Pages

Saturday, June 23, 2012

Hookah እና አሜሪካ

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ ‹‹የኛ ሰው በአሜሪካ›› የሚል ርዕስ ልሰጠው ፈልጌ ነበር፡፡ ችግሩ ይሄ ርዕስ አሜሪካንን ረግጠው በተመለሱ ሰዎች ስለተለመደ ባይተዋርነት ተስማምቶኝ ተውኩት፤ በሌላ በኩል የየኛ ሰው በአሜሪካ ኑሮ በሁካ ብቻ አይገለፅም የሚል ርህራሄም ተሰምቶኛል፡፡

ሁካ - የሺሻ አሜሪካዊ ስሟ ነው፡፡ አዲስ ጋይድ የምትባል፣ በቀለም የተንቆጠቆጠች፣ ዲዛይኗ እና ጠረኗ ያማረ፣ ጽሁፎቿ ዋዘኛ፣ ዳያስፖራውን ኢላማ ያደረገች መጽሄት በአጋጣሚ እጄ ገብታ ሳገለባብጣት ማስታወቂያ እንደሚበዛባት አስተውያለሁ፡፡

ካየሁዋቸው ማስታወቂያዎች ውስጥ - በተለይም የአበሻ ካፌና ሬስቶራንቶቹ ማስታወቂያዎች ከዘጠኙ ስምንቱ ሁካን በስዕል ወይም በጽሁፍ አስተዋውቀዋል፡፡

የሁካ ማጨሻዋ እቃ በወርቃማ ቀለም የተንቆጠቆጠ፣ ዙሪያው በአረቢያል መጅሪስ የደመቀ፣ አፋቸው ላይ ጡሩምባ መሳይ የሁካውን ጫፍ የሰኩ ወይም እንደፈላ ጀበና ከአፋቸው ጢስ ቡልቅ፣ ቡልቅ የሚያደርጉ ሴቶች፣ ወዘተ፣ ወዘተ ለቁርስ ቤቶቹ ማስታወቂያ ሳይቀር ፍጆታ ሁነዋል፡፡

‹‹የኛ ሰዎች በአሜሪካ›› ታሰቡኝ!
ዘመድ ጥየቃ፣ ወይም ሚስት/ባል ፍለጋ፣ ወይም የቆጠቡትን አጥፍተው ለመመለስ የሚሄዱ ዳያስፖራዎች ‹‹የለመለመ ጫት ናፍቆኛል!›› የሚሏት ነገር ትዝ አለችኝ፡፡ የአገራችን ሰው ጫት መቃምን ዘመነኝነት ካደረገው ሰነባብቷል፡፡ ለጫት ግድ የለውም የሚባለው ሰው እንኳን ቅዳሜ እና እሁድን ማሳለፊያው ጫት ነው፡፡ እንዲያውም ‹‹ትልልቆቹ››፣ በየሳምነቱ የሥራ ቀናት ‹‹ቢዚ›› የሆኑት ሰዎች እሁድ እሁድ ‹‹ዛፍ ላይ እንውጣ›› እየተባባሉ ነው የሚጠራሩት፡፡ (ባለፈው ሰሞን የኛ ፕሬስ የተባለ ጋዜጣ ‹‹አርቲስቱ ከጓደኞቹ ጋር ጫት ለመቃም በየቀኑ አንድሺህ ብር ያወጣል›› ብሎ ያወራት ወሬ ስንት ፍልስምና አፈላስማኛለች መሰላችሁ? ስንት ሰው በአንድ ሺህ ብር በወር ስንት ቤተሰብ ለማስተዳደር አስማት በሚሰራባት አገር ውስጥ ‹‹አርቲስቱ›› በቀን አንድ ሺህ ብር ለጫት - ‹አጀብ!› አያሰኝም?)

የእንጦጦ ጎዳናዎች ዳርቻ ላይ ተኮልኩለው የሚቆሙ መኪኖች - ውስጣቸው ዙርባ ጫት ዙሪያ የሰፈሩ ባለጠጎች አሉባቸው፡፡ ፒያሣ ከማሕሙድ ሙዚቃ ቤት ወደ ሰይጣን ቤት ቁልቁል ባንኮ ዲሮማ ተደግፈው ሲወርዱ የሚያገኟቸው መኪኖችም የሚቆሙት ይህንኑ ጉዳይ ለማስፈጸም ነው፡፡ ሌላም፣ ሌላም ቦታ! በጫት ምርቃና የተጻፉ ፖለቲካዊ ትንታኔዎች በየጋዜጦቹ፣ በጫት ምርቃና የሚቀርቡ ፕሮግራሞች በየኤፍ ኤም ሬዲዮዎቹ፣ በጫት ምርቃና የሚወጡ ፖለሲዎች በየቤተመንግስቱ (ይቅርታ በቤተ መንግስቱ)፣ በጫት ምርቃና….?

ቢሆንም ግን ይሄ የአገርቤት አመል ውቅያኖስ ያቋርጣል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን እውነታው የእኛ ሰው - አገር አቋርጦ ሲሄድ ለሱሳሱስ ዕውቅና ከመስጠት የተሻገረ ስልጣኔ እንደማያገባው - ሬስቶራንቶችን በምግብ ምስል ከማስተዋወቅ ይልቅ - በሁካ ማጨሻ ጋን ማስተዋወቅ - እንደማሕበረሰብ ዋጋ የምንሰጠውን ነገር ግን እያስታወሰ የሚያስተዛዝበን ነገር ነው፡፡

እኔ እዚህ ቁጭ ብዬ ሳስበው በቅድሚያ የሚያቃጭልብኝ የዳያስፖራ ፖለቲካ ነው፡፡ በአገርቤት ያሉ አርቲስቶች በምርቃ የሚጽፉት ድርሰት እና ፊልም - መጀመሪያ ላይ ዋና ገጸ ባሕሪው የሚጠራበት ስም ተረስቶ መጨረሻ ላይ ሌላ ሲሆን ገጥሞኝ ያውቃል፡፡ አሁንም በሁካ ቤት ምክር የተመሰረቱ የዳያስፖራ ፓርቲዎች አገራችንን…… (እናንተ ጨርሱልኝ!)

---
ይሄ ጽሁፍ ከደሙ ነፃ የሆኑ ዳያስፖራዎችን አይመለከትም፡፡

1 comment:

  1. ...በሁካ ፖሊሲ ያውኳታል፡፡ ብዬ ጨረስኩልህ ፡)
    naodlive

    ReplyDelete