Pages

Monday, November 4, 2013

ነዋሪዎቹ ለምን እርሻውን አቃጠሉት?


በቅርቡ ከሰማናቸው ዜናዎች ውስጥ አንዱ ‹‹በጋምቤላ በሕንዳዊው ኩባንያ ቨርዳንታ ሐርቨስት የተያዘው እርሻ በአካባቢው ሰዎች እሳት ተለቀቀበት›› የሚል ይገኝበታል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እርሻውን ማቃጠላቸው ስህተት እንደሆነ አምናለሁ፤ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በነርሱ ቦታ ሳልሆን ልፈርድባቸው አልደፍርም፡፡ ይልቁንም በዚህ መረጃ ላይ ተመስርቼ ‹‹ለምን›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም የዛሬ ሁለት ዓመት (ኦክቶበር 16፣ 2011) ‹‹ቀጣዩ እሳት በምን ይመጣ ይሆን?›› በሚል ስጋታቸውን የጻፉት በዚያው ክልል ትልቅ የእርሻ ቦታ የገዛውን የካሩቱሪስታን ኩባንያ የመጀመሪያ ምርቱን የሰደድ እሳት ከበላበት በኋላ ነበር፡፡ ይህ በሆነ ልክ በሁለት ዓመቱ ነው ዘንድሮ ሌላኛው የሕንድ ኩባንያ እርሻ ላይ ነዋሪዎቹ እሳት የለቀቁበት፡፡

ብዙ የሚታወቀውና 300ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት በየዓመቱ ተከፋፍሎ የሚከፈል 50 ሚሊዮን ብር ሊዝ የተከራየው ካሩቱሪስታን (ካራቱሪ) ነው፡፡ የግብርና ድርጅቶቹ የሥራ ማስኬጂያ ገንዘባቸውን የሚያገኙት ከዚሁ አገር በመሆኑ ኢንቨስትመንቱ በዚህ ረገድ የሚያስገኘው ጥቅም የለም፤ እንዲያውም ‹ካራቱሪ 62 ሚሊዮንብር የባንክ ዕዳውን መክፈል አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ የሠራተኞች ጡረታ ተቆራጭ እና የገቢ ግብር ለመንግሥት አላስገባም› ብሎ ሰንደቅ ጋዜጣ የዘገበው በቅርቡ ነበር፡፡ ከመሬት ሊዙ ይገኛል የሚባለው ጥቅም ‹‹የቴክኖሎጂ ሽግግር›› ነው፡፡ ነገር ግን የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች እያበሳጨና በሌላም፣ በሌላም ከወዲሁ በተለይ ለነዋሪዎቹ አለመመቸቱን ምልክቶች ያሳያሉ፡፡

ይህን የእርሻ መቃጠል ስናነሳ በታሪክ ወደኋላ ተጉዘን ዘመነ መሳፍንት ላይ እንደርሳለን፡፡ በዘመኑ አቅም ያለው ሁሉ ባላባት የነበረበት እና ምስኪኑን ገበሬ በተደጋጋሚ እያስገበረ ያስመርር ነበርና የወቅቱ ገበሬ ገና ወታደሮች መምጣታቸውን ሲሰማ የገዛ መኸሩ ላይ እሳት ይለቅ ነበር ይሉናል የታሪክ ባለሙያዎች፡፡

ታሪክ ራሱን ደገመ!

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ያዋሰኝ በ2011 በFSS የታተመ የደሳለኝ ራሕመቶ ጥናት (LAND TO INVESTORS: Large-Scale Land Transfers in Ethiopia) መንግሥት የመሬት ልማት የሚለውን መቀራመት ችግሮች በአምስት አንኳር ነጥቦች ያስቀምጧቸዋል፡፡ እኔ በራሴ አገላለጽ እንደሚከተለው እዘረዝራቸዋለሁ፡-

1. የገጠር ኢኮኖሚ መዛባት
ለውጭ ባለሀብቶች የሚያደላው ይህ ስርዓት ግዙፍ የግብርና ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚዎች ከመሆናቸውም ባሻገር የትናንሽ ገበሬዎቹን ኢኮኖሚ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በማቃወስ የሀብት ልዩነቱን ይበልጥ ያሰፋዋል፡፡ ፉክክሩም ‹‹ባላቸውና በሌላቸው›› መካከል ይሆናል፡፡ በረዥም ጊዜ ሀብታሞቹ በኬሚካሎች ይዘቱን አራቁተው ሲሄዱ ድሀዎቹ ደረቅ መሬታቸውን ታቅፈው ይቀራሉ፡፡

2. የተጠቂነት ስሜት
የመሬት ነጠቃው /ኢንቨስትመንት የሚሰጥበት መንገድ/ ግልጽነት የጎደለው እና ያለነዋሪዎቹ ሙሉ ፈቃደኝነት የሚከናወን በመሆኑ፣ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ በተጨማሪ ሰሚ እና ዋስትና የማጣት ስሜት /voiceless-ness and insecurity/ በነባሮቹ ማኅበረሰቦች ላይ ይፈጥራል፤ ስለሆነም ነዋሪዎቹ ‹‹ኢንቨስትመንቱን›› በቀና አይቀበሉትም ወይም ሊቀበሉት የሚያስችል ምክንያት የላቸውም፡፡

3. ‹‹የማያልፍለት ድኻ ሀብታም የመጋበዙ›› ጉዳይ
የውጭ ባለሀብቶች ምርታቸውን ስለሚያቀርቡለት አካል መደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ ስምምነት የለም፡፡ እንደምሳሌ የሕንድ ኩባንያዎች እዚህ ያመረቱትን ከፊሉ የአገራቸውን ‹‹የምግብ ክፍተት›› ለመሙላት፣ ከፊሉን ደግሞ ለሌሎች አገራት በጥሩ ትርፍ ለመሸጥ ነው መሬት ከኢትዮጵያ የገዙት፡፡ ኢትዮጵያ ግን በየዓመቱ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማት እና ከውጭ እጆቿን ዘርግታ የምትለምን አገር ናት፤ (እጅ መዘርጋት መፍትሔ ይመስል!)

4. የቴክኖሎጂ ሽግግር ብሎ ነገር አለመኖር
የግዙፍ ግብርና ፕሮጀክቶች በባሕሪያቸው ትላልቅ ማሽነሪዎችን የሚጠቀሙ በመሆናቸው እና በበሬና ገበሬ ትከሻ አራሽ የገበሬ ቤተሰቦች ቴክኖሎጂ ሽግግር ያድርጉ ቢባል እንኳን ከነዚህ ግዙፍ ማሽነሪዎች ምንም ማግኘት አይችሉም፡፡ ስለዚህ አንዱ የመንግሥት መሬት በርካሽ የመቸብቸብ ግብ መቼም የተባለለትን አያመጣም፡፡

5. ሌሎች አማራጮች አልተቀመጡም
መንግሥት መሬት ለግዙፍ የግብርና ፕሮጀክቶች ማከራይትን እንደብቸኛ አማራጭ በመያዙ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች እንደተሞከረው መሬቱን፣ የደን እና የእንስሳት ይዘቱን እንደጠበቀ የገቢ ምንጭ ማግኛ አማራጭ መፈለግ ይቻል ነበር፡፡ በተለይም የጋምቤላ ደን እና የእንስሳት ይዘት /ecosystem/ በግዙፍ ግብርና ስም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በረዥም የጊዜ ሒደት ወደማይመለስበት የደን ሀብት መራቆት ደረጃ ይደርሳል፡፡

እንግዲህ ገበሬዎቹን የሕንዶቹን እርሻ ለማቃጠል ያበቃቸው ከነዚህ ችግሮች አንድ ሁለቱ ብቻ ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ ከዚያም የባሱ ናቸው፡፡

መንግሥት አያውቅም እንዳይባል ብዙ ምሁራን ብለውት፣ ብለውት ደክሟቸው ነው የተዉት፡፡ ስለዚህ አጥኚው (ደሳለኝ ራሕመቶ) እንደሚሉት ‹‹ill-conceived›› (በክፋት የተፀነሰ) ሐሳብ ስለሆነ፣ በእኔ እምነት መፍትሔው የስርዓቱን ክፋት በሠላማዊ ሁኔታ እስከገጥግ መታገል ነው፡፡

1 comment:

  1. I have looked at your articles and they are well written and supported with facts. Keep it up. I also want you to check out www.ethiopianarchive.wordpress.com if your interested I would like to start sharing documents that can be archived. I'm interested in preserving our books and expanding their availability to promote more writing.

    ReplyDelete