Pages

Wednesday, March 14, 2018

የኃይሌ ገ/ሥላሴ ችግሩ፣ በሀብት መክበሩ!

ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የዛሬ 8 ዓመት ገደማ፣ በመስከረም ወር 2003ቱ የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ ተገኝቶ ንግግር አድርጎ ነበር። እናም "እናንተ ፖለቲካውን ሥሩ፣ ንግዱን ለኛ ተዉልን" የሚል ንግግር አድርጓል። ንግዱን አልተዉለትም። ሆኖም ምንጩ በሚታወቀው ሀብቱ እየተፎካከራቸው ነው። እነርሱ በወቅቱ የፈለጉት በሕዝቡ የሚወደደውን ሰው ወደ መድረካቸው በማምጣት ከሕዝባዊ መውደዱ መሻማት/መፎካከር ነበር። ከዚያ ቀጥሎ ለመጀመሪያ ግዜ ክብረወሰን ሲሰብር የለበሰውን ቲሸርት ለወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሥጦታ አበረከተላቸው። መብቱ ነው ግን ይህም አልበቃው፣ በአትሌቲክስ ሜዳ ክብረወሰን ሲሰብር ከተሰማው ደስታ ይልቅ እዚያ መድረክ ላይ በመገኘቱ የተሰማው ደስታ እንደሚበልጥ ተናገረ። ይሁን። ዞሮ ዞሮ ግን ኃይሌ ለዚህ ሙገሳው በምላሹ የጠየቀው 'ውለታ' "ንግዱን ተዉልን" የሚል ብቻ ነበር። በርግጥ ከዚያ በፊት "የአገር መሪነት ማን ይጠላል?" የሚል ቃል ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፤ የግንባሩ አባል ቢሆን የሆነ የአመራር ቦታ የሚከለክሉት አይመስለኝም። ሆኖም ከዚያ በፊት የነበረው የፖለቲካ ልምድ ግን የቅንጅት አመራሮችን በሽምግልና ሥም ይቅርታ ያስፈረመው የአገር ሽማግሌዎች አባልነት ብቻ ነበር። 

ኃይሌ ገብረሥላሴን በመተቸት ለመጻፍ ስንጀምር "ኃይሌ ለአገር ውለታ የዋለ፣ ከአትሌቲክስ ጡረታ ቢወጣም በኢኮኖሚው መስክ ብዙ ሰው ለመቅጠር የበቁ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተሠማራ" የሚሉ ማባበያዎችን ማስቀመጥ እንደ ደንብ ተቆጥሯል። እኔ ይህን አላደርግም። ለትችት የሚቀርቡት ሰዎች ስለአገር ምንም ውለታ ያልዋሉ ሰዎች ናቸው ማለት አይደለም። ሁሉም የአቅሙን አዋጥቷል። ኃይሌም ቢሆን በፍትሕ ዓይን ከማንም አይበልጥም። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ተቃውሞ ደግሞ የፍትሓዊነት ጥያቄ ነው። የፍትሓዊ አስተዳደር፣ የፍትሓዊ ውክልና፣ የፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል፣ የፍትሓዊ ዳኝነት፣ ወዘተ።

ከሁለት ዓመት በፊተ፣ በሕዳር ወር 2008 ቢቢሲ ሬድዮ ላይ ቀርቦ የነበረው ኃይሌ "ዴሞክራሲ ለአፍሪካውያን ቅንጦት ነው" ብሏል። 'ዳቦ ይቅደም' ማለቱ ነው። ሆዱን ያልሞላ ሰው ነጻነት አያስፈልገውም ከሚለው "የባርነት ለዳቦ" አስተሳሰብ ጋር የተስተካከለ አባባል ነው። አንድም በድሃ መሳለቅ ሲሆን፣ አንድም ደግሞ በዘር መፈረጅ ነው። ኃይሌ ለመናገር ያለው ድፍረት መልካም ነበር። የሚያሳዝነው ለሚናገረው ነገር ይዘት እና ውጤት ቅንጣት አለመጨነቁ ነው። ብዙ ሰዎች በሱ ንግግር የሚበሳጩት ካለው ሕዝባዊ ተቀባይነት አንፃር ንግግሩ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ነው። 'ከነጻነት ዳቦ ይቀድማል' የሚል መልዕክት ያለው ንግግር ሲያደርግ፣ ለሕዝቡ ጭቆናውን ለልማት ሲባል ቻሉት ማለቱ ነው፤ ለመንግሥቱ ደግሞ ሕዝባችሁን ዳቦ እየሰጣችሁ፣ ብትረግጧቸው ምንም አይለይም እያለ ነው። ነገሩ ከዘረኛ ነጮች አመለካከት ጋርም ይሠምራል። ለቅኝ አገዛዝ የተሰጠው አስተያየት (ማብራሪያ) ተመሳሳይ ነው። አፍሪካውያን ድህነት ይዘው እንጂ የምዕራባውያኑን ልብስ ቢያጌጡበት ያምርባቸዋል። የተመጣጠነ ምግብ ቢበሉ ይስማማቸዋል። እንደ ሕዝብ ሉዓላዊነታቸው ቢከበርላቸው ደስ ይላቸዋል። አፍሪካዊ ስለሆኑ የቅንጦት አይሆንባቸውም። ልማትና ዴሞክራሲም የሚጣረሱ ነገሮች አይደሉም። ሁለቱንም ባንዴ ማቅረብ ይቻላል። አፍሪካውያንም እንደሌላው ሁለቱንም ባንዴ ቢያገኙ አይጠሉም።

ከሰሞኑም በድጋሚ ኃይሌ አወዛጋቢ መልዕክቱን በድጋሚ አስተላልፏል። በኢቢሲ ከፓስተር ዳንኤል ጋር ቀርቦ የተናገረው ንግግር ውስጥ የሚያስቆጣ ይዘት ያላቸው ንግግሮች ደንቅሯል። ለምሳሌ "የውጭ እንትን ያለበት… የሚታይበት ነገር" በማለት የገለጸው እና በኋላ ሲተነትነው የግብጽ ስፖንሰርነት አለበት ለማለት እንደፈለገ የሚያስታውቀው ንግግሩ አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያን በቂ ብሶት የሌላቸው ይመስል የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳ ሰምቶ የውጭ ተልዕኮ አስፈፃሚዎች ሥራ ማስመሰል ተገቢ አይደለም። የውጪ ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተቃውሞ ሊደግፉ ይችላሉ እንጂ ሊፈጥሩት አይችሉም። አለቀ። 

ሲቀጥል ደግሞ "ቤት በመዝጋት፣ ትራንስፖርት በመዝጋት" መቃወም "የትም አገር የሌለ" ነገር ነው። ብሎ አጣጥሎታል። በመሠረቱ ኃይሌ ብዙ አገራት መሔዱ እውነት ነው። ነገር በሔደባቸው አገሮች ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ስርዓት፣ ለተቃዋሚዎች ተሳትፎ የሚሰጡትን ቦታ እና የሕዝብን ጥያቄ የሚያስተናግዱበትን መንገድ ያጠና ወይም ለማጥናት ግዜ ያገኘ አይመስለኝም። 

ሕዝቦች ወይም የሕዝብ ክፍሎች ጥያቄ ወይም ቅሬታ ሲኖራቸው፣ ሲያሻቸው በመሾምና በመሻር፣ ሲያሻቸው ፖሊሲ በማስወጣት እና በማስከለስ የሚኖሩበት ዘመን ላይ ነን። የኛው መንግሥት ደግሞ መጀመሪያ በነፍጥ ራሱን ሾመ፣ በመቀጠል ፍትሓዊ ባልሆኑ የምርጫ ሒደቶች ሥልጣኑን አስቀጠለ። የሕዝብ ወኪል ማኅበራትን እና ሚድያዎችን አደከመ። በዚህ መንገድ ተናጋሪ እራሱ፣ ፖሊሲ ቀራጭ እራሱ፣ ሁሉ ነገር ራሱ ከመሆኑ የተነሳ የተቃውሞ መንስዔዎቻችሁን ሳይቀር እኔ ራሴ ነኝ የምነግራችሁ አለ። ሕዝቦች በድርጅት የጀመሩትን ተቃውሞ አደናቀፈ። ድርጅቶች ፈርሰውና ተዳክመው ዜጎች በየፊናቸው መቃወም ቀጠሉ። 

ኃይሌ የተቃወመው የሠላማዊ ትግል መንገዶችን ነው። በመሠረቱ በሠላማዊ ትግል ሦስት ደረጃዎች አሉ። የመጀመሪያው ማግባባት ነው፤ በጽሑፍ፣ በሠልፍ… ብዙ ተሞክሮ ሰሚ አልተገኘም። ሁለተኛው፣ አለመተባበር ነው፤ መንግሥት መር ጥፋቶች ሲፈፀሙ የነዚያ ተግባራት አካል ላለመሆን ብዙ ተሞክሯል፣ እየተሞከረም ነው። ግን ሦስተኛውም ተጀምሯል። ጣልቃ መግባት፤ መንግሥት ለጥያቄዎች መልስ አልሰጥም ሲል እና ችግሮች ከድጡ ወደማጡ እየገቡ ሲያስቸግሩ ጣልቃ ገብቶ ይበቃል እንደማለት። ይህ ደረጃ ችግሩ እነርሱን ስለማይነካቸው ብቻ ሠላማዊ ትግሉን የሚቃወሙት ሰዎች የችግሩ ጥልቀት ባይገባቸውም ጫፍ ጫፉ እንዲታያቸው ማድረግ ነው። ችግሩ ከማይገባቸው ሰዎች መካከል የናጠጡ ሀብታሞች ይገኙበታል። 

በመሠረቱ የኃይሌ ችግር የብቻው አይደለም። የሙለር ሪል ኢስቴት ባለቤት አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ከአንድ ታዋቂ የጀርመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ዝግጁ አይደለችም" ብለዋል። የሚገባቸው መልስ ከላይ ለኃይሌ ከተሰጠው የተለየ ሊሆን አይችልም። ጥያቄው 'ሀብታሞችን ከሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተፃራሪ የሚያቆማቸው ምንድን ነው?' የሚል ነው። 

ለመልሱ ደጋግሜ ወደጠቀስኩት የአሴሞግሉ እና ሮቢንሰን 'Economic Origin of Democracy and Dictatorship' የሚል መጽሐፍ ላይ ያገኘሁት ኅልዮትን ልዋስ። የኢኮኖሚ ልኂቃን ሁሌም የአምባገነንነት ደጋፊዎች ናቸው። የሀብት ክፍፍል በሰፋ ቁጥር ሕዝቦች ያምፃሉ። ይህ ዴሞክራሲ በግዚያዊነት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ነገር ግን አሁንም የኢኮኖሚ ልኂቃኑ የመንግሥት ግልበጣ ደግፈው በኢኮኖሚ የብቻ የበላይ የሚያደርጋቸውን አምባገነናዊ ስርዓት ያቆማሉ። ማለትም ከድሀው ብዙኃን እጅግ የራቀ ሀብት ያላቸው ባለፀጎች ባሉበት አገር ዴሞክራሲ አይፈጠርም፤ ቢፈጠርም አይፀናም። ኃይሌ ገ/ሥላሴ እና ሌሎቹም ባለፀጎች ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ለዴሞክራሲ እንዳልተዘጋጁ የሚናገሩት ወይም እንዳይዘጋጁ የሚፈልጉት የኢኮኖሚ ልኂቅነት ጥቅማቸውን (privileges) ለማካፈል ስለሚቸግራቸው ነው። 

አሁን ኃይሌ በይፋ ፖለቲከኛ መሆን እንደሚፈልግ እየተናገረ ነው። ፖለቲከኝነት የሕዝብን ውክልና አግኝቶ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚሠራበት መሆኑን ተረድቶ፣ ይህን የኢኮኖሚ ልኂቅነት ቦታውን እስከመታገል መድረስ መቻል እንዳለበት ከአሁኑ በይፋ ያስብበት ዘንድ ጊዜው አሁን ነው። 

No comments:

Post a Comment