ጨርቆስና ቦሌን ምን አገናኛቸው? በርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም ጨርቆስና ቦሌ ተለያይተው አያውቁም - በቀልድም በድንበርም፡፡ በኑሮ መቀለድ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የኑሮአችን አካል ነው፡፡ የጨርቆስ እና የቦሌ ጉርብትናም በኢትዮጵያ እየሰፋ ለመጣው የኑሮ ደረጃ ልዩነት በርካታ አዳዲስ ቀልዶችን አበርክቷል፡፡ ምንም እንኳን የጫወታዬ ዓላማ ቀልዶቹን ለአደባባይ ማብቃት ባይሆንም አንድ ስሜቴን የነካ ቀልድ ግን ሳላስታውስ ማለፍ አይቻለኝም፡፡ ቀልዱ የተነገረው ወንድማማቾቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ መንግስታችን በወቅቱ ‹‹ፈንጂ ማክሸፊያ›› ወጣቶች ያስፈልጉት ነበርና‹ወዶ ዘማች› የሚለው ቃል ወረት ሆኖ ነበር፡፡ እናም የሃገራቸው መወረር ያስቆጣቸው የቦሌ ልጆች ገንዘብ አዋጥተው ለጨርቆስ ሰፈር ‹ወዶ ዘማቾች› ደሞዝ እንዲከፈል አበረከቱ ተብሎ ተቀለደ፡፡
ከዚህ ቀልድ በኋላ ግን አንድ ጥያቄ በጭንቅላቴ ሲጉላላ ከረመ፡፡ ‹‹የሃብታምና የድሃ ሕይወት የዋጋ ልዩነት ስንት ነው?››