በበፍቃዱ ኃይሉ
ሰሞኑ ‹‹የሕገ-መንግሥቱ›› ይከበር የበይነመረብ ዘመቻ 2ኛ ዙር በአንቀጽ 29 (ሐሳብንና
አመለካከትን የመያዝና የመግለጽ መብት) ይከበር ዙሪያ በዞን ዘጠኝ አስተባባሪነት እየተካሄደ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ለዘመቻው ግብአት
እንዲሆኑ አንዳንድ እውነታዎችን ስለሕገመንግሥቱ እና ስለቀደሙት፣ ስለአተገባበሩም ጭምር እነሆ፡-
ሐምሌ 30/1966 በንጉሡ ነገሥት
መንግሥት ረቂቅ ሕገ-መንግሥት፡-
አንቀጽ 25/1
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሐሳብ
ነፃነት አለው፡፡ ማናቸውንም ሐሳብ በንግግር፣ በጽሑፍ ወይም በሌላ ዘዴ የመግለጽና የማሰራጨት እንዲሁም ሌሎች የገለጹትን የማወቅ
መብት አለው፡፡
አንቀጽ 25/2
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ
ሪፐብሊክ መስከረም 1/1980 ያወጣው ሕገ-መንግሥት፡-
አንቀጽ 47/1
የኢትዮጵያውያን የንግግር፣ የጽሑፍ፣
የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ትዕይንተ ሕዝብ የማድረግና በማኅበር የመደራጀት ነጻነት የተረጋገጠ ነው፡፡
አንቀጽ 47/2
መንግሥት ለነዚህ ነጻነቶች ተግባራዊ
መሆን አስፈላጊውን ቁሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት (ሕዳር 29/1987)፡-
አንቀጽ 29
የአመለካከት እና
ሐሳብን በነጻ የመያዝና
የመግለጽ መብት
1. ማንኛውም
ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት
የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ
ይችላል፡፡
2. ማንኛውም
ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት
ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት
አለው፡፡ ይህ ነጻነት
በሀገር ውስጥም ሆነ
ከሀገር ውጭ ወሰን
ሳይደረግበት በቃልም ሆነ
በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣
በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ
ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና
ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት
ነጻነቶችን የካትታል፡፡
3. የኘሬስና
የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣
እንዲሁም የሥነ ጥበብ
ፈጠራ ነጻነት ተረጋግጧል፡፡ የኘሬስ
ነጻነት በተለይ የሚከተሉትን
መብቶች ያጠኝልላል፣
ሀ/
የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም
መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ/
የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት
መረጃ የማግኘት ዕድልን፡፡
በተራ ቁጥር 1 እና 2 ላይ እንደተመለከተው ንጉሡም ሆኑ ደርግ ሙሉ ሐሳብን የመግለጽ
መብት መውጫቸው/መውደቂያቸው ሰዓት ላይ ለመስጠት ሞክረዋል/ሰጥተዋል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የሽግግር መንግሥቱ ሕገ-መንግሥት ላይ
የብሔሮች መብት እስከመገንጠልን ያሰፈረ ቢሆንም ስለሐሳብ ነጻነት የሚናገረው የለም፡፡ በ1987ቱ ሕገ-መንግሥት ግን የተሻለ የሚባል
የሐሳብ ነጻነትን ፈቅዷል፡፡ ከሌሎቹ መንግሥታቶች እርምጃም የሚለየው የፕሬስ ሕጉ ወጥቶ በተግባር ላይ የሚውልበት መንገድ መመቻቸቱ
ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም ነገሮች ባሉበት አልቀጠለም፡፡ የተሻሻለው የፕሬስ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅና ሌሎችም መልሰው የመብቱን
ወሰን አጥብበውታል፡፡ ነገር ግን አሁን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ገደብ የሚከናወነው በአስተዳደራዊ አፈና ነው፡፡
ከ1983 ወዲህ ያሉ እውነታዎች፡-
1.
የመጀመሪያው ነጻ ጋዜጣ ‹‹ዕይታ››
ይባላል፤ የፕሬስ አዋጁ ከመውጣቱ በታኅሳስ ወር 1984 መታተም ጀምሯል፡፡ የቅጁ ብዛት ከ50,000 እስከ 70,000 ይደርስ ነበር፡፡
በወቅቱ በርካታ ‹‹የስም ማጥፋት›› ክሶችን በመንግሥት አስተናግዷል፡፡ በመጨረሻም የቅጂ ብዛቱ ወደ 5,000 ደርሶ በጥቅምት ወር
1986 ሕትመቱ ተቋርጧል፡፡ (ቅድመ ምርጫ 97 አካባቢ ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች እትም እስከ 1050,000 ድረስ ከፍ ብሎ የነበረ
ቢሆንም ከዚያ በኋላ እያሽቆለቆለ መጥቶ በ2004 መጨረሻ ላይ ሕትመቱ የተቋረጠው እና የወቅቱን እጅግ ከፍተኛ ቅጂ ያሳትም የነበረው
ነጻ ጋዜጣ ፍትሕ ነበር፡፡ ፍትሕ የታገደበትን የመጨረሻ እትሙን በ30,000 ቅጂ ነበር ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያዘዘው፡፡
በጥር ወር ስርጭት ላይ ከዋሉ ጋዜጦችን ያስመዘገበው የሪፖርተር እሁድ እትም ሲሆን እሱም 11,000 ነው /የብሮድካስት መረጃ/)
2.
እስከ ሐምሌ 1989 ብቻ
265 ጋዜጦች እና 120 መጽሔቶች ሕጋዊ ፈቃድ ወስደዋል፡፡ …… (በጥር ወር ለስርጭት የበቁት 12 የፖለቲካ ጋዜጦች፣ 6 የስፖርት
እና 1 የጤናና ስነልቦና ጋዜጦች እና 21 መጽሔቶች ናቸው፡፡)
3.
በሕግ ባይከለከልም በኢትዮጵያ
ለአንድም የግል ተቋም የቴሌቪዥን አገልግሎት አልተፈቀደም፡፡ ብቸኛው የግል አገር አቀፍ ሬዲዮ ስርጭት የፋና ሬዲዮ ሲሆን ሬዲዮ
ፋና ንብረትነቱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ነው፡፡ ሬዲዮ ፋና በተለያዩ ከተሞች ኤፍ ኤም ስርጭቶችን በማሰራጨት፣ የራሱን
ሕንፃ በማስገንባት ወደኮርፖሬትነት ለማደግ የቻለ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ሬዲዮ ጣቢያ ነው፡፡ ሸገር እና ዛሚ ኤፍ ኤሞች ሌሎች
‹‹በገለልተኛ›› የተያዙ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ሲሆኑ፤ የሸገር ትኩረት ማኅበራዊ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ የዛሚ ትኩረት ደግሞ የመንግሥትን
ፖሊሲ ማበረታታት እና ማሞካሸት ላይ ያተኮረ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment