የመንግስት
መሥሪያ ቤቶች እጣ ክፍሎቼ እንዳልሆኑ እየተረጋገጠ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን እርሜን ‹ኢሚግሬሽን› ብሄድ ለሦስት
ሰዓታት በግዞት እንደቆየሁ አጫውቻችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ጠዋት ደግሞ የጓደኛዬን ጉዳይ ላስፈጽም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰነድ
ማረጋገጫ ቢሮ ተገኘሁ፡፡ እዚህ እንደከዚህ ቀደሙ አካላዊ ጥቃት ባይደርስብኝም - መንግስታችንን በኪራይ ሰብሳቢነት እንድታዘበው
የሚያደርገኝ ነገር ተከስቷል፡፡
ነገሩ ወዲህ
ነው፡፡ የሰነድ ማረጋገጫ ሥራ የሚባለው ሰነዱን ባለቢሮዎቹ ተኮር ብለው ካዩት በኋላ ማሕተም ይመቱበታል - አለቀ፡፡ ይህ ሥራ የ30
ሰከንድ ሥራ ቢሆንም ብዙ ያስከፍላል - በጊዜም፣ በገንዘብም፡፡
እኔ የሄድኩት
አንድ የትምህርት ማስረጃ ሰነድ ላይ የእውነተኛነት ማረጋገጫ ማሕተም ለማስመታት ነው፡፡ ይህንን ሰነድ ሌላ ቦታም ቀደም ብሎ ማረጋገጫ
ማሕተም ማስመታት በቅድመ ሁኔታነት ተከናውኗል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሰነዶች ማረጋገጫ ቢሮ ደግሞ ከግቢ ውጪ ጥቂት፣ ጊቢ ውስጥ
ደግሞ በአግዳሚ ወንበር እና ከዚያ የተረፈው ግድግዳ ተደግፎ ቆሞ የተሰለፈ ብዙ ሰው አለ፡፡ ያንን መጠበቅ - በተለይ እንደኔ ላለውና
በስጋ ሳይሆን ባጥንት ብቻ ለቆመ ሰው - ወገብን ይፈታተናል፡፡
በግምት ለሁለት
ሰዓታት ያህል በሰልፍ ጠብቄያለሁ፡፡ ተሰልፌ ግን ስሰጋ የነበረው ስለወገቤ፣ ስለጥበቃው ወይም ከምሳ ሰዓት በፊት ወረፋው ባይደርሰኝስ
ስለሚለው አልነበረም፡፡ እነዚህኞቹ እዳቸው ገብስ ነው፡፡ እኔን የጨነቀኝ ይህን ሁሉ ሰዓት ጠብቄ ያላሟላኸው አንድ ነገር አለ ተብዬ
ሰልፉን እንደገና እንድጀምር ብደረግስ?



