Pages

Sunday, March 4, 2012

እቴጌ ጣይቱ ብጡል እና እቴጌ አዜብ መስፍን

From አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ይህንን ጽሁፍ ማንበብ ለሚፈልጉ፡- ማስጠንቀቂያ ቁጥር አንድ፤ ጽሁፉን በከፊልም ሆነ በሙሉ ለቀዳማይት እመቤቲቱ ማስነበብ አይፈቀድም፡፡ ማስገንዘቢያ ቁጥር ሁለት፤ እቴጌ አዜብን አንቺ እቴጌ ጣይቱን አንቱ እያልኩ የጻፍኩት፤ እቴጌ አዜብ ወጣት ስለሆነች (ወይም እንደወጣት ስለሚያደርጋት) ሳይሆን ከኢቲቪ በቀር አንቱ ብሎ የሚጠራት ሰው ሰምቼ ስለማላውቅ÷ እንደአርቲስት ‹አንቱ› አትባል ይሆናል ብዬ ነው፡፡

የዛሬን አያርገውና የሃገራችንን እቴጌዎች ጀብዱ መዘንጋት አይቻልም ነበር፡፡ እቴጌ ተዋበች ካሣን ‹‹እኔ ጀግና ወንድ እወዳለሁ›› እያሉ በጠላት ላይ የማያወላዳ አቋምና እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጓቸው ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ብጡልንም የምናውቃቸውና የምናስታውሳቸው በዚሁ መሰል ጀግንነታቸው ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ የአድዋ ጦርነት ላይካሄድ፣ ኢትዮጵያም የውጫሌ ውል አንቀጽ 17ን ተቀብላ ልትቀጥል የምትችልባቸው ዕድሎች እንደነበሩ የሚገምቱ የታሪክ ባለሙያዎች አሉ፡፡ 

እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ ይሄ ዛሬ የምንመካበት ጥቁር ሕዝቦች ነጮችን ለመጀመሪያ ጊዜ ድል የነሱበት፣ ያልታጠቁ ሕዝቦች የታጠቀና የሰለጠነ ሰራዊትን መደምሰስ እንደሚችል ያሳየንበት የአድዋ ድል አይፀነስም ነበር፡፡ ከዚያም በላይ እቴጌ ጣይቱ ባይኖሩ ኖሮ የአድዋ ጦርነትን አናሸንፍም ነበር (ወይም እናሸንፋለን ለማለት ይከብድም ነበር) ምክንያቱም የጦርነቱ መደምደሚያ ከሆነው የአድዋ ጦርነት በፊት መቀሌ ላይ - ጣሊያኖቹ የሰሩት ምሽግ፣ ጫማ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያን የማያስደርስ፣ በባለእሾህ የሽቦ አጥር የታጠረ፣ በጠርሙስ ስብርባሪ መሬቱ የተነጠፈ ነበር፡፡ ያንን ምሽግ ሰብረው መግባት የሞከሩት ኢትዮጵያውያን የሳት እራት ሆነው ቀርተዋል፡፡
በመጨረሻ ግን ጣሊያኖቹን ውሃ፣ ውሃ የሚያሰኝ መላ ለኢትዮጵያውያን አርበኞች የዘየዱት እቴጌይቱ ነበሩ፡፡ መፍትሄውም ጠላት የሚጠቀምበትንና ከምሽጉ አቅራቢያ የሚገኘውን የውሃ ምንጭ ገድቦ መክበብ ነበር፡፡ በሦስት ሜትር ካብና የእሾህ ሽቦ ታጥሮ የመሸገው የኢጣሊያ ሰራዊት በውሃ ጥም አለቀ፡፡ በመጨረሻም እጅ ለመስጠትና ለእርቅ ደረሰ፡፡ ይሄ ድል ባይገኝ ኖሮ አርበኞቻችን ቀስ በቀስ ረግፈው፣ ጣሊያኖችም ድልን ሊያጣጥሙ ይችሉ ነበር - ምስጋና ለጣይቱ!

እምዬ ምኒልክ ‹‹እምቢ›› ካፋቸው ማውጣት የሚቸግራቸው ሰው በመሆናቸው የማይጥማቸው ነገር ሲከሰት ‹‹እሺ፤ ነገ›› ማለት ያበዙ ነበር ይባላል፡፡ ነገር ግን በአገር ጉዳይ እሺታ ብቻ ሳይሆን እምቢታም ወሳኝ ስለሆነ ያንን ክፍተት በመሙላት እቴጌ ጣይቱ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አዜብስ? ወ/ሮ አዜብ ከባለቤቷጋ ከአንድ ባሕር ነው የተቀዳችው፤ ሁለቱም እሺ አያውቁም፡፡ እሷ እንኳን እሺታ ብታውቅ የባለቤቷን ክፍተት ትሞላ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ከእምቢታዋም በላይ ያልተጻፈው የከልካይነት መብቷ ጉዳይ ነው፡፡

በእቴጌ ጣይቱ ዘመን የነበረው ስርዓት እንደሚፈቅደው ጣይቱ ከምኒልክ ያልተናነሰ ስልጣን ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ያንን ስልጣናቸውን ተጠቅመው ቢሾሙ፣ ቢሽሩ አይገርምም፡፡ ወ/ሮ አዜብ ግን ወደዚያ ስርዓት ተመልሳ ይሁን ወይም በገዛ ፍቃድዋ ሳይታወቅ፣ ከዘመኑ ባፈነገጠ አሠራር የመሻርና የመሾም ባለመብት ነች እያሉ ብዙዎች ይምጰረጰሩላታል፡፡ ድንገት የሕወሃት ፖሊት ቢሮ አባል ሆና መገኘቷ፣ መጀመሪያ ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን ለባለቤታቸው ሊያወርሱ ነው እንዴ በሚል አስደንግጦን ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንደዛቱት ከለቀቁ፣ በወዘሮዋ አማካኝነት በእጅ አዙር የሚመሩበትን መንገድ መፍጠራቸው አይቀሬ ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ አንዳንድ የዳያስፖራ መንደር መረጃዎችም ይህንኑ እየነገሩን ነው፡፡ ወይዘሮ አዜብ የሕወሃትን አመራር በባለቤቷ በኩል እያሾረችው መሆኑ ያስከፋቸው የሕወሃት ሰዎች እንዳሉ ተጽፎ አንብበናል፡፡

ይሄ ብቻም አይደለ፤ በመላው ዓለም ከተለመደው የፕሬዚደንት ሚስት ቀዳማይነት - ቀዳማይ እመቤትነቱን ከግርማ ወልደጊዮርጊስ ባለቤት የቀማችው ሴትዮይቱ የኢሕአዴግን በኢትዮጵያ ግዙፍ የኢኮኖሚ ሞኖፖሊ የመፍጠር ሕልም ታሳካለች የተባለላት ሰው ናት፡፡ ለዚያም ይመስላል የኤፈርት ሥራ አስፈፃሚዎች አንዷ ለመሆን የበቃችው፡፡ በጫት የውጭ ንግድም ቢሆን ተወዳዳሪ አልተገኘላትም፡፡ ከዚህም በላይ አሁን ደግሞ በሁሉም ቢዝነሶች ላይ እጆቿን ማስገባት እንደምትፈልግ እየተነገረ ነው፡፡ ወ/ሮ አዜብ ግን በዚህ አትስማማም፡፡ እንዲያውም ለልጆቿ የስኮላርሺፕ ለመክፈል ፍዳዋን እንዳየች ነው እሷ የምትናገረው፡፡ “ሃብት ፍለጋ ቢሆን ኖሮ” ብላለች ከECTV ጋር አድርጋ በነበረው ቃለ ምልልስ፣ “የመለስን ጭንቅላት መሸጥ ይቻል ነበር፤ ከመሪዎች ሁሉ ድሃ እኛ ነን”  ብላ ቁጭቷን ተናግራለች፡፡

ባለፈው ሰሞን ኃይሌን የሪዞርትህ ባለድርሻ አድርገኝ እያለችው ነበር ሲባል ሰምቼያለሁ (አቶ በረከት ስምኦንስ ቢሆኑ ‘ሲባል ሰምቻለሁ’ እያሉ አይደል መጽሃፋቸውን የጻፉት?)፣ ከባለፈው ሰሞን በፊት ደግሞ አሁን ከሃገር ኮብለለው ብሔራዊ የሽግግር ምክርቤት የመሰረቱት የዩኒቲ ዩንቨርስቲው ዶ/ር ፍስሐ እሸቴንም በቢዝነስ ካልተሻረኩህ እያለች ታስቸግራቸው ነበር አሉ፡፡ ምን ያልተባለ አይሸትም (Rumor has it!) ዶ/ሩ ራሳቸውምበስተመጨረሻ የሴቶች ፓንአፍሪካ ዩንቨርስቲን ሊከፍቱ የ20 አፍሪካ ዲፕሎማቶች ከፈረሙላቸው በኋላ “አዜብ ከለከለችኝ” አላሉም?

“ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ በስተጀርባ ጠንካራ ሴት አለች” ይባላል፡፡ አዎ! የአድዋ ድልን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ካበሰሩት ዳግማዊ ምኒልክ ጀርባ እቴጌ ጣይቱ ነበሩ፡፡ 21 ዓመታትን ወንበራቸው ሳይናጋ ከተቀመጡት ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ ጀርባም÷ ወ/ሮ አዜብ መስፍን አለች፡፡

------
In my defense for her, ወ/ሮ አዜብ የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ ማሕበር ምክትል ፕሬዚደንት በመሆን ሰብአዊ ተግባር ላይ መሰማራቷ ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment