Pages

Saturday, August 6, 2011

ለመደገፍ መደገፍ፤ ለመቃወም መቃወም

ቲፎዞነት የጋርዮሽ ስርዓትን ይመስለኛል፡፡ ሰዎች በቡድን ሆነው አንድን ነገር ብቻ በፍጹም ልቦና ለመደገፍ የመቁርባቸው ነገር - ካሰቡት ያስቃል፡፡ ሰዉ ሁሉ በየፊናው የሚደግፈው የእግር ኳስ ቡድን፣ የፖለቲካ ቡድን፣ የሃይማኖት ቡድን፣ የፆታ ቡድን ራሱ ሳይቀር ያበጃል፡፡
ማንቸስተር ዩናይትድ (ብልጫ አወዛጋቢ ቢሆንም) በጨዋታ ብልጫ አርሴናልን ቢረታ እንኳን የአርሴናል ደጋፊዎች ‹‹በጨዋታ በልጠናል›› ብለው መሟገታቸው፣ ወይም ደግሞ የቡና ደጋፊዎች ‹‹ጊዮርጊስ ከፍሏል›› ማለታቸውን አያቆሙም፡፡

የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ኢሕአዴግ የፈለገውን ያክል የሚያስቀይም አዋጅ ቢያወጣና ርምጃ ቢወስድ ‹‹ትክክል ነው›› ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ከመሟገት አይመለሱም፡፡ የተቃዋሚዎቹም ቡድን እንዲያው ነው፡፡ በእያንዳንዷ የገዢው ፓርቲ ርምጃ ላይ የትችት እና ተቃውሞ በትራቸውን ከማሳረፍ አይመለሱም፡፡ (እሺ - አንመለሰም ካላልኩኝ ራሴን ማፅደቄ ነው፡፡) ከቡድኖቹ ቁማር ጀርባ ያለችውን ሃገር ማሰብም ያስፈልጋል::የሃይማኖተኞች ቡድንም ከዚህ የተለየ አመለካከት የላቸውም፡፡ የእነርሱ እምነት ብቸኛውና ከፈጣሪ የሚያቆራኝ ሁነኛ መንገድ ሲሆን የሌሎቹ ግን የጥፋት መንገድ ነው፡፡ እመኑኝ እናንተ ስላመናችሁት ብቻ ሃይማኖታችሁ ፍፁምና እውነተኛ አይደለም፡፡ እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ በየገዛ ሃይማኖታችሁ እና እምነታችሁ የቀኖና ልዩነትና መከፋፈል ባለተፈታተናችሁ - ነበር!

የፆታ ቡድንም አለ፡፡ ‹‹የፆታ ጋርዮሽ›› እያልኩ እጠራዋለሁ፡፡ ሴቷ ለሴቷ፣ ወንዱ ለወንዱ እየተቧደኑ ‹‹ሴቶች እኮ፤ ወንዶች እኮ›› እየተባባሉ መወነጃጀል በሽ፣ በሽ ነው፡፡

እና ምን ይጠበስ?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ የጋርዮሽ ስርዓት (ቡድነኝነት) ያልሰለጠነ ሕዝብ መለያ ነው፡፡ በርግጥ ሰዎች በተናጥል የማይችሉትን ችግር ለመቅረፍ (ሥራ ለመሥራት) ይቧደኑ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንድ አሳብ አይሆኑም፡፡

ስለዚህ?
ስለዚህ መደገፍ ወይም መቃወም ያለብን ቡድኑን ሳይሆን የቡድኑን ሐሳብ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ እዚህጋ ለመናገር የፈለግኩት ተቀልብሶ ከፓርቲ ሕልውና አስፈላጊነትጋ የሚቃረን ነገር እንዳልተናገርኩ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ሆኖም ሁልጊዜ በቡድናችን ውስጥ እውነትና ትክክለኛነት ብቻ እንዳለ ማመን ገደል ይሰዳል፡፡ መቧደናችን ካልቀረ በቡድኑ ውስጥ ያለው ችግር ላንዳችን ካልታየ፣ ለሌላችን ሊታየን ይገባል፡፡

ርቀን ሳንጓዝ በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኦባማ አሜሪካን ከብድር ቀውስ ለማውጣት እና ቀደም ሲልም የጤና ዋስትናን በተመለከተ ያቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች በበርካታ የገዛ ፓርቲያቸው አባላት (ዴሞክራቶች) ተቃውሞ ገጥሞት - ተፈትኗል፡፡ በመጨረሻ ቢያልፍም፡፡

(እነሱ ስለሰለጠኑ፤) እኛና አሜሪካን አወዳደርክ አትበሉኝና በእኛ ፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን ምክረ ሐሳቦች ለመቃወም የሚዘረጉ የኢሕአዴግ አባላት እጆችን አይተን እናውቃለን? ይሄ የጋርዮሽ (የቡድነኝነት) አስተሳሰብ ነው፡፡ ለመደገፍ ሲሉ ብቻ መደገፍ፡፡

በመጨረሻም
ኢትዮጵያዊ ሆይ፤ የምትደግፈው አካል ሐሳብ ሁሉ እውነት/ጠቃሚ አይደለም፡፡ የምትቃወመው አካል ሐሰብ በሙሉ ሐሰት/ጎጂ አይደለም፡፡ እውነቱ ሁሌም ተቃራኒ ሐሳብ የመኖሩ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment