“እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ፣ እህሌ የሚደርሰው ለፍልሰታ”
(በፍቃዱ ኃይሉ)
For English, click here.
የኮሪደር ልማቱ በተለይ የመሐል አዲስ አበባን ገጽታ እስከወዲያኛው እየቀየረው ነው። ለአቅመ ማስተዋል ከደረስኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ አዲስ አበባ በግንባታ ላይ ነች፤ ሆኖም ከ2016 ጀምሮ እያስተናገደች ያለውን ያክል የነባር ሰፈሮች መፍረስ ግን አይቼ አላውቅም። የቀድሞዎቹ ፒያሳ እና ካዛንቺስ ተሰናብተዋል፤ አዲሶቹ ገና አልተወለዱም። በአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ይኖሩ የነበሩት ብዙ ሰፈሮች ፈርሰዋል፤ በምትካቸው ማራኪ ፓርኮች እየተገነቡ ነው። ያለ ጥርጥር መሐል አዲስ አበባ እያማረባት ነው፤ ቀድሞ መሐል ከተማ እናየው የነበረው ግርግር እና ማኅበራዊ ቫይብ ግን ከነዋሪዎቹ ጋር አብሮ ወደ ከተማዋ ዳርቻ ፈልሷል። የመሐል ከተማው የመንገድ ጥርጊያዎቹ፣ የእግረኛ መንሸራሸሪያዎቹ፣ መናፈሻ ፓርኮቹ፣ የመኪና ማቆሚያዎቹ፣ ወዘተ አስፈላጊም ውብም ናቸው ብዬ አምናለሁ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰፈሮች ውስጥ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት የኖሩ ቤተሰቦች አሁን ወደ ከተማው ዳርቻ ተገፍተው ለመናፈሻዎቹ ቦታ ለቀዋል። አሁን በፒያሳ እና ካዛንቺስ ትልልቅና ዘመናዊ አፓርታማዎች እየተገነቡ ነው። ይህ ክስተት፣ ድሆችን ከመሐል ከተማ ገፍቶ አስወጥቶ፣ በምትካቸው ዘመናዊ አፓርትመንቶችን መግዛት የሚችሉ ባለፀጋዎችን የሚስብ ("class replacement") እየመሰለ ነው።
በዚህ መነሻ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ከፈለግኩ የቆየሁ ቢሆንም ስፈራ ስቸር ዘግይቻለሁ። ነገር ግን ቢያንስ መሠረታዊ፣ ሕጋዊና ሞራላዊ ጥያቄዎች የማንሳት መብታችን ይጠበቃል በሚል ተስፋ ከብዙ በጥቂቱ ለመጻፍ ተደፋፍሬያለሁ። ዓላማዬ የልማት ሥራውን ማጥላላት ወይም ማወደስ አይደለም። ይልቁንም ይህ የአዲስ አበባን መልክና ገጽታ፣ የነዋሪዎቹን ባሕልና አሰፋፈር ለዘለቄታው እየቀየረ ያለ እና ምናልባትም በከተማዪቱ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጦሰኛ (consequential) ኹነት ለልማቱ ዋጋ በከፈሉት (የልማት ተነሺዎች) አንደበት ምን ዓይነት ዋጋ እንዳለው ለመጠየቅ ነው።
በግሌ ተወልጄ ያደግኩበት እና የቤተሰቦቼ እና የአብሮ አደጎቼ ቤተሰቦች መንደር በወንዝ ልማት ፕሮጀክት ሳቢያ ፈርሶብኛል፤ በምትኩ መናፈሻ ፓርክ እየተገነባ ነው። በጽሑፌ የእኛን ሰፈር ነዋሪዎች ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ሌሎችንም ምሳሌዎች በማጣቀስ “በሒደቱ የልማት ተነሺዎቹ ሕይወት ይሻሻላል (ይበለፅጋል) ወይስ ይከፋል (ይደኸያሉ)?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እሞክራለሁ።
የኮሪደር ልማቱ እና የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ (macroeconomic implication) ምን እንደሚሆን፣ ከባለሙያዎች እንሰማለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ለጊዜው ግን የኔ ዳሰሳ የልማት ተነሺዎቹን ሕይወት የሚመለከት ነው።
መግባቢያ
በዚህ ጽሑፍ የምዳስሰው የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት የሚባሉትን በተመለከተ ነው፤ የጫካ ፕሮጀክት የመሳሰሉ ግዙፍ እና ምሥጢራዊነት የሚበዛበቸውን ፕሮጀክቶች በተመለከተ ለጊዜው በዚህ ዳሰሳ አላካተትኳቸውም። በመርሕ ደረጃ በጽሑፌ የምዳስሳቸው ሁለቱ ፕሮጅከቶች አስፈላጊነት ላይ ብዙ ጥያቄ የለኝም፤ ያሉኝም ጥያቄዎች የዚህ መጣጥፍ ዓላማ አይደሉም።
ልማት ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊም ነው። ለአንድ የመሠረተ ልማት ከአንድ አባቢ የተነሱ ሰዎች፣ በሌላ አካባቢ ሲሰፍሩ ፍላጎቶቻቸው ካልተሟሉላቸው ልማቱ ጎድሎ ይሆናል። ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ መልስ የማፈላልግለት ጥያቄ ፕሮጀክቶቹ፣ በተለይ ለልማት ተነሺ ከሆኑት ነዋሪዎቹ የቀደመ እና አሁናዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንፃር “ወደ ብልፅግና ይመራሉ” ወይስ በተቃራኒው “ሊያደኸዩ ይችላሉ?” የሚል ነው። ጽሑፉን ለመጻፍ የግል ምስክርነቴን፣ የተወሰኑ የልማት ተነሺ ሰዎች ምስክርነት፣ የዜና ምንጮች፣ እና በጉዳዩ ላይ የምርምር ሥራ እየሠሩ ያሉ ሰዎች አስተያየት በግብዓትነት ተጠቅሜያለሁ። ሐተታዬ በአዲስ አበባ ስላሉት ሁለቱ ፕሮጀክቶች (የኮሪደር እና የወንዝ ዳር ልማት) እንጂ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉትን አይመለከትም። በአዲስ አበባ ውስጥም የልማት ተነሺ ንግድ ቤቶችን ሁኔታ አልዳሰስኩም። (የሆነ ሆኖ አንባቢዎች እንዲረዱልኝ የምፈልገው ይህ ጽሑፍ በምንም ዓይነት የክስተቱን ሙሉ ገጽታ ማሳየት እንደማይችል ነው።)
ጽሑፉን የቀድሞዎቹ ሠፈሮች አመሠራረት እና ዕድገትን በመተረክ እጀምርና፣ የአፈራረሱ ሒደት፣ ለተነሺ ነዋሪዎች የተሰጠውን ካሣ እና ምትክ በመዘርዘር፣ ሒደቱ በልማት ተነሺዎቹ ኢኮኖሚያዊ ዕጣ ፈንታ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ በማሳየት ወደ መደምደሚያው እሸጋገራለሁ።