Sunday, July 22, 2012

የእንቆቅልሹ እንቆቅልሾች


ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ሲሞቱ፣ መኳንንቱ ለሕዝቡ የ‹እምዬ›ን ሞት ለማርዳት ፈርተው ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊስ ዳግማዊው ‹ዳግማዊ-ምኒልክ› ለመሆን በቅተው ይሆን እንዴ? ይህቺን ጽሁፍ እስካሰናዳሁባት ሰዓት ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው፣ በጠና ታመዋል እና ሞተዋል የሚሉ ‹‹ታማኝ ምንጮች›› ከየአቅጣጫው እየፈለቁ ነው፡፡ እውነታውን ምሎ የሚናገር ሕዝብ ወይም የሕዝብ አባል ግን የለንም፤ ጉዳዩ በእንቆቅልሽ የተሞላ ነው፡፡

አሁን፣ አሁን ገዢው ፓርቲ የራሱ ዋሾነት ሳያንሰው የአማራጭ መረጃ ምንጮችን ታማኝነት እስከወዲያኛው ለማድረቅ ሆነ ብሎ የሚጫወተው ‹ጌም› ያለ እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ በ‹‹ታማኝ ምንጮች›› በኩል የሐሰት መረጃዎችን ማፍሰስ፣ በጣም እስኪናፈሱ መጠበቅ፣ ወሬዎቹን በከፊል የሚያረጋግጡ መግለጫዎችን መስጠት፣ መጨረሻ ላይ ግን ወሬዎቹ በሙሉ ‹‹ከአሉባልታ›› ያልበለጡ መሆናቸውን አረጋግጦ የዜና ምንጮቹን ተአማኒነት መግደል፡፡ ለኔ፣ መለስ ቢያንስ በቅርቡ ወደቢሯቸው መመለስ ከቻሉ ተናፋሽ ወሬዎችን ለማመን ይሄ የመጨረሻዬ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት የዚህ እንቆቅልሽ እነቆቅልሾች ስለሆኑት ነገሮች ትንሽ ልበል፡፡

Tuesday, July 10, 2012

እውነቱ እና ፍርሃቱ


የፍራቻ ፖለቲካ እና የፖለቲካ ፍራቻ - ጥንድ በኢትዮጵያ መሪዎችና ሕዝቦች መሀል የተጋረጡ የጦር መሳሪያዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡ ካልፈራ ፖለቲከኞቹ የፍራቻ ፖለቲካ ይጫወታሉ፣ ፖለቲከኞቹ የፍራቻ ፖለቲካ ካልተጫወቱ ሕዝቡ ፖለቲካን ይፈራል፡፡ የሁለቱም ውጤት አንድ ነው፤ ውጤቱም ሕዝቡ መሪዎቹን የሚያስከፋ ነገር መናገርም ሆነ መተግበር ይፈራል፡፡

የፍራቻ ፖለቲካ፤ በገዢው እና ተቃዋሚዎቹ
ጥንት፣ ወትሮም ንጉሥ የማይከሰስ በመሆኑ መንግስታት ሕዝቦቻቸውን ማስፈራራታቸው የደንብ ያህል ነበር፡፡ ‹‹የተማረ ይምራን›› መባል ከተጀመረበት እና ደርግ የንጉሡን መንበር ከተረከበበት ጊዜ ወዲህም ግን ‹‹ደንቡ›› አልቆመም፡፡ ደርግ ‹‹አብዮቱን›› ሊቀለብሱ የሚንቀሳቀሱትን በሙሉ እንደማይምራቸው በሕዝብ ፊት ምሎ ዘመተባቸው፡፡ አብዮቱን ከሚቀለብሱት እንዳንዱ ላለመሆን የፈራ በሙሉ የኢሠፓ አባል ሆኖ በወንድሙ ላይ ዘመተ፡፡ ቀሪው ‹‹መሀል መስፈር›› የፈለገውም፣ ከፍራቻው’ጋ እንደተሟገተ 17 ዓመታት ኖረ፡፡

ኢሕአዴግ ቀርቶ የፍራቻ ፖለቲካ የቀረ ከመሰለ በኋላ ግን መልኩን ቀይሮ መጣ፡፡ አብዮቱን መቀልበስ፣ ሕገመንግስቱን መቀልበስ በሚል ተተካ፡፡ መንግስት የተቃወመውን ሁሉ በሆነ ስም በመፈረጅ ስለሚወነጅል፣ ላለመፈረጅ የሚሰጋው ሁሉ ወደወጣበት ምሽግ ተመልሶ ገባ፡፡ ‹‹ፖለቲካ እና ኮረንቲ›› የሚለው አባባል የተፈጠረው ያኔ ነው፡፡

የፍራቻ ፖለቲካን፣ ኢሕአዴግ በሌላም አካሔድ ይጫወትበታል፡፡ እንደገዢው ፓርቲ ዲስኩር ከሆነ፣ ኢሕአዴግ ከወረደ ወይም ተቃዋሚዎች ወደስልጣን ከወጡ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ/ነፃነት ተዳፍኖ ይቀራል፣ የሃይማኖቶች እኩልነት አደጋ ላይ ይወድቃል፣ ልማቱ ይደናቀፋል… ወዘተ፣ ወዘተ፡፡

Wednesday, July 4, 2012

የባለፀጋዋን አገር ዜጋ፤ አቶ ድህነትን እናስተዋውቅዎ


ከዕለታት አንድ ቀን ከምሣ መልስ ቡና የምጠጣበት ካፌ ተሰይሜያለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአዲስ አበባ መስተዳደር ፕሮግራም ይተላለፋል፡፡ ፕሮግራም አቅራቢያዋ በእኛ ቲቪ ያልተለመደ ዓይነት ፕሮግራም እያቀረበች ነው፡፡ አንዷ መምህርት ትናገራለች ‹‹ልጆቹ ራሳቸውን ይስታሉ›› አለች፡፡ ልጆቹ ያለቻቸው እሷ የምታስተምርበት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎችን ነው፡፡

‹‹እናነሳቸውና ካፌ ወስደን ውሃ አጠጥተን፣ ዳቦ አብልተን ስንለቃቸው ደህና ይሆናሉ፤›› አለች መምህርቷ፡፡ ‹‹በኋላ ላይ ሲደጋገምብን ጠይቀናቸው- ለካስ የሚወድቁት ምግብ ከበሉ ሁለት ሦስት ቀን እየሆናቸው ነው፡፡››

ያንን ፕሮግራም ተመልክተው ከእንባቸው ጋር ያልታገሉ ሰዎች አልነበሩም፡፡ ሕፃናቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቸቸው የተነጠሉ ሲሆኑ፣ ያልተነጠሉትም ቢሆኑ ቤተሰቦቻቸው በየቀኑ የመመገብ አቅም የሌላቸው ነበሩ፡፡ የኋላ ኋላ በደረሰኝ መረጃ ያንን ፕሮግራም ያቀረበችው ጋዜጠኛ ‹‹በመርዶ ነጋሪነት›› ከአለቆቿ ተግሳፅ ደርሶባታል፡፡

Friday, June 29, 2012

አምስት የኢትዮጵያ ጠላቶች


‹‹ኢትዮጵያ አገሬ›› ከሚለው ሐረግ በቀር በዚህ ዘመን አንገት የሚያስቀና ነገር ማግኘት እየከበደ ነው፡፡ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ፣ ፍቅራችን እየጠወለገ፣ ተስፋችን እየመነመነ.. መጥቷል፡፡ መንስኤው እንደውጤቱ እልፍ ነው፡፡ እኔም እንደወትሮዬ አምስት አጀንዳዎችን አንስቼ አንድነታቸውን የማስደመድምበት ምክረ መጣጥፍ ይዤ ቀርቤያለሁ - እነሆ!

1ኛ
‹‹ገበታ ንጉሥ ነው››
ገበታ እንደንጉሥ የሚቆጠርባት ኢትዮጵያ ገበታን ለማግነን ምክንያት አላት፡፡ የዓለም ስልጣኔ እምብርት የሆነችው ግብጽ ጥንታዊና ዘመናዊ ከተሞቿ የተቆረቆሩት በአባይ ወንዝ ዳርቻ ነው፡፡ ግብጽ ምድሯ ውሃ ባያፈልቅም ከደጇ በሚያልፈው ውሃ ሕዝቦቿን ከረሃብ ለመታደግ ችላለች፡፡ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ምሳር ይቆረጣል›› ነውና ተረቱ ኢትዮጵያ ግን የረሃብ ምሳሌ ነች፡፡ ከሰማይ ዝናብ ዘነበ/አልዘነበ በሚል የምግብ ዋስትናዋን በሚትዮሮሎጂ ዕድል ላይ የጣለችው ኢትዮጵያ የረሃብን ነገር ታውቀዋለች እና ‹‹ገበታ ንጉሥ ነው›› እያለች ብትተርት አይፈረድባትም - ረሃብ አንደኛ ጠላቷ ነውና፡፡

2ኛ
‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም››
ኢትዮጵያውያን አማኞች ናቸው፡፡ ክርስትና ከመፈጠሩ በፊት አክሱም ሃውልትን ያስቆማቸው እምነታቸው ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ በፈጣሪ ፈቃድ እንጂ በሰው ጉልበት ይሆናል ብለው አያምኑም፡፡ ይህንን በርካታ ምሳሌና የኑሮ ዘይቤያቸው ይመሰክራል፡፡ እርግጥ በዘመናዊዋ እና በቀድሞዋ ኢትዮጵያ መካከል ልዩነት ይኖራል ብሎ መጠርጠር መልካም ነው፡፡ እንደምሳሌም ጥንታዊዎቹ የአክሱም ሐውልትን ያቆሙት በትግል እንጂ በዕድል አይደለም፤ ሌላ ምሳሌ፣ ቀደምት የላሊበላ ታሪክ ጸሃፊዎች ላሊበላ የታነፀው እነዚህ ታሪክ ጸሃፊዎች የኢትዮጵያውያንን የእጅ ሥራ ‹‹ታድለው›› እንጂ ‹‹ታግለው›› ያገኙት ስላልመሰላቸው ከነዚያኞቹ እነዚህኞቹ ያንሳሉ - እምነትን በመምረጣቸው ብቻ ሳይሆን መታደልን ቁጭ ብለው በመጠበቃቸው፡፡

‹‹ጠንቋይ መቀለብ›› የተሰኘች አባባል አለች፤ ‹‹ማወቅን›› ትወክላለች፡፡ በአገራችን ‹አዋቂ› የሚለው ቃል ‹ጠንቋይ› ከሚለው እኩል ያገለግላል፡፡ የእጅ ሥራ ባለሙያዎች ጥሩ ስም የላቸውም - ‹‹ቡዳ›› ናቸው፡፡ አሁንም ድረስ በሥራው ግን በቶሎ የተሳካለት ሰው/ነጋዴ ‹‹ምን የተለየ ሥራ ሰርቶ ነው?›› ብሎ ሊማርበት ከሚፈልገው ይልቅ ‹‹አስጠንቁሎ/አስደግሞ ነው›› እያለ የሚያማው ተመልካች ይበዛል፡፡ ከሥራ ይልቅ ምትሃት ዋጋ አለው፡፡ ድህነቱንም ሮጦ ያመለጠ ሰው ግፋ ቢል ‹‹ፈጣሪ ረዳው›› ይባል እንደሆን እንጂ ‹‹ለፍቶ አገኘ›› የሚባልበት ጊዜ እምብዛም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ችግር ላይ ነች - ዜጎቿ ለስኬት አቋራጭ መንገድ ያስሳሉ - አምልኮን ወይም እምነትን የሙጢኝ ብለው ‹‹የቆጡን ሲጠብቁ፣ የብብታቸው››ን ያጣሉ፡፡

3ኛ

Thursday, June 28, 2012

የተመቻቸ ጊዜ መጠበቅ?

ኅወሓትን ለ10 ዓመታት የመሩት አቦይ ስብሃት፣ የመሪነቱን ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈቃዳቸው ካስረከቡ 23 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ለአዲስጉዳይ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ፣ አቦይ ስብሃት ‹‹የኅወሓትም ሆነ የኢሕአዴግ ሕገ-ደንብ አንድ ኃላፊ በስልጣን ላይ የሚቆይበትን ዓመት አይገድብም፡፡…›› ብለው ተናግረዋል፡፡ እውነት ነው፤ እንኳን የፓርቲው የአገሪቱ ሕገ-መንግስትም ለ‹‹ትዕምርትነት›› የሚቀመጠውን ፕሬዚደንት የስልጣን ዘመን ሲገድብ፣ የክልል ፓርላማን እስከመበተን ስልጣን የተቸረውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዘመነ መንግስት አይወስነውም፡፡

ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት ነገር ይወዳል፡፡ ለምሳሌ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 39 ላይ ‹የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል› ብሎ ይጽፍና ‹መገንጠል›ን ምን አመጣው ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች በመፈቃቀር እና በመፈቃቀድ አብረው የሚኖሩት የመለያየት መብት እንዳላቸው ስንነግራቸው ነው›› ብሎ ይከራከራል፡፡ በዚህ ‹‹ሕገ-መንግስታዊ አተረጓጎም›› ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመነ መንግስት አለመገደብን የምመለከተው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ (ወይም የኢሕአዴግ) የስልጣን ዘመን አለመገደቡ፣ አንድ፤ አቦይ ስብሃት እንዳሉት ‹‹…ፕሮግራሙን ማዕከል አድርጎ የጋራ አመራርን እስካረጋገጠ ድረስ…›› ችግር የለውም ለማለት ይመስላል፣ ሁለት፤ የስልጣን ዘመኑ ሳይገደብ በገዛ ፍቃዱ ይለቃል የሚል ተስፋ ይዞ ይሆናል - ልክ እንደመገንጠል/አለመገንጠሉ፡፡ ሦስት፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ቁጭ ባሉበት የሊቀመንበሩ የሥልጣን ዘመን ይወሰን የሚል ጥያቄ ማንሳት ለአባላቱ አስፈርቷቸው ይሆናል፡፡

ስልጣንን መልቀቅ ለምን ያስፈልጋል (101)?

Saturday, June 23, 2012

Hookah እና አሜሪካ


ይህንን ጽሁፍ ለመጻፍ ስነሳ ‹‹የኛ ሰው በአሜሪካ›› የሚል ርዕስ ልሰጠው ፈልጌ ነበር፡፡ ችግሩ ይሄ ርዕስ አሜሪካንን ረግጠው በተመለሱ ሰዎች ስለተለመደ ባይተዋርነት ተስማምቶኝ ተውኩት፤ በሌላ በኩል የየኛ ሰው በአሜሪካ ኑሮ በሁካ ብቻ አይገለፅም የሚል ርህራሄም ተሰምቶኛል፡፡

ሁካ - የሺሻ አሜሪካዊ ስሟ ነው፡፡ አዲስ ጋይድ የምትባል፣ በቀለም የተንቆጠቆጠች፣ ዲዛይኗ እና ጠረኗ ያማረ፣ ጽሁፎቿ ዋዘኛ፣ ዳያስፖራውን ኢላማ ያደረገች መጽሄት በአጋጣሚ እጄ ገብታ ሳገለባብጣት ማስታወቂያ እንደሚበዛባት አስተውያለሁ፡፡

ካየሁዋቸው ማስታወቂያዎች ውስጥ - በተለይም የአበሻ ካፌና ሬስቶራንቶቹ ማስታወቂያዎች ከዘጠኙ ስምንቱ ሁካን በስዕል ወይም በጽሁፍ አስተዋውቀዋል፡፡

የሁካ ማጨሻዋ እቃ በወርቃማ ቀለም የተንቆጠቆጠ፣ ዙሪያው በአረቢያል መጅሪስ የደመቀ፣ አፋቸው ላይ ጡሩምባ መሳይ የሁካውን ጫፍ የሰኩ ወይም እንደፈላ ጀበና ከአፋቸው ጢስ ቡልቅ፣ ቡልቅ የሚያደርጉ ሴቶች፣ ወዘተ፣ ወዘተ ለቁርስ ቤቶቹ ማስታወቂያ ሳይቀር ፍጆታ ሁነዋል፡፡

‹‹የኛ ሰዎች በአሜሪካ›› ታሰቡኝ!

Sunday, June 17, 2012

እነአልበርት አይንስታይን ስለዘንድሮው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ይላሉ?


ስም ያለው ነገር ሁሉ ‹‹ያለ›› ነገር ነው እያለ ከልጆቹ’ጋ ሲሟገት የነበረ አንድ ጦማሪ ወዳጄ፥ ስማቸው ከመቃብር በላይ የዋለላቸው ሰዎችም ስማቸውን የሚጠሩ ሰዎች እስካሉ ድረስ ‹‹የሉም›› ማለት አይቻልም - ምክንያቱም ‹‹አሉ›› ብሏል፡፡ መከራከሪያው ለዚህ ጽሁፍ መንደርደሪያ ግብአትነት ብቁ ስለሆነ ያለምንም ክርክር ተቀብዬዋለሁ፡፡ የጨዋታዬ ርዕሰ ጉዳይ ግን ‹‹ያለ›› እና ‹‹የሌለ›› ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም አንዳንድ ሕያዋን ሰዎች ከተናገሯቸው ሕያው ንግግሮች መካከል እያጣቀሱ የዛሬውን የአገራችንን ፖለቲካ መሄየስ ነው፡፡ በምናባዊ ሳይንስ ሊቁ አልበርት አይንስታይን ብንጀምርስ?

1. አልበርት አይንስታይን
“The world will not be destroyed by those who do evil, but by those who watch them without doing anything.” (ዓለማችን የምትጠፋው ክፉ በሚያደርጉ ሰዎች ሳይሆን ክፉ ሲያደርጉ እያዩ ዝም በሚሏቸው ሰዎች ነው፡፡)

በኢትዮጵያ የፖለቲካ እውነታ በየጓዳው ከመንሾካሾክ እና ከመብሸቅ ባሻገር ይሄ መንግስት (ይሄ ገዢ) ያለእኛ ተገዢነት እና ፈቃደኝነት ሊጨቁነን እንደማይችል ገብቶን የተነጠቅነውን ነፃነት ለማስመለስ የምንሞክር እጅግ ጥቂቶች ነን፡፡ በተለይም ‹‹ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ብዙሐኑን ስላላማከለ አንድ ቀን አገሪቱ ወደማትወጣው ችግር ውስጥ ትገባለች፣ ወዘተ. ወዘተ...›› እያሉ የጋን ውስጥ ትንታኔያቸውን የሚሰጡት ነገር ግን ለጋዜጣ እንኳን ማብራሪያ ለመስጠት ‹‹ስሜ ከተጠቀሰ አይሆንም›› የሚሉ ምሁራን ከአጥፊው ገዢው ፓርቲ ይልቅ - ለጥፋቱ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

Transforming Ethiopia’s Exclusionary Constitution into an Inclusive One

Before introducing my proposal, I would like to explain my motivation for writing this now. One of the outcomes of the National Dialogue o...