Pages

Monday, July 25, 2016

“ጨዋ” ነዎት “ባለጌ”?



በፍቃዱ ኃይሉ*

ሐምሌ 27/2007 ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ቀናኢ-ፍትሕ ለሆኑ ሰዎች በሙሉ የመርዶ ቀን ነበር፡፡ ስለ ሠላማዊነታቸው የተመለከታቸው በሙሉ የፈረደላቸው፣ ባንድ ወቅት መንግሥትም በወኪሉ በኩል ሲደራደራቸው የነበሩ፣ ለሦስት ዓመታት ያክል በሕግ የበላይነት አምነው ችሎት ፊት የሠላማዊነታቸውን ማስረጃ ሲደረድሩ የቆዩት (በተለምዶ በሚጠሩበት ሥማቸው) የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊኮሚቴዎችእስከ 22 ዓመት የሚድረስ የፅኑ እስራት ፍርድ ተጣለባቸው፡፡ ይህንን ዜና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) 730 የቀን ዜና እወጃው ጀምሮ ሲለፍፈው ነበር፡፡ ከዜናው ጋር በማነፃፀሪያነት የቀረበው ሌላ ዜና ግን ግቡን ስላልመታ ይመስላል ማታ አልተደገመም፡፡ ያልተደገመው ዜና በተመሳሳይ አንቀፅ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስለተፈረደባቸው ሰዎች ነው፡፡ እነዚህኞቹ መሣሪያ ታጥቀው የተወሰኑ ሰዎችን ገድለዋል፡፡ ሆኖም እንደ ኢ.ብ.ኮ. ዘገባየቅጣት ማቅለያ በማስገባታቸው” 14 ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ዜናዎቹን ያዳመጡ ሰዎች ግን ማነፃፀር የቻሉት የሠላማዊነት ቅጣት መክበዱን ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “Military and militarism in Africa: the case of Ethiopia” ባሰኙት ጥናታቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡-

“በመካከለኛውዘመን እንዳየነው [ጨዋ] ማለት መሣሪያ ታጣቂ ማለት ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ትርጉሙ ተለውጦ መልካም ፀባይ ያለው ማለት ሆነ፡፡ በተመሳሳይ፣ የቃሉ ተቃራኒ የሆነውባለጌየሚለው ቃልም የሚወክለው ጭሰኛውን (ማለትም መሣሪያ የማይታጠቀውን) ነበር፡፡ አሁን የዚህም ቃል ትርጉም ተለውጦ መጥፎ ፀባይ ያለው ማለት ሆኗል፡፡” (እራሴው እንደተረጎምኩት)

እንግዲህ ኢሕአዴግም የሚያስበው በቀደመው ዘመን ጨዋእናባለጌትርጉም ነው ማለት ነው፤ ለእርሱ መሣሪያ ከታጠቀ ይልቅ ሠላማዊ ይባልግበታል፡፡ (‹ይባልግበታልበአሁኑ ትርጉም!) ስለዚህ አቀጣጡም በዚያው መሠረት መሆኑን መግቢያ አንቀፁ ያመለክታል፡፡

የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ገዢዎች (‹አመራሮችአላልኩም፤ አይመጥናቸውም) የመንግሥትን ሥልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን (ለሁለት ዐሥርት ዓመታት) ሠላማዊ ትግሎችን በፅኑ ተቃውመዋል፡፡ እንዲያውምየሚችለን ካለ በትጥቅ ትግል ይሞክረንየሚል መፈክር በተደጋጋሚ አስደምጠዋል፡፡ ዓላማቸው ግልጽ ነው፡፡ ያዋጣናል፣ እናሸንፍበታለን የሚሉትን የትግል ሜዳ እየመረጡ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችስ? ገዢው በመረጠላቸው ሜዳ (battlefield) ቢገጠሙት ይሻላል ወይስ ሠላማዊነትን የሙጥኝ ቢሉ? የትኛው ያዋጣል? የትኛው ይቀላል? ከሕወሓት ምን መማር ይቻላል? አምባገነኖች እንዴት ሥልጣን ላይ ይሰነብታሉ?

ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመፈለጌ በፊት ነገሩ ሁሉ ለለውጥ ነው እና በዚህ ጽሑፍ ውስጥለውጥየሚባለውን ነገር ልበይን፡፡ለውጥማለት በዚህ አገባቡወደ ሕዝባዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚደረገው ሽግግርነው፡፡


አመፃዊ የትግል ስልት ያዋጣል?

ሠላማዊ ያልሆነ ትግል በሙሉ የትጥቅ ትግል አይደለም፡፡ አመፃዊ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ከትጥቅ ትግል ወዲያ ሠላማዊ የማይባሉ ስልቶችንም እንዲያካትትልኝ ስለፈለግኩ ነው፡፡ በዚህ መስፈርት አመፃዊ ትግል በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከአገሪቱ ታሪካዊ ሁነትም፣ ከዓለምቀፍ ተሞክሮዎችም በመነሳት ያዋጣል ወይ የሚልውን እንጠይቃለን፡፡ ለዚህ ጥያቄ በዚህ ጽሑፍ ሰጥቼ የማልፈው ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የሚመጡልኝን መልሶች ነው፡፡

1ኛ - የዴሞክራሲ መንገድነት

ዴሞክራሲ በየትኛውም መመዘኛ መንገድ እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ ይህም ማለት አንድ አገር የሆነ የጊዜ ነጥብ ላይዴሞክራሲያዊ ሆነ፤ በቃ አበቃ! › የሚባልበት ፈሊጥ የለም፡፡ ዴሞክራሲያዊነት ማለት ሁሉንም ሕዝባዊ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ (በብዙኃን አመራርና ሕዳጣን መብት ጥበቃ፣ በሕግ የበላይነት፣ በወቅታዊ እና ነጻ ምርጫ…) መፍታት መቻል ነው፡፡ ይህ የማይቆም፣ መድረሻ የሌለው ጉዞ ነው፡፡ የአመፃ ትግል ዴሞክራሲን ማምጣት አልሞ ሲደረግ ከመነሻው ዴሞክራሲን እንደመድረሻ ስለሚቆጥረው ስህተት ይሆናል፡፡ በአካሄድም ቢሆን አመፃዊ ዴሞክራሲያዊነት ስለማይኖር ምናልባት ነባሪውን ፍፁማዊ አምባገነን በለዘብተኛ አምባገነን (Benevolent dictatorship) መተካት ካልቻለ በቀር አመፃ ለዴሞክራሲ መንገዱን እንደሚከፍት ዋስትና አይሰጥም፡፡

2- “ውሻ ወደትፋቱ ይመለሳል

ምንም እንኳንነጻ አውጪዎች” በብረት ነጻነትን፣ በእኛ ጉዳይ ዴሞክራሲን እናመጣለን ብለው ቢሸፍቱም - የሚያውቁትም፣ የሚለምዱትም የብረት (አፈሙዝ) ሕግን ነውና - በዓለም እንደታየው መጀመሪያ ላይ ዴሞክራሲያዊነትን ለማስመሰል ቢሞክሩም ቆይተው ግን በብረት ሥልጣናቸውን ማቆማቸው የተለመደ እውነት ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስነው የባሕሩ ዘውዴ ጥናት እንዲህ ይላል፦

“…ሥልጣን የራሱ የሆነ የማይሻር አመክንዮ አለው፤ ለአብዮታዊ ዲስኩር አያጎበድድም፡፡ ስለዚህ በሕዝባዊ ድጋፍ ተመርኩዞ በአፍሪካ ግዙፍ ከሆኑት ወታደራዊ ሠራዊቶች አንዱን የደመሰሰው ኢሕአዴግ የራሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ መልሶ ወታደራዊ ኃይል ላይ መንጠላጠሉ የሚያስገርም አይደለም፡፡…”

በዚህ ረገድም ስናስበው አመፃዊ ትግል እኛለውጥየምንለውን እንደሚያመጣልን ዋስትና መስጠት አይቻልም፡፡

3- “እኛእናእነርሱእንሆናለን

አመፃዊ ትግል (በተለይ የትጥቅ ትግል) አንድን ሕዝብ ቢያንስ ለሁለት ይከፍለዋል፡፡ (እንደ ሶሪያ ዓይነቶቹ ከዚያም በላይ ከፋፍለውት አሳይተውናል፡፡) ስለዚህ በትግሉ ወቅት የወገን እና የጠላት እየተባሉ የሚፈረጁ የአንድ ሕዝብ ሁለት ክፍሎች፣ ከትግሉ በኋላም በዚያው ዓይን መተያየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው አሁንም በገዢዎቹ የሕወሓት ልኂቃንና ደጋፊዎቹ መካከልና በሌሎች ኢትዮጵውያን መካከል ያለው ልዩነት (ያውም 25 ዓመት በኋላ) የሁለትዮሽ ነው፡፡ ቂም የያዘ እና ያስያዘ ሁለት ወገን ካለ፣ ቂመኛው መልሶ ስለሚሸፍት እንደመጀመሪያው ሁሉንጉሥ ያለ ለውጥእንደጉልቻ እያቀያየረ ይሔዳል፡፡ ዴሞክራሲ መሠረታዊ ሕዝባዊ ስምምነት (consensus) ስለሚጠይቅ አመፃዊ ትግል ዴሞክራሲን እንደማያስገኝ ይህም አንድ ማሳያ ነው፡፡

4- ለፍቶ መና

ሕወሓት የዱር ትግሉን ጨርሶ ቤተ መንግሥት ሲገባ ከገጠሙት ፈተናዎች አንዱታጋዮቹን ምን ላድርጋቸው?” የሚለው ነው፡፡ 17 ዓመት ሙሉ በዱር በገደሉ ሲዋደቁ ከርመው የሥልጣን በትሩን ሲጨብጡ፣ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎችን በሙያ ብቃት ብቻ ለመሾም (አላሰቡም እንጂ) ቢያስቡም ለትግሉ ስኬት የመማርና የሙያ ልምድ የማካበት ዕድላቸውን ያባከኑትን ሰዎችአፍንጫችሁን ላሱሊሏቸው አይችሉም፡፡ ምንም እንኳን ታጋዮቹ የሚታገሉት ለዓላማ (cause) ነው ቢባልም፣ ድል ሲቀናቸው የዓላማው ፍሬ የመጀመሪያው ተቋዳሽ ለመሆን ከመጓጓት አይተርፉም፡፡ ሰው ናቸውና፡፡ ስለሆነም በወታደራዊ አስተዳደር (ማለትምማዕከላዊነት እና ከላይ ወደታች የትዕዛዝ መሥመር በሚሠራ የአስተዳደር ዘዬ) የሠለጠኑ ሰዎች ከወረዳ እሰከ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሲገቡ ዴሞክራሲን (ከታች ወደላይ የሚወሰንበትን አሠራር) ያመጣሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ያውም ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የኃላፊነት ቦታዎችን እንዲይዙ ለምርጫ ቢቀርቡ በዕውቀትና ልምድ ማነስ ስለማይመረጡ ከታገሉለት ስርዓት ጋር ቅራኔ ውስጥ በመግባት እንደማያጨናግፉት ምንም ዋስትና የለም፡፡ ይህም አመፃዊ ትግልን ለዴሞክራሲ እንዳይመች ያደርገዋል፡፡

5- ዴሞክራሲን ይኖሩለታል እንጂ አይሞቱለትም!

ሕውሓቶች 17 ዓመት ሲታገሉ፣ 60 ነፍስ መስዋዕት ሲያደርጉና ከዚያ በላይ ሲገድሉ፣ ተስፋ ያደርጉ የነበሩት እንደ ሃይማኖት ያመልኩት የነበረውን ማርክሳዊ-ሌኒናዊ ርዕዮተ ዓለም ነበር፡፡ ትግሉ ድል ሲቀናው ግን የታገሉለት ርዕዮተዓለምአለፈበት፡፡ በዓለም እንደ መንግሥት ፀንቶ ለመኖርነጭ ካፒታሊዝም መቀበል ነበረባቸው፡፡ እንደ ገብሩ አሥራት ንግግርአልባንያ፣ አልባንያ እየተባለች እንደ ሞዴል የተጠራችው አገር ትግሉ ሳይጠናቀቅ ብትንትኗ ወጣ፡፡ ሕወሓትም የሞተለትን እና የገደለለትን ስርዓት ንቆየዘመኑንያዘ፡፡ እንግዲህ የአመፃ ትግልን ከሚያስፈሩ ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ ምናልባት ለሚለወጥ ርዕዮተ ዓለም መልሶ የማይገኝ የሰው ልጅ ነፍስ መስዋዕት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ለሰዎች አንፃራዊ ሠላም እና ደኅንነት ሲባል መሞት ያውም በገፍ - ምክንያታዊ አይደለም፡፡

በለውጥትግል ዓለሞች ሁሌም (እንደየተመልካቹ) ጠርዘኛ (radical) እና መሐከለኛ (moderate) አቋሞችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ፡፡ አመፃዊውንም ሆነ ሠላማዊውን ትግል የሚመርጡትን ሰዎች እንደ ጠርዘኛ የሚቆጥሯቸው አሉ፡፡ ራሳቸውን አማካይ ብለው ይጠራሉ፡፡ የሚሰጡትም ምክንያት ሠላማዊውም ሆነ አመፃዊው ትግል ለየብቻ መቆም አይችልም የሚል ነው፡፡ በኃይል ሥልጣኑን የያዙ ሰዎች ከሠላማዊዎች ጋር መደራደር እና ለለውጥ ፈቃደኞች የሚሆኑት አማፂዎቹን በመፍራት ነው ይላሉ፡፡ ይህንን እንስማማበት ቢባል የአማፂዎችን ሚና ወስዶ የሚጫወተው ማን ነው? በግሌ እኔ የምኖርለት እንጂ የምሞትለት ግብ የለኝም፡፡ አመፃዊ ትግል ደግሞ ለመግደልም ብቻ ሳይሆን ለመሞትም መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ በበኩሌ እኔ የማልገባበትን የትግል መሥመር ሌሎች እንዲገቡበት የምመክርበትም ሞራል የለኝም፡፡ እንዲያውም እስከ መሞት በሚደርስ ወኔ የሚታገሉ ሰዎች ካሉ ለሠላማዊ ሜዳ ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይችለላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡

በሠላማዊ እና በአመፃዊ ትግሎች መካከል ያለው ልዩነት የሕይወትና የሞት ያክል ነው፡፡ በሠላማዊ ትግል ትልቁ ፈተና እስር ነው፡፡ አልፎ፣ አልፎ ሞት የሚከሰትባቸው ሠላማዊ ትግሎች ቢኖሩም የአመፃዊ ትግሎችን ያክል እልቂት የሚያስከትሉ አይደሉም፡፡ ጌታቸው ማሩደርግን ለአመፃ ትግል መጋበዙ ይብስ አረመኔ ያደርገዋልየሚል ስጋት እንደነበረው ሕይወት ተፈራ “Tower in the sky” ላይ ገልፃዋለች፡፡ ስጋቱ አልቀረም፤ ለኢሕአፓ የ‹ነጭ ሽብር› ምላሽ ደርግ በ‹ቀይ ሽብር› አገሩን በደም አጠበው፡፡ ትግሉ በሁለት ገዳዮች መካከል ስለነበር ኃያሉ ገዳይ አሸንፎ ወጣ፡፡ በድኅረ ምርጫ 97 የቅንጅት መሪዎች (በተለይ እነ ልደቱ) ስለ ጆርጂያና ዩክሬን የቀለም አብዮት የቀሰቀሱትን ሕዝብ እንዴት ሠላማዊ መሆን እንዳለበት ስላልነገሩት፣ በድንጋይ ውርወራ እና ጎማ በማቃጠል ብሶቱን ገለጸ፤ አጋጣሚው ግን ለኢሕአዴግ ሕዝባዊ ብሶቱን ለማፈን ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም እንዳይደገም ዕድሉን እንዲዘጋ መንገድ ጠረገለት፡፡ አሁንም የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴች አሉ፡፡ በተለይ በኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባት ሥም የተጨፈለቁ ሠላማዊ ታጋዮችን ቁጥር ወኅኒ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንግዲህ መደራደሪያ ይሆናል የተባለው የአመፃ ትግልም ሠላማዊውን ለማደናቀፊያ እያዋለ ነው ማለት ነው፡፡

አመፃዊው ትግል ውስጥ (በተለይ በትጥቅ ትግሉ) ሌላም ፈታኝ ጉዳይ አለ፡፡ ሕዋሓት ለድል የበቃውየሻቢያ የትሮይ ፈረስ ሆኖ ነውየሚሉ አሉ፡፡ ሕወሓት ጫካ እያለ የማይደራደርባቸው ከነበሩ አቋሞቹ ውስጥየኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ነው፤ እና የሚፈታው በነፃነት [መገንጠል] ነውየሚለው አንዱ ነበር፡፡ ሻቢያ ያን ሕልሙን በሕወሓት አሳክቷል፤ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ አማፂዎች ወዳጅ ሆኗል፡፡ ሻቢያን እንደ ኢትዮጵያ ወዳጅ መቁጠር የሚቻልበት መሥፈርት አይታየኝም፡፡ አዲሶቹ አማፂዎችም እንደ ሕወሓት የሻቢያ የሌላ አጀንዳ የትሮይ ፈረስ እንዳይሆኑ እሰጋለሁ፡፡


ሠላማዊ ትግል ስንል?

 

ሠላማዊ ትግል ደርዘ ብዙ ትንቅንቅ ነው፡፡ አንዳንዶች ‹ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ መጠቀም ነው› ብለው ያምናሉ፤ ነገር ግን በዚህ የማይወሰንበት ጊዜ አለ፡፡ ሠላማዊ ትግል ከነፍስ ማጥፋት፣ አካላዊ ጉዳት ከማድረስ እና ንብረት ከማውደም መቆጠብን ብቻ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ‹ሠላማዊ› የተባለው፡፡ ለምሳሌ ሕዝባዊ እምቢተኝነት (Civil disobedience) አንድ የሠላማዊ ትግል ዘርፍ ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ትንሹ) “ኢ- ፍትሐዊ ሕጎች፤ ሕጎች አይደሉም” ይል ነበር፡፡ በዚህ ፍልስፍና ነው ለሕግ አለመታዘዝ የሚወለደው፡፡ ለምሳሌ በአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ ያሉትን አግላይ ሕጎች በሠላማዊ ትግል ለመቃወም የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ከነደፋቸው ስልቶች አንዱ ለአግላይ ሕጎች የማይታዘዙ (እና በዚያ ሳቢያ ለመታሰር ፈቃደኞች የሆኑ /እስር እንደትግል/ የሚቆጥሩ) ሰዎችን መልምሎ ማሰማራት ይገኝበታል፡፡ ተግባሩ ሠላማዊ ነው፤ ግን ሕጋዊ አይደለም፡፡ ሕጉ ኢ-ፍትሐዊ ነውና፡፡

በኢትዮጵያ፣ በአብዛኛው የሚስተዋሉ ከኢ-ፍትሓዊ ሕጎች ይልቅ የሕግ የበላይነት ማጣት ነው፡፡ የማበላለጥ ጉዳይ ሆኖ እንጂ ኢ-ፍትሓዊ ሕጎች የሉም ማለትም አይደለም፡፡ ሕዝብን ለማደንቆር (እንዳይነቃ) የወጣው የመያድ ሕግ እና ሁሉን ነገር ሽብር ያሰኘው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግጋት በዚህ ረገድ ሳይጠቀሱ አይታለፉም፡፡ 

ሆኖም የሕግ የበላይነትን ባለማክበር የሚፈፀሙ ጥፋቶች ይህንን አምባገነን ስርዓት የበለጠ ይገልጹታል፡፡ ለምሳሌ መደራጀት ይፈቀዳል (በሕግ)፣ በተግባር ግን ይደናቀፋል፡፡ ይህንን በሠላማዊ መንገድ መታገል የሚቻለው ከስርዓቱ ጆሮ ጠቢዎች በላይ የሆነ (ነገር ግን በሕግ ያልታወቀ) ሠላማዊ ድርጅት በመፍጠር ነው፡፡ የፕሬስ ነጻነት በሕግ ተፈቅዷል፤ በተግባር ግን አይቻልም፡፡ ከቴክኒካዊ ማደናቀፊያ እስከ ጋዜጠኛ ማሰር በሚደርሱ ሕገወጥ ተግባሮች ነው ይህ የሚሆነው፡፡ ዘመኑ ይህን ለማሸነፍ ምቹ ነው፡፡ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከአፈናውም ከእስሩም በላይ የሆነ (በእነዚህ እርምጃዎች የማይደናቀፍ) የመረጃ ማቅረብ ወይም ሕዝባዊ ንቃት የመፍጠር ሥራ መሥራት ድርጅታዊ መረብ መፍጠር ይቻላል፡፡ የአገራችን የሠላማዊ ትግል ፈቀቅ አለማለት አማራጭ መንገድ ከማጣት ይልቅ ያለመፈለግ የፈጠረው ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ “ሠላማዊ ትግል አልፈልግም” እያለ ቢሆንም እየሔዱ ፊት ለፊት መላተም ብቻ (አስፈላጊ ቢሆንም) በቂ አይደለም፡፡ አስፈላጊነቱ የስርዓቱን ሕገ-ወጥነት ለማሳየት ሲሆን በቂ የማይሆነው በዚህ የኢሕአዴግ ባሕሪ ፊት ለፊት መላተም ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ነው፡፡ ፊት ለፊት መላተም ሲበዛ፣ መጠቃት ስለሚበዛ ሰዎች ትግሉን ከመቀላቀል ይልቅ በፍርሓት እንዲርቁት ያደርጋል፡፡ ይህን ችግር፣ በትጥቅ ትግል ቋንቋም ቢሆን ሲያስረዱ አቶ ገብሩ አሥራት (‹ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ› ላይ) እንዲህ ብለዋል፦

“አንድ አባት ገበሬ ‹ልጆቼ እንታረዳለን፣ መሬት ቀውጢ ትሆናለች እያላችሁ አትቀስቅሱ፡፡ የዚህ ዓይነት ቅስቀሳ ሰው ወኔው እንዲሞት፣ ተስፋ እንዲቆርጥና አንገቱን እንዲደፋ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እናቸንፋለን፣ ተቃርበናል፣ አይዟችሁ፣ በርቱ፣ ብላችሁ ብትቀሰቅሱ ይሻላል› ብለው መክረውን ነበር፡፡”

ቢያንስ በእኔ እምነት፣ ያውም ለቆረጠ እና ዓላማውን በቅጡ ለሚያውቅ ሰው ሠላማዊ ትግል ከአመፃዊ ይልቃል፡፡ እርግጥ የፍትሕ እጦት ትውልድ እየበላ የምንታገስበት አንጀት አይኖረን ይሆናል፡፡ ሆኖም አመፃዊ ትግል ፍትሕ የምናገኝበትን መንገድ ማሳጠር አይችልም፡፡ የካርል ማርክስ “There is no short cut to history” (‹ለታሪክ አቋራጭ መንገድ የለውም› ብሒል) እዚህ ይሠራል፡፡ ሚስተር ኪንግ በሠላማዊ ትግል ጎዳና ሦስት ደረጃዎች አሉ ይላል፡፡ መንቃት (Awareness)፣ መደራጀት (Organize) እና መተግበር (Action) በቅደም ተከተል የሚመጡ የሠላማዊ ትግል ሒደቶች መሆናቸውን ይናገራል፡፡ አሁን ችግር የሆነብን ተግባሩ እየቀደመ ነው፡፡ ጥቂት የነቁ እና የተደራጁ (ሁለቱንም ያሟሉ) አደባባይ ሲወጡ ወይም በሆነ የትግል ተግባር ሲጠመዱ ገዢው በቀላሉ ይጨፈልቃቸዋል፡፡ ለተመልካችም ሕዳጣን ያስመስላቸዋል፡፡ በሠላማዊ ትግል ሕዝብ ኃይል የጨበጠውን ገዢ የሚያሸንፈው በብዛት ነው፡፡ ብዙዎችን በኃይል መጨፍለቅ አይቻልም፡፡ እንግዲህ ስለመደራጀት ቀደም ሲል ለመጥቀስ ሞክሬያለሁ፤ አስፍቶ ማሰብ የእያንዳንዳችን ቀጣይ ድርሻ ይሆናል፡፡

መንቃት ለምንና ለማን?

‹ለውጥ› የሚፈልጉ ለውጥ አማጪዎች (Activists) ሕልማቸውን ብቻቸውን ይዘውት ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ ለሌሎች ማጋራት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ነው ተከታይ ማፍራትም ሆነ፣ ያፈሩት ተከታይ ሕልማቸውን ማስቀጠል የሚቻላቸው፡፡ ሕልማቸው ከራሳቸው አልፎ ሌሎች ላይ መጋባት ከቻለ ነው ከራስ-ሥዩምነት ወደ ሕዝበ-ሥዩምነት መሸጋገር የሚችሉት፡፡ ብዙኃን የሚመሩት/የሚሳተፉበት ትግል የመክሸፍ ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡ የ1953ቱን ስዒረ መንግሥት እንደምሳሌ እናስታውሰው፡፡ በወቅቱ የንጉሡ ደጋፊዎች እና የስዒረ መንግሥቱ ደጋፊዎች ያደረጉትን ውጊያ ጣልያናዊው አንጄሎ ዴል ቦካ (la negus ባሰኙት መጽሐፋቸው ላይ) እንዲህ ተርከውታል፦

“ለሰዐታት የዘለቀ ውጊያ መንገዱ ላይ ተካሒዶ ነበር፤ ሕዝቡ ግን በወታደሮቹ መካከል የነበረውን ጦርነት ያለውገና (indifference) ይመለከተው ነበር፡፡” (እንግሊዘኛው ትርጉም ገጽ 260)

በዚህ ታሪክ የምናስታውሰው ብዙኃኑ ለአመፃ የሚኖረውን ምላሽ ብቻ ሳይሆን ውጊያው ለምን እየተካሔደ እንደሆነ እንኳን ግንዛቤ እንዳልነበረው ነው፡፡ ደራሲው ሲቀጥል፦

“…ግርማሜ ንዋይና ወርቅነህ ገበየሁ [የወቅቱ የደኅንነት ሹም]፣ ሁለቱም በአሮጌው መንግሥት መውደቅ ብዙ ነገር ማግኘት እንደሚችል በቂ ግንዛቤ አለው ብለው የአዲስ አበባን ሕዝብ በመገመታቸው የምር ስህተት ፈፅመዋል፡፡”

ይሁን እንጂ የንጉሡ መንግሥት ከዚያ በኋላ የቆየው 13 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ያ በኢትዮጵያ ታሪክ በአግባቡ የተደራጀ እና ዘመናዊ ሠራዊት እና የደኅንነት ተቋም የመሠረተው የመጀመሪያው መንግሥት የወደቀው ያለመሣሪያ ጩኸት ነው፡፡ በሕዝቡ መንቃት እና በሐሳብ መበለጥ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ‹ሕዝቡ/ተማሪዎች “መሬት ላራሹ” ሲሉ በወቅቱ መሬት የባላባቶች በመሆኑ መንግሥት በሐሳብ ተበለጠ… ወደቀ› ይላል፡፡ አንጄሎ ዴል ቦካ ለዚህ ለውጥ የስዒረ መንግሥቱ ሙከራ አስተዋፅዖ እንደነበረው አልሸሸገም፡፡ ከሙከራው በኋላ ሕዝቡ ነቃ ይላል፦

“[ከዚያ በፊት የነበሩት] ሌሎች አማፂዎች፣ እነባልቻ፣ ጉግሳ ወሌ፣ እና ኃይሉ ተ/ሃይማኖት በማዕከላዊው ኃይል ላይ ያመፁት በጥላቻ፣ በቀል ወይም ምኞት ብቻ ተነድተው ነበር፡፡ ለአገሪቱ ያቀረቡት አማራጭ ራዕይ አልነበራቸውም፡፡” (ገጽ 264)

የስዒረ መንግሥቱ ሞካሪዎች ግን ነበራቸው፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ያንን ራዕይ ከአፈሙዝ ፉክክሩ ነጥለው መመልከት ችለዋል፡፡ በወቅቱ አመፁን የደገፉ 200 ተማሪዎች ሰልፍ ወጡ እና ከትምህርታቸው ታገዱ፡፡ ቆይተው ግን ይቅርታ ጠየቁና ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመለሱ፡፡

እኔ (የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ) የቅድመ እና ድኅረ ምርጫ 97ን ጉዳይ እንደዚህኛው ስዒረ መንግሥት ሙከራ ነው የምመለከተው፡፡ ያኔ ተማሪዎቹ ይቅርታ ጠይቀው ትምህርት ቤት ሲመለሱ የተከሰተው ዝምታ የተቀረፈው የአብዮቱ ሰሞን ነው፡፡ ዝምታቸው የተገፈፈው ሕዝባዊ ንቃቱን ተከትሎ ነው፡፡ ሕዝብ የነቃ’ለታ ምንም እንኳን ወታደራዊው ጁንታ (ደርግ) ቢነጥቃቸውም ለውጥ መጥቶ ነበር፡፡ አሁንም ሕዝብ መንቃት ያለበትን ያህል ሲነቃ ለውጥ ይመጣል፡፡ እኛ ዘብ ሆነን መጠበቅ የሚኖርብን የደርግ ዓይነቱ የለውጥ ሌባ እንዳይዘርፈን ነው፡፡


እስከዚያው ከሕወሓት መማር

የሚቀናቀኑትን አካል በቅጡ መረዳት ግማሹን መንገድ መምጣት ነው፡፡ የሕወሓትን ታሪክ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና ወዘተርፈ መለየት ለሠላማዊ ትግላችን ሰፊ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡


ትምህርት አንድ፤ ዛፉ እንዳይጎብጥ፥ ችግኙን ማረቅ

ሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት በአውራ ፓርቲ ሥም፣ አሀዳዊ ፓርቲ ስርዓት እየዘረጋ ነው፡፡ መላ አገሪቱ ከቀበሌ እስከ ፓርላማ በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ የተቃኙ፣ የአንድ ፓርቲ ሰዎች እንዲሞሉት አድርጓል፡፡ ይህ አመል ኢሕአዴግ የመንግሥት ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ የመጣ ይመስላል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ሕወሓት ከቀድሞ ወዳጁ ሻዕቢያ የተማረው “በአንድ ሜዳ ሁለት ኃይል አይኖርም” የሚል አባባል አለው፡፡ በዚህ ፍልስፍና ሻዕቢያ ጀብሃን አጠፋ፡፡ ሕወሓት ደግሞ ግገሓት(?)፣ ኢዴኃ (EDU)፣ ኢሕአሠን በኃይል ደምስሷል፡፡ ሕዋሓት ደርግን ከመደምሰሱ በፊት አምባገነኑን ደርግን እንወጋለን ብለው ግን ደግሞ ከሱ በጥቂቱ የተለየ የፖለቲካ ፍልስፍና ይዘው ከጎኑ የተሰለፉ ኃይሎችን አጥፍቷቸዋል፡፡ ይህ የጫካ አመሉ ያደገበት ሕወሓት (ኢሕአዴግን ለብሶ) ከተማ ሲገባ የቱንም ያክል “ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው አማራጭ ነው” እያለ ቢፎክርም፣ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን መታገስ አልቻለም፡፡

ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወገኖችን ቀርቶ በውስጡ የሚከሰቱ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን እንኳን መታገስ አይችልም፡፡ ትግል ላይ በነበሩት ጊዜ የተነሳው የመጀመሪያው ‹ሕንፍሽፍሽ› (ቀውስ) ‹የአሽዓ (አክሱም፣ ሽረ እና አደዋ) ሰዎች የሥልጣን የበላይነት (ልክ አሁን የትግራይ ልሒቃን የሥልጣን የበላይነት በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ በዛ እንደምንለው) ፓርቲያችን ላይ እየታየ ነው› የሚል አቤቱታ ያቀረቡ አባላቱን በማስወገድ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በ1993 በተፈጠረው ቀውስ ደግሞ የሉአላዊነት ጥያቄ ያነገቡ አባላቱን የውስጥ ሕገ-ደንቡን (ሕወሓትን በማዳን ስም) ሽሮ፣ ምርጫ ቦርድ ባለበት አገር በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ማሕተም የተፃፈ ደብዳቤ ነበር ያሰናበታቸው፡፡ ይህ ባሕል ከጫካ ተከትሏቸው የመጣ ባሕል ነው፡፡ የውብማር አስፋው ‹ፊኒክሷ ሞታም ትነሳለች› ባለችው መጽሐፏ እንዲህ ትለናለች፦

ሕወሓት ደንብ መሠረት አንጃ መፍጠር እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ያስከትል ስለነበር፣ የሕወሓት ፖሊት ቢሮ ይህንን ሲያስቀምጥ በማኅበሩ አመራር ውስጥ የማይፈልጋቸውና የሚጠላቸው የአመራር አባላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመለክት ነበር፡፡…” (ገጽ 112፣ ጋዜጠኛ ዮናስ በላይ እንዳጣቀሰው)

እነዚህ ችግሮች ሥር ሰደው ነው የአሁኑን አማራጭ ሐሳብ የማይቋቋም ኢሕአዴግ የፈጠሩት፡፡ ይህንን የ1993ቱ የሕወሓት ቀውስ ወቅት ከፓርቲው ከወጡት ታጋዮች መካከል አረጋሽ አዳነ ለጥሕሎ መጽሔት በሰጠችው ቃለምልልስ ከሥር ከሥሩ ባለመታረሙ የመጣ ጣጣ ነው በማለት ከታሪክ እንድንማር ትመክረናለች፦

“እነዚህ ሁሉ [ጥያቄዎችን በኃይል የመጨፍለቅ] ችግሮች ገና ድሮ ከመፈጠራቸው፣ [ሥ]ር ከመስደዳቸው በፊት ቀደም ብለን ለዚህ ሁሉ መሠረት የሆኑትን ችግሮች […] አስተውለን ከሥር ከሥር ወይም ደረጃ በደረጃ እየታገልናቸው ያለመምጣታችን አሉታዊ ፍፃሜ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡” (ገጽ 77፣ ዮናስ በላይ፣ የትግራይ ሕዝብ፣ ወያኔዎቹና ሽፍቶቹ)

የቀድሞ የሕወሓት ታጋዮች ፀፀትም ሆነ የአሁን ታሪኩ የሚያስተምረን ዴሞክራሲ መንገድ እንጂ መዳረሻ አለመሆኑን ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያልመጣ ኃይል ዴሞክራሲን ሊያመጣ አይችልም፡፡

ትምህርት ሁለት፤ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር መቁረጥ

ሕወሓት ደርግን ወግቶ ለድል እንዲበቃ በተለይ ሁለት ዘዴዎች ረድተውታል፡፡ ሠላማዊ ታጋዮች እነዚህን ዘዴዎች በራሳቸው መንገድ ተርጉመው ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ደርግን እራሱን መጠቀሚያ ማድረግ ነው፡፡  ሕወሓት የደርግን ክፋት ለራሱ ተቀባይነት መግዣ በማድረግ ተጠቅሟል፡፡ ለምሳሌ በትግል ወቅት የማረካቸው ወታደሮች ‹ተሐድሶ› ካሠለጠናቸው በኋላ ሁለት አማራጭ ይሰጣቸው ነበር፡፡ አንድ ከጎን ተሰልፈው ደርግን እንዲወጉ፣ አልያም ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ፡፡ የትኛውንም ቢመርጡ ሕዋሓት ያተርፋል፡፡ ተመላሾቹ የገጠማቸውን ለቀሪው ወታደር ስለሚናገሩ ወታደሩ በወኔ ለመዋጋት ይለግማል፤ እነርሱም ተመልሰው ሕወሓትን አይወጉም፡፡ የደርግ አባል የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ደበላ ዴንሳ ተመላሽ “ምርኮኞችን መልሶ ማዝመት” ደርግን እንዲሸነፍ ያደረጉት ብለው ከዘረዘሯቸው 13 ነጥቦች አንዱ አድርገውታል፡፡ ሠላማዊ ታጋዮች ተቀናቃኜ የሚሉትን አካል ከጎናቸው ማሰለፍ የሚችሉበትን ስልት መንደፍ አለባቸው፡፡ በሐሳብ በመብለጥ!

የሕወሓት ወገን የነበሩ በመሆናቸው ብቻ በለውጡ እንደማይቀጡ ዋስትና ይፈልጋሉ፤ ሁለተኛ በለውጡ ሐሳብ መማረክ አለባቸው፡፡

ሁለተኛው፣ የሕዋሓት ብልሐት ደርግን የሚዋጋበትን መሣሪያ ከራሱ ከደርግ ማግኘት መቻሉ ነው፡፡ የአሁን ሠላማዊ ታጋዮች ሕዋሓት (ኢሕአዴግን ለማሸነፍ ወይም በዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ስርዓት ለመተካት የራሱን መሣሪያዎች መጠቀም መቻል አለባቸው፡፡) ሕገ መንግሥቱን፣ የመንግሥት መዋቅሮችን፣ የመንግሠት ሠራተኞችን፣ ወዘተርፈ ለሠላማዊው ትግል የሚፈይዱበትን ዘዴ መቀየስ ይበጃል፡፡

ትምህርት ሦስት፤ እያዝናኑ መታገል

ሕወሓት ትግሉ ሕዝቡ ውስጥ ሥር እንዲሰድ ከረዱት መንገዶች መካከል ሳይጠቀስ የማይታለፈው ኪነትን መጠቀም መቻሉ ነው፡፡ በተለይ በዘፈን ረገድ የተሠሩ ሥራዎች በወኔ የሚቀሰቅሱ፣ ሕልም እንዲያልሙ የሚረዱ እና የራሳቸውን የዘመን ወግ (Folklore) መፍጠር የቻሉ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ‹ንገሪን እንደ ሐለፋይ . . . › የሚለው (በትርጉሙ “ንገሪኝ እስቲ እናቴ፣ ወዴት ነው የሔደው አባቴ?” የሚል) የማሚት እና ብርሃነ (ሐለፋይ) የቅብብሎሽ (duet) ዘፈን፣ አሳዛኝ እና የተከፈለው መስዋዕትነት ለሚመጥነው ዋጋ መሆኑን የሚዘክር ዘፈን ነው፡፡ ይህንን ዘፈን ትግሪኛ ተናጋሪ ጓደኞቼን “ንገሪኝ እስኪ እናቴ፣ ለዚህ ነበር ወይ የሞተው አባቴ?” በሚል ምፀት እንዲቀይሩት ጠይቄያቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡… ጥበብ (ኪነ ጥበብም ይሁን ሥነ ጥበብ) በጥቅሉ ከአመፃዊ ይልቅ ለሠላማዊ ትግል መሣሪያ መሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ በዓለማችን ብዙ ትምህርት የሚሆኑ ሥራዎችን አይተናል፡፡ የማርያ ማኬባ ፀረ-አፓርታይድ ዜማዎች፣ የቦብ ማርሌይ የነጻነት ሬጌምቶች፣… እና በአገራችንም የቴዲ አፍሮ “ጃ ያስተሰርያል” ከነዚሁ ተርታ ይመደባል፡፡ የቀድሞዎቹን የጦር ሽለላዎችና ቀረርቶዎች በመጠቀም ያውም ለዚህ ትውልድ ጆሮ በሚስብ መልኩ በሂፕሆፕ (ራፕ) መልኩ፣ የለውጥ ሰባኪ ግጥሞች ተጽፈውለት መሥራት ይቻላል፡፡ ኬናን የተባለ ካናዳ-ሶማሊያዊ ራፐር ይህንን አሳይቷል፡፡
በጥበብ ረገድ የሚደረጉ ሠላማዊ ተጋድሎዎች በዘፈን ብቻ ሊገደቡ አይገባም፡፡ በሥዕል፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በቲያትር፣ ፊልም፣ ካርቱኖች እና ሌሎችም አማራጮች ቀርበው ሁሉንም እንደየፍላጎቱ ሊደርሱት ይገባል፡፡



የአምባገነኖች ድጋፍ ማግኛ ምንጭ

ጂን ሻርፕ የዐረቡ ዓለም አብዮት የሚባለውን እንዲቀጣጠል ነዳጅ ጨምሯል የተባለለትን “ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ” የተሰኘ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ መጽሐፉ ውስጥ አብዛኛዎቹ አስረጂ ምሳሌዎች አምባገነኖች መሠረታቸው ሕዝብ መሆኑን ነው የሚነግሩን፡፡ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በተደጋጋሚ “ጭቆና የሚሸከመው ትከሻ ይፈልጋል” የሚሉን ይህንን ነው፡፡ አምባገነኖች ሕዝብ ጭቆና ለመሸከም ትከሻውን እንዲሰጣቸው ብዙ መንገዶቸን ይጠቀማሉ፡፡ የ‹ሠላማዊ ትግል 101› ጸሐፊ ግርማ ሞገስ ሦስት ነገሮችን ይጠቅሳሉ፦ እነዚህም ፈቃደኝነት፣ ፍራቻ ወይም ግዴለሽነት ናቸው፡፡ የሚኪያቬሊ ፍልስፍናም (‹The Prince› ላይ እንደተገለጠ) “ነገሥታት በመወደድ ብቻ ሳይሆን በመፈራትም ነው የሚኖሩት”፤ ከተቻለ ወዶ እና ፈቅዶ የሚተባበር፣ የሚታዘዝና ለምዶበት የሚታመንላቸውን፤ ይህ ሲከብድ ትልቅ ሠራዊት በመገንባት ወይም የደኅንነት መረባቸው ትልቅ፣ ብልህ እና አስተማማኝ እንደሆነ በማስወራት ሕዝባቸውን እያስፈራሩ ትከሻው ላይ ይወጣሉ፡፡ ይህ ብቻውን ስለማያቆማቸው ያገኙትን ሞኝ ለማታለል ተቀባይነት የሚያስገኝላቸውን ዘዴም መዘየዳቸው አይቀርም፡፡

መንግሥታት ሥልጣን ላይ የሚቆዩት የተወሰነ ቅቡልነት (Legitimacy) እስካላቸው ድረስ ነው፡፡ የቀድሞ ነገሥታቶቻችን ራሳቸውን “ሥዩመ እግዚአብሔር” በማለት ቅቡልነትን ለማግኘት ይጥሩ ነበር፡፡ ጳጳሳቱም (ሲሦ ቀላዳቸውን ለማግኘት) ይህንኑ ለሕዝቡ ይሰብኩ ነበር፡፡ ለአሁኖቹ መሪዎች ይህ አያዋጣም፡፡ ሕዋሓት የዘውግ ብሔርተኝነትን (ዕኩልነትን አስጠብቃለሁ በሚል ሥም) ቅቡልነትን ሊገዛበት ሞክሮ ነበር፤ ብዙም አላስኬደውም፡፡ አሁን ደግሞ “ልማታዊነት” የተባለውን ጨብጧል፡፡ ድሃ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች እንደሚያዘናጉት በመረዳት “መጀመሪያ ዳቦ” እያለ እስከዚያው የመጨቆኛ ካርድ ለማግኘት ይጥራል፡፡ በዚህ አካሔድ ዊኒ ማንዴላ ተናግረውታል እንደሚባለው “ወፍራም ባሪያ” መፍጠር ይፈልጋሉ፡፡  

አባገነኖች፣ ልዩ ፍጡሮች?

አምባገነንነት የሚፈጠረው ሰዎች ያልተገደበ ሥልጣን ሲገጥማቸው ራሳቸውን መግዛት ስለሚከብዳቸው ነው፡፡ ብዙዎች የዓለማችን አምባገነኖች መጀመሪያ ምስኪን “ነጻ አውጪዎች” ነበሩ፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስን እንኳን ብንወስድ ዐፄነት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት የድሃ አባት ነበሩ፤ ያውም ከበዝባዥ ፊውዳል ባለሀብቶች እየዘረፉ ለድሃ የሚያከፋፍሉ ዓይነት፡፡ ኋላ በትረ ሥልጣኑን ሲይዙ ግን በገዳይነት የሚወዳደራቸው አጡ፡፡  የአገሬ ሕዝብ ስራት ያዝ ብለው እምቢ አለኝ” እያሉ በስርዓት ማስያዝ ሥም ሕዝቡን ፈጁት፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን ውስጣቸው የነበረው ቅንነት እየወቀሳቸው “አቤቱ አምላኬ፣ እባክህን ግደለኝ እና ሕዝብህን ነጻ አውጣ” እስከማለት ደርሰው እንደነበር እንግሊዛዊ እስረኞቻቸው ጽፈዋል፡፡ ሰዎች ሠላማዊነትን መምረጥ የሚኖርባቸው ከራሳቸው ድብቅ አውዳሚነት ራሳቸውን መጠበቅ ስለሚከብዳቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ - አምባገነንነት ባሕል ነው ማለት ይቻላል፡፡ አምባገነኖቻችን በቁልምጫ ነው የሚታወሱት፡፡ “መንጌ”ን መጥቀስ ይቻላል! አባወራዎች በቤተሰቡ ላይ ፍፁማዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ መምህራን በክፍል ተማሪዎቻቸው ላይ ፍፁም የበላይ ተደርገው ይሾማሉ፡፡ አለቆችም በምንዝሮቻቸው ላይ እንዲያው ናቸው፡፡ ሁሉም አቅሙ በፈቀደው ላይ ፍፁማዊ ኃይልን እና የበላይነትን መጠቀምን ባሕላችን ያበረታታል፡፡ ዘበኛው በደጅ ጠኚው ላይ፣ አሠሪው በሠራተኛዋ ላይ ኃያል ነው፡፡ ዕድሩ ሰብሳቢው አይለወጥም፤ የትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ እስኪሞት አይሻርም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲው ሊቀመንበር አይቀየርም በዚህ ባሕል ውስጥ እየኖርን የአገር መሪ ብንቀያየርም “ተረኛ ጨቋኝ” እንጂ ዴሞክራሲን አናመጣም፡፡

የአምባገነኖች አንድ ዓይነትነት

አምባገነን አገር ወይም ብሔር የለውም፡፡ ቋንቋ የለውም፡፡ ሁሉም ያልሠለጠኑ ሕዝቦች ውስጥ ያለ ዕዳ ነው፡፡ አማር ቦንጎ ጋቦንን ለ42 ዓመታት ገዝቷል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎችን ለቤተዘመዱ አከፋፍሏል፡፡ ልጁ እሱ ሲሞት ሥልጣኑን ወርሷል፡፡ ሴት ልጁ የፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ነበረች፡፡ ባሏ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፡፡ በሥሙ ያልተሠየመ ነገር የለም፤ ቦንጎ ዩኒቨርስቲ፣ ቦንጎ አየር ማረፊያ፣ ቦንጎ ሆስፒታል… ሌላው ቀርቶ የትውልድ ከተማው ቦንጎቪል ተብላለች፡፡ እኛም አገር ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ እስከ መለስ ዜናዊ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡

የኮትዲቯሩ ሆፎኤት-ቦይኚ 6 ጊዜ የፕሬዚዳንት ምርጫን አሸንፏል፡፡ ያውም 99.7 በመቶ አማካኝ ድምፅ አግኝቶ! የአንዱን አምባገነን ታሪክ መስማት፣ የሌላኛውን እንደመስማት ነው፡፡

አምባገነኖች ሥራቸውን ልባቸው ስለሚያውቀው ይፈራሉ፡፡ የደኅንነት ሠራተኞቻቸውም ፍርሐታቸውን ለማረጋጋት የውሸት መረጃ ይሰጧቸዋል፡፡ የዩጋንዳው ኢዲ አሚን ዳዳ ለምሳሌ “ሕዝቡ በፕሬዚዳንቱ ፍቅር አብዷል” የሚል የደኅንነት ሪፖርት ደርሶት እንደነበር ተነግሯል፡፡  አሁን፣ አሁን የአገራችን ባለሥልጣኖችም በጋዜጣ መግለጫዎቻቸው የሚያሳዩት ባሕሪ እንዲህ ዓይነት ሪፖርት የደረሳቸው በሚመስል መልኩ ነው፡፡

የራሺያው የቦልሼቪኮች ፓርቲ (እ.ኤ.አ. በ1917 ጀምሮ እስከ 1940 ብቻ) በ23 ዓመታት ውስጥ ከ24 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ የቀረው አንድ ጆሴፍ ስታሊን ብቻ ነበር፡፡ 8ቱ ተገደሉ፣ 7ቱ “በተፈጥሮ አጋጣሚ ሞቱ” ተባለ፣ 7ቱ “የደረሱበት ጠፋ” ተባለ፣ አንዱ ታሰረ፡፡ ቀሪው አንድ አምባገነን ብዙ ሚሊዮኖችን ፈጀ፡፡ ይህንን ስታሊኒስታዊ አመራር (ተቀናቃኞችን ማጥፋት) ከልባቸው ያሳደሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንደስታሊን ማዕከላዊ ኮሚቴውን ባዶ ከማድረግ ይልቅ፣ ታዛዥ አላዋቂዎች እንዲሰበሰቡበት አደረጉ፡፡ ልዩነቱ ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን ሞት ቀደማቸው፡፡ የቀሩት አባላት የሚያደርጉት ጠፋቸው፡፡ ስለዚህ የሟቹን ሌጋሲ (“ትሩፋት”) እናስቀጥላለን በማለት በመለስ የተሾሙለትን ዓላማ እያስፈፀሙ ነው፡፡

ምርጫ በአምባገነኖች አገር

በአምባገነኖች አገር ምርጫ ማለት አሸናፊውን (ገዢውን) አጅቦ ለድል ማብቃት ማለት ነው፡፡ ወይም አምባገነኖቹ የሚፈልጉት እንደዚያ እንዲሆን ነው፡፡ ‹The Dictator› የተሰኘው ፊልም ነገሩን ግልጽ አድርጎታል፡፡ አላዲን የተባለው የዋዲያ መሪ የራሱን ኦሎምፒክ አዘጋጅቶ፣ ራሱ ተወዳድሮ ያሽንፋል፡፡ ውድድሩን ተኩሶ የሚያስጀምረው ራሱ ነው፡፡ የሚቀድሙትን ተወዳዳሪዎች እየተኮሰ ይጥላቸዋል፡፡ መጨረሻ ላይ ራሱ ያሸንፋል፡፡ ምርጫ ለአምባገነኖች እንዲህ ቀላል ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ አሸንፌ ድሌ ይከበርልኛል ብለው ከሚያስቡ የአላዲንን ሽጉጥ የጨበጠ እጅ ቢይዙ የተሻለ ያዋጣቸው ነበር፡፡ የአምባገነን መንግሥት ተፎካካሪ ፓርቲዎች የአምባገነንነት መንግሥት እጅ መያዝ አለባቸው፡፡

አገዛዙ ወይም የአገዛዙ ልሒቃን በምን ጥገኛ እንደሆኑ መለየት እና ያንን መንፈግን እንደትግል መሣሪያ (መደራደሪያነት) መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የእኛ አምባገነኖች ተፎካካሪዎቻቸውን የሚጥሉት በየትኛው እጃቸው ነው? የኃይል ምንጫቸው ምንድን ነው? ሠላማዊ ትግሉ ሊሠራው የሚጠብቀው የቤት ሥራ ነው፡፡


ግብታዊ ጩኸት፣ ለቅስፈት…

ሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነን መሆኑ ታውቋል፡፡ ምርጫ እንደሚያጭበረብር ታውቋል፡፡ የሲቪል ማኅበራት ፓርቲዎችን ገቢ በማሳጣት፣ መሪዎቻቸውን በማሰር፣ ውስጣቸው ክፍፍል በመፍጠር እንደሚያዳክማቸው ታውቋል፡፡ ነጻ ፕሬሶችን እንደሚያደናቅፍ ታውቋል፡፡ ሠላማዊ ትግሉ ከነዚህ በላይ ሆኖ የሚያሸንፍበትን መንገድ (Strategy) መንደፍ አለበት፡፡ ነገር ግን ያልታወቀም ነገር አለ፡፡ ኢሕአዴግ አስካሁን አልተፈተነም፡፡ ለቀላሏ ፈተና (ድኅረ ምርጫ 97 ለገጠመው ተግዳሮት) የሰጠው ምላሽ ያልተመጣጠነ ነበር፡፡ እርግጥ ያ አጋጣሚ ተቃዋሚው ሠላማዊነቱን ያጣበት ነበር፡፡ የመንግሥት እርምጃ ግን የቻይናውን (የታይናንሜን ስኩዌር) እርምጃ ያስታውሰናል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት አደባባይ ወጥተው አንገባም ያሉትን ሰልፈኞች የቻይና መንግሥት ታንክ ሳይቀር ይዞ አደባባይ በመውጣት ነው ሰልፉን የበተነው፡፡ ኢሕአዴግ የደርግን ያክል ቢፈተን ከደርግ አይብስም ወይ? እነዚህን ያወቅናቸውን እና ያላወቅናቸውን የኢሕአዴግ ባሕርያት ማሰላሰል የሠላማዊ ትግሉን መሥመር ለመወጠን ወሳኝ ቁምነገር ነው፡፡ እስከአሁን የነበረው ዓይነት ሁሉም በየፊናው ያሰኘውን የሚያደርግበት፣ ያልታሰበበት መፍጨርጨር፣ በአጭር በአጭሩ ከመሰበር በቀር ምንም አልፈየዱም፡፡ ብዙ ጊዜ አምባገነኖች የሠላማዊ ትግልን አከርካሪ ለመስበር የሚጠቀሙበት ዘዴ ሠላማዊ ያልሆነ ነገር እንዲሠሩ ማድረግን ነው፡፡ ሠላማዊ ትግሉ ሁለቱን እርከኖች (ማንቃት እና ማደራጀት) አልፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምር ሠላማዊነቱ እና ደኅንነቱ እንዴት ይጠበቃል?

ሐዲስ ዓለማየሁ “የልምዣት” ላይ “የጨለማው ንጉሥ” የተባለ በበሻህ ዘለሌ የሚመራ ቡድን ፈጥረዋል፡፡ ቡድኑ ሕዝብ የበደሉ ባለሥልጣናትን እየገደለ፣ ለምን እንደተገደሉ የሚገልጽ ማስታወሻ ጽፎባቸው ይሰወራል፡፡ ኋላ ግን ቡድኑ ከበሻህ ዘለሌ ቁጥጥር ውጭ ሆነ፡፡ የቡድኑ አባላት መነሻቸውን ረስተው ገንዘብ ለመዝረፍ ተሰማሩ፡፡ ይህንን ቁንፅል የመጽሐፉን ታሪክ እዚህ መጥቀሴ የግብታዊ ርምጃን የመጨረሻ ውጤት ከዚህ የተሻለ የሚያሳይልኝ ምሳሌ ስለሌለ ነው፡፡


መጀመሪያ የብብቷን…!

በተቃዋሚው ጎራ የተለመደ ድክመት አለ፡፡ ተቃዋሚው የቱንም ያክል በትንሽ አቅም ቢንቀሳቀስ፣ የሚጠብቀው ውጤት ብዙ ነው፡፡ ይህ የስስት ባሕሪ የያዘውን ጭምር ያሳጣዋል፡፡ በምርጫ 97 ተቃዋሚው ከመቼውም የበለጠ (31.6% ያህል) የፓርላማ ወንበር እንዳገኘ ኢሕአዴግ አምኖለታል፡፡ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ አልነበረም፡፡ ሆኖም ተቃዋሚው ‹ኢሕአዴግ ምርጫውን ቢያጭበረብርስ በማለት አማራጭ ውጥን  (Plan B) ያላዘጋጀ በመሆኑ የያዘውን ይዞ ማልቀስ ሲኖርበት የያዘውንም አጥቷል› በማለት አቶ ግርማ ሞገስ ‹ሰላማዊ ትግል 101 ላይ› ይከራከራሉ፦

“በትግሉ ሜዳ መቆየት ያለብህ ያገኘኸውን ድል ሳትነጠቅ ተጨማሪ ድሎችን ማግኘት የሚያስችል ተጨማሪ አቅም እንዳለህ እርግጠኛ ስትሆን ብቻ ነው፡፡›” (ገጽ 199)

“…ተቃዋሚው የነበረውን የተሻለ አማራጭ በምርጫ ያገኘውን ፓለቲካዊና ድርጅታዊ ድል ከነእንከኑ መቀበል ነበር፡፡” (ገጽ 205)

የውሸት ምርጫ አምባገነኖች ዓለምዐቀፍ ድጋፍ ለማግኛ የሚጠቀሙበት ‹ዕውቅና› መግዣ ነው፡፡ የፈለገውን ያክል ተፎካካሪዎቻቸውን ቢደፈጥጡም፣ እነርሱን መጣል የሚችል ሠላማዊ ስትራቴጂ መንደፍ የሚቻለው ግን ምርጫን አስታኮ ነው፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚዎች የያዙትን ይዘው፣ በምርጫዎች መሐል ራሳቸውን ወንበር መነቅነቅ በሚያስችላቸው መንገድ ማደራጀት እና ማዘጋጀት አለባቸው -ከነፈተናው፡፡ ፈተናው ሠላማዊ ታጋዮች ወደ ትግል የሚገቡበት እንጂ ከትግል የሚወጡበት ምክንያት መሆን የለበትም፡፡

“ምን ተይዞ ጉዞ?”

ተቃዋሚው ዘንድ በችኮላ የሚወሰኑ ግብታዊ ርምጃዎች ለዘላቂ ክሽፈት መንስኤ እንደሚሆኑ ተመልከተናል፡፡ የተደራጀ እና የነቃ ማኅበረሰብ በሌለበት ሠላማዊ ሰልፍ መጥራት - አንድም በሚገኘው ሰው ማነስ (ትግሉ የሕዳጣን እየመሰለ)፣ አንድም ለአገዛዙ ምት እየተመቸ ከሚጠራው የሚያባርረው ሰው እንዲበዛ ያደርጋል፡፡ (ከምርጫ 97 ወዲህ እንኳ አንድም ሰው ያልወጣባቸው ሁለት የአብዮት ጥሪዎች ተደርገዋል፡፡) በሌላ በኩል የተለያዩ አድማዎችን ለመጥራት ብዙ ነገሮችን ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ አብዮት ባለታክሲዎች ያደረጉት አድማ ወደር የለውም፡፡ ጆን ያንግ ‘Peasants Revolution in Ethiopia’ ላይ ‹አዲስ አበባ ሽባ ሆና ዋለች› ብለው ጽፈዋል፡፡ በአምስት ሣንቲም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አገር ተንቀጠቀጠ፡፡ ይህንን እያስታወሱ የታክሲ ሥራ ማቆም አድማዎች በቅርብ ጊዜያትም ተጠርተዋል፡፡ ችግሩ ግን እነሱን የሚመለከት መነሻ አልነበረውም፡፡ እንዲያውም በድኅረ ምርጫ 97 የተጠራው በራሳቸው ተነሳሽነት በመሆኑ በከፊል ተሳክቷል፡፡ ግን ያለምንም ትርፍ ከ5 ቀናት በኋላ ወደነበረበት ቀስ በቀስ ተመልሷል፡፡ ለምን?፦

ሾፌሮቹ፣ ባለቤቶቹ፣ ረዳቶቹ ምን ይብሉ? ኤርምያስ ለገሠ (“የመለስ ትሩፋት” ባለው መጽሐፉ ላይ) ‹ሥራው እንዲቀጥል ከመንግሥት ጋር መሞዳሞድ የጀመሩት ሱስ ያናወዛቸው ተራ አስከባሪዎች ናቸው› ይላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ድል አድራጊነት አድማው ከሽፏል፡፡ ጥቁር አሜሪካውያን በሞንትጎምሪ ከተማ (አላባማ) የጥቁሮችን መገለል በመቃወም በከተማ አውቶቡስ ላለመሳፈር ሲያድሙ፣ ጥቁሮች የሚጓጓዙባቸውን አማራጮች አመቻችተው ነበር፡፡ በአገራችን ሕወሓት/ኢሕአዴግን የኢኮኖሚ ትብብር ለመንፈግ ሲባል ‹ከነእከሌ አትግዙ› የሚሉ የአድማ ምክሮች ብዙ ጊዜ ተደምጠዋል፡፡ ግን አልተሳኩም፤ ምክንያቱም ሸማቹ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ አድማዎች የሚጠሩ ከሆነ፣ ጉዳታቸው (ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው) አድማ መቺው ላይ ሳይሆን አምባገነኑ አካል ላይ መሆኑን (ወይም መሆን የሚችልበት መንገድ) ማረጋገጥ የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡


መውጪያ

‘ከታሪክ የምንማረው ከታሪክ እንደማንማር ነው’ የሚለው አባባል የመጣው ለሰዎች የሚቀለው የሚያውቁትን መደጋገም ስለሆነና ያንኑ ስለሚያደርጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው፡፡ እንኳን በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል፣ ልጅ ከአባቱ ሥልጣን የሚወስደው በጦርነት ወይም በኃይል ነው፡፡ (‘ታላቁ ንጉሥ ቀዳማዊ እያሱ’ በ17ኛው ክ/ዘመን መስክ ጉብኝት ደርሶ ሲመለስ ጎንደር በብዙ መልኩ ተቃውሳ ጠበቀችው፡፡ በዚያ ላይ የሚወዳት እቁባቱ ሞታለች፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ንጉሡ ጣና ደሴት ካሉ ገዳሞች ገብቶ መነነ፡፡ ልጁ ተክለሃይማኖት አጋጣሚውን ተጠቅሞ ንግሥናውን አወጀ፡፡ ሆኖም ግን አባቴ ተመልሶ ንግሥናዬን ይቀማኛል በሚል ስጋት እዚያው ጣና ደሴት ላይ አስገድሎታል፡፡)

ይህ የታሪክ ዥረት ፈሶ፣ ፈሶ እኛ ጋር ደርሷል፡፡ የእኛ ትውልድም፣ እንደቀድሞው ሁሉ በትረ-ሥልጣኑን በኃይል ከጨበጠው ኃይል ጋር ተፋጧል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “ዴሞክራሲ ማለት ሕዝቦች ከጦር ሠራዊት (የበላይነት) ነጻ ሲወጡ ማለት ነው” ይላል፤ እንደ ኮስታሪካ የጦር ሠራዊታችንን በትነን (እስካሁን 68 ዓመት ሞልቷቸዋል) በሠላም መኖር ባይሆንልን እንኳን ጦር ሠራዊቱን፣ ፖሊስ እና የደኅንነት አካሉን የማንፈራ እና የማናፍርበት እንዲሆን ብዙ መታገል አለብን፡፡ በመታደል የሚገኝ የለምና፡፡ ጥያቄው ‹ከትግል ሒደቱ “ጨዋ” ወይስ “ባለጌ” ይወጣን ይሆን?› የሚለው ነው፡፡

የተለመደውን የጦርነት ታሪክ እናስቀጥላለን ወይስ አዲስ ታሪክ ለመሥራት   ተዘጋጅተናል?

===
*ይህ ጽሑፍ አምና (ነሐሴ 2007) ከማረሚያ ቤት ተልኮ በአምስት ክፍሎች ዞን ፱ ላይ የወጣ ሲሆን፣ አሁን (ሐምሌ 2008) ከጥቃቅን የአርትኦት ሥራ ጋር በድጋሚ ተጠቅልሎ ነው የታተመው፡፡

No comments:

Post a Comment