥ ብለው ይገዙለታል፤ በእጅ አዙር መብታቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ ማለት ነው። በነገራችን ላይ አምባገነኖች ዜጎች እንዳይቀሟቸው የሚፈሩትን መብት በመንጠቅ በዜጎቻቸው መብት ላይ ያላቸውንሥልጣንበማሳየት የበለጠ ዜጎች እንዲግገዙ ያደርጋሉ እንጂመብቴን እንዳይነጥቀኝ ብሎ ታዝዛልኛለች/ታዝዞልኛልና አልነጥቀውምብለው አያስቡላቸውም።

የቋንቋ አጠቃቀማችን የነገሮች አረዳዳችንን፣የነገሮች አረዳዳችን ደግሞ አኗኗራችንን፣አኗኗራችን ደግሞ የመንግሥታችንን ዓይነት ይወስናል።

በማኅበረሰባችን ዐሳብ ውስጥ መንግሥት የአገር መሪው (head of State) ነው። ትንሽ ሲያድግ ደግሞ መንግሥት ገዢው ፓርቲ ነው። አንዳንዴ በሌላ መንገድ ደግሞ በአገር እና በመንግሥት መካከል ያለው ልዩነት ይምታታል፡፡ በመንግሥት የተማረሩ ዜጎች የአገሪቱን ሥም እንኳን መስማት እስከመጠየፍ የሚደርሱት በመንግሥት፣ በሕዝቡ እና በአገሪቱ መካከል ያለው ልዩነት ሲምታታባቸው ነው፡፡ ችግሩ ከመንግሥቱ ይሁን ከአገረ-መንግሥቱ (ወደታች እንበይነዋለን) ወይም ከሕዝቡ/ከአገሩ ለመለየት የተቸገረ ሕዝብ/ልኂቅ እንደመገንጠል፣ እንደመሰደድ ያሉ መፍትሔዎችን ይመርጣል፡፡

ይህንን ለመጻፍ የተገደድኩት የተለያዩ ሰዎችመንግሥትወይምኢትዮጵያእያሉ ሲጽፉ እነዚህን (ከታች የምዘረዝራቸውን ልዩነቶች) ሳያጤኑ ይሆንና በተለይ ማንን ለማለት እንደፈለጉ ግራ የሚገባኝ ግዜ እየበረከተ ስለመጣ ነው፡፡ በአንድ ቋንቋ እያወራን መሆናችንን በመጠራጠር!

በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ‘Government’ (‹መንግሥት›) እና ‘State’ (አሁን አሁንአገረ-መንግሥትእየተባለ ያለው) ቃላትመንግሥትበሚለው ቃል ነው በጥቅሉ የሚተረጎሙት። በፖለቲካዊ እሳቤ ግን እነኚህ ሁለቱ የተለያየ ትርጉም ነው ያላቸው። የጉግል ተርጓሚን ተውሰን ብያኔያቸውን እናጢን፣

Government (መንግሥት) ~
“the group of people with the authority to govern a country or state.” (በግርድፉ፣አንድን አገር ለማስተዳደር/ለመምራት ሥልጣኑ ያላቸው ሰዎች ስብስብ”)

State (አገረ-መንግሥት) ~
“a nation or territory considered as an organized political community under one government.” (በግርድፉ፣በአንድ መንግሥት ሥር የተዋቀረ የአንድሕዝብወይም አካባቢ የፖለቲካ ማኅበረሰብ”)

የላይኛው ፍቺ መንግሥት (government) እና አገረ-መንግሥት (State) መካከል ያለውን ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ለማስረዳት በቂ ነው። በምሳሌ ብንመለከተው፣ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነው። ቀደም ሲል ደርግ (ወታደራዊ ኮሚቴው) ነበር፡፡ መንግሥት ይቀያየራል። አገረ-መንግሥት ግን ከአንድ መንግሥት የበለጠ ዕድሜ አለው፡፡ ለምሳሌ የአሁኒቷ ኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት ከዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ በአንድ ዓይነት ካርታ (ከመጠነኛ የአጭር ወቅቶች ልዩነት ጋር) እስካሁን አለ፡፡ ነገር ግን የተለያዩ መንግሥታት መጥተው ሲያልፉ የተለያየ አስተዳደር ተከትለዋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያን አገረ-መንግሥት ይቃወማሉ፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ አሁን ባላት ቅርፅ መቀጠል የለባትም እያሉ ነው ማለት ነው፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያን መንግሥት ይቃወማሉ፤ እነዚህኞቹ ፀባቸው አገሪቱን ከሚያስተዳድሩት ቡድኖች ጋር ነው ማለት ነው፡፡ አገረ-መንግሥቱን እና መንግሥቱን በመቃወም መካከል ያለውን ልዩነት የማያስተውለው ብዙኃን ደግሞ በመሐል ቤት ከነፈሰው ጋር ይነፍሳል፡፡ ልዩነቱን የማይረዳ ብዙኃን እንደሌለ ለመረዳት ፅንሰ-ሐሳቦቹን ነጣጥለው የሚገልጹ ቃላት ብዙኃን የሚናገሯቸው የአማርኛ ወይም የኦሮምኛ ቋንቋዎች ውስጥ አለመኖራቸውን እንደማስረጃ ወስጄ ነው፡፡ በኦሮምኛ ‹mootummaa› የሚለው ቃል ሁለቱንም ‘Government’ እና ‘State’ የሚሉትን ቃላት ለመተርጎም ይውላል፡፡ (በነገራችን ላይ ተቋማት የማይፀኑልን አዲሱ መንግሥት ሲመጣ የአሮጌውን መንግሥት አሻራ ለማጥፋት የአገረ-መንግሥቱን ቅርፅ ድራሹን በማጥፋት ስለሚጀምር ነው። ምክንያቱም አገረ-መንግሥቱን ከመንግሥቱ ለይቶ አያየውም።)

በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ዘጠኝ የክልል አገረ-መንግሥታት እና አንድ የፌዴራል አገረ-መንግሥት አለ፡፡ ይህ የቅርፅ ጉዳይ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ፦

፩ኛ፣ እኛ በፌዴሬሽኑ ውስጥ መሆን አንፈልግም፣መነጠልእንፈልጋለን የሚሉትም፤

፪ኛ፣ ፌዴሬሽኑ አያስፈልግም ማዕከላዊ አገረ-መንግሥት ይኑረን የሚሉትም፤

፫ኛ፣ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር ላይ ችግር የለብንም ሥልጣን ክፍፍሉ እና አተገባበሩ ላይ እንጂ የሚሉትም፤

፬ኛ፣ ፌዴሬሽን መሆኑ ላይ ሳይሆን አወቃቀሩ ላይ ችግር አለብን የሚሉትም፤

ሁሉም መንግሥትን ይቃወማሉ፡፡ ነገር ግን ምክንያታቸው አንድ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ አገረ-መንግሥቱንም ጭምር ነው የሚቃወሙት ነገር ግን ራሳቸውን ግልጽ ማድረጊያ ቋንቋ ስለሚያጥራቸው ሁሉም ቡድኖች ሳይግባቡ እንደተግባቡ ሆነው አብረው ይሠራሉ፡፡


፫. Nation, Country, State (የትኛው ነው አገር? የትኛው አይደለም?)

ለዚህንኛው ንዑስ ርዕስ እንደመንደርደሪያ፣ፌሚኒዝምንበተመለከተ ደጋግሞ የሚነሳ አንድ ክርክር ላስታውስ፡፡ፌሚኒዝምበአጭሩ፣ በራሴ አተረጓጎም የሴቶች የዕኩልነት ንቅናቄ ነው፡፡ ንቅናቄው በተለይ በባሕል እና በቅርፅወንዳዊየሆነውን ዓለም ለሴትም ዕኩል ዕድል (opportunity) እንዲሰጥ (‹ሴታዊየማድረግ ሳይሆንሴታዊ) የማድረግ ዓለምዐቀፍ ንቅናቄ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች “‹ፌሚኒዝምከምዕራባውያን የተጫነብን፣ ለአፍሪካውያን እንግዳ አስተሳሰብ ነው፤ ማስረጃውም ቃሉን የሚተካ ለምሳሌ አማርኛ የለምየሚል ዓይነትሙግትነው፡፡ ተመሳሳይ ሙግቶችሊብራሊዝም በተመለከተም ሲሰነዘር ሰምቻለሁ፡፡ፌሚኒዝምለአፍሪካ እንግዳ ሐሳብ ነው በሚለው ላይ አልስማማም፣ ነገር ግን ሐሳቡ እንግዳ ነው ለሚለው ተጨባጭ ማስረጃ ቢኖርም እንኳን ሙግቱ ቂላቂል ነው፤ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ዘመን አመጣሽቴክኖሎጂዎች› (ራሱን ይሄን ቃል ጨምሮ) እንደ ዘመን አመጣሽ አስተሳሰቦች ሁሉ የአገር ውስጥ አቻ ቃል የላቸውም፡፡ ነገር ግን ከተቻለ የቴክኖሎጂዎቹን ሥራ የሚገልጽ ቃል ፈልገን እንጠቀማለን፣ ካልሆነ ደግሞ ከቴክኖሎጂዎቹ ጋር ተያይዞ የመጣውን የባዕድ አገር ቃል እየተጠቀምን እንቀጥላለን እንጂ ቴክኖሎጂው አፍሪካዊ አይደለም፣ ከምዕራብ የመጣ ነው ብለን ሳንጠቀምበት አንቀርም፡፡

ባሕል እና ሥልጣኔም እንዲሁ ነው፤ ከባዕድ አገራት (ባዕድ የሚለው አግላይ በመሆኑ ባልጠቀምበት እመርጥ ነበር) ሲመጡ ከትውፊታዊው ባሕላችን እና ሥልጣኔ የተሻለ ከሆነ እንኳን በዘመነ ሉላዊነት በጋርዮሽ ዘመንም ቢሆን ከመቀበል እና የራስን ከመጣል አንተርፍም፡፡ ቋንቋ ደግሞ የባሕል ዋና ቅንጣት ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋችን እና የቋንቋ ክኅሎታችን ዘመኑ መስጠት የሚችለውን ያህል እንዲረዳ እና እንዲያስረዳ የተቻለውን ያህል መለጠጥ አለበት፡፡

አገርስንል ምን ማለታችን ነው?

ቀደም ብዬ፣ “‹State› የሚለውንናአገረ-መንግሥትእያልን አሁን-አሁን የምንተረጉመውን ቃል መንግሥትየሰፋ ትርጉም ይሰጣል፤ ፅንሰ-ሐሳቡ ግን ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ነው ብዬ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ቃሉ (‹State›) ‹መንግሥትከሚለው ብቻ ሳይሆን የሚምታታውአገርከሚለውም ጋር ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ቃሉመንግሥትየሚለውን በከፊል፣አገርየሚለውንም በከፊል እንደሚገልጽ በመረዳቷ/ ነውአገረ-መንግሥትየሚለውን ጥምረ-ቃል መጀመሪያ የተጠቀመ//በት ሰው የመረጠ//ው፡፡ ‹country› የሚለው ቃል አገር፣ ‹nation› የሚለው ቃል ደግሞሕዝብተብለው በቀላሉ (በተለምዶ) ይተረጎማሉ፡፡ ነገር ግን ትርጉሞቹ እውን እያግባቡን ነው? ምሳሌ በማንሳት እንጀምር!

ዞን የበኩር የበይነመረብ ዘመቻውንሕገ-መንግሥቱ ይከበር!› በሚል ርዕስ ሲያደርግ የተጠቀመበት (እና ኋላ በአንዳንዶች ተቃውሞ ስለገጠመው፣ ሁሉን ዐቀፍ ለማድረግ ሲባል የተፋቀው) /ነገር ‹Our Nation is Ethiopia, Our Nationality is Ethiopian and We are the People of Ethiopia.› የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ ትርጉሙን በአማርኛ ለማስቀመጥ አልሞከርንም ነበር፡፡ ምናልባት ብንሞክር ኖሮ እንዲህ የሚሆን ይመስለኛልአገራችን ኢትዮጵያ፣ ዜግነታችን ኢትዮጵያዊ፣ እኛ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ነን፡፡ ነገሩ ችግር ያለው አይመስልም፤ አንዳንድ የበይነመረብ ላይ የዘውግ-ብሔርተኝነት (ethno-nationalist) አራማጆች ግን በዚህ መንገድ አልተረዱንም ወይም ሊረዱን አልፈለጉም ነበር፡፡ ‹Ethiopia is not a nation; it is an empire› (‹ኢትዮጵያብሔርአደለችም፤ ግዛተ-ዐፄ ናትእንደማለት) የሚል ነበር አንዱ አስተያየታቸው፡፡

ኢትዮጵያብሔርአይደለችም፤ ብሔሮችስብስብ ነችየሚለው አስተሳሰብ መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው አባባል ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ስሌትብሔራዊመዝሙር፣ብሔራዊ ቡድንእናብሔራዊ ደኅንነትየሚባሉት ነገሮች ትርጉማቸው ምንድን ነው? ለመመለስ ያስቸግራል፡፡ ነው ወይስአገራዊእየተባሉ መተካት አለባቸው? “የኢትዮጵያ ብሔራዊ…” የሚባል ነገር ካለ ኢትዮጵያብሔርናት የሚል ሐሳብ ውስጡ ያለ ይመስለኛል፡፡

“Nation-State” የሚል ፖለቲካዊ ቃል አለ፤ በቀላሉ ሲተረጎምአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን ያቀፈ አገረ-መንግሥት ማለት ነው ለምሳሌ እንግሊዝኔሽን-ስቴትናት፡፡

 dictionary.com ብያኔ መሠረት፦

Nation ~
a large body of people, associated with a particular territory, that is sufficiently conscious of its unity to seek or to possess a government peculiarly its own. (‹ብሔር የራሳችን የሚሉት መንግሥት ያላቸው/የሚፈልጉ እና ኅብረታቸውን የሚያውቁ፣ በአንድ ግዛት ሥር የተሰባሰቡ ሕዝቦች ናቸው፡፡)

ወይም 

the territory or country itself (ግዛት ወይም አገር)
Nation-state: a sovereign state inhabited by a relatively homogenous group of people who share a feeling of common nationality. (‹ብሔረ-መንግሥት የወል ብሔርተኝነት ስሜት በሚጋሩ አንፃራዊ ወጥ ማንነት ባላቸው ሕዝቦች የተመሠረተ ሉዓላዊ አገረ-መንግሥት)

Country ~
a state or nation (‹አገር አገረ-መንግሥት ወይም ብሔር)

ወይም

the territory of a nation (የአንድ ብሔር ግዛት)

ኢትዮጵያ የብሔረ-መንግሥታት ፌዴሬሽን ነች፤ ቢያንስ በሕግ ድንጋጌ መሠረት፡፡ ነገር ግን የደቡብ ክልልን እንደምሳሌ ብንወስድ ደግሞ ክልሉን ብሔረ-መንግሥት ብለን ለመጥራት ከላይ ከሰጠነው ብያኔ አንፃር መግባባት አንችልም፡፡ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትየሚባል ነገር አለ/የለም የሚለው ጭቅጭቅ መቋጫ ሊያገኝ ያልቻለውብሔርበሚለው ቃል ላይ መግባቢያ ላይ መድረስ ስላልቻልን ይመስለኛል፡፡ብሔርተኛየሚለው ቃል ያለው ትርጉም በራሱ አዎንታዊ ይሁን አሉታዊ መገመት እንኳን አልተቻለም፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ችግርብሔር› (Nation) የሚለውን የመበየን አይደለም፡፡ ዘውግ (ethnicity) አንድ ብሔርንዑስ ስብስብ ነው፡፡ ማለትም አንድ ብሔር ውስጥ ብዙ ዘውጎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የዘውግን የፖለቲካ ትርጉም ስንመለከት ደግሞ በኢትዮጵያ በተለምዶብሔርየሚለውን ከምንበይንበት የተለየ አይደለም፡፡ ዘውግ በዋነኝነት በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ነገር ግን በቋንቋ ብቻ ያልተወሰነ የሕዝቦች የወል ማንነት ነው፡፡ ይህ ትርጉም ኢትዮጵያ ውስጥብሔርእያልን የምንጠራቸው ቡድኖችን በትክክል ይገልጻቸዋል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

ኦሮምኛ ሁለቱን ቃላት (ብሔር፡ saba; አገር: biyyaa) የተሻለ የሚገልጻቸው ይመስላል፡፡ አማርኛ የተዋሰው ቃልጎሳም፣ ምንጩ ከዚያው ነው የተቀዳው፡፡ በኦሮምኛጎሳየሚለውን ቃል፣ ዘውግ ከምንለው ጋር ዕኩያ ነው የሚሉ አሉ፤ ከዚያም አጥብበው በእንግሊዝኛ ‘tribe’ ከሚለው እና በዘር ሐረግ ከሚቆጠረው ጋር የሚያመሳስሉት አሉ (በእርግጥም ይህንኛው ለእውነታው የቀረበ ይመስላል)፡፡ጎሳየምንለውን ቃል በነባራዊው ሁኔታብሔርየምንለውን ነው የሚተካውብሔርእነዚህን ጎሳዎች ዐቀፏ ኢትዮጵያ ናት የሚሉ አሉ፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም፣ የዘውግ ፌዴራሊዝም፣ የብሔር ፌዴራሊዝም እያልን በምንፈልገው ሥም በጠራነው ቁጥር ፌዴራሊዝሙም የተለያየ ትርጉም ያለው ፌዴራሊዝም ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስንቃወመው ወይም ስንደግፈውም (እንደአጠራራችን/አተያያችን) የተለያየ ዓይነት ፌዴራሊዝም ነው የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው ማለት ነው፡፡


፬. Nationalism, Ethnocentrism, Racism (የትኛው ዘረኝነት ነው? የትኛው አይደለም?)

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብዙ አደናጋሪ ቃላት የታጨቀ ነው፡፡ ‘Nationalist’ (‹ብሔርተኛ›) የሚለውን ቃል በብዙ መልኩ መስማት የተለመደ ነው፤ አንዳንዴ አዎንታዊ ትርጉም ሲኖረው፣ ሌላ ጊዜ አሉታዊ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በፊት፣ በፊት ‹ኢትዮጵያዊ› ኅብረት አራማጅ የሆነ ሰው ነበር ‹ብሔርተኛ› ተብሎ የሚጠራው፥ አሁን፣ አሁን ደግሞ የዘውግ ብሔርተኛው (ethnonationalist) ነው ‹ብሔርተኛ› የሚባለው፡፡

በብሪታኒካ እንሳይክሎፔዲያ ብያኔ መሠረት፦
 ideology based on the premise that the individual’s loyalty and devotion to the nation-state surpass other individual or group interests. (ብሔርተኝነት ~ አንድ ግለሰብ ለብሔረ መንግሥቱ ያለው ታማኝነት እና ቁርጠኝነት የግለሰብ ወይም የቡድን ፍላጎቶችን የሚያልፍበት ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡)

ወይም

Nationalism, translated into world politics, implies the identification of the state or nation with the people—or at least the desirability of determining the extent of the state according to ethnographic principles. (ብሔርተኝነት ~ በፖለቲካ ቋንቋ ሲተረጎም - አገረ መንግሥትን ወይም አገርን በሕዝቡ መግለጽ፣ ወይም ደግሞ ቢያንስ አገረ መንግሥቱ በዘውጋዊ መሠረታዊ መርሖች እንዲገለጽ ያለ የፍላጎት መጠን ነው፡፡)

Racism ~
any action, practice, or belief that reflects the racial worldview—the ideology that humans are divided into separate and exclusive biological entities called "races," that there is a causal link between inherited physical traits and traits of personality, intellect, morality, and other cultural behavioral features, and that some races are innately superior to others. (ዘረኝነት ~ ሰዎች የተለያዩ እና ግንኙነት የሌላቸው “ዝርያ” የምንላቸው፣ በዘር ሐረግ በሚወረሱ አካላዊ፣ ሰብኣዊ፣ ንቃተ ሕሊናዊ፣ ሞራላዊ እና ሌሎችም ባሕላዊ መገለጫዎች የሚለዩ እና አንዳንድ ዘሮች ከሌሎች የበለጡ ናቸው በሚል ርዕዮተዓለም ላይ የተመሠረተ ተግባር ወይም እምነትን የሚያንፀባርቅ ዓለማዊ በዘር ላይ የተመሠረተ ምልከታ ነው፡፡)


‹ብሔርተኝነት› እና ‹ዘረኝነት› የሚሉት ሁለቱ ትርጉሞች ስንመለከት፤ ‹ብሔርተኝነት› በአብዛኛው በፖለቲካ ፍላጎት የሚደነገግ ሲሆን፣ ዘረኝነት ተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሆኖም፣ በኢትዮጵያችን የፖለቲካ ንግግር ውስጥ በዘውግ (ethnicity) ላይ የተመሠረተውን ማንነት ‹ዘር› እያሉ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ የብሪታኒካ ኢንሳይክሎፔድያ በዘር እና ዘውግ መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚከተለው ነው የሚያስረዳው፦

“የዘውግ ማንነት እና መገለጫዎች በ[ማኅበራዊ] ትምህርት የሚገኝ ነገር ነው፡፡ ዘር ግን በደም የሚወረስ እና መለወጥ የማይቻል ነገር ነው ተብሎ የሚታመን ነው፡፡ የዘውግ ማንነት ጊዜያዊ እና ሥር የሰደደ ላይሆን ይችላል፡፡ ዘር ግን በተፈጥሯዊ እውነታዎች ላይ የተመሠረተ እና የማይቀየር እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡”

ይህ የዘውግ እና የዘር ልዩነት ነው የ‘ethnocentrism’ (ዘውገኝነት)ን ትክክለኛ ትርጉም እንድናገኝ የሚረዳን፡፡ በዚሁ መሠረት፣ ዘውገኝነት ማለት የአንድ ዘውግ ሕዝብ ባሕል ከሌላው ይበልጣል ብሎ ማሰብ ማለት ነው፤ ይህም ዘውገኝነት እንደዘውጋዊው ማንነት ጊዜያዊና ሥር ያልሰደደ ነው፡፡

ስለዚህ የሦስቱ ማለትም ብሔርተኝነት (Nationalism)፣ ዘውገኝነት (Ethnocentrism) እና ዘረኝነት (Racism) ልዩነት - የመጀመሪያው ፖለቲካዊ፣ ሁለተኛው ባሕላዊ፣ ሦስተኛው ተፈጥሯዊ የማንነት ብያኔዎች ላይ መሠረት በመጣላቸው የሚገኝ ነው፡፡ (ይህ እንግዲህ ብሔራዊ ማንነትን ብቻ ሳይሆን በ‹ዘር› ላይ የተመሠረተውን ማንነት በራሱ “የለም” የሚል አቋም የሚያራምዱትን ምሁራን ሐሳባዊ ክርክር ሳናነሳ ከቀረን ነው፡፡)

በኢትዮጵያ ‹ዘረኝነት› የሚለው ቃል በዘውግ ላይ የተመሠረተ ማበላለጥን ለመጥቀስ አገልግሎት ነው የሚውለው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ብዙዎችን የሚያስማማው የዘር ትርጉም ተፈጥሮ ላይ የተንጠለጠለ ነው፤ የሚመሠረተውም “የቆዳ ቀለም፣ የፊት ቅርፅ እና የፀጉር ዓይነት ልዩነትን” በማስቀመጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ፣ ለምሳሌ በፖለቲካ ተቀናቃኝነታቸው የምናውቃቸውና ብዛታቸውን ብንደምራቸው ከ80 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብን የሚወክሉትን ሦስቱን - የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የትግራይ ክልል ሕዝቦች በሕግ ድንጋጌ ‹ብሔር› ተብለው ቢጠሩም በፖለቲካ ተዋስኦ ውስጥ እንደ‹ዘር› የሚቆጥሯቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሕዝቦች የቆዳ ቀለማቸውን፣ የፊት ቅርፅ እና የፀጉራቸውን ዓይነት አይቶ መለየት አይቻልም፡፡

ስለዚህ በተለይ በአማርኛ ‹ዘረኝነት› የምንለው እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በዘውገኛ ልኂቃን መካከል የሚነሳ ሽኩቻ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ትክክለኛ አገላለጽ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያው የማንነት ሽኩቻ ከዘረኝነት ይጠብባል፤ ዘውገኝነት ነው፡፡ ብሔርተኝነት ደግሞ የፖለቲካ ኅብረት ለመፍጠር ሲባል በግለሰቦች እና በግለሰቦች ስብስብ የሚገባ ቃል ኪዳን ነው ልንል እንችላለን፡፡ በዚህም ረገድ፣ በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ጥቂት ብሔርተኝነት እና ብዙ ዘውገኝነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሁን በተዋስኦዋችን ውስጥ የምንመለከተው ኢትዮጵያዊነትንም፣ ዘውጋዊነትንም ‹ብሔርተኝነት› እያሉ የመጥራት ድንግርግር የሚወለደው የፖለቲካዊ ቁርጠኝነታችን ለየትኛው ቡድን ነው የሚለውን ካለመመርመር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment