ሁሉም ሰዎች ይናገራሉ፤ ሁሉም ሰዎች ብሶት አላቸው። ነገር ግን የሁሉም ንግግር እና ሐሳብ የሁሉንም ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም። በዚህም ምክንያት ተናጋሪ እንጂ አዳማጭ የለም፤ ብሶት እንጂ አዘኔታ የለም። ምክንያቱም ‘አገናዛቢነት’ የለም፤ አንዳቸው የሌላኛቸውን ሁኔታ እና እውነታ ለማገናዘብ ሲሞክሩ አይታይም።
አገናዛቢነት የሚናገሩት ነገር ያለበትን ጥቅል ሁኔታ ከግምት ውስጥ ለማስገባት መሞከር ነው። ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ የሚያነጋግሩን ክስተቶች ድንገታዊ መነሻ ይኑራቸው እንጂ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወይም አካባቢያዊ አንድምታ ይኖራቸዋል። እነዚህን ማገናዘብ ያስፈልጋል፤ የፖለቲካ ተዋስዖዎቹ የአንድን ወገን በደል፣ የአንድን ክስተትን አደገኝነት፣ ወዘተርፈ አተኩረው ሊናገሩ ይችላሉ። ጉዳዮቹ ግን ከአንድ ወገንም፣ ከአንድ ክስተትም የሰፉ እና ውስብስብ ናቸው። ውስብስብነታቸውን ያላገናዘበ ንግግር ችግሩን የመፍታት አቅም ከማጣቱም ባሻገር፣ ምናልባትም ችግሩ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊቆልል ይችላል።
ግጭት አገናዛቢነት
የነውጥ አዘል ግጭቶች ቦታዎችና ክስተቶች ዳታ (ACLED) የተባለ እ.አ.አ. በ2019
ኢትዮጵያ ውስጥ 300 ገደማ የፖለቲካ ነውጦች፣ 680 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት አድርጎ ነበር። የ2020ውን ገና ቆጥረው
የጨረሱት አይመስለኝም፤ ሆኖም ከዚህ ጽሑፍ ጋር ሕዳር ወር ላይ ያወጡትን ግጭቶች ያሉባቸውን ቦታዎች የሚያመለክት ካርታ አስቀምጥላችኋለሁ።
ግጭቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ እውነታዎች ናቸው። ግጭቶች እዚህም እዚያም አሉ። ነገር ግን የፖለቲካ ተዋስዖዎቹ ግጭት አገናዛቢ አይደሉም። መጀመሪያ ግጭት አገናዛቢነት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ ልሞክር።
ግጭት አገናዛቢነት ማለት “ንግግሮች እና ተግባራት ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና
ነባራዊ ዐውዱን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በተናጋሪዎቹ ወይም በተግባራቱ አከናዋኞች ላይም ይሁን በተደራሲዎቻቸው ላይ ወይም በሌሎች
ሦስተኛ ወገኖች ላይ የሥነ ልቦናዊም ይሁን የአካላዊ ጥቃት ሊያደርስ የሚችል ቋንቋ ባለመጠቀም ወይም ተግባር ባለማከናወን ግጭት
አስወጋጅ የንግግር እና አሠራር ሒደት” ማለት ነው።
ብዙዎቹ በፖለቲከኞች፣ በአክቲቪስቶች፣ ወይም ጋዜጠኞች የሚደረጉት ተዋስዖዎች ንግግሮቹ ስለሚያስከትሉት ጦስ እምብዛም
አይጨነቁም። በዚህም ምክንያት በግጭት ላይ ግጭት፣ በቀውስ ላይ ቀውስ እየተደራረበ ይሔዳል። በነገራችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የተናገሯቸው
ንግግሮች የጥላቻ ወይም ሐሰተኛ መረጃ በውስጣቸው ሳይኖር ነባራዊውን እውነታ እና ዙሪያ ገቡን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ በመሆናቸው
ብቻ - በሌላ አነጋገር ግጭት አገናዛቢ ባለመሆናቸው ሳቢያ
በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። ለግጭቶቹ ግን ማንም ኃላፊነት አይሰማውም፣ በነርሱ ግጭት አለማገናዘብ ምክንያት ለጠፋው ሕይወትም ይሁን
ንብረት መፀፀትም የተለመደ አይደለም።
ግጭት አገናዛቢነት የታመቁ ወይም ይፋዊ ግጭቶችን እንዲሁም ነውጥ አልባ ወይም ነውጥ አዘል ግጭቶችን መኖራቸውን፣ ንግግሮች ወይም ተግባራት እነዚህን ሊያባብሱ ወይም ሊያከስሙ እንደሚችሉ መረዳት እና በተቻለ መጠን ግጭቶቹን ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን በመቀነስ፣ ሊያከስሙ የሚችሉትን በመጨመር ላይ ማተኮር ነው።
“እኛ” ብቻ እንዳልሆንን ማገናዘብ
ማገናዘብ የሚገባን ይፋዊ ግጭቶችን ብቻ አይደለም። የታመቁ በርካታ ግጭቶች አሉ። የታመቀ ግጭት ብዙ ጊዜ ግጭት ውስጥ
በሚገቡት ወይም ውጥረት ውስት ባሉ ቡድኖች መካከል ያለ፣ ያልተገለጠ አንዳንዴ ውጥረቱ በመሐከላቸው ባለው የተዛባ የኃይል ግንኙነት
ምክንያት እንዳለ ባልተረዱ ወይም ባልተነጋገሩ አካላት መካከል የሚገኝ ያደፈጠ ግጭት ነው።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በተለያዩ ብሔሮች፣ በተለያዩ እምነት ተከታዮች፣ በተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አራማጆች፣
በተለያየ የኢኮኖሚ መደብ አባላትና ፆታን መሠረት ያደረገ፣ ወዘተ ያደፈጠ፣ ያልተገለጠ፣ እምቅ ግጭት አለ። ለዚህ ነው ንግግሮቻችን
እና ተግባራቶቻችን ሁሉ “እኛ” ብቻ ሳንሆን “ሌሎችም” እንዳሉ እንዲሁም እነርሱም ፍላጎቶች እና ስሜቶች እንዳሏቸው ማገናዘብ የሚኖርብን።
የፖለቲካ መዝገበ ቃላታችን ውስጥ የብሔር ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የእምነት ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም
ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የኢኮኖሚ መደብ ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የፆታ ልዩነቶችን ማገናዘብ የሚል ነገር እምብዛም አይታይም። በነዚህ
ሁሉ መሐል የኃይል ግንኙነት እርከኖች አሉ፣ የታሪክ እና የአረዳድ ትርክርት ልዩነቶች አሉ፣ የመደብ ልዩነቶች አሉ። ባላገናዘብን
ቁጥር የምንጨፈልቃቸው ብዙዎች አሉ።
የትግራይ ጦርነት ጥቅምት 24 ሕወሓት የሰሜን ዕዙን ስታጠቃ ይጀመር እንጂ ብዙዎቻችን ከዛሬ ነገ ተጀመረ እያልን ስንፈራው
የቆየነው ጉዳይ ነው። የሕወሓት ተቃዋሚዎችም፣ የሕወሓት ወዳጆችም የሌሎችን ጥቅምና ጉዳት፣ ስጋትና ተስፋ አገናዝበን አናውቅም።
ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊትም ይሁን በኋላ ለዚህ ወይም ለዚያ ቡድን የሚያስከትለው ድል ወይም ሽንፈት፣ አልያም የትርክትና መልካም
ገጽታ መቆጣጠሩ እንጂ በዚህ የሥልጣን ሽኩቻ ሰለባ የሚሆነው ሕዝብ፣ በዚህ ሳቢያ በሕዝቦች መካከል የሚመባባሰው ዘላቂ የወዳጅነት
መሻከር አላሳሰበንም። በዚህ አስተሳሰብ፣ አነጋገር፣ እና አተገባበር ሰላም ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። የትግራይ ጦርነት
የግጭት አላገናዛቢነታችን ዋና ማሳያ እንጂ ብቸኛው አይደለም።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተደጋጋሚ የሚፈነዳ እና የብዙዎችን እልቂት ያስከተለ ነውጥ አለ። ስለ ነውጡ ባለን ቁንፅል መረጃ
ላይ ተመሥርተን ከመቋሰል በቀር ግጭት አገናዛቢ የሆነ እርምጃ
ተራምደን አናውቅም። በአካባቢው ያለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? በሕዝቦች መካከል ያለው
ታሪካዊ ግንኙነት እንዴት ነበር? እነዚህን ያላገናዘቡ ድምዳሜዎች እና ብሶቶች የቁራ ጩኸቶች ከመሆን አያልፉም።
አገናዛቢነት “እኛ” ያለንበት ሁኔታ እና “እኛ” ነሮችን የምንመለከትበት አምባ ላይ ሁሉም ሰው አለመኖሩን ማገናዘብንም ይጨምራል። ይህ በተለይም ገደኝነቶችን (privileges) አምኖ ከመቀበል ጋር ይያያዛል። “እንዴት እነዚህ ሰዎች እንዲህ ማድረግ ተሳናቸው?” ብለን የምንላቸው ነገሮች “ከኛ ገደኝነት” (our privileges) የመነጨ መሆን አለመሆኑን ማገናዘብ ያስፈልጋል። “እነዚህ” ያልናቸው ሰዎች “እኛ” ያለን የመረጃ፣ የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ዕድሎች አላቸው ወይ የሚለውን ማገናዘብ ምናልባትም ወደ ችግሩ ምንጭ ሊመራ የሚችል አብርኆት ሊያመጣልን ስለሚችል ደጋግሞ መመርመር ያስፈልገናል።
አገናዛቢነት ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት በምን ይለያል?
ፖለቲካዊ ትክክለኝነት (politically correctness) የሚባለው ንግግሮች ወይም ገለጻዎች የተገለሉ ወይም ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዳይዘነጋ
ወይም እንዳያገልል የሚደረግ ጥንቃቄ ነው። መጥፎ ነገር ባይሆንም ጥንቃቄው ችግሩን በመቅረፍ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ
ንግግሮች በተጋላጭ እና የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ተቀባይነት እንዳያጣ ወይም ለትችት እንዳይዳረግ ለመጠበቅ ያለመ ነው።
ግጭት አገናዛቢነትም ይሁን ሌሎች ነባራዊ ሁነታዎችን ማገናዘብ ግን ግጭቶች ወይም ሌሎች ማኅበረፖለቲካዊ፣
ወይም ማኅበረኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች እና ልዩነቶቹ የማኅበረሰብ ክፍሎቹ ላይ የሚያሳርፏቸው አሉታዊ፣ ሥነ ልቦናዊም ይሁን አካላዊ ተፅዕኖዎች
እንዳይባባሱ ሆነ ተብሎ የሚደረግ ለፍትሐዊነት የቀረበ የፖለቲካዊ ተዋስዖ እና ተሳትፎ ዘዴ ነው።
አገናዛቢነት ችግርን ከሁሉም አቅጣጫዎች ለማየትና ለመቅረፍ መሞከር ነው።
አገናዛቢነት እውነታውን መካድ ወይም መሸሸግ አይደለም፤ አወዛጋቢ ሊሆን ከሚችል ነገር መጠበቅም አይደለም።
ይልቁንም ለእውነታው ለመቅረብ መሞከር ነው። በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ብንመለከት አንድ ወገን ብቻውን ተጠቂ፣ ሌላ ወገን
ብቻውን አጥቂ የሆነባቸው አጋጣሚዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ብዙዎቹ ድንገተኛ ክስተቶች ሳይሆነ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ
የብሔር ናቸው ስንል የሃይማኖት፤ የሃይማኖት ናቸው ስንል የኢኮኖሚ መደብ፤ የኢኮኖሚ ናቸው ስንል የአካባቢያ
(geographic)፤ የአካባቢ ናቸው ስንል የባሕል፤ የባሕል ናቸው ስንል የፆታ ሁነው እናገኛቸዋለን። ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያውያን
ችግር የአንድ ጉዳይ ወይም የአንድ ወገን አለመሆኑን ነው። ይህንን ውስብስብነት ለማገናዘብ በሞከርን ቁጥር ወደ ችግሮቹ እውነተኛ
መንስኤ መጠጋት እንችላለን።
No comments:
Post a Comment