‹‹በእግዚአብሔር ስም እምልላችኋለሁ የማውቀው ነገር የለም…›› አለ እየጮኸ፡፡
‹‹ገልብጡት›› አለ ኮማንደሩ፤ አላመነውም ነበር፡፡
ከግራና ቀኙ ቆመው የነበሩት ሁለቱ ፖሊሶች ገፍትረው በአፍጢሙ ደፉት፡፡
ወለሉ የአፈር ስለነበር ብዙም አልተጎዳም፡፡ እግሮቹ ቋንጃ ላይ ወፈር ያለ ቧንቧ ብረት አስገብተው እግሮቹን የኋልዮሽ በመጎተት
በጠፍር መሳይ ገመድ ከወገቡጋ አሰሯቸው፡፡ የቧንቧ ብረቱን ዳርና ዳር ይዘው ሲያነሱት ቁልቁል ተዘቀዘቀ፡፡ አንጠልጥለው ግድግዳው
ላይ የተሰኩ ሁለት አግድም ምሰሶዎች ላይ ሰቀሉት፡፡
‹‹አሁንስ አትናገርም?›› አለው ኮማንደሩ፡፡
‹‹ኧረ እኔ ምንም የማውቀ…›› የጀመረውን ሳይጨርስ በፊት አንደኛው ፖሊስ
በያዘው ደረቅ ጎማ ጀርባውን አደረቀው፡፡
‹‹እውነቱን ትናገራለህ ወይስ አትናገርም?›› አለው ኮማንደሩ በድጋሚ፤
ከመናገር ይልቅ ዝም ማለት ያዋጣል በማለት ዝም አለ፡፡
‹‹ትናገራለህ፣ አትናገርም›› አለው ኮማንደሩ፤ ዝም አለ!
ሁለቱም ፖሊሶች በደረቅ ጎማቸው ተፈራረቁበት፤ ‹‹እናገራለሁ፣ እናገራለሁ…››
አለ በጩኸት፡፡ ዱላውን አቆሙለት ነገር ግን የሚናገረው ስላልነበረው ዝም አለ፡፡
‹‹ተናገራ፣…›› አለ ኮማንደሩ በብስጭት ጩኸት እያምባረቀ ከጥቂት ደቂቃዎች
ዝምታ በኋላ፡፡
‹‹እ…ግ…ዚ…አ…ብ…ሔ…ር…ን… ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡›› አለ የመሐላውን
እያንዳንዷን ድምፅ አጥብቆ እየጠራ፡፡ ቁጥሩን ለማያስታውሰው ጊዜ ሁለቱ ፖሊሶች በደረቅ ጎማቸው ጀርባው ላይ ተረባረቡበት፡፡
‹‹አትናገርም፣… ›› አለ ኮማንደሩ፡፡
‹‹ምን ልናገር…? በእግዚአብሔር አታምኑም… ኧረ እባካችሁ…››
‹‹እስከ ጥዋት ድረስ አስብበት… እስክትናገር ድረስ ከዚህ አትወርድም››
ብሎት ኮማንደሩ ክፍሉን ለቆ ወጣ፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች እጆቹን በካቴና ጠርንፈው ሲያበቁ ኮማንደሩን ተከትለው ከወጡ በኋላ በሩ በላዩ
ላይ ተጠረቀመ፡፡ ቤቱ ዓይን በሚያወጣ ጨለማ ተዋጠ፡፡ እንደዘቀዘቁት ይቆያሉ ብሎ አላመነም ነበር፡፡ ከአሁን አሁን አንዳቸው ተመልሰው
ይመጣሉ ብሎ አሰበ፣ ተመኘ፣ ፀለየ - ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡
ያጠፋው ጥፋት ምን እንደሆነ አልገባውም፡፡ ድምፁን አውጥቶ ጮኸ፣ ተለማመነ…
ነገር ግን መጥቶ የሚረዳው ሰው ቀርቶ የሚሰማው ሰው መኖሩን እስኪጠራጠር ድረስ መልስ አጣ፡፡ በካቴና የታሰሩትን እጆቹን የሚያረግበት
ቦታ አጣ፡፡ ወደላይ ሲያደርጋቸው በደቂቃ ውስጥ ክንዱ ይዝላል፡፡ ወደታች ሲለቃቸው ሰውነቱን ከመጎተትም በተጨማሪ ጣቱን የሚቆጠቁጥ
ድንዛዜ ይሰማዋል፡፡ ከላይ እግሮቹ መሐል ያለው ብረት ጉልበቱን ለሁለት በጥሶ ሊወጣ የደረሰ ይመስል ወጥሮ ይዞታል፡፡
እያንዳንዷ ደቂቃ የሰዓት ያክል ረዘመችበት፡፡ እልፍ የስሜት መለዋወጦችን
በደቂቃዎች ውስጥ ያስተናግዳል፡፡ ድንገት የማቅለሽለሽ ስሜት ተሰማው፡፡ እዚያው የተዘቀዘቀበት ሊያስመልሰው እንደሆነ ገባው፤ ነገር
ግን ውጦ ሊመልሰው አይችልም - ተዘቅዝቋል፡፡ ሆዱ ውስጥ ያለው ምግብ ወጣ፡፡ በተዘቀዘቀው ፊቱ፣ በግንባሩ ላይ ቁልቁል ፈሰሰ፡፡
‹‹አምላኬ ካላዳንከኝ ቶሎ ግደለኝ…›› ብሎ ፀለየ፡፡ ያጠፋውን ጥፋት አያውቅም፡፡
ፖለቲካ አይወድም፤ ‹ፖለቲካና ኮረንቲን ከሩቁ› ባይ ነው፡፡ ፖሊሶቹ ተመልሰው ሲመጡ ምን እንደሚላቸው ግራ ገብቶታል፡፡ ካልሆነ
መዋሸት እንደሚሻል እያሰበ ነው፡፡ ምን ብሎ ይዋሻል? ውሸቱንስ እንዴት እውነት ማስመሰል ይቻላል? ሕመሙ… በአግባቡ ማሰብ አላስቻለውም፡፡
በክፍሉ ውስጥ የሚሰማው ብቸኛ ድምፅ እምባው በግንባሩ ላይ ፈሶ መሬት ላይ ሲንጠባጠብ የሚወጣው ድምፅ ብቻ ነው፡፡ አፍንጫው እየተዝረከረከ
የሚያወጣው ፈሳሽ ዓይኑ ውስጥ እየገባ ያሰቃየው ጀመር፡፡ ከእግር ጥፍሩ እስከራስ ፀጉሩ ድረስ ሕመም ይሰማዋል፡፡
ቀስ በቀስ ግን ሰውነቱ እየቀዘቀዘ መጣ፡፡ መጀመሪያ እግሮቹን አጣቸው እንደተዘቀዘቀ
ነው፡፡ እግሮቹ ከላይ መታሰራቸው ይታወቀዋል፡፡ ግን ሕመሙ አይሰማውም፡፡ ደንዝዟል፡፡ ሊያንቀሳቀሳቸው ሲሞክር አይችልም፡፡ እግሮቹ
ከላይ ይኑሩ አይኑሩ እርግጠኛ መሆን አቃተው፡፡ ጨለማ ነው፣ ምንም ዓይታየውም፡፡ አዕምሮውም እግሮቹን ማዘዝ አቅቶታል፡፡
ወደታች የተንጠለጠሉት እጆቹ ጣቶች ደም አርግዘው በማበጣቸው ሊፈነዱ የደረሱ
ይመስላሉ፡፡ ጥዝጣዜያቸው እከኩኝ፣ እከኩኝ ቢያሰኝም የሚያክበት ትርፍ እጅ አልነበረውም፡፡ ከላይ እየቀዘቀዘ፣ ከታች እየተቃጠለ
ነው፡፡ ሕይወቱ ቀስ በቀስ እየወጣች እንደሆነ ተሰማው፣ ፈራ፡፡ ቀድሞ ግደለኝ ብሎ የለመነውን አምላኩን ደግሞ ‹‹አትግደለኝ››
እያለ በሹክሹክታ ይለማመነው ጀመር፤ ከዚያ በኋላ የሚያስታውሰው ነገር የለም፡፡
----
----
ቅዝቃዜ ይሰማዋል፡፡ ሙሉ ሰውነቱ ይቀዘቅዛል፡፡ ጭው ባለ ሜዳ ላይ ብቻውን
በጀርባው ተንጋሏል፡፡ ዝናብ እየዘነበ ነው፡፡ ዝናቡ ግን የሚንጠባጠብ ዝናብ አይደለም፡፡ ሰማዩ የተቀደደ ይመስል ጎርፍ ነው እላዩ
ላይ የሚወርደው፡፡ ዝናቡ ይቋረጥና፣ ጥቂት ቆይቶ መልሶ ይደፋበታል፡፡ ሰውነቱ ዝሏል፡፡ በትግል ዓይኖቹን ገለጣቸው፡፡ አንዱ ፖሊስ
የውኃ ባልዲ ይዞ ቁልቁል ይመለከተዋል፡፡ አዎ፣ ትዝ አለው፡፡ ታስሮ ነበር፡፡ ተዘቅዝቆ ሲገረፍ ነበር፡፡ ዘቅዝቀው ሰቅለውት ጥለውት
ሄደው ነበር፡፡ አዎ፣ ትዝ አለው፡፡ ያ ሁሉ ስቃይ፡፡ አሁን ወርዷል፡፡ መሬት ላይ ተዘርሯል፡፡ ውኃ እየደፉበት ነበር፤ ዝናብ አይደለም
ማለት ነው፡፡ ድጋሚ ሊጠይቁኝ ነው የመጡት ብሎ አሰበ፤ ምን ሊላቸው ነው?
‹‹ተነስ!›› አለው ፖሊሱ፡፡
መነሳት አልቻለም፡፡ እጁን ዘረጋለት፡፡ ‹‹እንኳን ደስ አለህ፤ ነጻ መሆንህ
ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህ ከሁለት ቀን በኋላ ትለቀቃለህ›› አለው፡፡ ‹‹እንደዚያ ካሰቃያችሁኝ በኋላ…?›› ብሎ መጠየቅ አልቻለም፡፡
ፈርቷቸዋል፡፡ ለሁለት ቀናት እንዲያገግም እዚያው ‹‹ማረሚያ›› ቤት ውስጥ አቆዩትና ነጻ ወጣ፡፡ ‹‹አገሪቷን ለቅቄ መጥፋት››
አለብኝ እያለ ነው በልቡ፤ ሁሉንም ነገር በጥርጣሬና በፍርሐት እየተመለከተ ነው፡፡ ነጻ መውጣቱን እንኳ ማመን አልቻለም፡፡ ምናልባት
ቅዠት ቢሆንስ?!
ሁለት፣ ሦስት እያለ አንድ ሳምንት ሞላው፡፡ መረጋጋት ጀመረ፡፡ ገጠመኙን
ለማንም መናገር አልፈለገም፡፡ የገዛ ጥላውን ሳይቀር እየተጠራጠረ ነው፡፡
ብዙ ነገር አሰኘው፡፡ እንደሰው መሳቅ፣ መጫወት፣ በቀን ክፉ ያቋረጠውን
ኑሮ መቀጠል አማረው፡፡ ከቤቱ ወጥቶ መንገዱ ይዞ ዝም ብሎ ይጓዝ ጀመር፡፡ በጠንካራ ሐሳብ የታጀበ መንገድ፡፡ እመንገዱ ላይ ያገኘው
አንድ ኢንተርኔት ካፌ ዘው ብሎ ገባ፡፡ ኢሜይሉን ከፈተው፡፡ ምንም ያላነበበው ኢሜይል የለም፡፡
‹‹እንዴ?...›› አለ ለራሱ፡፡
የመጨረሻው ኢሜይል ከቀድሞው የሥራ ባልደረባው እሱ የታሰረ ዕለት የተላከ
ነበር፡፡ አላነበበውም፤ ግን የተነበቡ ኢሜይሎች ውስጥ ተቀምጧል፡፡ ትዝ ሲለው የኢሜይል አድራሻውን እና የይለፍ ቃሉን ለኮማንደሩ
ተናግሮ ነበር፡፡ ‹አንብበውታል ማለት ነው› አለ፤ የሥራ ባልደረባው የፌስቡክ ፖለቲከኛ ስለነበር በዚያ ጉዳይ አይስማሙም ነበር
- በእሱ ጉዳይ ይሆን ያሰሩኝ ብሎ ጠረጠረ፤ ነገር ግን ከሱጋ የነበራቸው ግንኙነት የሩቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደውጭ አገር ሄዶ
ነው እየተባለ ቢወራም በድንገት ከሥራ ቀርቶ መልቀቁን ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ እንዲያውም ወደውጭ አገር መሄዱን ሲሰማ ‹‹ለካስ
ፌስቡክ ላይ ፖለቲካ የሚጽፈው ጥገኝነት ለመለመኛ ነው?›› ብሎ ነበር፡፡ ምን ብሎ ጽፎልኝ ይሆን ብሎ ቢያስብም መክፈት ግን አስፈራው፡፡
ፖሊሶቹን መልሶ እንደመጥራት አስፈራው፡፡
ብዙም አላስቻለውም፤ ብዙ ካመነታ በኋላ መልሶ ኢሜይሉን ከፈተው፡፡ እንዲህ
ይነበባል፡-
‹‹አሁን ለምጽፍልህ ነገር ይቅርታ እንድታደርግልኝ እለምንሃለሁ፡፡ ሆኖም፣
ነፍሴን ለማትረፍ ከዚያ ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ፖሊስ በማላውቀው ነገር ይዞ ሲያሰቃየኝ ነበር የከረመው፡፡ አብረውህ የሚሠሩትን
አጋልጥ እያሉ ሲቀጠቅጡኝ እና ምስጢር ካወጣሁ እንደሚለቁኝ ቃል ሲገቡልኝ፥ አንተንና ሌሎችም ስማቸው የመጡልኝን የሥራ ባልደረቦቼን
እና ጓደኞቼን ስም ዘርዝሬ ነገርኳቸው፡፡… ከለቀቁኝ በኋላ በሌላ ስቃይ ድንበር አሳብሬ ጎረቤት አገር ገብቻለሁ፡፡ አሁን የምመክርህ
ነገር፣ ማቄን ጨርቄን ሳትል አገር ለቀህ እንድትወጣ ነው፡፡ አለበለዚያ አንተንም ይይዙህና ምንም የማያቁ ሰዎችን ስትጠቁም… ተጠቋቁመን
ማለቃችን ነው…››
ያነበበውን ማመን አቃተው!
----
ይህ አጭር ልቦለድ የተጻፈው ዛሬ በተለቀቀው የሰብኣዊ መብቶች ታዛቢ
የማዕከላዊ ፖሊስ
ጣብያ የማሰቃየት ተግባር ማጋለጫ ሪፖርት ላይ በወጡ ሐሳቦች ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment