በዚህ ርዕስ ረዥም መጣጥፍ መጻፍ ከጀመርኩ ረዥም ግዜ ሆነኝ፡፡ እስካሁን አላለቀም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ጉዳዩ ስሜት የሚነካ እና በስሜት የሚነዳ ስለሆነ ፈርቼው ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋስኦዋችንን በተከታተልኩት ቁጥር የተረዳሁት አንድ ነገር ቢኖር "ብሔርተኛ ነኝ" በሚሉ እና "ብሔርተኛ አይደለሁም" በሚሉት ሰዎች መካከል ያለው ልዩነት ብሔርተኝነትን የማመን እና የመሸሸግ ችሎታ ልዩነት ነው፡፡ ወይም ደግሞ አንዳንዴ ልዩነቱ ግለሰቦቹ የሚያራምዱት ብሔርተኝነት የሚያቅፋቸው ሰዎች ቁጥር የበዛ መሆኑ ‹ብሔርተኝነቱን› የመሸሸግ ዕድል ያገኛል፡፡ በጣም በተሳሳተ መደምደሚያ ላለመጀመር ያክል "ብሔርተኝነት" ደረጃው እና ልኩ ይለያይ ይሆናል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ከውስጡ የወጣለት ሰው የማግኘት ዕድላችን ጠባብ ነው ብለን እንስማማ፡፡ የሆነ ሆኖ፣ ‹ብዙኃን ብሔርተኛ ናቸው› የሚል መደምደሚያ ይዤ ነው ይህንን የምር አጭር ያልሆነ መጣጥፍ፣ ረዘመብኝ ካልኳችሁ መጣጥፌ ጨልፌ እና ጨምቄ የማስነብባችሁ፡፡
የመጀመሪያው አንቀፄ እንደሚያመለክተው ‹ብዙኃን ብሔርተኞች ናቸው›፡፡ ‹ብሔርተኝነት ቅዱስ ነው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ ማንሳት ‹ብዙኃን ቅዱስ ናቸው ወይስ እርኩስ?› የሚል ጥያቄ እንደማንሳት ያስፈራል፡፡ ቢሆንም እንጋፈጠዋለን።
ብሔርተኝነት ሲበየን
ብዙዎቹ ዓለም ዐቀፍ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ምሁራን ለብሔርተኝነት ያላቸው ንቀት የትየለሌ ነው፡፡ ንቀቱ አንድም ብሔርተኝነት ‹ማኅበራዊ ፈጠራ› (social fabrication) ነው ከሚል የመነጨ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የሰው ልጅን ያክል ባለ ብሩሕ አእምሮ በአጋጣሚ በበቀለበት ማኅበረሰብ ብቻ መበየን ከእውነታው የራቀ ስለሚሆን ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የብሔርተኝነት የመዝገበ ቃላት ፍቺው "ተመሳሳይ ባሕል ያላቸው ሕዝቦች ፖለቲካዊ ነጻነት መፈለግ" ወይም "በአገር በጣም የመኩራት ስሜት" ነው (P.H. Collin (2014))፡፡
ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ብሔርተኝነትን የሚበይነው እኔንም በሚያስማማ መልኩ ነው፡- "የአንድ ግለሰብ ታማኝነት እና ቁርጠኝነት ከሌሎች ግለሰቦች እና ቡድኖች ፍላጎት በላይ ለብሔረ-መንግሥቱ (nation state) ማድላት ላይ የተመሠረተ ርዕዮተዓለም ነው"። በዚህ መሠረት ቀጣዮቹን ርዕሰ ጉዳዮች እያነሳን እንጥላለን፡፡
ሰዎች ለምን ብሔርተኛ ይሆናሉ?
ለዚህ ጥያቄ ቀላል መልስ እሰጣለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ብሔርተኛ የሚሆኑት ፈቅደው እና አቅደው ሳይሆን ባጋጣሚ ነው፡፡ አጋጣሚው የሚጀምረው ‹የት እና ከማን ተወለዱ?› ከሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ብሔርተኝነትን በንባብ እና በውይይት ሊያዳብሩት ይችላሉ እንጂ የሚጀምሩት ግን በውርስ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ብሔርተኝነት ራሳቸውን በአንድ የብሔር አባልነት የሚጠሩ ሰዎች እስኪኖሩ ድረስ አይኖርም፡፡ የሆኑ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እና የሚያስተሳስራቸው ማኅበራዊ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን በአንድ ማንነት ለይተው መጥራት ሲጀምሩ ወይም በሌሎች በዚያ ማንነት መጠራት ሲጀምሩ ብሔርተኝነት ተጀመረ ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ብሔርተኝነት በስሎ እና ጎርምቶ የሚወጣው እነዚያ ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ ሲያስቡ፣ እና/ወይም በማንነታቸው ሳቢያ በሌሎች እየተጠቁ እንደሆኑ ሲያስቡ ነው፡፡ ብሔርተኝነት የሚጎመራው የጋራ ማንነት ላይ ጥቃት ያደርሳሉ ተብለው የሚታሰቡ የተለየ ማንነት እንዳላቸው የሚታመኑ ጠላቶች ሲኖሩ ነው፡፡