(በፍቃዱ ኃይሉ)
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዐቢይ አሕመድ እርካብና መንበር በአባዱላ ገመዳ የተቀየሰ ይመስለኝ ጀምሯል። ምክንያት አለኝ። አባዱላ በተቀናቃኞቹ ጃዋር መሐመድም፣ ዐቢይ አሕመድም አድናቆት የተቸራቸው ሰው ናቸው።
ጃዋር መሐመድ፣ 'አልፀፀትም' በሚለው መጽሐፉ በጣም ጥቂት ሰዎችን ነው በአዎንታዊ ያነሳው። ከነዚህ ሰዎች መካከል አባዱላ ገመዳ አንዱ ናቸው። በዚህ መጽሐፉ ላይ ጃዋር እንደሚለው፣ አባ ዱላ "ኦሮሚያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ስለሚያውቃት ስለመጣችሁበት ወረዳ ጉዳይ ቦታዎችን እና ሰዎችን በስም እየጠራ ያዋራችኋል። ይህ ሁኔታው ለሰውዬው ፖለቲካ ያላችሁን ጥላቻ ለጊዜውም ቢሆን ረስታችሁ እንድታዳምጡት ይጋብዛል። አሜሪካ ሳለሁ የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ለመቀየሰ የአገዛዙን የውስጥ አሠራር እና አመለካከት ለመረዳት ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረኝ ከአባዱላ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር ያዳበርኩት ግንኙነት ጠቅሞኛል" ብሏል። ጃዋር ከመንግሥት ለውጡ አስቀድሞ ክፍተቱን ለመሙላት የሚችል ፓርቲ እንዲያቋቁም አባ ዱላ ምክር ለግሰውት እንደነበርም ጽፏል። እሱም በበኩሉ ከኦሕዴድ መኮንኖች ጋር ሲነጋገር "ለውጡን ቢመሩ" ብሎ ከጠቆማቸው ሰዎች አንዱ አባዱላ ገመዳ ነበሩ። እርሳቸው ላይ የነበረው ብቸኛው ቅሬታ ፖለቲካው ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው እንደ ለውጥ መሪ አይወሰዱም የሚለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የአባዱላን ሥም 'የመደመር መንገድ' በሚለው መጽሐፋቸው በአዎንታዊ መልኩ አንስተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መጽሐፍ ለውጡ እንዴት እንደመጣ ያትታሉ። ሆኖም እኛ የምናውቀውን "ቲም ለማ" ጭራሹኑ አይጠቅሱትም። ይልቁንስ "መጋቢታውያን" እያሉ በሚጠሯቸው፣ በእርሳቸው እና ደመቀ መኮንን ተጠንስሶ ስለተከናወነው ለውጥ ይተርካሉ። እዚህ መጽሐፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባዱላ ገመዳ “የተለየ ቅርበትና ወዳጅነት” እንደነበራቸው ጽፈዋል። ሌላው ቀርቶ ጄነራል ከማል ገልቹ እና ኮሎኔል አበበ ገረሱ ሠራዊቱን ከድተው የኤርትራ አማፂያንን ሊቀላቀሉ ሲሄዱ እንዳነጋገሯቸውና፣ አባዱላና እሳቸው በችግሩ ቢግባቡም የትግል ስልቱ ከውስጥ መሆን አለበት ብለው እንደወሰኑ በመጥቀስ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “partners in crime” (ለወንጀል የሚተማመኑ ወዳጆች) እንደነበሩ ፍንጭ ይሰጡናል።
ዛሬ የብልፅግና ቁንጮ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች ወይ ኦሮሞ አልያም ፕሮቴስታንት ናቸው። ስለዚህ ሁኔታ ከአንድ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ የኦሮሞ ፖለቲከኛ ጋር ስናወራ የነገረኝም ነገር በዚህም የአባዱላን ተፅዕኖ ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል። 'አባዱላ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኢስላሚስት ንቅናቄ ጋር እየተጋባ ሲቸግራቸው፥ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኦርቶዶክስ ክርስትና ጋር ተኳርፏል፣ ከኢስላሚስቶች ጋር መወዳጀቱ ደግሞ ዓለም ዐቀፍ ቅቡልነት ይነሳዋል፣ ስለዚህ ፕሮቴስታንት ኦሮሞዎች ቢመሩት ይሻላል ብለው በማሰብ እነ ዐቢይ አሕመድን ወደ ፊት አመጧቸው' ብሎኛል።
ተርዬ ኧስተበ (Terje Østebø) ባለፈው ግንቦት ባሳተመው ጥናታዊ ጽሑፉ ላይ ይህንን የሚያጠናክር ሐተታ "አባዱላ... ብዙ ክርስቲያኖችን ወደፊት በማምጣት በምዕራባውያን ዘንድ የኦሮሞ ፖለቲካ ልኂቃኖች የሙስሊሞች የበላይነት አለበት የሚለውን ገጽታ ለማስተካከል ሞክረዋል" በማለት ጽፏል። አባዱላ ወደ ፊት ካመጧቸው ፕሮቴስታንቶች ውስጥ ለማ መገርሳ፣ ሽመልስ አብዲሳ፣ አዳነች አቤቤንና ራሳቸው ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ብዙዎቹ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ ይላሉ ተመራማሪው። አባዱላም እኤአ በ2009 ከኦርቶዶክስ ወደ ፕሮቴስታንት መቀየራቸውን ጥናቱ ይጠቅሳል።
ፋክት መጽሔት ላይ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከለውጡ ዓመታት በፊት ዐቢይ አሕመድ የማዕከላዊ ኮሚቴን ተቀላቅለው የአባዱላን ውለታ ለመመለስ እየሠሩ ነው በሚል በጨረፍታ ይጠቅሳቸዋል። በወቅቱ የጋዜጠኛው ግምት አባዱላ በኢሕአዴግ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ዐቢይን እየተጠቀሙበት እንደሆነ ነበር። ሆኖም፣ እርሳቸው ዐቢይን ወደ ፊት እያመጡ፣ ወይም ዐቢይ ለራሳቸው መንገድ እየጠረጉ፣ ወይም እርስ በርስ እየተናበቡ እየሠሩ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ይከብደናል። ነገር ግን በውጤቱ ስንመዝነው፣ በአንድም በሌላም መልኩ አባዱላ ለዐቢይ አሕመድ እርካቡ ነበሩ ማለት የምንችል ይመስለኛል።

 
 
