Pages

Monday, May 30, 2011

ከአሜን ወዲህና ከአሜን ወዲያ ማዶ

በአገራችን ሰው ተመርቆ ሲያበቃ ዝም ማለት የለበትም - ‹‹ከአሜን ይቀራል!›› ይባላል፡፡ አሜን በፀጋ መቀበል፣ ይሁንልኝ፣ ይደረግልኝ እንደማለት ነው፡፡ ይሄ የዓለማችን ዕውቅ ደራሲዎች ‹አዎንታዊ አስተሳሰብ› ወይም ‹ተስፈኝነት› (optimism) የሚሉት ዓይነት እሳቤ ነው፡፡ ሰሞኑን ‹ተኣምራዊው ኃይል› በሚል የተተረጎመውን የርሆንዳ ባይርኔን መጽሃፍ እያነበብኩ ነበር፡፡ የአዎንታዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ነች፡፡ እኔም የአዎንታዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ ነኝ ባይ ነኝ፤ ሰዎች ግን ብዙ ብሶት ሳወራ ስለሚሰሙ ከአሉታዊዎች ተርታ ያሰልፉኛል፡፡ ለዚያ ነው ዛሬ የ‹አሉታዊ አስተሳሰብ› ወይመ ‹ጨለምተኝነት› (pessimism) አቀንቃኝ ሁኜ ልሟገት የተነሳሁት፡፡

Pessimism ስሙ አያምርም፤ ጨለምተኝነት ነው፡፡ ነገር ግን የስሙን ያህል ክፉ ነው ወይ? ዓለማችንንስ ያቀኗት እውን አዎንታዊ አሳቢዎች (optimists) ብቻ ናቸው? የሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡ አዎንታዊ አሳቢዎች(optimists) ስለ አሉታዊ አሳቢዎች (pessimists) ያላቸው አመለካከት ራሱ ጨለምተኛ (pessimist) ነው፡፡ የአሉታዊ አሳቢዎች ድርሻ በአዎንታዊ አሳቢዎች እይታ አፈር ድሜውን በልቷል፤ እየበላ ነው፡፡

በአንድ አስቂኝ አባባል እንጀምር፡-

"ጨለምተኛ (pessismist) ማለት በባለ አንድ አቅጣጫ መንገድ ላይ ግራ ቀኙን አይቶ የሚሻገር ሰው ነው፡፡"
በአባባሉ የተገለፀው አሉታዊ አሳቢ ያጠፋው ጥፋት ምንድን ነው? ያልታሰበ አደጋ ቢመጣስ በሚል መስጋቱ አይደለም? ‹ዕውቀት ያጠፋሃል፥ ጥንቃቄ ይከልልሃል› ይል የለም እንዴ መጽሃፉስ ቢሆን? ይሄ በአዎንታዊ አሳቢዎች ዘንድ በምናባዊ ችግር ላይ የተመሰረተ ስጋት ነው፤ ሰውየውን ከጉዞው ያደናቅፈዋል አንጂ አይጠቅመውም! በመሰረቱ የአሉታዊ እና አዎንታዊ አሳቢዎች፣ ሁለቱም ምናባውያን ናቸው፤ አንደኛቸው በምናባዊ ስጋት ሲወጠሩ ሌላኛቸው ምናባዊ ስኬትን ያልማሉ፡፡ እርግጠኛ በማይሆኑበት መጪ ጊዜ አንደኛቸው ሲፈሩ ሌላኛቸው ይደሰታሉ፡፡

አሁን ስሙ ማነው ብላችሁ እንድታስጨንቁኝ የማልፈልገው የTIME መጽሄት ጸሃፊ ‹‹አሜሪካውያንን ልዕለ ኃያል እንደሆኑ ለምዕተ ዓመት ያክል እንዲዘልቁ ያደረጋቸው ስጋታቸው ነው፡፡›› ሲል ጽፏል፡፡ ‹የምን ስጋት?› ያላችሁ እንደሆን፤ አሜሪካውያንን ሌት ተቀን የሚያባንናቸው ‹‹ልዕለ ኃያልነታችንን ተቀማን፣ አልተቀማን›› የሚለው ስጋት ነው - አሜሪካውያንን ሁሌም ቁንጮ የሚያደርጋቸው፡፡

የTIME መጽሄት ጸሃፊ ከሌላ ባልደረባው ጋር በአመክንዮ በተሟገተበት በዚህ ጽሁፉ፥ ባልደረባው ‹‹አሜሪካ እያሽቆለቆለች ነው›› ብሎ ዕልፍ ማስረጃ ሲያቀርብ እሱ ግን ‹‹የለም አሜሪካ አሁንም ቁጥር አንድ ናት፤ እንዲያውም የአሜሪካ ኃያልነት ከአሁን፥ አሁን አበቃለት የሚለው ስጋት ነው አንደኝነቷን እንደጠበቀች የሚያኖራት›› ሲል ተሟግቷል፡፡

እነዚህን ሁለት ጋዜጠኞ ስንመዝናቸው አንዱ ተስፈኛ (optimist)፣ ሌላኛው ጨለምተኛ (pessimist) ሁነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሆኖም ተስፈኛው ተስፋውን የጣለው በጨለምተኞች ስጋት ላይ ነው፡፡ ይሄ ስጋት፣ ይሄ አሉታዊ አሳብ ባይኖር ኖሮ አሜሪካ - አሜሪካ አትሆም ነበር ነው የሚለን፡፡ እንግዲህ ተስፈኞ የማነቃቃት (motivation) ሥራ ይሰራሉ፤ ለውጡን የሚያመጡት ወይም የሚጠብቁት ግን ከጨለምተኞቹ ነው፡፡

ጨለምተኞቹ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢመጣስ ብለው ይሰጋሉ፣ ተስፈኞች የመሬት መንቀጥቀጥን መቋቋም የሚያስችል መንገድ ይኖራል ብለው ተስፋ ይሰጧቸዋል፡፡ ጨለምተኞቹ እውን ያደርጉታል፤ ምክንያቱም ስጋቱ ዕረፍት አይሰጣቸውም፡፡

ጨለምተኞች ወደፊት የሕይወት ዋስትና ባጣስ በሚለው ሐሳብ ዕረፍት ያጣሉ፤ ተስፈኞች ለወደፊቱ ዋስትና የሚሆን ሃብት ማካበት እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል፡፡ ጨለምጸኞቹ ሃብቱን ይፈጥሩታል፡፡ በዚህም አለ በዚያ የለውጡ አማጪዎች ጨለምተኞቹ ሲሆኑ የቅስቀሳውንና የሙገሳውን ድርሻ የሚወስዱት ግን ተስፈኞቹ ናቸው፡፡

የተስፈኞቹ ዓለም ምናባዊነቱ ሲጋነን ቅጥ ያጣል፡፡ የርሆንዳ መጽሃፎች The Secret እና The Power ሁለቱም ማጭበርበር ይቀናቸዋል:: ‹‹ከጥንቆላ ተለይተው አይታዩም›› የሚሉም አሉ፡፡ እውነቱን ለመነጋገር በነዚህ መጽሃፎች የከበረ ሰው ካለ ደራሲዋ እና ተርጓሚዎቹ ናቸው፡፡

ደራሲዋ በሁለቱም መጻህፍትዋ የምትናገረው ስለምትሃታዊ ሐሳቦች ነው፡፡ በመጀመሪያው መጽሃፏ ላይ ምስጢሩ ያለችው የስበት ሕግም ሆነ፥ በሁለተኛው ላይ ታላቁ ኃይል ያለችው ፍቅር ሁለቱም ስሜትን ከመቀስቀስ ባሻገር ለውጡን የማምጣት አቅም የላቸውም፡፡ ሰባት ቢሊዮን ሰው በሚኖርባት ዓለም ፥ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችን አስደናቂ ገጠመኞች በማጣቀስ በምትሃታዊ ሐሳቦች ስኬታማ መሆን ይችላል ማለት ‹ሳያይ በሚያምነው› የዋህ ሕዝብ መሳለቅ ነው፡፡ በዚህም ደራሲዋ ብዙዎች በምኞት እየተብሰከሰኩ ኑሯቸውን እንዲገፉ አድርጋለች፡፡

በዕውቀቱ ስዩም ገና ከጅምሩ በአወዛጋቢነቱ አቻ ያልተገኘለትን ‹‹ከአሜን ባሻገር›› የተሰኘ አምድ በአዲስ ጉዳይ መጽሄት ላይ ከፍቷል፡፡ የአምዱ ዓላማ ‹ዝም ብለሽ ተቀበይ የሰጡሽን ብቻ› የተሰኘውን ባሕላችንን መተቸት ይመስላል፡፡

በዕውቀቱ እውነት አለው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የውሃ ቧንቧችን ጠብታ ሲነፍገን፣ መብራት ሲቋረጥብን፣ ስልካችን ኔትወርክ ሲቸግረው - ‹‹ውይ ውሃ የለችም፣ ውይ መብራቱ ጠፋ፣ አይ ኔትወርክ የለም›› ብለን፣ ‹‹አሜን›› ብለን መቀበል ይቀናናል፡፡ ግብር እና ታሪፍ እየከፈልን የምናስተዳድራቸው መስሪያቤቶች ባሻቸው ሰዐት እያገለገሉን፣ ባሻቸው ሰዐት አገልግሎቱን ሲነፍጉን ‹‹እንዴት ይሆናል?›› የሚል እምቢተኝነት ቢኖረን ኖሮ ነገሮች ከድጥ ወደማጡ እየሄዱብን አንቸገርም ነበር፡፡ ገዢዎቻችን ያሻቸውን ሲያደርጉን አሜን ብለን በመቀበል ፈንታ ‹‹ዋ!›› ብንላቸው ኖሮ፥ ‹‹ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ›› አይሉንም ነበር፡፡ ‹‹ከአሜን ይቀራል›› የሚለው ተረት ሁልቀን አይሰራም፡፡

ከዚያም በላይ የሚያሳፍረው ግን የተወሰደብን ውሃ፣ መብራትና ኔትወርክ ተመልሶ ሲመጣ፥ ‹‹እሰይ (አሜን)›› ብለን ውለታ የተዋለልን ያክል በደስታ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታችን ነው፡፡

ባለው የሚደሰት - optimist - ያለው ይበቃዋል፤ ባለው የማይረካ፣ የማያንቀላፋ ጥም ያለው - pessimist - ደግሞ ለውጥና መሻሻል ይፈልጋል፤ ያመጣዋልም፡፡ የሰለጠኑት እና ያልሰለጠኑት ዓለማት ልዩነትም ይሄው ነው፡፡ ከባሕር ወዲህ ብዙ ‹አሜን› አለ፤ ከባሕር ማዶ ጥቂት ‹አሜን› አለ፡፡ ‹አሜን› የማይሉት አሜን እስከሚሉ ይጨመርላቸዋል፡፡

እንደ optimist ይሆናል፣ ይሳካልኛል ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ እንደ pessimist ግን በዚህች እንቅፋት በበዛባት ዓለም ላይ ባይሆንስ፣ እንቅፋት ቢገጥመኝስ ብሎ ማሰብ እንቅፋቱን ለመጋፈጥ የሚያስችል አቅም ከወዲሁ ለማበጀት ይረዳል፡፡

Be optimist about pessimism.

No comments:

Post a Comment