Pages

Wednesday, June 14, 2017

የቂሊንጦ እሳት፣ ወላፈኑን የቀመሱት እና በሰበቡ የተከሰሱት

(ፎቶ፤ ደህናሁን ቤዛ)

ይህ ታሪክ በደርግ ዘመን የተፈፀመ አይደለም። በኢሕአዴግ ዘመን የተፈፀመ የበደል ታሪክ ነው።… የምነግራችሁ ታሪክ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ "ለተሀድሶ ሥልጠና" ወደ አዋሽ ሰባት የፖሊስ ካምፕ የተጓዝኩትን ያስታውሰኛል። "ከሥልጠናው" ሰነዶች በአንዱ ላይ፣ በደርግ ግዜ ይፈፀሙ የነበሩትን የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች "ሰምቶ ማመን የማይችል ትውልድ ተፈጥሯል" ይላል። አባባሉ የኢሕአዴግን በትር እየቀመሱ ለኖሩ በጣም ያስቆጣል። ቀጥሎ የማወራላችሁ ታሪክ የደናሁን ቤዛ ታሪክ ነው። ደናሁን ደርግን የማያውቅ ወጣት ነው። ኢሕአዴግን ብቻ እያየ አድጎ ኢፍትሐዊነቱን መቀበል ያቃተው የመርሃዊ፣ ጎጃም ልጅ ነው።

ደናሁን በእነዘመኑ ካሴ በእውቄ መዝገብ፣ በፀረ ሽብርተኝነቱ አዋጅ ከተከሰሱት 9 ሰዎች 3ኛው ነው። ባለፈው ሳምንት የእስር ግዜውን ጨርሶ በፍቺ ተሰናብቷል። ከአባሪዎቹ መካከል አሸናፊ አካሉ በቂሊንጦ እሳት አነሳሽነት ክስ ተመሥርቶበታል። አንሙት የኔዋስ የተባለው ደግሞ ይህንን ለዐቃቤ ሕግ ከሚመሰክሩት መካከል ሥሙ ተጠቅሷል።
ቁጥቡን ደናሁንን የተፈታ'ለት አግኝቼው ነበር። ብዙ ነገር ተጨዋወትን። ሸዋሮቢት ወስደው በካቴና አስረው ሰቅለው ሲገርፉት ካቴናው የእጁ ወርች ላይ፣ እግሩ የታሰረበት ገመድ ደግሞ ከቁርጭምጭሚቱ በላይ ያወጡትን ሰምበር እያሳየኝ ነበር። ይህ ድርጊት ከተፈፀመበት 9 ወር ገደማ ቢሆንም ጠባሳው እስካሁን ከሰውነቱ አልከሰመም። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ስቃይ ውስጥ ምንም ያልሠራውን ወንጀል ባለማመኑ ይመስላል፣ ወይም ደግሞ ምናልባት ሌሎች እስረኞች ሥሙን ስላልጠቀሱ ከጓደኞቹ ቀላቅለው አልከሰሱትም፤ አባብለው ምስክር እንዲሆንባቸውም ማድረግ አልቻሉም።

የደናሁን ጀብዱ
የደናሁን ጥንካሬ የመጣው፣ ምናልባትም ካለፈው ልምዱ ይሆናል። ደናሁን እንዳጫወተኝ በትውልድ አካባቢው ያለውን ኢፍትሐዊነት ከጓደኞቹ ጋር መቃወም የጀመረ ሰሞን ከመኢአድ ሰዎች ጋር እየተገናኘ ማውራት ጀምሮ ነበር። አንድ ቀን ግን ድንገት በደኅንነት ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ዋለ። ወዲያው አንድ ትዕዛዝ ተሰጠው። "በል ጓደኞችህን ደውልና ቅጠራቸው።" ደናሁን ደወለ፤ "ሃሎ እከሌ፣ እኔ ተይዣለሁ እራሳችሁን አድኑ።" ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ሲደበደብ አደረ። እስከ ማግስቱ ጓደኞቹ ስልኩ ላይ መደወል ተያይዘዋል። ደኅንነቶቹ ሁለተኛ ትዕዛዝ ሰጡት፣ "በል አንሳውና አምልጫለሁ፣ የት ላግኛችሁ?" በላቸው አሉት። 'እንግዲህ ከዚህ በላይ አልችልም፤ ከገባቸው ይግባቸው' ብሎ እንደታዘዘው አደረገ። "እዛ የምናውቀው ቤት ና" አሉት። ሒድ ምራ ተባለ። ደናሁን ከኋል ከኋላው ታጅቦ እየመራ እያለ፣ ጓደኞቹን አሳልፎ መስጠት አላስቻለውም። ድንገት ፈትለክ ብሎ ሮጠ። ጓደኞቹንም ጠርቶ አብረው አመለጡ። በግዜው የታያቸው አማራጭ መሸፈት ብቻ ነበር። እዚያው የተገኘው ጫካ ውስጥ፣ የተገኘውን መሣሪያ ይዘው ሸፈቱ። የደናሁን እናት ለመያዣነት አንድ ቀን ታሰሩ። ደናሁን አሁንም ሳይማረክ ሲቀር ተፈቱ፤ ደናሁን ሌሊት ሔዶ ዓይናቸውን አየ። ከዚያ በኋላ በሌላ ቀን በተቀነባበረ ዘመቻ ከነጓደኞቹ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ደናሁን ከጓደኞቹ ጋር በደኅንነት ቢሮ ብዙ ስቃይ አየ። የግራ ጆሮው በደረሰበት ድብደባ መስማት አቁሟል። (ቂሊንጦ እያለ ሐኪም ቤት ይመላለስ ነበር።) ከዚያ በፊት የማያውቃት አዲስ አበባ ዓይኑ በጨርቅ ተሸፍኖ ገባ። ማዕከላዊ ከአራት ወር በላይ ቆይቶ ክስ ተመሥርቶበት ቂሊንጦ ዞን ሁለት ተመደበ።

የፍርድ ቤት ክርክሩ ከ3 ዓመት በላይ ፈጅቷል። ከአባሪዎቹ ጋር የተለያየ ቅጣት ሲቀበሉ እሱ 5 ዓመት ከመንፈቅ ነበር የተፈረደበት። ወደ ዝዋይ ወኅኒ ቤት ከመጫኑ በፊት ግን - ነሐሴ 28, 2008 - የቂሊንጦ እስር ቤት በእሳት ጋየ።
የቂሊንጦ አስተዳደር በሽብር የተከሰሱትን  እና ሌሎች "የማይወዳቸውን" እስረኞች ሸዋ ሮቢት በማዛወር "ባልታወቁ ሰዎች" እንዲመረመሩ አደረገ።

ምርመራው እንዴት ነበር?
ደናሁን ላይ ሸዋ ሮቢት የደረሰበትን ሰምቼ ቂሊንጦ ጥየቃ ሔድኩኝ እና ከተከሳሾቹ ጥቂቶቹን አናገርኩኝ። እግራቸውን ሊያሳዩኝ ባይችሉም፣ እጃቸው ላይ የተሰቀሉበት ካቴና ያወጣባቸውን ክርክር ጠባሳ አሳዩኝ። ምርመራው ወንጀል ለማጋለጥ በታክቲክ አልተካሔደም። ይልቁንም፣ "ከእስር ቤት ለማምለጥ ብለን እስር ቤቱን በእሳት አጋይተነዋል" ብላችሁ እመኑ የሚል ነበር። በማመን ብቻ ስቃዩ አይቆምም። ተጠርጣሪዎቹ የመርማሪዎቹን ቃል ሲያምኑ፣ ይህንን ለማድረግ "ከማን ጋር ምን አሴራችሁ?" በመሳሰሉ ጥያቄዎች ነገሩን ከስቃይ ለእፎይታ ሲሉ ያመኑት ሳይሆን የምር የተዘጋጁበት እስኪመስል ድረስ ምርመራው ይቀጥላል። የዐቃቤ ሕግ እና "የመርማሪዎቹ" መመሳሰል የሚታየው ሁለቱም ክስተቱን ለጥጠው ከግንቦት ሰባት ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ነው።

ከተከሳሾቹ በጥቂቱ
ሚስባህ ከድር ከፖለቲካ ጋር ያልተያያዘ ክስ የነበረበት እስረኛ ነው። አሁን ከክሱ ነጻ ቢወጣም በቂሊንጦ እሳት ሰበብ የሽብር ሴራ ክስ ከተመሠረተባቸው 38 ሰዎች ውስጥ 22ኛው በመሆኑ በፍቺ አልተሰናበተም። ሚስባህ ሴራውን በገንዘብ ደግፈሃል የሚል ክስ ነው የተመሠረተበት። ስለምርመራ ሒደቱ ሲያጫውተኝ "አውራ ጣቶቼ አንድ ላይ በጅማት ታስረው፣ በካቴና እጆቼ ተጠፍረው ሲሰቅሉኝ ሕመሙ ሁሉ ወደ አውራ ጣቶቼ ሔደ። ጣቶቼ ሊፈነዱ ደረሱ።" ካለ በኋላ "በዚህ አጋጣሚ ነፍሳችን አውራ ጣታችን ጫፍ ላይ እንዳለች ለማረጋገጥ ቻልኩ" በማለት አሰቃቂውን ታሪኩን ይቀልድበታል። በዚህ ዓይነት ከተሰቀሉ በኋላ አንድ እግራቸው ወደጎን ተወጥሮ ይታሰሩና ውስጥ እግራቸው ይገረፋል። ራሳቸውን እንዳይስቱ ቶሎ ቶሎ ውኃ ይደፉባቸዋል።

ሚስባህ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተሰቅሎ እያለ "መርማሪው" ስልክ በሆነች ሴት ሲደወልለት የተናገረውን በጣም እያዘነ ነበር የነገረኝ። "የት ነህ? ብላው ይመስላል፣ "አሁን ቶርኖ ቤት ነኝ" አላት።

ሌላኛው ተከሳሽ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የአዲስ የልብ ሕክምና ሆስፒታል ባለቤት ናቸው። ከ30 ዓመታት በላይ በስዊድን ሀገር ያካበቱትን ልምድ ይዘው ነው ኢትዮጵያ የመጡት። ከጉምሩክ ባለ ሥልጣናት እና ነጋዴዎች (ከእነ መላኩ ፈንታ) ጋር ነው በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት። እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ተከራክረው ከክሱ ነጻ ቢወጡም ከእስር አልተፈቱም። ምክንያቱም እዚሁ መዝገብ ላይ 13ኛ ተከሳሽ ናቸው። የእርሳቸውም ክስ እንደሚስባህ "የሽብር ሴራውን" በገንዘብ ደጉመዋል የሚል ነው። ዶ/ር ፍቅሩ የቂሊንጦ እሳት የተነሳ ዕለት ታመው ቃሊቲ ወኅኒ ቤት ሕክምና ላይ ነበሩ። ከሳሾቻቸው "እሳቱ ከመነሳቱ ቀድመው ራሳቸውን አሳምመው ነው ለሕክምና የሔዱት" በሚል ለክሱ ረቂቅ ገጽታ አላብሰውታል።

የመዝገቡ አንደኛ ተከሳሽ የአየር ኃይሉ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ነው። ማስረሻ ሰጤ "ከአየር ኃይሉ ኮብልሎ ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀል ሲል ተይዟል" በሚል ተከሶ የተፈረደበት እስረኛ ነው። እሳቱ በተነሳ ዕለት ቅጣት ክፍል ውስጥ [ከእነ በቀለ ገርባ ጋር] ከውጭ ተቆልፎበት ነበር። ክሱ፣ "ከእስር ቤት አምልጠው ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ ያሰቡ ሰዎችን አደራጅቷል" የሚል ይዘት አለው።

ፍቅረማርያም አስማማው "ሠላማዊ ትግል አያዋጣም" ብለው ከሰማያዊ ፓርቲ በመውጣት ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ ሲሔዱ ከተያዙት ሦስት ወጣቶች አንዱ ነው። አራት ዓመት ተፈርዶበት ወደ ዝዋይ ከተዛወረ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነበር ቂሊንጦ እሳቱ የተነሳው። እሱም "ሴራው" ውስጥ አለበት ተብሎ ተከሷል።

የዚህ የክስ መዝገብ ጭብጥ "ሴራው ከወራት ጀምሮ ሲመከርበት የነበረ ነው" ይላል። በርግጥ ከእሳቱ ጋር በተያያዘ ሌሎችም 121 እስረኞች በእነ ያሬድ ሁሴን መዝገብ ተከሰዋል። እነዚህኞቹን የክስ መዝገቡ "የዱርዬው ቡድን" ይላቸዋል። በነፍስ ማጥፋት ነው የተከሰሱት። እነሱ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ሲሆኑ፣ 38ቱ ደግሞ "የሴራው" ባለቤቶች መሆናቸው ነው።

የእሳቱ መንስዔ ምን ነበር?
እሳቱ ከመነሳቱ በፊት "አተት እንዳይገባ" በማለት አስተዳደሮቹ ከቤተሰብ የሚመጣ ምግብ እንዳይገባ በሚል ከልክለው ነበር። እህል ውኃ የማይለውን የማረሚያ ቤቱን "ደያስ" ጭራሽ ከማይቀምሱት እስረኞች ጀምሮ አልፎ አልፎ ብቻ ጠያቂ ያላቸው እስረኞች ሳይቀሩ ውሳኔውን በፅኑ ተቃውመውታል። በዚሁ ሳቢያ የተጀመረው አድማ ነው እሳቱን እስከመቀስቀስ የደረሰው። ጉዳዩን ለማጣራት ባደረግኩት ሙከራ "እሳቱን" የቆሰቆሱት እስረኞች ናቸው። እሳቱ ወዲያው ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አንድ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ሲያስረዳ፣ ዞን ሁለት ጊቢ ውስጥ ጥቁር ጭስ ከመሙላቱ የተነሳ ነፍሳቸው የተረፉት ሰዎች ግድግዳ እየዳበሱ ነው የወጡት። ብዙም ጉዳት ያልደረሰበት ዞን አንድ ውስጥ የነበሩ ሌላ የዐቃቤ ሕግ ምስክር "እጄን ወደላይ አድርጌ ከዞኑ ግቢ ልወጣ ስሞክር ከጎኔ አንድ ሰው በጥይት ተመቶ ሲወድቅ ደንግጬ ተመለስኩ" ብለው ምስክርነት ሰጥተዋል። ታሪኮቹ ሲገጣጠሙ። መንስዔው የቤተሰብ ምግብ መከልከላቸው ያስነሳው ተቃውሞ ነው። እሳቱን የለኮሱት የተወሰኑ እስረኞች ናቸው። ከእሳቱ እና ከጭሱ ለማምለጥ ከዞን ጊቢዎች የሮጡት የጥይት እራት ሆነዋል። አስለቃሽ ጭስም ይተኮስባቸው ነበር። በጭስ ታፍነው የሞቱም አሉ። ከሳሾች ለሀሉም ሟቾች ተከሳሾችን ጥፋተኛ ለማድረግ እየጣሩ ነው፤ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ግን "በጥይት የተገደሉ ስላሉ ይህን ያደረጉ የጥበቃ አባላት መጠየቅ አለባቸው" ብሏል ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት። ሪፖርቱ ሟቾቹ 23 ናቸው ቢልም፣ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት ግን ሟቾቹ ከ70 በላይ ናቸው ብሏል። በወቅቱ እዚያ የነበሩ እስረኞችም ቁጥሩ ከ23 እንደሚበልጥ ያለጥርጥር ይናገራሉ።

ክሱ እንዴት እየሔደ ነው?
በጣም የደኅንነት ሠራተኞች እና የጥበቃ አባላት ክትትል በሚደረግበት የዚህ መዝገብ ችሎት፣ ዐቃቤ ሕግ 85 ምስክሮች አስመዝግቧል። በዐሥር ቀናት ስሚ የተደመጡት ስድስት ምስክሮች ብቻ ናቸው። ተከሳሾቹ በምርመራ ወቅት የደረሰባቸውን የሰብኣዊ መብት ጥሰት አቤት ብለዋል። ችሎቱ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ትዕዛዝ ጽፏል። ኮሚሽኑ ግን የሚያረካ መልስ አልሰጠም። እኔ የተመለከትኩት አገናኝ የተባለ እስረኛን በተመለከተ በኮሚሽኑ የተሰጠውን መልስ ነው። ኮሚሽኑ "እስረኛው መደብደቡን በምስክር ቢያስረዳም የደብዳቢዎቹን ማንነት ማስረዳት ስላልቻለ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መፈፀሙን ማረጋገጥ አልቻልኩም" የሚል ምፀት የተሞላው መልስ በጽሑፍ አቅርቧል።

አብዛኛዎቹ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች እስረኞች በመሆናቸው ተከሳሾቹ "ተገድደው ነው በሐሰት የሚመሰክሩት" በማለት እያማረሩ ነው። የሚሰማቸው የሚያገኙ አይመስልም።
በዚህ ዓይነት ዐቃቤ ሕግ ሁሉንም ምስክሮች አስደምጣለሁ ካለ ሒደቱ እጅግ ረዥም ግዜ ይወስድበታል።

የደናሁን መጨረሻ
ከመርሃዊ ተነስቶ ማዕከላዊ፣ ከዚያም ቂሊንጦ ገብቶ ከሸዋ ሮቢት ምርመራ በኋላ ከዚህ አዲስ ክስ የተረፈው ደናሁን ወደ ዝዋይ ተዛወረ። ማዕከላዊ የቆየበት ጊዜ የእስር ጊዜው ላይ እንዲቆጠርለት ቢጠይቅም አልተካተተለትም። እንዲያም ሆኖ በአመክሮ ሚያዝያ 21፣ 2009 መፈታት ነበረበት። የቂሊንጦ እሳት ከመነሳቱ ሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ደናሁን ለመጨረሻ ጊዜ ከመታሰሩ በፊት ሌሊት ያያቸው እናቱ የመሞታቸው መርዶ ተነግሮት ነበር። ከዚያ መሪር ሐዘኑ ሳይወጣ ነው ሸዋ ሮቢት ተልኮ የተደበደበው። መርማሪዎቹ የእናቱን ሞት ሳይቀር እያነሱ በቁስሉ ላይ እንጨት ይሰዱበት እንደነበር አጫውቶኛል።

ይህ በእንዲህ እያለ በግንቦት ወር የመጨረሻ ሳምንት፣ ደናሁን ቤዛ ከዝዋይ ወኅኒ ቤት በድንገት በፍቺ ተሰናበት። የማያውቃትን አዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ተመለከታት። ከዚያም ወደትውልድ አካባቢው በመሔድ ቤተሰቦቹን ተቀላቀለ። ደናሁን በእስር ቆይታው አንገቱን መጽሐፍት ውስጥ ቀብሮ ሲያነብ ነው የከረመው። "የአገራችንን ሁኔታ በደንብ የተረዳሁት ከመታሰሬ በፊት ሳይሆን በኋላ ነው" ይላል። አሁን ከቤተሰቡ ጋር ተቀላቅሏል። ወንድሙ የእናቱን ሞት ከቤተሰቡ ጋር እርም እያወጣ መሆኑን ነግሮኛል። ይሁን! ለቅሶም ቢሆን ከወገን ጋር ያምራል።

No comments:

Post a Comment