Pages

Friday, February 10, 2012

አማርኛ በመዝገብ ላይ


ዘፍጥረት 29÷11-16 (በግዕዝ)
በሚያውቁት ቋንቋ መናገር አንጀትን ያርሳል፡፡ ለዚህም ነው አንዳንዶቻችን በውጭ ቋንቋ፣ ከውጭ አገር ሰዎች አውርተን ስናበቃ ነፃ የመውጣት ስሜት የሚሰማን፡፡ ‘ሶሲዮሎጂስቶች’ ቋንቋን ከባሕል ገንቢ ወይም ገላጭ ቅንጣቶች መካከል ዋነኛ ሲሉ ያኖሩታል፡፡ የአንድ ማሕበረሰብ ባሕል እና ዕውቀት በቋንቋው ውስጥ ይገለጣል፡፡ ምንም እንኳን ቋንቋዎች ሁሉ ሙሉ ናቸው ብንልም÷ ባሕሉ የማያውቃቸው ብዙ ቃላቶች ግን እንደሚኖሩት መካድ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ በአማርኛችን snow (‘ስኖው’) ለሚለው ቃል አንድም አቻ ትርጉም የለውም፡፡ በሰሜን አሜሪካ እና ሩሲያ መካከል፣ አላስካ አካባቢ የሚኖሩ የዚያው አካባቢ ጥንታዊ ሕዝቦች (እስኪሞዎች ይበላሉ) ስኖውን የሚወክሉ በርካታ ቃላቶች አሉዋቸው፡፡ ለምሳሌ አፑት ~ መሬት ላይ የተከመረ ስኖውጋና ~ እየዘነበ ያለ ስኖውፒቅሲርፖቅ ~ አየርላይ እየተንሳፈፈ ያለ ስኖውቂሙቅሱቅ ~ የስኖው ሰፈፍ፡፡

በሃገራችን አሁን ዘመን እየቀየረን መጣ÷ እንጂ ሴትን ለማማለል ገዳይነት ነበር የሚያስፈልገው፡፡ አንበሳ መግደል፣ ጠላትን በመግደል… ለዚህም ነው Romance ለሚለው ቃል ትርጉም (በአማርኛ) የማይገኝለት፡፡ ብቸኛው romanticነት ጀግንነት ነበርና፡፡ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ወራጅ ወንዞች እንጂ ውቅያኖሶች አይጎራበቱትም÷ ለዚህ ነው በአማርኛ waterbank፣ shore፣ beach ለመሳሰሉ ቃላት ትርጉም ማግኘት የሚቸግረን፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር የአማርኛ ቃላቶችን ወደእንግሊዝኛ ልንመልስ ስንሞክርም ይገጥመናል፤ ችግሩ እንግሊዝኛው ላይ እርግጠኛ መሆን ስለሚቸግረን ይሄ፣ ይሄ ማለት ያስፈራናል፤ እላይ የተዳፈርነው የራስ መቼም የራስ ነው በሚል ብሒል ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ‹ይሉኝታ› ለሚለው የአማርኛ ቃል የእንግሊዝኛ አቻ አንድ ቃል ፈልጌ አጥቻለሁ፡፡ ምናልባት አፈ-እንግሊዞቹ ይሉኝታ ስለማያውቁ ይሆን?

ለዚህም ነው ቋንቋዎች ቃላት እንዲዋዋሱ የሚመከሩት፡፡ ቋንቋ ሲወራረሱ ባሕልም ይወራረሳሉ፡፡ romance እና dating የሚሉ ቃላትን ስንዋስ ተግባሩንም ጭምር ነው፡፡ እንግዲህ አፈ-እንግሊዞቹም ይሉኝታ የሚለውን ቃል ሲዋሱ አብረው ሐሳቡንም ይዋሳሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ የሚበረታታ ተፈጥሯዊ ሒደት ሆኖ ሳለ፤ አንዳንዴ ከባዕድ ቋንቋዎች የምንዋሳቸው ቃላት የእኛን ለማንኳሰስ ብቻ ካልሆነ በቀር ፋይዳ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ቃላቱ እኩያ ሃገርኛ ቃላት አሏቸውና ነው፡፡ ይህንንም አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ "ቋንቋና ቋንቋ መወራረሳቸው ያለ ቢሆንም፣ የራስን እየገደሉ የባዕድን መውሰድ ግን ዝሙትነት ነው" ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ሰሞኑን አንድ የአማርኛ (በአማርኛ) መዝገበ ቃላት ሳገላብጥ ነበር፡፡ የባሕሩ ዘርጋው ‹ዘርጋው የአማርኛ መዝገበ ቃላት› ነው፤ በ1994 የታተመ፡፡ መዝገበ ቃላቱ ከ22,000 በላይ ቃላትን እንደያዘ ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡ 11 ዋቢ መጽሃፍቶችን ተጠቅመው ነው ያሰናዱት፡፡ መዝገበ ቃላት ማሰናዳት እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ጸሃፊው መግቢያው ላይ ገልጸዋል፡፡ እኔም ስለምስማማበት ለዚህ ስራቸው ያለኝ አድናቆት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ሆኖም ማተኮር የምፈልገው ሰፊው መልካም ሥራ ላይ ሳይሆን፣ ጥቂቶቹ ለኔ እንከን መስለው የታዩኝ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ በርግጥ እንከኖቹ ላይ ማተኮር ያስፈለገኝ መወያየቱ ለወደፊቱ ይጠቅማል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡

የመጀመሪያው ቅሬታዬ የተነሳው ቀደም ብዬ ከጠቀስኩት ከአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ አባባልጋ ይያዛል፡፡ ይኸውም ባሕሩ ዘርጋው በመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ አላግባብ የእንግሊዝኛ ቃላቶችን መዶላቸው ነው፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ “(ቋንቋውን) ያዳብሩታል፣ ያጠናክሩታል ብዬ ያሰብኳቸውን ለብዙ ጊዜ በቃል ሲነገሩ የቆዩ በጣም ብዙ የውጭ ቃላት እንዲገቡ አድርጊያለሁ” ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ እርሳቸው የተዋሷቸው ቃላቶች ከላይ በመግቢያዬ እንደጠቀስኳቸው ዓይነት ትርጓሜ የሚቸግራቸው ቃላቶች እንዳልሆኑ ታዝቤያለሁ፡፡ ለዚህም እንዲረዳችሁ ጥቂቶቹን እነሆ፡-
ሆስተስ (hostess)፣ ሎጂክ (logic)፣ ሚነራል (mineral)፣ ማስ ሜድያ (mass media)፣ ማፕ (map)፣ ሪኔይሳንስ (renaissance)፣ ሲምፖዝየም (symposium)፣ ሴልፎን (cell phone)፣ ሻምፒዮን (champion)፣ ቡቲክ (boutique)፣ ቱሪስት (tourist)፣ ቴክኒሽያን (technician)፣ ትራጄዲ (tragedy)፣ ቾክ (chalk)፣ አርቲፊሻል (artificial)፣ አድሚኒስትሬሽን (administration)፣ አፐራተስ (apparatus)፣ ኢንፎርሜሽን (information)፣ ኦፊሰር (officer)፣ ኩኪስ (cookies)፣ ኬብል (cable)፣ ዲሬክተር (director)፣ ዲክሽነሪ (dictionary)፣ ዲክቴተር (dictator)፣ ጁስ (juice)፣ ጆርናል (journal)፣ ጎል ኪፐር (goal keeper)፣ ፋይናንስ (finance)፣ ፒክኒክ (picnic)፣ ፓራግራፍ (paragraph)፣ ፕሮብሌም (problem) እና ወዘተ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባሕሩ ዘርጋው በመዝገበ ቃላቶቹ ውስጥ አንዳንዶቹን የተውሶ ቃላት የተረጎሙበት መንገድ እንግሊዝኛውን በአማርኛ፣ አማርኛውን በእንግሊዝኛ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ በዚያ ላይ ለአንድ ቃል በእንግሊዝኛና በአማርኛ የተለያየ ትንታኒያዊ ትርጉም የሚመስልም አለ፡፡ ለአብነት ያክል የሚቀጥሉትን እንመልከት፡-
ማእድን ክምችት፤ ብረት ነክነትና ሌሎችም ሚኒራሎች በበቂ ብዛት ሲገኙ፡፡

ሚኒራል፤ ቅልጥ አለት ውስጥ በሚገኙ ልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች ውህደት የተፈጠሩና የተለያዩ ቅርፅና ቀለም ያላቸው አለት ገንቢ ወይም ማዕድን ገንቢ ቁሶች

ካርታ፤ ስ. 1. ማፕ÷ በልዩ ልዩ መስፈርት የሚዘጋጅ የምድር ገፅታ÷ የቤት÷ የመንገድ ንድፍ ያለበት ማስረጃ፡፡…

ማፕ፤ ስ. ካርታ÷ አንድ ቦታ ምን እንደሚመስል÷ የት እንደሚገኝ÷ ምን አይነትና ቅርፅና ስፋት እንዳለው÷ እርቀቱንና አቅጣጫውን÷ ስለአካባቢው የአየር ሁኔታ÷ ስለሚያበቅለው እፅዋት…

በሌላ በኩል ደግሞ ባሕሩ ዘርጋው በመቅድማቸው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ ጥናት በ1973 “ሀ፣ ሐ፣ ኀ፤ ሠ፣ ሰ፤ አ፣ ዐ፤ ፀ፣ ጸ መካከል ሐ፣ ኀ፣ ሠ፣ ዐ፣ ጸ፣ ኸ እንዲሰረዙ” መወሰኑን ይነግሩናል፡፡ እኔም በግሌ ከዚህ በፊት በጻፍኩት አንድ ጽሁፍ ላይ አንድ የነዚህ ቃላት ድግግሞሽ (ከግዕዝ በተረፈ ለአማርኛ) ከፈተናነት ተጨማሪ ፋይዳ አለው ወይ የሚል ጥያቄ አንስቼ መልስ ማጣቴን ገልጫለሁ፡፡ ፬ቱ ሞክሼ ሆህያት በሚለው ጽሁፋቸው ዲ/ን ኅሩይ ባየ በተቃራኒው ይከራከራሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የዲ/ን ኅሩይ ጽሁፍ የሚያረካ አመክንዮ ሊያስቀምጥልኝ አልቻለም፡፡ የተለመደው ማፈንገጥን (ወይም ለውጥን) የመቋቋም ፍላጎት ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ዓይነቱ ችግር በኔ ጽሁፍ ውስጥም ይስተዋላል - ስሜ ላይ ኃይሉ ለሚለው ሌሎቹን (ሀ ወይም ሐ) ካለመጠቀም ጀምሮ፡፡ ሆኖም ጽሁፉን ከዘመናዊው የኮምፒዩተር የቁልፍ ሰሌዳ ጋር ለማስማማት ስንሞክር የሚገጥመንን ፈተና ተደጋጋሚ ሆሄያትን ማስወገድ እንደመፍትሄ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት በሌላ ጽሁፌ ማነሳሳቴ ይታወሳል፡፡

ባሕሩ ዘርጋው በመዝገበ ቃላታቸው መቅድም÷ “…(በመዝገበ ቃላቱ ውስጥ) ለሚገኙት ግድፈቶች ይቅርታ እየጠቅኩ÷ የሚሰጡትንም ገንቢ እርማቶችና አስተያየቶች በደስታ እቀበላለሁ” ብለዋል፡፡ ይሄ አስተያየትም ከደረሳቸው እንደሚጠቀሙበት አልጠራጠርም፡፡

ምርቃት
የዛሬ 163 ዓመት፣ እ.ኤ.አ. በ1841 የታተመ ከአማርኛ ወደእንግሊዝኛ እና ከእንግሊዝኛ ወደአማርኛ የሚመልስ (ሁለት ባንድ) መዝገበ ቃላት በወዳጄ ጥቆማ ከኢንተርኔት ላይ አውርጄ÷ እየተመለከትኩ ነበር፡፡ መዝገበ ቃላቱ እንግሊዝ አገር የተዘጋጀ ቢሆንም አሁን የሚገኘው በአሜሪካ፣ ኮርኔል ዩንቨርስቲ እንደሆነ መግቢያው ላይ ተጽፏል፡፡ የመዝገበ ቃላቱ መግቢያ ላይ ከዚህ በፊት የዚህ ዓይነት ሥራ የታተመው ይህንኛው መዝገበ ቃላት ከመታተሙ 143 ዓመት በፊት የታተመው Lexicon Amharico-Latinum, Frankfort, 1698 እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህንኛውን መዝገበ ቃላት ከበይነመረብ (Internet) ላይ ፈልጌ ለማውረድ ብሞክርም ለጨረታ የቀረበ በመሆኑ አልቻልኩም፡፡ መጽሃፉ የተገመተለት ዋጋ ከ200 እስከ 300 ዩሮ ቢሆንም መነሻ ዋጋው ግን 100 ዩሮ ነው፡፡ መዝገበ ቃላቱን ኢትዮጵያውያን ቢገዙት ታሪክን የመግዛት ያህል ዋጋ ይኖረዋል፡፡

መዝገበ ቃላቶቹ አማርኛ ቋንቋ ምን ያህል ለውጦችን በነዚህ ጊዜያት እንዳስተናገደ ከመናገራቸውም ባሻገር፣ በቅዱስ መጻህፍትና በጥንታዊ የታሪክ ድርሳናት ላይ ለምናነባቸው አንዳንድ ቃላቶች ፍቺ ያስገኙልናል፡፡ ከዚህም በላይ በጊዜ ሒደት ውስጥ ትርጉማቸው የተቀየሩ ቃላቶች በጥንታዊ ድርሳናት ውስጥ የነበራቸውን ትርጉም በመረዳት ትክክለኛ እና ወቅታዊ ትርጓሜ ለማስገኘት ያስችላሉ እላለሁ፡፡

ይህንን ጽሁፍ ከመደምደሜ በፊት ግን በ1841 ታተመ ያልኩዋችሁ መዝገበ ቃላት ውስጥ ያገኘሁዋቸውን አንዳንድ ወጣ ያሉ ትርጉሞች ላስነብባችሁና ልሰናበታችሁ:-
Champion ~ ጨካኝ
Juice ~ ያታክልት ውኃ፡፡ of fruits: ብሪንጥ፡፡
Thanksgiving ~ ስብሓት፡፡
Memoir ~ ዝክር፡፡
መኪና ~ mountain in Lasta
ሰራሪ ~ sailor, navigator, rider

No comments:

Post a Comment