Pages

Tuesday, January 31, 2017

ጉደኛውን ተራራ (Tullu Gudo) አየነው!

ዝዋይ ሐይቅ፣ በተለምዶ ዝዋይ በምትባለው ባቱ ከተማ ዳርቻ ላይ፣ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ፣ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 100 ማይሎች ርቆ የሚገኝ፣ 440 ስኵዌር ኪሎ ሜትር የሚሰፋ፣ ብዙም የማይወራለት፣ ብዙም ያልለማ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ፋይዳው የላቀ፣ ትልቅ ሐይቅ ነው። ሐይቁ 5 ደሴቶች አሉት። በደሴቶቹ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስር የሚተዳደሩ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች አሉ፤ የታቦታቱ ቁጥር 44 ነው ይባላል።

በቱሉ ጉዶ ደሴት ላይ ባለችው የማርያም ቤተ ክርስትያን ጊቢ ውስጥ አንድ ሙዚዬም አለ። ሙዚዬሙ ውስጥ 'መጽሐፈ ሔኖክ' የሚባለው ዝነኛ መጽሐፍ አለ አሉ። ሔኖክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የኖህ ቅድመ አያት ነው ተብሎ ይታመናል። የአዳም ስድስተኛ የልጅ ልጁም ነው። ሔኖክ ከእግዜር ጋር በምድር ላይ ተንሸራሽሮ የጻፈው የጉዞ ማስታወሻ ነው 'መጽሐፈ ሔኖክ'። መጽሐፉ መጽሐፍ ቅዱስ ጥራዝ ውስጥ ባይካተትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤት በጣም ይከበራል። በዓለም ዙሪያም ታሪካዊ ፋይዳው ትልቅ ነው። የመጽሐፈ ሔኖክ ምዕራፎች ከፊሎቹ 300 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ከፊሎቹ ደግሞ 100 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጁ እንደሆነ በታሪክ ተመራማሪዎች ይታመናል።

የመጽሐፈ ሔኖክ ታሪክ ሲወሳ መጀመሪያ (የኛ ከሆነው የግዕዙ መጽሐፍ በፊት) ፍልስጤም ውስጥ በእብራይስጥ እና በአርማይክ ቋንቋ ከተጻፈ በኋላ 800 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የገባበት ጠፍቶ ነበር። ከዛ ምንም እንኳ ከፊል የላቲን ትርጉሙ በአውሮጳ ቢኖርም፣ በ7ኛው ክፍለ ዘመን (ከ1,500 ዓመታት በኋላ) ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉው የግዕዝ ትርጉሙ መኖሩ ተሰማ። ከዛ በኋላ መጽሐፉን ለመስረቅ አውሮጳዎች ያልደከሙት የለም። ግን ሳይሳካ ቆይቷል። የፈረንሳዩ ንጉሥ ሊዩስ ፲፬ ኮልበርት የተባለ መልዕክተኛ ልኮ ሞቶበታል። ሌላኛው ፈረንሳዊ ኒኮላስ ፒርስ ለማሰረቅ ሲደክም ኖሮ በተሳካለት ማግስት ሞተ። መጽሐፉን ከሟች የተረከበው ጆብ ሉዶልፍ የተሰረቀው መጽሐፍ 'የገነትና ሲኦል ምሥጢራት መጽሐፍ' መሆኑን አወቀ። በመጨረሻ፣ እኤአ በ1770 ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ ጎንደር ላይ ተሳካለት። በሁለት ዓመታት ሁለት ቅጂ ጽፎ ቢወስድም፣ እሱ 'ከጉዞዬ ሁሉ በጣም አጓጊውና የማይገኘው ትሩፋቴ' ያለውን ማንም አላመነውም ነበር። 'ውሸታም ተብሎበታል' (ፍሊፕ ማርስደን እንደተረከው።) አሁን መጽሐፈ ሔኖክ ቱሉ ጎዶ ደሴት ላይ ይገኛል አሉ። በ9ኛው ክ/ዘመን አሕመድ ኢብን ኢብራሒም (በተለምዶ ግራኝ መሐመድ ወይም አሕመድ ግራኝ የሚባለው) ሙስሊም ጦረኛ የክርስቲያኑን መንግሥት ሲወጋ ክርስተያኖች ተሰደው ወደ ደሴቶቹ መምጣታቸው ይነገራል። ያኔ አክሱም ይገኛል የሚባለው 'ታቦተ ፂዮን'ም እዚያ ቆይታ ማድረጉ ይነገራል። ግራሀም ሀንኩክ 'ታቦተ ፅዮንን ፍለጋ' ተብሎ በተነገረው መጽሐፉ ላይ የታቦታትን መብዛት 'ዛፍን ለመደበቅ ጫቃ ውስጥ መትከል' የሚል ተረት አጣቅሶለታል - ታቦተ ፅዮንን ለመደበቅ ይሆናል በሚል።

ወደ ቱሉ ጉዶ ማስታወሻችን ስንመለስ፣ ወደዚያ ለመሔድ ያቀድነው አዋሽ 7 "ተሀድሶ" ላይ ሳለን ነበር። (አብረን የሔድነው እኔ፣ እያስጴድ ተስፋዬ እና ቴዎድሮስ እሸቱ እንዲሁም አዋሽ ሰባት አብሮን ያልነበረው በላይ ማናዬ ነበርን።) አዋሽ 7 አንድ የዛይ ብሔረሰብ ተወላጅ ተዋውቀን ነበር። የሚተዳደረው በአሳ አስጋሪነት ነው። በሕዝባዊ አመፁ ወቅት ከመንገድ ላይ ታፍሶ ነው እዚያ የመጣው። ሆኖም ስለአመፁ መንስዔና ምንነት የሚያውቀው ነገር አለ ለማለት ይቸግራል። ስለዛይ ማኅበረሰብ ሲያወራልን ለማየት ጓጓንና ቀጠሮ ያዝን። የዛይ ብሔረሰብ አባላት የሚኖሩት ቱሉ ጉዶ የተባለው የዝዋይ ደሴት ላይ ነው። የሚናገሩት ቋንቋ ትግርኛም ጉራግኛም ይመስላል። ግን ሁለቱንም አይደለም። ብዛታቸው 3000 ገደማ ነው ይባላል።

ቱሉ ጉዶ አፋፍ ላይ፣ በማርያም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ቆመን ቁልቁል ከሳር ጎጆዎች መካከል የቆርቆሮ ጣሪያ ያላቸው ሁለት ቤቶች አየን።  (ከታች በጀልባ እየተንሳፈፍንም አይተነው ነበር።) ደሴቷ ላይ የሚኖሩት ሕዝቦች እስከ 6ኛ ክፍል የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነው። ከዚያ በላይ ለመማር 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው አሰላ ወይም 24 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ዝዋይ በጀልባ መጓዝ አለባቸው። የሚተዳደሩት በእርሻ ወይም በግብርና ነው። በመስኖ የሚያለሙት አትክልት ያስጎመጃል።

እኛ ወደ ቱሉ ጉዶ የሔድነው በዝዋይ ስለሆነ ጀልባ ላይ ለመሔድ አንድ ሰዓት ተኩል፤ ለመመለስም እንደዚያው ፈጅቶብናል። የቱሉ ጉዶ ደሴት ከደሴቶቹ ሁሉ ጎላ ያለ እንደጡት መንታ ዓይነት ተራራ ነው። ይህንን ለማወቅ ግን ተራራውን መቅረብ ይጠይቃል። እስከዚያው አንድ ጉብታ ብቻ መስሎ ነው የሚታየው። ደሴቱ ከርቀት እየታየ ግን ቢሔዱ፣ ቢሔዱ የማይደረስበት ዓይነት ደሴት ነው።

ሌላው አስገራሚ ነገር፣ ደሴቱ ዙሪያ ያሉ ተንሳፋፊ ድንጋዮች ነገር ነው። በዙሪያው ተኮልኩሎ ሲታይ እንደማንኛውም ድንጋይ ይመስላል። ሲያነሱት ግን እንደቡሽ የቀለለ ነው። ወንዝ ላይ ሲጥሉትም ይንሳፈፋል። እርስበርሱ ሲጋጭ ደግሞ እንደማንኛውም ድንጋይ ጠንካራ ነው - ይፋጫል። ቢጠረብ እንደጀልባ ማገልገሉ አይቀርም። የትኛውም ያየሁት ባሕር ዳርቻ ላይ እንዲህ ዓይነት ድንጋይ ገጥሞኝ አያውቅም።

የሔድንበት ዕለት "ያስተርዮ ማርያም" (ጥር 21) ዋዜማ ስለነበር ብዙ ሰዎች ወደ ደሴቷ ሔደው ነበር። መጽሐፈ ሔኖክ አለበት የተባለው ሙዚየም ግን ዝግ ስለነበር የመጎብኘት ዕድል አላገኘንም። አብዛኛው ሰው እዚያው አድሮ በማግስቱ የማርያምን  ታቦት ለማንገሥ ስለሔደ የጎልማሳ ሰው እጥፍ ያህል ቁመት ያለውን ቄጤማ ቀጥፎ የቤተ ክርስቲያኗ ግቢ ውስጥ ጊዜያዊ ምንጣፍ ሠርቷል። በላይ ማናዬ የቄጤማው ሐይቁ ውስጥ መብዛት ለሐይቁ አደገኛ እንደሆነና ሊያደርቀው እንደሚችል ስጋቱን ነግሮ እኔንም እንድሰጋ አድርጎኛል። ሐይቁ እና ደሴቶቹ በክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ብዙ ሊሠራበት ሲገባ ምንም አልተነካም። በቢሾፍቱ ሐይቆች ዙሪያ የሚታዩትን ሪዞርቶች ሩብ ያህል እንኳ በዝዋይ ሐይቅ ዙሪያ ቢኖር ለሐይቁ እንክብካቤ ማድረግ የሚቻልበት፣ እንዲሁም ሀብት የሚፈጠርበት ዕድል ይኖር ነበር።

ወደ ቱሉ ጉዶ ስንሔድ ስለደሴቱም ይሁን ስለሐይቁ የማውቀው ነገር ነበር ማለት አይቻልም። ስንመለስ በብዛት የጨመርኩት ነገር የበለጠ የማወቅ ጉጉት ነው። ዝዋይ ሐይቅ እና ደሴቶቹ ይሄን ሁሉ ውበት እና ታሪክ አዝለው ሲኖሩ እኔ የት ነበርኩ?