Pages

Sunday, May 20, 2018

ሰው መሆን…

የሰው ልጆች ሰው ለመሆን ማለቂያ የሌለው አብዮታዊ ጉዞ ውስጥ ናቸው፡፡ እንደመታደል ሆኖ፣ የሰው ልጆች የላቀ እና እየላቀ የመጣ አእምሮ ባለቤት በመሆናቸው ምድርን እንደግል ንብረታቸው፣ ራሳቸውንም ተለይቶ እንደተመረጠ ፍጡር እየቆጠሩ፣ ምድርን ለራሳቸው ምቾት እያሾሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የሰው ልጆች በሠለጠኑ ቁጥር ርሕራሔያቸው እየጨመረ፣ አውሬነታቸው እየቀነሰ መጥቷል። የራሳቸውን ነጻነት የሚያከብሩትን ያክል የሌሎችንም ለማክበር እየተጉ መጥተዋል። የሰው ልጆች ዛሬ ከራሳቸው አልፈው ስለአካባቢያቸው ብዝኃ ሕይወት እስከመጨነቅ ደርሰዋል። የሰው ልጆች ረዥም ጉዞ ገና አላለቀም። የሰው ልጆች ሰው የመሆን ጉዞ የት ተጀመረ? በየት በኩል አለፈ? ዛሬ የት ደረሰ? ነገስ ወዴት ይጓዝ ይሆን? የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የሰው መሆንን ጉዞ በወፍ በረር በመቃኘት የሰውነትን ዓላማ መገመት ነው።

ቶማስ ፍሬድማን ሉላዊነት 3ኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጽፏል። የመጀመሪያው ደረጃ የአገረ-መንግሥታት እርስበርስ መተሳሰር ነው። ሁለተኛው ደረጃ የንግድ ኩባንያዎች ብዙ አገራት ላይ መሥራት መቻልና እርስ በርስ ግንኙነት ነው። የመጨረሻውና ሦስተኛው ደረጃ የሰዎች ድንበር ዘለል የአንድ ለአንድ ግንኙነት፣ የትብብር እና የውድድር ዕድል መጨመሩ እና መጠናከሩ ነው። እውነትም ዛሬ ሉላዊ ዜጋ (global citizen) መሆን ከመቼውም ግዜ በላይ ቀሏል። ይህ ክስተት የሰው መሆን ጉዞ አቅጣጫ ድንበር የለሽ የዓለም ዜጋ መሆን መሆኑን ይጠቁመን ይሆን?

በዓለማችን አሁን ላይ በአንድ ወቅት 7 ሺሕ ገደማ ቋንቋዎች ነበሩ። በአጥኚዎች ትንበያ መሠረት ከነዚህ ውስጥ በመጪዎቹ መቶ ዓመታት ውስጥ የሚቀሩት መቶዎቹ ብቻ ቢሆኑ ነው። በተረፈ ቀሪዎቹ ወይ ተናጋሪ በማጣት፣ ወይ ከሌላ ጋር ተዳቅለው አዲስ ቋንቋ ተወልዶ፣ ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት ይሞታሉ። በዚህ አካሔድ ስንገምተው ምናልባትም የሆነ ግዜ ዓለማችን ጥቂት ወይም አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር የሰው ዘር መኖሪያ ትሆናለች። ይህ ምንን ያመለክታል? የሰው ልጅ ብዙ ሆኖ ጀምሮ አንድ ሆኖ እንደሚጨርስ? ወይስ፣ በሒደቱ ከአንድ ወደ ብዙ ከዚያ መልሶ ወደ አንድ-ነት እንደሚጓዝ? ሌላም፣ ሌላም…

ጥንት የሰው ልጆችን ከአንድ ሥፍራ ከመንቀሳቀስ የሚያግዳቸው ተፈጥሮ ብቻ ነበር። ዛሬ ዛሬ፣ ተፈጥሮ በሰው ልጆች ቁጥጥር ሥር እየዋለች በሔደች ቁጥር ሰው ሠራሽ ድንበሮች የሰውን ልጆች እንቅስቃሴ እየገደቡ ነው። ሆኖም አገረ-መንግሥታዊ ኅብረቶች፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ እነዚህን ሰው ሠራሽ ድንበሮች መልሰው እየሰበሯቸው ነው። ዛሬ የዓለም አገራት ድንበራቸውን አጥረው በአንድ ወቅት የሁሉም የነበረችውን ዓለም ተከፋፍለው የኔ እና የእናንተ ተባብለዋል። ጆርጅ ፍሬድማን መጪዎቹን መቶ ዓመታት በተነበየበት መጽሐፉ ይህ አይቀጥልም ይለናል። እሱ እንደሚለው 21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የዓለማችን ኃያላን አገራት እንደዛሬ ሳይሆን ስደተኞችን መፀየፍ አቁመው በገንዘብ ለመግዛት እስከ መሻማት ይደርሳሉ። ይህንን እውነት ይሆናል ብለን እንገምትና የሰው ልጅ የነገ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚመስል በምናባችን እንሳል። ግምታችን ለእውነቱ እንዲቀርብ ግን ያለፈውን ግዜ ከጥንስሱ ጀምሮ በጨረፍታ እናስታውሰው።

ሰው ከመሆን በፊት

ኅዋችን ብዙ ስርዓተ ከዋክብትን ይዟል። ከነዚህ ስርዓቶች ውስጥ ሚልኪ ዌይ ጋላክሲ አለ። ሚልኪ ዌይ ጋላክሲ ውስጥ ካሉ የፕላኔት ቡድኖች ውስጥ የእኛዋ ስርዓተ ፀሐይ አለች። ፀሐይ እስካሁን በተለዩት ዘጠኝ ፕላኔቶች እና አጃቢ ጨረቃዎቻቸው ጉሮ ወሸባ ደምቃ በኅዋው ላይ ትንሳፈፋለች። ሳይንቲስቶች ዘመኑ በፈቀደላቸው መነፅር አሻግረው ሲመለከቱ ኅዋችን አሁንም ድረስ እየተለጠጠ፣ እየሰፋ ይገሰግሳል። በዚህ ዓይነት ብለው፣ ፍጥነቱን ቀምረው ወደ ኋላ በቤተ ሙከራ ውስጥ ተመልሰው ማየት ጀመሩ። በፍጥነት ወደ ኋላ 13 ቢሊዮን ዓመት ገደማ ኅዋችን ከምንምነት ወደ የዛሬው ኅዋነት ተዘዋወረ። ይህንን ታሪካዊና ሳይንሳዊ የመላምት ነጥብ ሳይንቲስቶች ‘ትልቁ ፍንዳታ’ (The Big Bang) ይሉታል። ይህንን አንዳንዶች የሥነ ፍጥረት መጀመሪያ ይሉታል። አጀንዳችን ሥያሜው ስላልሆነ ቀጣዩን ሒደት እንከተል…

የዛሬ አራት ቢሊዮን ተኩል ዓመት ገደማ መሬት የእሳት ኳስ ነበረች። ኅዋችን ከትልቁ ፍንዳታ በኋላ የፍንዳታዎች ቀጠና ሆኗል። ስርዓተ ፀሐይ ሲመሠረትም በተመሳሳይ ፍንዳታ ነው። ፀሐይና ምድርን ጨምሮ በዙሪያዋ የሚሽከረከሩት ፕላኔቶች የተፈጠሩት በአንድ ፍንዳታ ነው። የኋላ ኋላ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች እና የተቀጣጣይ ጋሶች ከእሳት ኳሷ መውጣት ምድርን የውኃ ባለቤት በማድረግ ቀስ በቀስ የመቀዝቀዝ ዕድል ሰጣት። ኳሷን እረፍት በነሷት ግዙፍ ፍንዳታዎች እና የመቀዝቀዝ ሒደት ውስጥ፣ የፕላኔታችን በመጠኑ የቀዘቀዘ የብስ ባብዛኛው መገጣጠም ችሎ ነበር። ቀሪዎቹ ደግሞ እልፍ ብጥቅጣቂ ደሴቶች ሆነዋል። የዛሬ 750 ሚሊዮን ዓመት፣ ከያኔ 200 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የተመሠረተው ትልቁ አህጉር (ሳይንቲስቶች ሮዲና ብለውታል) ተሰነጣጥቆ ብዙ ትናንሽ አህጉሮች ተፈጥረዋል። በእንዲህ ዓይነት፣ በከርሰምድር ውስጥ ባለ ሙቀት እና ፍንዳታ ምክንያት የምድር የብሱ ክፍል በውኃ አካሏ ላይ ከዚህ ወደዚያ እየተላጋ ሲገጥምና ሲሰባበር ከርሞ ነው ዛሬ (ሰዎች ለፖለቲካ እና ታሪክ አቀማመር እንዲመቻቸው ሰባት ነው ያሏቸው አህጉሮች ቁጥር) ላይ የደረስነው። ያቺ የእሳት ኳስ ምድር፣ ምንም እንኳን እሳት በሆዷ ይዛ እስከዛሬ ብትቀጥልም የበረዶ ኳስ የሆነችበትም ዘመን ነበር። የዛሬ 717 ሚሊዮን ዓመት ገደማ ምድር ድንገት ቀዘቀዘች። ይህም ለሕይወት መከሰት ሁነኛ ማዳበሪያ ሆኖ ቆየ።

ሕይወት በምድር ላይ ለመጀመሪያ ግዜ የተከሰተው የዛሬ 3.5 ቢሊዮን ዓመት ገደማ ነው ተብሎ ይገመታል። ውኃ ውስጥ በአንድ ሕዋስ የተከሰተው ሕይወት፣ ዛሬ ውኃውንም፣ የብሱንም አዳርሶ ከምድራችን አቅላጭ ሞቃታማዎቹ የሞት ሸለቆ (አሜሪካ)፣ አዚዚያ (ሊቢያ) እና ዳሎል (ኢትዮጵያ) ጀምሮ እስከ… በቅዝቃዜ ቁርጥማት ገዳይ የሆኑት የአንታርክቲካ ተራሮች፣ ማክኪንሌ ተራራ (አሜሪካ) እና ቬርኮያንስክ (ሩሲያ) ድረስ ራሳቸውን ለአካባቢው የአየር ሁኔታ አስማምተው መኖር የቻሉ ሕይወት ያላቸው እልፍ አእላፍ ባለብዙ ሕዋስ ዝርያዎች ይኖራሉ።

በምድር ላይ አሁን ያሉ ሕይወት ያላቸው ዝርያዎች ከ100 ሚሊዮን እስከ ትሪሊዮን ይደርሳሉ የሚሉ የተራራቁ ግምቶች አሉ። ሳይንቲስቶች የመዘገቧቸው ግን ሁለት ሚሊዮን አይደርሱም። የሆነ ሆኖ፣ በምድራችን ሕይወት ከተከሰተ ጀምሮ እስከዛሬ ከኖሩት ሕይወት ያላቸው ዝርያዎች ዘራቸውን ማስቀጠል ሳይችሉ የቀሩት 99 በመቶ ናቸው ተብሎ ይታመናል። በአስትሮይድ እና ምድር ግጭቶች፣ በገሞራ ፍንዳታዎች እና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በከባቢ አየር ለውጦች፣ በምግብና መጠጥ እጦት፣ በበሽታ ወረርሽኝ፣ በእርስ በርስ ሽኩቻዎች እና ወዘተ እንደዳይኖሶር ግዙፍ ከሆኑት ጀምሮ ባለአንድ ሕዋስ ዝርያዎች ሳይቀሩ ዘራቸውን ማስቀጠል ተስኗቸው ከስመዋል። እነዚህ ፈተናዎችን ሁሉ በዝግመተ ለውጥ እየታገሉ ከሌሎች እልፍ የእፅዋት እና እንስሳት ዝርያዎች ጋር እስከዛሬ መድረስ የቻሉት ሰዎች፣ ዛሬ ላይ ሕይወት ያላቸው ዝርያዎች ሁሉ ‹ንጉሥ ነን› እያሉ ነው። እንዴት ንግሥናውን ተቀቡ? እስከ መቼስ ነግሠው ይኖሩ ይሆን?

‘ብልሑ ሰው’

‘ሆሞ ሳፒየንስ’ ሳይንቲስቶች ለዛሬ ሰው የሰጡት ሥያሜ ነው። የቃሉ ምንጭ ላቲን ሲሆን፣ ትርጉሙም ‘ብልሑ ሰው’ የሚል ነው። ብልሑ ሰው በሳይንሳዊ አደራደር በእንስሳት ግዛተ-ዐፄ፣ በጅማትና ነርቭ አገነባብ፣ በአጥቢዎች መደብ፣ በቅድመ ዐዋቂነት ስርዓት፣ በማኅበራዊ አደረጃጀት ንዑስ ስርዓት፣ ከታላቁ ጦጣ ቤተሰብ፣ ከሰው ዝርያዎች ሥር ይመደባል። ከሰው ዝርያዎች ውስጥ እነ ቋሚው ሰው (homo erectus)፣ ቅሪቱ ከተገኘበት አካባቢ የፍሎሬስ ሰው ተብሎ የተሰየመው (homo floresiensis) እንዲሁም ሆሞ ሀቢሊስ፣ ሆሞ ሄይደልበርገንሲስ፣ ሆሞ ናሌዲ እና ሆሞ ኒያንደርታል አሉበት። ሆኖም ዕድል ቀንቶት ዛሬ ላይ የደረሰው፣ መድረስ ብቻ ሳይኖን ምድርን ሳያጠፉ ዝርያውን ማጥፋት የማይቻል የሚመስል ዐቅም የገነባው ብልሑ ሰው ብቻ ነው።

የብልሑ ሰው የመጨረሻ ተቀናቃኞች ኒያንደርታሎች ነበሩ። ድንክዬዎቹ ኒያንደርታሎች በዩሬዥያ አካባቢ በብዛት ነበሩ። የመጨረሻ የኒያንደርታል ዝርያዎች በምድር ላይ በሕይወት የተመላለሱት የዛሬ 12 ሺሕ ዓመት ገደማ ነው። በብልሕነታቸው ብልሑን ሰው የሚቀናቀኑት ኒያንደርታሎች ዛሬም ድረስ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ብልሑ ሰው፣ ምናልባትም ራሱን የምድር ንጉሥ አድርጎ መቀባት አይችልም ነበር። ወይም ደግሞ ዛሬ በነጭ እና ጥቁርነት ዘር እና በንዑስ ባሕል የልዩነት ዘውግ ላይ የተመሠረተው ሽኩቻ ደረጃውን ከፍ አድርጎ ከሌሎች ዝርያዎች ጋር ይሆን ነበር። የሆነ ሆኖ ኒያንደርታሎች ብልሑ ሰው ውስጥ አሻራ ሳይጥሉ አልከሰሙም። ዛሬ በምድር ላይ የሚመላለሰው እያንዳንዱ ሰው 6 በመቶ የሚገመት የኒያንደርታሎችን ዲኤንኤ በደሙ ይዞ ይዞራል። ለዚህ ጉዳይ የተሰጠው ሳይንሳዊ መላምት “የመዳቀል ኅልዮት” ይባላል። ለካስ እንኳን አንዱ የዛሬ ሰው ዘር ከሌላው ዘር እና ዘውግ ሰው ቀርቶ፣ ብልሑ ሰው እና ኒያንደርታሎችም ሲዳቀሉ ኖረዋል? ይህ ማለት ግን ፍቅር ነበራቸው ማለት አይደለም። እንዲያውም እርስ በርሳቸውም ዛሬ የዱር እንስሳት የሚገጥሙትን ዓይነት ጦርነት ሲገጥሙ ነው የኖሩት። ሁለቱ የመጨረሻ የሰው ዝርያዎች ተዳቅለው እና ተጫርሰው ብልሑ ሰው ለዛሬ ለመትረፍ በቅቷል። የሰው መሆን ጉዞ የሚጀምረው ከሰው ዝርያዎች ሁሉ ብልሑ ሰው አሸንፎ ከተረፈ በኋላ ነው።

የሰው መሆን ጉዞ…

ፍልሰት እና ስደት የሰው ልጆች ዝርያ በተበተኑበት ሁሉ ቋንቋቸውን እና ባሕላቸውን እየነጠሉ እና እያሳደጉ ቀጠና ከተከፋፈሉ በኋላ የመጡ ፅንሰ ሐሳቦች ናቸው። የሰው ልጆችን ዓለም ያካለለ እንቅስቃሴ፣ በበኩሌ ዙረት ብዬ ብጠራው እመርጣለሁ። ዙረት የሰው ልጆችን ሰው ካደረጓቸው እርምጃዎች አንዱና ዋነኛው ነው። የዙረቱ መንስዔ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ገፊና ጎታች ሁኔታዎች ናቸው። ዋነኛው ገፊም፣ ጎታችም ሁኔታ የኅላዌ (survival) ጥያቄ ነው። ይህንን የኅላዊ ጥያቄ የሚፈታተን አደጋ ሲመጣ ሽሽት እንዲሁም ይህንን የኅላዊ ጥያቄ የሚያረጋግጥ ዕድል ሲገኝ ማሳደድ የሰው ልጆች የዘላለም የዙረት መንስዔ ሆኗል።

በጣም ተቀባይነት ያለው የሰው ልጆች የመጀመሪያው የዙረት ሳይንሳዊ ናሙና "ከአፍሪካ ወደ ውጭ" የሚባለው ነው። ዘረመል ላይ ተመሥርተው በተደረጉ ጥናቶች እንደተገመተው፣ የሰው ዝርያ አሁን ኢትዮጵያ ከምንለው የፖለቲካ ክፍለ ዓለም የመነጨ ነው። የብልሑ ሰው ዝርያ ለረዥም ዘመናት የኖረውም እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ነው። ከአንዲት የአፍሪካ ብልሕ ሰው ማሕፀን በመነጩ ሰዎች የተጀመረው ዙረት ደግሞ፣ ዛሬ የሰው ዝርያ ዓለምን እንዲያዳርስ ሰበብ ሆኗል። ዙረቱ በዋነኝነት ከአፍሪካ ቢጀምርም በየደረሰበት የመዳቀል እና ከአካባቢ ጋር የመስማማት ዝግመተ ለውጥ በማስመዝገብ እና ወደፊት ብቻ ሳይሆን ወደኋላ የደርሶ መልስ ጉዞ እያደረገ ዝርያውን እያደሰ ብዙ ቁጥር እንዲያፈራ አድርጎታል። ብልሑ ሰው ከተከሰተ ከ140 ሺሕ ዓመታት በኋላ (ማለትም የዛሬ 60 ሺሕ ዓመት ገደማ) ጀምሮ አህጉር አቋራጭ ዙረቱን ጀምሯል። ሳይንቲስቶች ብልሑ ሰው ቅሪቱ ላይ እየተወ የሚያልፈውን ዘረ መል እና (ድቅሉን ለመረዳት) ያስከተለውን ልዩነት እየመዘገቡ የዙረቱን ዱካ ተከትለውታል።  የዙረቱ መንስዔ በምድራችን ለመጨረሻ ግዜ የተከሰተው ቅዝቃዜ (የበረዶ ዘመን) ለብልሑ ሰው ኑሮን ስላከበደበት ነበር። በዚህ ግዜ የሰው ልጅ ዝርያ ሊጠፋ ጥቂት ነበር የቀረው። ያኔ የተረፉት ጥቂት የሰው ዝርያዎች ዕድል ባይቀናቸው ኖሮ ዓለማችን ዛሬ፣ በደኖች የተሞላች የአራዊቶች ምድር ሆና ትቀር ነበር ብሎ መጠርጠር አይከብድም።

በመጨረሻ የታየው የበረዶ ዘመን ባሕሩን ወደ ግግር በረዶ ጥርጊያነት ቀይሮት ስለነበር ለብልሑ ሰው የእግር ዙረት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር። ብልሑ ሰው በአፍሪካ የቀረውን ዝርያውን ትቶ፣ በዛሬዋ ጅቡቲ በኩል ወደ ዛሬዋ የመን ተሻግሮ በዛሬዋ ሕንድ ጠረፍ በማቋረጥ ደቡብ ምሥራቅ እስያ እና የዛሬዋ አውስትራሊያ ከ10 ሺሕ ዓመታት በኋላ ለመድረስ ችሏል። ጉዞው በየሔዱበት እየተ:ራቡ እና እየተዳቀሉ፣ እየሰፈሩ፣ ለዘመናት እየከረሙ፣ ሕፃናትና ደካማውን እዚያው እየተዉ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የትየለሌ ትውልዶችን ያፈራረቀ በመሆኑ የትኛውም ትውልድ መጓዙን፣ ቀሪውም መቅረቱን ሳያውቅ ነው ዝርያውን በዓለም የበተነው። ሁለተኛው ዙር ዙረት ሲቀጥል ብልሑ ሰው ደቡብ እና መካከለኛው እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅን ረገጠ። ከዚያም ወደ አውሮፓ።

የዛሬ 15 ሺሕ ዓመት ገደማ በዚሁ የመጨረሻው የቅዝቃዜ ዘመን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ፣ የባሕር ጠለል በጣም ዝቅ በማለቱ፣ በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮች ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ ጥርጊያ ሠርተው ነበር። በዚህ ታግዞ ሲጓዝ የከረመው የብልሑ ሰው ዝርያ በ1ሺሕ ዓመት ውስጥ ሰሜን አሜሪካን መርገጡም ታውቋል። ክርስቶፈር ኮሎምበስ የዛሬ 500 ዓመት ገደማ ሕንድን ሲፈልግ አሜሪካን አግኝቶ "አዲስ ዓለም" ብሎ ከመሰየሙ እልፍ ዓመታት በፊት ጀምሮ አያቶቹ ቀድመው ሰፍረው ይኖሩ ነበር። የጥንት፣ የድሮ፣ ወይም የዘንድሮ የሰው ልጆችን ከሚያመሳስሏቸው ነገሮች ዋነኛው የዙረት ዓመላቸው ነው።

የሰው ልጆች ከሚጠሏቸው ወይም ቶሎ ከሚሰለቿቸው ነገሮች ሁሉ በአንድ ቦታ እና ሁኔታ ተወስኖ መቀመጥ ነው። ከሰው መሆን ሒደት ጋር አብሮ እያደገ የመጣው የዙረት ችሎታቸው በእግር ከማዝገም በአየር እስከ መብረር ደርሷል። ከእግር እስከ ከብት ጀርባ፣ ከጋሪ እስከ መኪና፣ ከባቡር እስከ አውሮጵላን የተፈለሰፉት ኅላዌውን ለማረጋገጥ መሔድ የማይታክተውን የሰው ልጅ ፍላጎት ለማርካት ነው። በየብስ ብቻም አይደለ፣ የሰው ልጅ በዋና፣ በታንኳ፣ በጀልባ እና መርከብ ሲጓዝ ነው የኖረው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ በአካል መጓዝ ሳይችል ሲቀር በሐሳብ መጓዣ መንገድ ፈጥሯል። እነዚህ የቴክኖሎጂ ምጥቀቶች የሰውን ዝርያ እግር እንጂ አገር የሌለው ሆኖ እንዲቀጥል ረድተውታል። ደብዳቤ፣ ስልክ፣ ራዴዮ፣ ቴሌቪዥን፣ በይነመረብ የዚሁ ፍላጎት ፈጠራዎች ናቸው። ለዚህ ሁሉ ያበቃው ታዲያ ብልሕነቱ ነው።

የሰው መሆን ጉዞ በአብዮት የተሞላ ነው ብለናል። የሰው ልጆችን ዝርያ ከሌሎች የእንስሳት ግዛተ-ዐፄ (Kingdom Animalia) ነጥሎ ያወጣው የመዞር ችሎታው ሳይሆን ‘የዕውቀት ዝግመተ ለውጥ’ (Cognitive Evolution) ያጎናፀፈው የአዋቂነት አብዮት ነው። ይህ ግን በገዛ ጥረቱ የተገኘ ሳይሆን በተፈጥሮ ዝግመተ ለውጥ የታገዘ ስኬት ነው። ምንም እንኳን የሰው ዝርያ ከፍተኛ የሥራ መግፍኤ በማንገብ፣ ራሱን በመረዳት፣ ችግሮቹን በመፍታት፣ ባሕል እና ቋንቋ በማፍራት እና በማስቀጠል ወደር ባይገኝለትም ሌሎችም ዝርያዎች መጠኑ የተለያየ የዕውቀት ባለቤቶች ናቸው። ጅቦች፣ ዶልፊኖች፣ ጦጣዎች እና ሌሎችም በየደረጃው ራስን ከመ:ረዳት፣ ችግሮችን ለመፍታት እስከሚያስችል ዕውቀት ድረስ ባለቤቶች ናቸው።

ዩቫል ሐራሪ ‘ሳፒየንስ’ በሚለው ድንቅ መጽሐፉ እሱ ‘የዕውቀት አብዮት’ የሚለው የዕውቀት ዝግመተ ለውጥ “ከፈነዳ ወዲህ ለብልሑ ሰው አንድም ‘የተፈጥሮ’ ሊባል የሚችል የኑሮ ዘዬ የለም”። ተፈጥሯዊ የኑሮ ዘዬ ላይ ግን የሰው ልጆች ክርክር ተቋርጦ አያውቅም። ነገር ግን የኑሮ ዘዬን እየመራ ያለው ባሕላዊ ምርጫ ነው። በዚህም ማኅበራዊ ዝግመተ ለውጥ ተከስቷል። ለዚህ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገው ደግሞ የብልሑ ሰው የሐሜት ችሎታ ነው። ዩቫል ሐራሪ የሰው ልጅ ውሸትን ለዘለቄታ የማቀነባበር፣ እንዲሁም የሐሜት እና የማማት ችሎታው ከቀሪዎቹ እንስሳት ሁሉ ነጥሎ ለወግ ማዕረግ እንዳበቃው ይተርካል። አንድ ሰው፣ በአንዴ 150 ያህል ሰዎችን በብቃት የማማት (ከጀርባቸው ስለነርሱ የማውራት) ችሎታ አለው። ይህም ለማኅበራዊ መዋቅሮች፣ ለባሕሎች፣ እሴቶች፣ ሃይማኖቶች፣ ሴራዎች እና ሌሎችም ስርዓተ ማኅበሮች እና ትስስሮች መሠረት ጥሏል።

የቋንቋ አብዮት

በዩቫል ሐራሪ ድምዳሜ መሠረት ሰው ስኬታማ ሐሜተኛ መሆን እንዲችል ቋንቋ የግድ ያስፈልገው ነበር ማለት ነው። በርግጥም አግኝቶታል። ይሁን እንጂ ቋንቋ መቼ እና እንዴት እንደተጀመረ ለመገመት ባለሞያዎቹ ሲቸገሩ ኖረዋል። ባንድ በኩል ቋንቋ ቀስ በቀስ እያደገ (በኮንቲኒዩቲ ኅልዮት) ነው ሙሉ የሆነው ከሚል፣ ድንገት ባንዴ ነው (በዲስኮንቲኒዩቲ ኅልዮት) የተከሰተው እስከሚል፤ በሌላ በኩል ተፈጥሯዊ ነው ከሚል የባሕላዊ ዕድገት ውጤት ነው እስከሚሉ ድረስ ክርክሮች አሉ። የሆነ ሆኖ በበርካታ መላምቶች ቋንቋ ከብልሑ ሰው ዝርያ ጋር አብሮ ተከስቶ ሲያድግ ከርሞ፣ የዛሬ 100 ሺሕ ዓመት ገደማ ነው ከባሕሎች ጋር አብሮ መባዛት የጀመረው ተብሎ ይታመናል። እ.ኤ.አ. በ1999 በተደረገ ቆጠራ በዓለም ላይ የነበሩት ቋንቋዎች ቁጥር 7 ሺሕ ገደማ ተገምቷል። ከነዚህ ውስጥ እጅግ ብዙዎቹ ከ10 ሺሕ በታች ተናጋሪ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህም ብዙዎቹ ቋንቋዎች በየጊዜው እየሞቱ (ተናጋሪ እያጡ) ይሔዳሉ፡፡ የቋንቋዎች ሕልፈት በፍጥነት ሔዶ ሔዶ በመቶ ዓመት ውስጥ ብዙዎቹ ቋንቋዎች ሞተው ጥቂቶች ይቀራሉ ተብሎ ለእርግጠኝነት በቀረበ ስሌት ትንቢት ተነግሯል። የቋንቋዎች አብዮት የሰው ልጅን በብዙ ቡድኖች ከፍሎታል፡፡ የብልሑ ሰው ዘሮች በቋንቋዎቻቸው የራሳቸውን ማንነት ለይተዋል፤ በብዝኃዊነት ውስጥ የቋንቋ ልዩነት ጉልህ ሚና አለው፡፡

የጽሑፍ አብዮት ደግሞ ቋንቋን ነፍስ ዘርቶበታል። የሰው ልጆች ጽሑፍን ባይፈለስፉ ኖሮ ምናልባትም ከእንስሳት አቻዎቻቸው እምብዛም የበለጠ አቅም ላያፈሩ ይችሉ ነበር ቢባል ብዙ ስህተት አይሆንም። ለዚህም ይመስላል ስለ ሥልጣኔ ሲወራ የራሱ ጽሑፍ የሌለው ሥልጣኔ፣ ሥልጣኔ ሊባል አይበቃም የሚል መከራከሪያ የመጣው። (ዛሬ ላይ 4 ሺሕ የሚጠጉ የራሳቸው ፊደል ያላቸው ቋንቋዎች አሉ። እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ሥልጣኔዎች ናቸው ማለት ይቻል ይሆናል።) ብልሑ ሰው የራስ ግንዛቤ ያለው እንስሳ በመሆኑ ራሱን እና አካባቢውን የመግለጽ ፍላጎቱ ከፍ ያለ ሆኖ ይመስላል ጽሑፍን የፈጠረው። ከብዙ ሺሕ ዓመታት ጀምሮ የእጆች ምስል በዋሻ ግድግዳ ላይ ማተም፣ የከብቶች እና ሰዎች ቅርፃ ቅርፅ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ራስን መግለጫ መንገዶች ነበሩ። የኋላ ኋላ ቃላት አቀነባብሮ ለመጻፍ ክብር በቅቷል። የዛሬ ታሪክ ጸሐፊዎች የሰው ልጅን ታሪክ ሲጽፉ በሁለት ከፍለው ነው። ቅድመ ታሪክ የሚሉት የሰው ልጅ ጽሑፍ ከመጀመሩ በፊት ያለውን በአርኪዮሎጂ ግኝቶች ላይ ተመሥርቶ የሚገመተውን ነው። የታሪክ ግዜ የሚሉት ደግሞ ሰው ታሪኩን ለቀጣዩ ትውልድ በሚተላለፍ ጽሑፍ/ምስል መግለጽ ከጀመረ ወዲህ ያለውን ግዜ ነው።

የእርሻ አብዮት

አዳኝ-ለቃሚው፣ ጥንታዊው ብልሑ ሰው፣ የለቀመውን ፍራፍሬ በድንጋይ ሰብሮ የፍራፍሬውን ስጋ ሲበላ፣ ፍሬው መሬት ይወድቅና ቆይቶ በራሱ ጊዜ ይበቅላል፡፡ ብልሑ ሰው በጊዜ ሒደት ይህን ሳያስተውል የቀረ አይመስልም፡፡ በዚህም መንገድ ይመስላል ራሱ አብቅሎ መብላት የተማረው፡፡ ብልሑ ሰው አብቅሎ መብላት የተማረበት ዘመን የእርሻ አብዮት ዘመን ተብሎ ነው በባለታሪኮች የሚታወቀው፡፡

የእርሻ አብዮት የሰው ልጅ እሳትን መቆጣጠር ከቻለበት እና ጀርሞችን በመግደል በሽታ መቀነስ፣ ጠላቶቹን ማባረር፣ ምግቡን ማጣፈጥ ከቻለበት ወዲህ ትልቁ ግኝት ነው። ብልሑ ሰው ድሮ ድሮ አዳኝ-ሰብሳቢ ነበር። አንዳንዴ አድኖ ስጋ፣ ሌላ ጊዜ ቀጥፎ ፍራፍሬ ይበላ ነበር። ይህ የተመጣጠነ ምግብ እንዲበላ እና ብዙ እንዲንቀሳቀስ ያደርገው ነበር። በዚህም የረጋ መቀመጫ ባይኖረውም ፈርጣማ አካል ነበረው። የዛሬ 10 ሺሕ ዓመት ግን በአባይ/ናይል ተፋሰስ ዳርቻ ላይ ከእርሻ ጋር መተዋወቁ ይህንን የኑሮ ዘዬውን ቀይሮታል። ብልሑ ሰው እህል ዘርቶ አብቅሎ መብላት ሲጀምር ዙረቱን ቀነሰ። ከዓመት ዓመት የሚበላው ጥራጥሬም አንድ ዓይነት በመሆኑ ፈርጣማነቱ ቀንሶ ከዱር አውሬዎች ጋር በጉልበት ሳይሆን በብልሐት ብቻ መጋጠም ጀመረ። ከዚህም በላይ ዙረቱን አቁሞ ከአንድ መንደር ጋር መዋደዱ ከቀዬው ጋር ራሱን እንዲያዛምድ አደረገው። ብልሑ ሰው በእርሻ ሰበብ በአንድ ቦታ ለረዥም ግዜ መክረምን ሲማር መኖሪያ ቤት መገንባት፣ ንብረት ማፍራት ጀመረ፡፡ ይህም ወደ ሥራ ክፍፍል እና ሙያ መፈጠር የሰው ልጅን መራው፤ አራሹ፣ ቤት ሠሪው፣ ቀጥቃጩ፣ ሸክላ ሠሪው ወዘተ… የየራሱን ሙያ እያዳበረ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች እና እርከኖች ተጧጧፉ፡፡

በተመሳሳይ አሰፋፈር በየቦታው ያሉ ማኅበረሰቦች በየቀዬያቸው አዳዲስ እምነት፣ አዳዲስ ባሕል፣ አዳዲስ የቋንቋ ዘይቤ ብሎም አዳዲስ ቋንቋ እያፈሩ የቀያቸውን ሰው እንደወዳጅ፣ ሌሎችን እንደባዳ መቁጠር ተማሩ። ለእርሻ መሬታቸው፣ እና ለመጠጥ ውኃቸው ከሌሎች ጋር ለመጋጨት እርስበርስ መተባበር አመጡ። ዛሬ አገረ-መንግሥት የምንላቸው ስብስቦች እርሻን ተከትሎ በአንድ ቦታ ተሰባስበው መኖር የጀመሩ ሰዎች መኖር እና የምርታቸው መጨመር የፈጠረው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች የሰፈሩት ሰዎች በቦታቸው ተወስነው ከመኖር ይልቅ ፍላጎታቸው እየጨመረ ሌላ አካቢዎች ላይ የሰፈሩ ሰዎች የሚያመርቱትን ምርት ማግኘት ይፈልጉ ጀመር፡፡ ይህንን ለማግኘት አንዳንዴ በግጭት እና በዘረፋ፣ ሌላ ግዜ ደግሞ በንግድ እና ልውውጥ ከሌሎች ጋር የጠብ ወይም የወዳጅነት ግንኙነት ማድረግን ተማሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስርዓተ ፆታ መፈጠርም ከእርሻ መጀመር ጋር ተያይዞ መጥቷል። (አዳኝ-ለቃሚ ማኅበረሰብ ውስጥ ሥርዓተ ፆታ (በወንድ እና ሴት መካከል የሥራ እና የደረጃ ድልድል) ነበር/አልነበረም የሚለው እስካሁንም አከራካሪ ነው።) ከከብት አርቢ ማኅበረሰቦች ይልቅ ግን በእርሻ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሴቷን ቤት አካባቢ የሚሠሩ ሥራዎችን እንድትሠራ እና ወንዱን ደግሞ የመስክ ሥራ እንዲሠራ የድርሻ ክፍፍል ፈጥሯል። ይህ ድልድል እየሰፋ ሔዶ ድልድሉ እስከማያስፈልግበት የዛሬ ዘመን ድረስ ዘልቋል።

የፖለቲካ ስርዓታት…

“ሰውን ሰው የሚያደርገው ምንድን ነው?” የሚለው ጥያቄ በተነሳ ቁጥር የተለያዩ መልሶች ይሰጣሉ፤ ሁሉም መልስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሰውን ሰው የሚያደርገው ወይም ያደረገው አንድ ነገር ብቻ አይደለም፡፡ አሪስጣጣሊስ “ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ብልሑ ሰው ፖለቲከኛ ሆኖ አልጀመረም፡፡ የሰው ልጆች ፖለቲካዊ ስርዓተ ማኅበርን ያገኙት ኅልውናቸውን ለማስጠበቅ በሚጥሩበት ወቅት ነው፡፡

የአዳኝ-ለቃሚው ማኅበረሰብ በውስጡ ከ50 እስከ መቶ የሚሆኑ ሰዎችን ነበር የሚይዘው፡፡ ያኔ በጋራ ያፈሩትን በጋራ ተካፍሎ መብላት ቀላል ነበር፡፡ የግጭት መንስዔም አይሆንም ነበር፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ እህል ማብቀል ሲማር፣ ማከማቸትም አብሮ ተማረ፡፡ ከዚያም በላይ በአንድ አካባቢ የሚያርሰው እና የሚሰፍረው ሰው ቁጥር መብዛት ተካፍሎ መብላትን ከባድ እና የግጭት መንስዔ ከመሆን ሊያቆስቆመው አልቻለም፡፡ ዝርፊያም እንደሙያ የተጀመረው ያኔ ነው፡፡ ጉልበተኛ ሽፍቶች ጠንካራ ሠራተኞች ለፍተው ያፈሩትን በጉልበታቸው በመውሰድ ከሌላው የበለጠ ምርት በማከማቸት ኃይላቸውን ያፈረጥሙ ጀመር፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ እየዘረፉ በሚሰወሩ ተንቀሳቃሽ ሽፍቶች ምትክ በቋሚነት ከአምራቾች የተወሰነ ምርት እየቀረጡ የሚሰበስቡ ቋሚ ሽፍቶች ተወለዱ፡፡ ቋሚ ሽፍቶቹ ከተንቀሳቃሾቹ ይልቅ ተመራጭ ነበሩ፡፡ ማኅበራዊ ሳይንቲስቱ ፕሮፌሰር ማንኩር ኦልሰን የዚህን ኀቲት ማስረጃ ሲያቀርቡ ተንቀሳቃሾቹ ሽፍቶች ያገኙትን ሁሉ ዘርፈው የሚሰወሩ ሲሆኑ፣ ቋሚዎቹ ግን አምራቹ ምስኪን ያመረተው ሁሉ ከተወሰደበት የማምረት ተነሳሽነቱ ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን ከፊሉ ተወስዶ ቀሪ የሚኖረው ከሆነ እና ከተንቀሳቃሽ ሽፍቶች ቀረጥ የሚከፈለው ቋሚ ሽፍታ የሚጠብቀው ከሆነ ቋሚውን ሽፍታ ወዶ ይቀበለዋል፡፡ ቋሚ ሽፍቶች ገቢያቸው እየጨመረ እንዲመጣ የግድ የሸፈቱበትን ማኅበረሰብ ደኅንነት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የቋሚ ሽፍቶቹ የተደራጀ ኃይል ሲወልድ ሲዋለድ የጦር መሪዎች፣ ከዚያም ራሳቸውን ሥዩመ-ፈጣሪ አድርገው የሳሉ ንጉሣዊ ስርዓቶች፣ መሳፍንታዊ ባሕሎች ተንሰራፉ፡፡ አሸናፊው ተሸናፊውን እየጣለ መግነኑን ቀጠለ፡፡

ነገሥታት እና የጦር መሪዎች የሚያስገብሩትን ሕዝብ እና አካባቢ እንደግል ንብረታቸው ይመለከቱ ነበር፡፡ ሥልጣናቸውም ፍፁማዊ እና ከሕዝባቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትም ፍፁም ጨቋኝ፣ ፍፁም ፈላጭ ቆራጭነት የተሞላበት ነበር፡፡ የሰው ልጆች ከፖለቲካዊ ማኅበሮች ጎን ለጎን ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን እና ማኅበሮችን ፈጥረዋል፡፡ ብዙዎቹ ሃይማኖቶች ኃይለኛው ደካማውን የሚያጠቃበትን ስርዓት በሞራል ሕግ ለማስቀረት ሞክረዋል፡፡ የሥነ ማኅበረሰብ ሊቁ ፍራንሲስ ፉኩያማ “ዛሬ እንደ አክራሪ ስርዓት የሚቆጠረው እስልምና እና የሸሪኣ ሕግ ባንድ ወቅት ያልተገራ ሥልጣንን፣ ዘረፋን፣ እና በሥልጣን መባለግን ለመከላከል ውሎ ነበር” ይላሉ፡፡ የአውሮፓ የሕግ የበላይነት ፅንሰ ሐሳብም ሥሩን የሰደደው ዛሬ እንደኋላ ቀር ከምትቆጠረው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የፖለቲካ ስርዓቶች አንዱ ካንዱ እየተጋጩ፣ አሸናፊው ተሸናፊውን እያወደመ ወይም እየዋጠ ማኅበራዊ መዋቅሮችን ሲፈጥር እና ሲያፈርስ ነው የኖረው፡፡ ፉኩያማ የቻይናን ፖለቲካዊ ዝግመተ ለውጥ ሲዘግብ ከ3 ሺሕ ዓመት በፊት 1,200 ያህል የተለያዩ ጎሳዎች እና የጎሳ መሪዎች እንደነበሯት ይገልጻል፡፡ በ500 ዓመታት ውስጥ ብዙዎቹ ተጨፍልቀው ወደ 30 ዝቅ ብለዋል፡፡ ከዚያ ወደ 16፣ ቀጥሎ ደግሞ ወደ 7 አገረ-መንግሥታት ዝቅ ብለዋል፡፡ በስተመጨረሻም፣ ሁሉም ተጨፍልቀው አንዲት ቻይና ቀርታለች፡፡ ፉኩያማ የመጀመሪያው ዘመናዊ አገረ-መንግሥት የሚሏት ቻይናን ነው፡፡ ይሁን እንጂ የቻይና ዝግመተ ለውጥ ለአምባገነናዊ ስርዓተ መንግሥት እንጂ ለዴሞክራሲ እንዳላዘጋጃት ይገልጻሉ፡፡ በጥቅሉ ኃያላን ኃይሎች ኃይላቸው በፈቀደላቸው መጠን በተፅዕኖ አድማስ (sphere of influence) የጀመሩት አስተዳደር አሁን አድጎ አድጎ መሥመራቸው በድንበር የተለዩ አገራት ወይም አገረ-መንግሥታት ፈጥሯል፡፡ ቻይኖች የቀዳሚነታቸውን ያክል ለምን ከሁሉም የበለጠ አልበለፀጉም የሚል ጥያቄ ደጋግሞ ይነሳል፡፡ በ15ኛው ክፍለዘመን ገደማ የቻይና ግዛተ ዐፄ ደኅንነቱን ለመጠበቅ ከውጪ ንግድ እና ግንኙነት ድንበሩን ዘግቶ ነበር፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ የሰው ልጆችን የዙረት እና ከሌሎች የመቀላቀል ነጻ ፍላጎት የሚጋጭ በመሆኑ ቻይናን አስከፍሏታል፡፡ ቻይና በሯን በዘጋችበት ወቅት፣ አውሮጳውያን ‹ሲኖፊል› (የቻይና ፍቅር) በሚሉት የጥንታዊ ቻይና ዘይቤ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የንቃት አብዮት (አብርኆት) አካሔደዋል፡፡

የጥንታዊት ቻይና የኑሮ ዘዬ የአውሮጳን አብርኆት፤ ከአይሁድ ቤተሰቦች የወጣው ክርስትና፣ በሮማውያን ንጉሥ (በመጀመሪያው የኒቅያ ጉባዔ) ለዓለም ተዳርሷል፡፡ ማንኛውም ዓለማዊ እሴት በቀደምት ፈጣሪዎቹ ተወስኖ አያውቅም፡፡ ዴሞክራሲን አቴናዎች ፈልስፈውት፣ ዳግም ነፍስ የዘሩበት ደግሞ የፈረንሳይ አብዮት እና የአሜሪካ ነጻነት አዋጅ ናቸው፡፡ በዓለም የሰው ልጅ ታሪክ እርግጠኛ ሆኖ መናገር የማይቻለው የፈጠራንም ይሁን የዘርን ምንጭ ነው፡፡ ዛሬ የሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ነዋሪዎች ከሚባሉት ውስጥ 2 እና 8 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው አያት ቅድመአያቶቻቸው እዚያው የነበሩት (ወይም የቀድሞ ሰፋሪዎች)፡፡ ቀሪዎቹ ሁሉ ኮሎምቦስ ሰሜን አሜሪካን አገኘሁ ካለ በኋላ የሔዱ ናቸው፡፡ የጥንት ፖለቲካዎች ማስገበር ላይ የተመሠረቱ ስለነበሩ ስለዘር ምንጭ ያሁኑን ያክል ደንታ አልነበራቸውም፡፡ የአገረ-መንግሥታት አመሠራረትም በጥቅም እሴቶቹ ላይ እንጂ በሰዎቹ የዘር ምንጭ ላይ አልተቋቋመም፡፡

አገረ-መንግሥት (state) ማለት በማክስ ቬበር አተረጓጎም “በአንድ ቀጠና ላይ የተጣለ የኃይል የበላይነት (monopoly of force) ነው”፡፡ ይህንን አንዳንዶች የአመፃ የበላይነት (monopoly of violence) ይሉታል፡፡ የሆነ ሆኖ እ.ኤ.አ. በ1215 ማግና ካርታ የተባለው የነገሥታቱን ሥልጣን የሚገድብ ቻርተር በእንግሊዙ ንጉሥ ጆን ተቀባይነት ሲያገኝ፣ አሸናፊ ጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ተሸናፊ ብዙኃኖችም ባለ መብት መሆን የሚችሉበት ስርዓት መንግሥት መሠረት ተጥሏል፡፡ ከዚያን ግዜ ወዲህ የሰው ልጅ ብዙ ተጋድሎዎችን፣ ብዙ አብዮቶችን በማካሔድ የመንግሥት ሥልጣንን የተቆጣጠሩ ገዢዎችን መብቶች በመቀነስ፣ ተጠያቂነታቸውን በመጨመር እና የተገዢ መደቦችን መብት በመጨመር ቀድሞ ከተፈጥሮ በቀር ፈተና ያልነበረበትን ነጻነታቸውን ለማስመለስ እየተጉ ነው፡፡ ዓለምን የናጠው የማርክስ የቡርዧ እና የሠራተኛ መደብ ግንኙነት ጥያቄ፣ እንደባርያ ይታይ የነበረውን ሠራተኛውን ኃይል መሠረታዊ መብቶቹ እንዲከበሩለት አስገድዷል፡፡ በባርያ ንግድ እና አሳዳሪነት የበለፀገችው አሜሪካ በባርነት ፍዳ የበሉትን ጥቁሮች የልጅ ልጆች መብት ቀስ በቀስ እንዲከፍል እያስገደዳት ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ወረራ ማንነታቸውን የተነጠቁ እና እንደ አውሬ የተቆጠሩ የሰው ዘሮች ታሪካቸውን ለመቀልበስ እየጣሩ ነው፡፡ የነጭ የበላይነት፣ የወንድ የበላይነት፣ የሀብታም የበላይነት የተባሉ ጥያቄዎች ሁሉ በሕግ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ባሕላዊ አብዮቶች ቀስ በቀስ ፈተና ውስጥ እየገቡ ነው፡፡ በሰው ልጆች የማያቋርጥ ዘንድ የለውጥ አብዮት የማያቆም ዥረት ነው፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ጥቂቶች ፖለቲካዊ ስርዓታት እና መንግሥታት ሉዓላዊነትን ለዜጎቻቸው በማጎናፀፍ የሰው ልጅ የዘላለም ፍላጎት የሆነው ነጻነት ለማረጋገጥ እየሞከሩ ነው፡፡ ብዙዎቹ ግን አሁንም ድረስ ከቋሚ ሽፍቶች የተለዩ አይደሉም፡፡

‘ማኅበራዊ ውል’

ከላይ በቋሚ ሽፍቶች እና ገባሪ ብዙኃን ያየነው የይሁንታ ስምምነት የሚጠቁመን ሐቅ አለ - በብዙኃን እና በልኂቃን መሪዎች መካከል ያለ ግንኙነትን መግራት፡፡ ብዙኃን የግል ነጻነታቸውን ይወዳሉ፡፡ ያሻቸውን የሕይወት ዘይቤ መከተል፣ ያሻቸውን ምርት ማምረት እና ያመረቱትን እንዳሻቸው ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሰው ልጆች መካከል ያለው በዕኩልነት ላይ ያልተመሠረተ ግንኙነት ይህንን አያስጠብቅላቸውም፡፡ እንኳንስ የኑሮ ዘይቤያቸውን እና ምርታቸውን መጠበቅ ቀርቶ፣ በሕይወት የመኖር መብታቸውን በራሱ ከኃይለኞች በግላቸው መጠበቅ አይችሉም፡፡ እዚህ ላይ ነው የሩሶ “ማኅበራዊ ውል” ኀቲት የሚከተለው፡፡ ብዙኃን ከተወሰኑ መብቶቻቸው ቆርጠው ለገዢዎቻቸው ይሰጣሉ፡፡ ገዢዎቻቸው ደግሞ በምላሹ ቀሪ መብቶቻቸውን ያስከብሩላቸዋል፡፡ ገዢዎች ይህን የሚያደርጉት ከተገዢ ብዙኃን በሚያገኙት ቡራኬ ነው፡፡ የገዢዎች “የኃይል የበላይነት” ስርዓት (order) ለማስከበር ይውላል፤ ብዙኃን ስርዓቱ በሚፈቅድላቸው ልክ ነጻ ፈቃዳቸውን ይፈፅማሉ፡፡ በዚህ ዘመን የገዢዎች የኃይል የበላይነት ብዙኃን ከሚፈቅዱት በላይ ተለጥጦ የዜጎቹን ነጻ ፈቃድ ጨፍላቂ ነው፡፡ ነገር ግን ከሰው ልጆች ታሪክ የምንረዳው፣ የሰው ልጅ ተጋድሎ ነጻነታቸውን ቀስ በቀስ ወደ ማረጋገጥ የሚያመራ መሆኑን ነው፡፡

የሰው ልጅ ቀጣይ አብዮት: ከነጻነት ወደ ነጻነት

በምድር ላይ ከብልሑ ሰው ዝርያ መከሰት ጀምሮ ያለውን የሰው ልጆች ታሪክ ስንመለከት ሰዎች ኅልውናቸውን ለማረጋገጥ ሲታገሉ፣ ሲዳቀሉ፣ ሲሸሹ፣ ሲያሳድዱ፣ ሲውጡ፣ ሲዋጡ ነው የኖሩት፡፡ ይህ አካሔዳቸው ወደፊትም ከጊዜ ወደጊዜ ቢቀንስም መልኩን ቀይሮ ይቀጥላል፡፡ በጥንት ግዜ የሰዎች ትልቁ ፈተና ተፈጥሮ ራሷ ነበረች፡፡ ሰዎች በሒደት የተፈጥሮ ፈተናዎችን መግራት ችለዋል፡፡ በመካከለኛው ዘመን ለሰው ልጆች ኅላዌ ፈታኝ የነበሩት ነገሮች የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ እና ረሀብ፣ የእርስበርስ ግጭቶች ነበሩ፡፡ ዛሬ ካለፉት መቶ ዓመታት አንፃር ሲታይ በነዚህ ምክንያቶች የሚያልቁት ሕዝቦች ቁጥር ቀንሷል፡፡ የፖለቲካ ስርዓቶች የሚገድቡት ነጻነቶች ቁጥር ቀንሷል፡፡ ይቀንሳልም፡፡

የሰው ልጆች በተፈጥሮ ላይ አብየዋል፤ የዕውቀት አብዮት፣ የእርሻ አብዮት፣ የቋንቋ እና የጽሑፍ አብዮት፣ የፖለቲካ አብዮት፣ ሁሉም አብዮት በተፈጥሮ ወይም በስሜት ላይ የመሠልጠን፣ ዕጣ ፈንታን የመቆጣጠር ወይም ኅላዌን የማረጋገጥ አብዮቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጆች የማያቋርጥ አብዮት ከተፈጥሮ ባርነት ብቻ ሳይሆን ከሰው ሰራሽ ባርነት ለመውጣትም እየተረባረበ ነው፡፡ ሰዎች በቴክኖሎጂ ተፈጥሮን ሲዋጉ፣ በፖለቲካዊ ስርዓቶች ደግሞ ከሰው አመጣሽ ፈተናዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ እየጣሩ ነው፡፡ ለስርዓት እና ለደኅንነታቸው የፈጠሩት እና የተቀበሉት የፖለቲካ ስርዓት በራሱም ከነጻነታቸው ሸርፎ መውሰዱ አልቀረም፡፡ ቢሆንም የሰው ልጆች የማያቋርጥ አብዮት የሰዎች ለሰዎች ባርነትን ቀንሷል፣ ቅኝ አገዛዝን አቋርጧል፣ በየርከኑ ያሉ ጭቆናዎችን እየታገለ ነው፣ ድህነትን እየተዋጋ ነው፣ ድንቁርና ላይ እየዘመተ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩን የሰው ልጆች ጉዞ የነጻነት ጉዞ መሆኑን ነው፡፡ የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ፈተና ነጻ መውጣት ይፈልጋሉ፡፡ የሰው ልጆች ከድህነት ነጻ መውጣት ይፈልጋሉ፡፡ የሰው ልጆች ከድንቁርና ነጻ መውጣት ይፈልጋሉ፡፡ ጉዟቸው ፍሬ አፍርቷል፡፡ በወረርሽኝ የሚረግፉት ሰዎች ቁጥር ቀንሷል፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከሞላ ጎደል በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው፣ ድህነት እየቀነሰ ብልፅግና እየበረከተ ነው፡፡ ኑሮ ከጥንቱ ቀሏል፣ የሰው ልጆች ክብር ከግዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ነገር ግን አብዮቱ ማለቂያ የለውም፡፡ ገና ይቀጥላል፡፡

በዓለም ላይ ብዙ ባሕላዊ እና ልማዳዊ ልዩነቶች አሉ፡፡ ሁሉም ባሕሎች እና ልማዶች የራሳቸው መልካም ጎን እንዳላቸው ደካማ ጎን አላቸው፡፡ ሁሉም የሰው ልጆች እነሱ ያሉበት ባሕል እና ልማድ ከሌሎች የተሻለ እና የበለጠ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ባሕሎች ሁሉ ዕኩል አላደጉም፡፡ ግን እነርሱም ቢሆኑ አዝጋሚ ዕድገት ውስጥ ናቸው፡፡ ከሌሎች ይቀየጣሉ፣ ይውጣሉ፣ ይዋጣሉ፣ አዲስ ልማድ ያፈራሉ፣ ያለውን ይሽራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ባሕሎች የግለሰቦችን ነጻነት ለቡድን ልማዶች የሚነጥቁ፣ ቀሪዎቹ ከቡድን ልማዶች ላይ ቆርሰው ለግለሰቦች ስብስቦቹ ነጻነት ያጎናፀፉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ባሕሎች መሠረታዊ አንድነት አላቸው፡፡ በሁሉም ባሕሎች ውስጥ በሕይወት መኖር ከመሞት ይሻላል፣ ጤና ከበሽታ፣ ነጻነት ከባርነት፣ ብልፅግና ከባርነት፣ አዋቂነት ከድንቁርና እንዲሁም ፍትሕ ከጭቆና ይመርጣሉ፡፡ ባሕሎቹ የሰው ልጆች ፍላጎት ማንፀባረቂያ ናቸው፡፡

የሰው ልጆች ዝርያ በራሱ በአዝጋሚ ለውጥ ውስጥ አልፏል፡፡ የዛሬ ሰዎች ከጥንት ሰዎች ጋር አንድ ዓይነት አካል፣ አስተሳሰብ፣ ማኅበራዊ መዋቅር አልነበራቸውም፡፡ ቀስ በቀስ እየተለወጡ መጥተዋል፤ ለውጡ በአብዛኛው በመሻሻል የተሞላ ነው፡፡ የሰዎች ቴክኖሎጂ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት፣ ሁሉም በአዝጋሚ ሒደት እየተለወጠ እና እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ሒደቱ ቀና ባይሆንም ውጤቱ ግን ቀና ነው፡፡

የሰው ልጆች ታሪክ ከጥንት እስከዛሬ የሚያረጋግጥልን የሚከተሉትን ነው፡-


  • የሰው ልጆች በአንድ ወቅት ከአውሬ ያልተለዩ፣ ቀስ በቀስ ሰዋዊነት እያዳበሩ የመጡ - ፍፁም ያልሆኑ፣ መቼም ፍፁም የማይሆኑ ነገር ግን በየጊዜው እየተሻሻሉ የሚሔዱ ፍጡሮች መሆናቸውን፤
  • የሰው ልጆች ኅልውናቸውን ለማረጋገጥ በሚፍጨረጨሩበት የብዙ ሺሕ ዓመታት ያፈሯቸው ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች ቢኖሩም - የትኛውም የኑሮ ዘዬ፣ እምነት፣ ባሕላዊ ወግ፣ ፖለቲካዊ ስርዓት ባሕላዊ/ልማዳዊ እንጂ ተፈጥሯዊ አለመሆኑን፤
  • ዛሬ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ለዘላለም እዚያ አካባቢ የኖሩ ሳይሆኑ፣ በሰው ልጆች የማያቋርጥ የደኅንነት እና የኅልውና ዙረት ውስጥ ሲቀያየሩ እዚህ የደረሱ መሆኑን እና እነዚያ ማኅበረሰቦች፣ ወደፊት በሌሎች ማኅበረሰቦች ሊተኩ የሚችሉ መሆኑን፤
  • የትኛውም ፈጠራ፣ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ዘር ወይም ባሕላዊ ዘውግ የጠራ አለመሆኑን፤ ሰዎች ሲዞሩ፣ ሲዳቀሉ፣ ሲወራረሱ፣ ሲዋዋጡ መኖራቸውን እንዲሁም የትኛውም ማኅበረሰብ የየትኛውም ፈጠራ ወይም ሌላ ነገር ሐቀኛ ባለቤት አለመሆኑን፤
  • የሰው ልጆች ኅልውናቸውን ለማረጋገጥ በሚፍጨረጨሩበት ሒደት የተፈጠሩት የፖለቲካ ድንበሮች፣ አገሮች፣ የብሔሮች አሰፋፈር፣ የባሕሎች ልዩነቶች፣ ሃይማኖታዊ እሴቶች በሙሉ ተፈጥሯዊ አለመሆናቸው፤ እንዲሁም እነዚህ ሁሉ በአንድ ወቅት የሰው ልጆች ሙሉ ነጻነታቸውን ለማስከበር ባለመቻላቸው ከፊል ነጻነታቸውን ቆንጥረው የሰጧቸው እና በምላሹም ቀሪ ነጻነታቸውን በሕግ፣ ደንቦች እና እምነቶች ለማስከበር መደራደሪያዎቻቸው የነበሩ መሆኑን፤
  • F  የትኛውም የምድር ክፍል፣ አህጉር ወይም ፖለቲካዊ አገር የየትኛውም ማኅበረሰብ ተፈጥሯዊ ንብረት እንዳልሆነ፤ ምድር የሁሉም የሰው ልጆች የጋራ ንብረት መሆኗን፤ የሁሉም የሰው ልጆች ኅልውናቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበት ሥፍራ ሁሉ የመሔድ ተፈጥሯዊ ፍላጎት እና መግፍኤ ያላቸው መሆኑን፤

በጥቅሉ የሰው ልጆች ታሪክ ከጥንት እስከ ዛሬ የሚያረጋግጥልን የሰው ልጆች ዓላማ ኅልውናቸውን ማረጋገጥ መሆኑን ነው፡፡ ሰዎች ኅልውናቸውን ለማረጋገጥ ከድንቁርና፣ ከጭቆና፣ ከበሽታ፣ ከድህነት… ነጻ መውጣት ይፈልጋሉ፡፡ ሰው መሆን የነጻነት ጉዞ ነው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ ያላስገባ የፖለቲካዊም ይሁን ማኅበራዊ ስርዓተ መዋቅር መፍረሱ አይቀሬ ነው፡፡

የሰው ልጆች የመጀመሪያም የመጨረሻም ዓላማ በክብር እና በነጻነት መኖር ነው!

(የግርጌ ማስታወሻ፤ ይህ መጣጥፍ የተዘጋጀው ካነበብኳቸው መጽሐፍት፣ ከተማርኳቸው ትምህርቶች፣ ከአደረግኳቸው ውይይቶች፣ ከተመለከትኳቸው ዘጋቢ ፊልሞች እና በድረገጾች ከታተሙ ትርክቶች፣ ከዜናዎች እና የግል ማሰላሰሎች ባፈራሁት ዕውቀት መሠረት ነው። ለቁጥር እና ጥሬ ሐቆች እንዲሁም ኅልዮቶች ማመሳከሪያ ከቃኘኋቸው ዋቢዎች በስተቀር ጸሐፊዎቹ ያልተጠቀሱበት ሁሉ ከአንድ ምንጭ በቀጥታ የተቀዳ ይዘት የለውም። ዋቢዎቹን መዘርዘር ያልቻልኩት ብዙ ስለሆኑ እና አንዳንዶቹ ይህን መጣጥፍ ስጽፍ እጄ ላይ ስለሌሉ ነው፡፡)

2 comments:

  1. የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ድምፅ

    ኢትዮጵያ አንደማንኛውም የአለም ሀገራት በህዝቦች ግጭትና ፍትጊያ የተፈጠረች ሀገር ናት። እኛ የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያለፈ ታሪኮቻችንን ለመማርያነት ካልሆነ በቀር ትኩረታችንን አሁን በእኛ ጊዜ ባለችው ሀገርና ወደፊት በምትቀጥል ሀገራችን ላይ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ሪቻርድ ፓንክረስት እንደጠቀሱት በአንድ ጋላክሲ ላይ በራሳቸው ዛቢያ በሚዞሩ የብሔር መንግሥታት መሀከል በሚፈጠር የንግድ አና የጋብቻ ትስስሮች ፣ የድንበርና የበላይነት ሽኩቻዎች የተመላ ነው። አሁን አኛ የምናያት ሀገር የሰለሞን ስርወ መንግስት ነገስታት ፣ የገዳ ስርአቶች አባ ገዳዎች ፣ የአዳል መንግሥታት አና ሌሎች ክልላዊ ስርዓቶችን ያስተናገደች አንጥፍጣፊ ቅሪት አመለካክቶችን ያዘለች ናት።

    አኛ ማንነን?
    የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የብሔር ስብጥሮች የተወለድን ነን።(ለምሳሌ: ከሀድያ አባትና ከሲዳሞ አናት ፣ ከሱማሌ አናትና ከትግሬ አባት ፣ ከኦሮሞ አባት አና ከአማራ እናት እና ከመሳስሉት)
    እናትና አባቶቻችን ከአንድ ብሔር ቢሆኑም እኛ ልጆቻቸው ከብሄሩ ባህልና ስርአት አንዲሁም ቌንቌ እርቀን በተለያዩ ከተሞች ያደግን።
    እራሳችንን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ብሔሮች በአንዳችውም መመደብ የማንመርጥ።
    በአጠቃላይ በአስተሳሰብም ፣በአስተዳደግም ሆነ በስሜት በአንድ የብሄረሰብ ቡድን ውስጥ ለመካተት የሚከብደን።

    ምን አነሳሳን?
    ያለፉ ታሪኮች ጥለውት ባለፉት አሻራ ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ በሆነው ሀገር በሚለው ጉዳይ ላይ የጋራ ስምምነት ባለማየታችን።
    ስለ አንድ ሀገር የሚያስረዱ ሀይሎች የእራሳቸውን ቡድን ጥቅም የሚያስከብር (የቌንቌ የባህል የበላይነት)፣ የታሪክ ጠባሳዎችን የማያክም፣ ምናባዊ በሆነ የሞራል የበላይነት የተሞላ ሆኖ በመገኘቱ።
    የብሔር መብቶችን አናስከብራለን የሚሉት ሀይሎች ሀላፊነት በተሞላው መልኩ አዲስ የአንድነት አማራጭ ከማቅረብ ይልቅ ጥግ መያዝንና ዘለቄታዊ መፍትሔ የማያምጡ አርምጃዎችን በመውሰዳችው።
    በእኛ ግምገማ የአንድነት ሀይሎች በሽፋን ያሉ የብሔር ቡድኖች ሆነው በሌላ በኩል በግልፅ የብሔር መብት ታጋዮች ተሰልፈው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ውይይት ውሉ የጠፋ አድርገውታል። አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና ከስሜት ይልቅ እውነት ላይ የቆመ አማራጭ ሀሳብ አጥተናል። ከሁሉም በላይ አሁን ላይ ግልፅ እየወጣ ያለው በተለይም በአንድነት ስም ያሉ የአማራ ብሔር ተወላጆችና በነፃ አውጪነት ስም ያሉት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መሀከል ባለው የጎሳ ንትርክ የእኛ ኢትዮጵያውያን ድምፅ እየታፈነ ይገኛል።

    እኛ የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ የጋራ ስምምነት አለን:
    ኢትዮጵያን የምናስባት አከራካሪ የሆኑ የታሪክ ፀሐፊዎች በተለያየ መልኩ የገለጿትን ሳይሆን አሁን መሬት ላይ ያለቸውንና የብዙ ህዝቦች ታሪክ ሀገር የሆነችውን ነው። በዚህም መሰረት ለምሳሌ ፉኛን ቢራ (ጉርሱም) በተወለደው አህመድ ግራኝ እና ደብረዳሞ በተወለደው ልብነ ድንግል አመራርነት የተካሄደው የ15ኛው መቶ ክፍለዘመን ጦርነት ለእኛ የኢትዮጵያውያን የእርስበእርስ ጦርነት ነው።
    አሁን ያለችውን የኢትዮጵያ ቅርፅ ለመፍጠር በአፄ ምኒልክና ከዛም በኋላ የተደረጉ አንቅስቃሴዎች
    በአመዛኙ የሁሉም ብሔርብሄረሰቦች እጅ አለበት ።
    የአማራ ብሄረሰብ የቌንቌ እና የባህል የበላይነት የጎላበት ነበር።
    በዘመኑ ፖለቲካ በአመዛኙ ጥሩ የሚባል የዲፕሎማሲ ሥራና የሀይል እርምጃ ተደባልቆበታል።
    በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች የሌላው ብሔር የሰራውን መልካም ታሪክ እንደራሳችው ታሪክ አድርገው ሊወስዱት ይገባል። በሌላ በኩል የተፈጠረን የታሪክ ስህተት ጠባሳው አሁን ላለነው ትውልድ እና ለሚመጣው ትውልድ እንዳይተላለፍ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ጥረት ሊያደርጉ ይገባል።
    ብሔር ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም የብሄርብሄረሰቦችን ባህልና ቌንቌ እንዲያድግ እንደሚረዳና ብሔሮች እራሳችውን በራሳችው አስተዳድረው ኋላም የጋራ ሀገርን በብቃት እኩል ለማስተዳደር እንደሚረዳ እንገነዘባለን። ሆኖም ይህ ፌደራሊዝም የፍታዊነት ምንጭና ጅማሬ ነው እንጂ ግብ ሊሆን አይችልም። ለዘለቄታው እውነተኛ አንድነት የሚያመጣ ከፈደራሊዝም ሌላ የተሻለ ሀሳብ እስካሁን አልቀረበም።
    በታሪክ አጋጣሚና በትግል ዘመን ርዝመት የተፈጠረ ከትግራይ ተወላጆች የተውጣጣ ቡድን አሁን ያለውን የፌዴራሊዝም ስርአት እንዲመጣ አግዟል። ሆኖም ሰላምንና መረጋጋትን ለማስፈን አገሪቷን በሚተማመኑት የአንድ ቡድን ሰዎች የተጀመረው ቁልፍ የፖለቲካ ቦታዎች ቁጥጥር ወደ ኢኮነሚው ተሸጋግሯል። ይህ ቡድን የኢኮነሚ ፍትሐዊነት ፈጥሯል ብለን አናምንም በመሆኑም የተፈጠረው የፖለቲካ ፍትሐዊነት በሸምቀቆ እንደታሰረ ይገኛል።
    ምን ይደረግ?

    የአንድነት ሀይሎች
    በምናብ ካለ አንድነት ወጥትው ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ያስገባ እውነተኛ አንድነትን ይገንዘቡ።
    አኩሪ ታሪኮችን ልዩነትን በሚያሰፋ መልኩ ሳይሆን ሁሉም ብሔረሰቦች ይኮሩበት ዘንድ በቅንነት ያስረዱ።
    የራስን ብሔር መብት የማስጠበቅ አጀንዳ ያለው በግልፅ ወጥቶ ሀሳቡን ያቅርብ።
    ለብሔር ነፃነት ታጋዮች (በተለይም ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ታጋዮች)
    እውነታው አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ተወለጃቾች እጅ አለበት። ታሪኩ የሚያኮራ ቢሆንም ባይሆንም። ስለዚህ የኦሮሞ ሕዝብ በታሪክም በመልከእ ምድር አቀማመጥም ይሁን በሕዝብ ብዛት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንድትቀጥል ሀላፊነት አለበት እንጂ ከማንም መብት ጠያቂ አይደለም።
    ለሕውሀት አባላት (ለደጋፊ የትግራይ ተወላጆች)
    በመሰረቱ ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ለሰላምና መረጋጋት ሲባል አባላቱ ቁልፍ የስልጣን እርከኖችን ተቆጣጥረው ቆይተዋል። ይህ የበላይነት ፍትሐዊ ባይሆንም የጋራ አመለካከትና ስምምነት በኢትዮጵያ ህዝቦች እስኪሰርፅ አስፈላጊ ሆኖ ይሆናል። ይሁንና በኢኮኖሚው ውስጥ የገባው ኢፍትህሐዊ የበላይነት ማንም የማይታገሰው ነው። ስለዚህ ያለውን ፌዴራሊዝም በእንጭጭነቱ የተመረዘ እንዳይሆን እውነተኛ ነፃነት ለብሄር ብሔረሰቦች በኢኮኖሚውም በፖለትካውም አትንፈጉ። ያለው አንፃራዊ የብሄርብሄረሰብ ነፃነት በኢኮኖሚና በህዝቦች ግንኙነት ተሳስሮ ወደ እውነተኛ አንድነት የሚያስከዴውን መንገድ አትዝጉ።
    እኛ የአዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ስጋቶቻችንና ተስፋዎቻችንን የምንጋራበት መድረክ መፍጠር እንዳለብን እንገነዘባለን። ሀቅ ላይ የተመሰረቱ ተግባራዊ መፍትሄዎችን ከየትኛውም አቅጣጫ ቢመጡ በጥሞና እናደምጣለን። አሁን ባለችው ሀገራችን ያለው ስር የሰደደ ድህንት ብሔር እንደማይመርጥ ሁሉ መፍትሄውም እውነተኛ አንድነት ነው።

    ReplyDelete