Pages

Sunday, September 23, 2018

በዴሞክራሲ ተስፋ መቁረጥ? (አይታሰብም!)

ትላንት አንድ የስዊድን ጋዜጠኛ "ሐሳብን ከመግለጽ ነፃነት ይልቅ ደኅንነቴን እመርጣለሁ" የሚል አስተያየት አዲስ አበባ ላይ እንደገጠማት ነገረችኝ። ዛሬ ደግሞ በጥዋቱ አንዲት አሜሪካዊ ጓደኛዬ በዋትሳፕ "ብጥብጥ ካለበት ዴሞክራሲ ይልቅ ሠላማዊ አምባገነንነት ይሻላል" የሚል ክርክር እንደገጠማት ነገረችኝ። በጣም ነው ያዘንኩት፤ ምክንያቱም እዚህ ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ የሚፈልጉ የፖለቲካ ቡድኖች እንዳሉ አውቃለሁ።

በመሠረቱ ዛሬ በጉዳዩ ላይ በአጭሩ መሞነጫጨር የፈልግኩት በነዚህ ሰዎች ብቻ አስተያየት ተነሳስቼ አይደለም። "ጭቆና ለምደን ነፃነት መሸከም አቃተን" የሚሉ አስተያየቶችን ደጋግሜ እሰማለሁ። ስህተቱ የሚጀምረው ዴሞክራሲም ይሁን ነፃነት ላይ "ደርሰናል" ከሚለው ድምዳሜ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ለማዋለድ በምጥ ላይ ነው ቢባል ይሻላል። እንደ አዋላጆቹ ብቃት ፅንሱ (ዴሞክራሲው) ይወለዳል ወይም ይጨናገፋል። አዋላጆቹ ካላወቁበት ደግሞ ፅንሱ እናትየውን ጨምሮ ይዞ ሊሔድ ይችላል። ስለዚህ ድምዳሜያችን ጥንቃቄ የሚያሻውን ጉዳይ ችላ እንድንለው ሊያደርገን ይችላል። ግን ዋነኛው የአረዳድ ችግር የዚህ ጉዳይ ብቻ አይደለም።

ሠላም በአምባገነንነት እና በዴሞክራሲ ውስጥ

አምባገነንነት ሕዝቡ "በቃኝ" ብሎ ቀና እስከሚል ድረስ ረግጦ የመግዛት ስልተ መንግሥት ነው። አምባገነኖች የበቃኝ ነጥብ ከመድረሷ በፊት ሁሉንም ነገር ስለሚያፍኑ ሠላም ያለ ያስመስላሉ። በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ ፀጥታ ስላለ ሠላም ያለ ይመስላል። ነገር ግን የታፈነ አመፅ አለ፤ የታፈነ ደም መፋሰስ አለ። ስለ አመፁም ይሁን ስለ ደም መፋሰሱ መነጋገር አይፈቀድም። የመረጃ ምንጮችም ይታፈናሉ። በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ የአመፁ መሪ መንግሥት ነው።

በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግን ሰዎች ቅሬታቸውን ሁሉ ያጮኻሉ፣ ትንሿም ብሶት ሳትቀር ትሰማለች። ይህ ራሳቸውን እንደሰጎን አሸዋ ውስጥ ቀብረው የሚኖሩትን ብዙዎች ከምቾት ዞናቸው ስለሚያስወጣቸው ሠላም ደፈረሰ ይላሉ። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፀጥታው ይደፈርስ ይሆናል እንጂ እንደ አምባገነናዊ ስርዓት ሠላም አይደፈርስበትም። ግጭቶች በዴሞክራሲያዊ ስርዓትም ውስጥ አሉ። ይሁን እንጂ ንግግር ስለማይታፈን ግጭቶችን በአካል ሳይከሰቱ በድርድር መፍትሔ ይፈለግላቸዋል፤ ከተከሰቱም በኋላ በአጭሩ ለመቅጨት ፈጣን መፍትሔ ለመፈለግ ዴሞክራሲ ያስችላል።

በጣም ስኬታማ የሚባሉት አገሮች ውስጥ ልዩነቶቻቸውን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት አቻችለው ኖረዋል፤ እኛም እንችላለን!

ሐሳብ እና አመፅ

"እመፅ ማነሳሳት" እና "የጥላቻ ንግግር" የሚባሉ ችግሮች አሉ። ነገር ግን ብዙዎች ቃላቱን የሚጠቀሙባቸው የማይፈልጉትን ሐሳብ ለማፈን ሲሆን ብቻ ነው። በመሠረቱ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ላይ ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት እንዲከበር ቁርጠኛ አቋም የተወሰደበት አንዱ ምክንያት ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት "አመፅ" እና "ለውጥ" መካከል ሚዛን መፍጠር ስለሚችል ነው። ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በአመፅ ያደርጉታል። እንዲናገሩት ሲፈቀድላቸው ግን የሚጋጩ ፍላጎቶቻቸውን ሳይቀር ማስታረቂያ መንገድ በመነጋገር ይፈልጋሉ።

በአገራችን መደራጀትም ይሁን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ታፍነው መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህ በእንዲህ እያለ የማኅበራዊ ሚድያ መከሰት ተናደው መድረክ ያጡትንም፣ የተስማሙ የሚመስላቸውንም የሚጋጩትንም በአንድ ግንባር አገናኛቸው። በዚህ መሐል ጎራ ለይተው በሐሳብ መቆሳሰላቸው የሚጠበቅ ነው። መሬት ላይ ለመግባባት መነጋገርን፣ የዜግነት መብት እና ግዴታዎችን ማወቅ እና ማክበርን የሚያስተምሩ ሲቪል ማኅበራት ቢያብቡ ኖሮ፥ ሐሳቦች በየጉዳዩ ላይ ዕውቀት ካላቸው ሰዎች አንደበት ተቀብለው የሚያንሸራሽሩ ሚድያዎች ቢያብቡ ኖሮ፥ ዛሬ አላዋቂዎች ባሻቸው ጉዳይ ላይ ደፋር ተንታኝ ሆነው ብዙ ተከታይ እና አድማጭ አያፈሩም ነበር። ለዚህ ያበቃን አምባገነንነት እንጂ ዴሞክራሲ አይደለም።

አሁንም ቢሆን መፍትሔው ማዕቀብ አይደለም፤ ነፃነት ነው። ሁሉም ሰዎች በነፃነት በተነጋገሩ ቁጥር አሸናፊ ሐሳቦች እየተንጓለሉ ይወጣሉ። "እውነት ለሐሰትም ሳይቀር ምስክር ነች" እንደሚባለው፥ የሚዋሹት እውነት በሚናገሩት ይጋለጣሉ፤ ጥላቻ የሚሰብኩት ፍቅር በሚሰብኩት ይሸነፋሉ።

መፍትሔው በሰው ልጅ ማመን ነው

አምባገነናዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት በሰው ልጆች ላይ ያለን እምነት መገለጫዎች ናቸው ብዬ አምናለሁ። አምባገነን ስንሆን ሰዎች መጥፎዎች ናቸው። ቁጥጥር፣ እገዳ እና ቅጣት ያስፈልጋቸዋል ብለን እናምናለን። ዴሞክራት ስንሆን ደግሞ በተቃራኒው በሰው ልጆች ቀናነት እምነት ይኖረናል። ሰዎች ሲያጠፉ እንኳን ለክፋት ወይም ክፉ በመሆን ሳይሆን በመሳሳት ነው ያደረጉት ብለን እናምናለን። ስለዚህ ዴሞክራት ስንሆን ለሰዎች ነፃነት፣ ከኃላፊነት እና ተጠያቂነት ጋር እናጎናፅፋለን።

በዴሞክራሲ ተስፋ ቆረጥን ማለት በሰው ልጆች ተስፋ ቆረጥን ማለት ነው።

No comments:

Post a Comment