ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም በአንድ ወቅት በፈፀሙት ድርጊት ተፀፅተው ይቅርታ ይጠይቁ እንደሁ በገነት ‹ማስታወሻ› ላይ ሲጠየቁ ‹‹ማንን ነው ይቅርታ የምጠይቀው? ወያኔን? ወያኔ እኔን ይቅርታ ጠይቆኛል?...ይህ የታገልንለትን ጉዳይ አለማወቅ ነው›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡ መንግስቱ በአስተዳደራቸው ማክተሚያ ሰሞንም፣ በመንግስት መገናኛ ብዙሐን እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ለአገሬና ለወገኔ ይበጃል ብዬ ባደረግኩትና በተሳተፍኩባቸው ተግባሮች ሁሉ በግሌ ሕሊናዬን የሚወቅሰኝ ነገር የለም›› ብለዋል፡፡
‹‹መ››ንግስቱ እና ‹‹መ››ለስ
መንግስቱና መለስ እያደር የሚያመሳስላቸው ነገር ተበራክቷል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹የነጋሶ መንገድ›› በተሰኘው ግለታሪካቸው እንደነገሩን የሕወሓት ተገንጣይ ቡድን ተሸንፎ ሲወጣ የነመለስ ቡድን (በተለይ አቶ መለስ) ‹‹ጃኬታቸውን አስወልቀን ሸኘናቸው›› እያሉ ሲፎክሩ ነጋሶ መለስን ‹‹መንግስቱን፣ መንግስቱን መሰልከኝ›› ብለዋቸዋል፡፡ እውነት ነው፤ (መ)ንግስቱና (መ)ለስ (መ)ንትያ ናቸው፡፡ እስኪ በዝርዝር እንመልከተው…