Pages

Thursday, March 11, 2021

‘አገናዛቢነት’ የሌለው ተዋስዖ

ሁሉም ሰዎች ይናገራሉ፤ ሁሉም ሰዎች ብሶት አላቸው። ነገር ግን የሁሉም ንግግር እና ሐሳብ የሁሉንም ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም። በዚህም ምክንያት ተናጋሪ እንጂ አዳማጭ የለም፤ ብሶት እንጂ አዘኔታ የለም። ምክንያቱምአገናዛቢነትየለም፤ አንዳቸው የሌላኛቸውን ሁኔታ እና እውነታ ለማገናዘብ ሲሞክሩ አይታይም።

አገናዛቢነት የሚናገሩት ነገር ያለበትን ጥቅል ሁኔታ ከግምት ውስጥ ለማስገባት መሞከር ነው። ብዙዎቹ በኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ የሚያነጋግሩን ክስተቶች ድንገታዊ መነሻ ይኑራቸው እንጂ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወይም አካባቢያዊ አንድምታ ይኖራቸዋል። እነዚህን ማገናዘብ ያስፈልጋል፤ የፖለቲካ ተዋስዖዎቹ የአንድን ወገን በደል፣ የአንድን ክስተትን አደገኝነት፣ ወዘተርፈ አተኩረው ሊናገሩ ይችላሉ። ጉዳዮቹ ግን ከአንድ ወገንም፣ ከአንድ ክስተትም የሰፉ እና ውስብስብ ናቸው። ውስብስብነታቸውን ያላገናዘበ ንግግር ችግሩን የመፍታት አቅም ከማጣቱም ባሻገር፣ ምናልባትም ችግሩ ላይ ተጨማሪ ችግር ሊቆልል ይችላል።

ግጭት አገናዛቢነት

የነውጥ አዘል ግጭቶች ቦታዎችና ክስተቶች ዳታ (ACLED) የተባለ እ.አ.አ. በ2019 ኢትዮጵያ ውስጥ 300 ገደማ የፖለቲካ ነውጦች፣ 680 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት አድርጎ ነበር። የ2020ውን ገና ቆጥረው የጨረሱት አይመስለኝም፤ ሆኖም ከዚህ ጽሑፍ ጋር ሕዳር ወር ላይ ያወጡትን ግጭቶች ያሉባቸውን ቦታዎች የሚያመለክት ካርታ አስቀምጥላችኋለሁ።

ግጭቶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ እውነታዎች ናቸው። ግጭቶች እዚህም እዚያም አሉ። ነገር ግን የፖለቲካ ተዋስዖዎቹ ግጭት አገናዛቢ አይደሉም። መጀመሪያ ግጭት አገናዛቢነት ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ ልሞክር።

ግጭት አገናዛቢነት ማለት “ንግግሮች እና ተግባራት ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ነባራዊ ዐውዱን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በተናጋሪዎቹ ወይም በተግባራቱ አከናዋኞች ላይም ይሁን በተደራሲዎቻቸው ላይ ወይም በሌሎች ሦስተኛ ወገኖች ላይ የሥነ ልቦናዊም ይሁን የአካላዊ ጥቃት ሊያደርስ የሚችል ቋንቋ ባለመጠቀም ወይም ተግባር ባለማከናወን ግጭት አስወጋጅ የንግግር እና አሠራር ሒደት” ማለት ነው።

ብዙዎቹ በፖለቲከኞች፣ በአክቲቪስቶች፣ ወይም ጋዜጠኞች የሚደረጉት ተዋስዖዎች ንግግሮቹ ስለሚያስከትሉት ጦስ እምብዛም አይጨነቁም። በዚህም ምክንያት በግጭት ላይ ግጭት፣ በቀውስ ላይ ቀውስ እየተደራረበ ይሔዳል። በነገራችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የተናገሯቸው ንግግሮች የጥላቻ ወይም ሐሰተኛ መረጃ በውስጣቸው ሳይኖር ነባራዊውን እውነታ እና ዙሪያ ገቡን ከግምት ውስጥ ያላስገቡ በመሆናቸው ብቻ - በሌላ አነጋገር ግጭት አገናዛቢ ባለመሆናቸው ሳቢያ በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። ለግጭቶቹ ግን ማንም ኃላፊነት አይሰማውም፣ በነርሱ ግጭት አለማገናዘብ ምክንያት ለጠፋው ሕይወትም ይሁን ንብረት መፀፀትም የተለመደ አይደለም።

ግጭት አገናዛቢነት የታመቁ ወይም ይፋዊ ግጭቶችን እንዲሁም ነውጥ አልባ ወይም ነውጥ አዘል ግጭቶችን መኖራቸውን፣ ንግግሮች ወይም ተግባራት እነዚህን ሊያባብሱ ወይም ሊያከስሙ እንደሚችሉ መረዳት እና በተቻለ መጠን ግጭቶቹን ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን በመቀነስ፣ ሊያከስሙ የሚችሉትን በመጨመር ላይ ማተኮር ነው።

“እኛ” ብቻ እንዳልሆንን ማገናዘብ

ማገናዘብ የሚገባን ይፋዊ ግጭቶችን ብቻ አይደለም። የታመቁ በርካታ ግጭቶች አሉ። የታመቀ ግጭት ብዙ ጊዜ ግጭት ውስጥ በሚገቡት ወይም ውጥረት ውስት ባሉ ቡድኖች መካከል ያለ፣ ያልተገለጠ አንዳንዴ ውጥረቱ በመሐከላቸው ባለው የተዛባ የኃይል ግንኙነት ምክንያት እንዳለ ባልተረዱ ወይም ባልተነጋገሩ አካላት መካከል የሚገኝ ያደፈጠ ግጭት ነው።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በተለያዩ ብሔሮች፣ በተለያዩ እምነት ተከታዮች፣ በተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አራማጆች፣ በተለያየ የኢኮኖሚ መደብ አባላትና ፆታን መሠረት ያደረገ፣ ወዘተ ያደፈጠ፣ ያልተገለጠ፣ እምቅ ግጭት አለ። ለዚህ ነው ንግግሮቻችን እና ተግባራቶቻችን ሁሉ “እኛ” ብቻ ሳንሆን “ሌሎችም” እንዳሉ እንዲሁም እነርሱም ፍላጎቶች እና ስሜቶች እንዳሏቸው ማገናዘብ የሚኖርብን።

የፖለቲካ መዝገበ ቃላታችን ውስጥ የብሔር ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የእምነት ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የኢኮኖሚ መደብ ልዩነቶችን ማገናዘብ፣ የፆታ ልዩነቶችን ማገናዘብ የሚል ነገር እምብዛም አይታይም። በነዚህ ሁሉ መሐል የኃይል ግንኙነት እርከኖች አሉ፣ የታሪክ እና የአረዳድ ትርክርት ልዩነቶች አሉ፣ የመደብ ልዩነቶች አሉ። ባላገናዘብን ቁጥር የምንጨፈልቃቸው ብዙዎች አሉ።

የትግራይ ጦርነት ጥቅምት 24 ሕወሓት የሰሜን ዕዙን ስታጠቃ ይጀመር እንጂ ብዙዎቻችን ከዛሬ ነገ ተጀመረ እያልን ስንፈራው የቆየነው ጉዳይ ነው። የሕወሓት ተቃዋሚዎችም፣ የሕወሓት ወዳጆችም የሌሎችን ጥቅምና ጉዳት፣ ስጋትና ተስፋ አገናዝበን አናውቅም። ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊትም ይሁን በኋላ ለዚህ ወይም ለዚያ ቡድን የሚያስከትለው ድል ወይም ሽንፈት፣ አልያም የትርክትና መልካም ገጽታ መቆጣጠሩ እንጂ በዚህ የሥልጣን ሽኩቻ ሰለባ የሚሆነው ሕዝብ፣ በዚህ ሳቢያ በሕዝቦች መካከል የሚመባባሰው ዘላቂ የወዳጅነት መሻከር አላሳሰበንም። በዚህ አስተሳሰብ፣ አነጋገር፣ እና አተገባበር ሰላም ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። የትግራይ ጦርነት የግጭት አላገናዛቢነታችን ዋና ማሳያ እንጂ ብቸኛው አይደለም።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በተደጋጋሚ የሚፈነዳ እና የብዙዎችን እልቂት ያስከተለ ነውጥ አለ። ስለ ነውጡ ባለን ቁንፅል መረጃ ላይ ተመሥርተን ከመቋሰል በቀር ግጭት አገናዛቢ የሆነ እርምጃ ተራምደን አናውቅም። በአካባቢው ያለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ሁኔታ ምን ይመስላል? በሕዝቦች መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት እንዴት ነበር? እነዚህን ያላገናዘቡ ድምዳሜዎች እና ብሶቶች የቁራ ጩኸቶች ከመሆን አያልፉም።

አገናዛቢነት “እኛ” ያለንበት ሁኔታ እና “እኛ” ነሮችን የምንመለከትበት አምባ ላይ ሁሉም ሰው አለመኖሩን ማገናዘብንም ይጨምራል። ይህ በተለይም ገደኝነቶችን (privileges) አምኖ ከመቀበል ጋር ይያያዛል። “እንዴት እነዚህ ሰዎች እንዲህ ማድረግ ተሳናቸው?” ብለን የምንላቸው ነገሮች “ከኛ ገደኝነት” (our privileges) የመነጨ መሆን አለመሆኑን ማገናዘብ ያስፈልጋል። “እነዚህ” ያልናቸው ሰዎች “እኛ” ያለን የመረጃ፣ የትምህርት፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ዕድሎች አላቸው ወይ የሚለውን ማገናዘብ ምናልባትም ወደ ችግሩ ምንጭ ሊመራ የሚችል አብርኆት ሊያመጣልን ስለሚችል ደጋግሞ መመርመር ያስፈልገናል።

አገናዛቢነት ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት በምን ይለያል?

ፖለቲካዊ ትክክለኝነት (politically correctness) የሚባለው ንግግሮች ወይም ገለጻዎች የተገለሉ ወይም ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንዳይዘነጋ ወይም እንዳያገልል የሚደረግ ጥንቃቄ ነው። መጥፎ ነገር ባይሆንም ጥንቃቄው ችግሩን በመቅረፍ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ ንግግሮች በተጋላጭ እና የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ተቀባይነት እንዳያጣ ወይም ለትችት እንዳይዳረግ ለመጠበቅ ያለመ ነው።

ግጭት አገናዛቢነትም ይሁን ሌሎች ነባራዊ ሁነታዎችን ማገናዘብ ግን ግጭቶች ወይም ሌሎች ማኅበረፖለቲካዊ፣ ወይም ማኅበረኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች እና ልዩነቶቹ የማኅበረሰብ ክፍሎቹ ላይ የሚያሳርፏቸው አሉታዊ፣ ሥነ ልቦናዊም ይሁን አካላዊ ተፅዕኖዎች እንዳይባባሱ ሆነ ተብሎ የሚደረግ ለፍትሐዊነት የቀረበ የፖለቲካዊ ተዋስዖ እና ተሳትፎ ዘዴ ነው።

አገናዛቢነት ችግርን ከሁሉም አቅጣጫዎች ለማየትና ለመቅረፍ መሞከር ነው።

አገናዛቢነት እውነታውን መካድ ወይም መሸሸግ አይደለም፤ አወዛጋቢ ሊሆን ከሚችል ነገር መጠበቅም አይደለም። ይልቁንም ለእውነታው ለመቅረብ መሞከር ነው። በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ብንመለከት አንድ ወገን ብቻውን ተጠቂ፣ ሌላ ወገን ብቻውን አጥቂ የሆነባቸው አጋጣሚዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ብዙዎቹ ድንገተኛ ክስተቶች ሳይሆነ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ የብሔር ናቸው ስንል የሃይማኖት፤ የሃይማኖት ናቸው ስንል የኢኮኖሚ መደብ፤ የኢኮኖሚ ናቸው ስንል የአካባቢያ (geographic)፤ የአካባቢ ናቸው ስንል የባሕል፤ የባሕል ናቸው ስንል የፆታ ሁነው እናገኛቸዋለን። ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያውያን ችግር የአንድ ጉዳይ ወይም የአንድ ወገን አለመሆኑን ነው። ይህንን ውስብስብነት ለማገናዘብ በሞከርን ቁጥር ወደ ችግሮቹ እውነተኛ መንስኤ መጠጋት እንችላለን።

Friday, January 8, 2021

US and the Social Media, Lessons for Ethiopia

(Click here to read in Amharic.)

Freedom of expression is a non-negotiable matter for the Americans. It is something they needed to do “the first amendment” of their constitution for. The first amendment states that "Congress shall make no law… abridging the freedom of speech, or of the press…". On January 6, 2021, Facebook and Twitter had suspended President Trump’s profiles for a day after his supporters forcefully raided Capitol Hill while Congress is at a meeting. While Americans are shocked by the incident, the social media corporations have been the ones that have denied a platform for the president who was accused by many of passing inciting messages. 

The Americans have not seen such a scandal for more than two hundred years since 1814 when British troops attacked Capitol Hill. It would not be an exaggeration to say that the social media conspiracy theories and misinformation campaigns have resulted in this chaos. In this note, I will briefly explore the necessity of freedom of expression and the contradicting challenge posed by social media.

Why We Need the Freedom of Expression?

There are four main reasons why freedom of expression must be respected. (1) because it is a natural right – for personal fulfillment, (2) to discover the truth, (3) to increase the decision-making power of individuals, 4) to avoid the violent consequences of the repression of the freedom of expression, and additionally (5) because it is a necessary condition to also watch the respect other rights.

Inciting speech and misinformation contradict the reasons why freedom of expression must be respected. That is why international conventions seek to establish a cautious framework for restricting freedom of expression (incitement to war and hate, racism, etc.) as well as principles (legality, legitimacy, and necessity). However, while Europeans who had experienced genocide have taken serious legal actions, the Americans have always said that the solution is more freedom.

By the way, although the differences between Europe and the United States are broad in terms of the law, this does not mean Europeans (such as Germany) are jailers of journalists. Nor their citizens are afraid to speak out their critics to the government. Americans have also created a culture of countering irresponsible public speaking with an attempt to counter even many micro-aggressions through public scrutiny. It is in authoritarian or semi-authoritarian regimes that restrictions of freedom of expression target journalists, or speeches can be left unaccounted for (mostly, in cases where the speaker is power). Of course, the ethics and professionalism of journalists is also low in these semi-authoritarian regimes, again driven due to the behavior of the governments.

Conspiracy Theories

One of the pitfalls of social media is the promotion of unsubstantiated conspiracy theories. Misinformation is not a new phenomenon; rather it is fundamentally old-aged. Benjamin Franklin is one of the founding fathers of the United States of America, who actually signed on the four most important documents of the Independence Declaration. Authors of “Like War”, a book that has analyzed the power of propaganda on social media, named Franklin as “the founding father of fake news in America”. Many states-persons have used misinformation as a tool to build a political and social system. Almost all political structures or social systems have been justified with propaganda backed by misinformation.

QAnon Conspiracy

Many supporters of Trump have been deceived by the QAnon conspiracy. It is “a wide-ranging, completely unfounded theory that says that President Trump is waging a secret war against elite Satan-worshipping pedophiles in government, business, and the media”. At the end of his reign, they believe that the president will win and Satan-worshipers and elites will end up jailed. Political arguments, ideology, and policy do not mean anything to the fast-growing believers of this conspiracy theory. Trump supporters come out to the streets wearing T-shirts or hats with the letter Q printed on them. Trump was asked to say that there was no such deep-state and that he was not at war with it, but he covered it up so as not to lose his supporters (saying that he doesn’t know about the movement but that he knows that ‘they like him’). In November 2020, one of the more than 70 candidates of the QAnon movement run for and one of them was elected to Congress. According to Pew Research, more than half of Americans have heard about the movement which started with unsubstantiated claims by an anonymous social media user about three years ago.

Beyond Conspiracy Theories…

Neither Trump's candidacy for the presidency in the US nor Britain's exit from the European Union would have been possible without social media. Despite the attempts of the fellow countries' citizens to convince us that it is Russia’s social media bots and propaganda machines that have created the dividing narratives on the social media, it is the citizens on the social media who have widened the preexisting divisions in their respective societies. Social media has empowered the extremists and gave them a platform to radicalize the less-informed members of each community.

Unlike before, activists of conspiracy write misinformation on social media and build up as many followers as they wish. It is usually the followers who are the real victims of misinformation and who pay the price for the interests of these conspiracy activists. "We are storming the Capitol; it is a revolution," said a woman who was asked by the media why she entered the building on January 6 as she got out crying. For those who are blinded by misinformation and propaganda, the election is not credible unless the result is what they want. Because the propaganda made them doubt everything that was coming from the other side.

Chinese Counterstrategy: Another Trouble

China has banned American social media from operating in its territory. In place of them, it has provided its own social media platforms that censors every political content not friendly to the government. The artificial intelligence behind the Chinese social media platforms doesn’t allow posting of contents that are not ‘allowed’ by the state; and, in cases, they are managed to be, they will soon be removed. This is something that many authoritarian regimes want to have. However, this is not the better alternative to the wild social media which radicalizes the youth and nurtures violent extremism. Rather, guided by the principles of restricting freedom of expression we have mentioned above (legality, legitimacy, and necessity), it is necessary to use artificial intelligence to filter out manipulative contents from the social media to make it a healthy platform as it needs to be (like countering computer viruses with antiviruses).

It is possible to build an ethical algorithm that filters out racist, hateful, organized disinformation, and inciting contests from the social media. Just as verified pages or profiles can be marked with a blue badge, it is also possible to reduce the impact of pages and profiles that repeatedly disseminate incitement, hateful content, false information, conspiracy theories, and the likes with yellow and/or red badges, periodically or permanently.

Social media is a unique and important platform for challenging authoritarian regimes. But, they have been a dangerous challenge for democratic institutions and for consolidating democracy in states that are trying to do transition to democracy.

The Test of Ethiopia

Ethiopians have used social media to force reform by the government. However, social media has been an instrument for fanning conflicts on the ground ending up reversing the progress of an optimist reform.

As a person who has been leading a monitoring team of social media activities in Ethiopia, I have observed that politicians and interest groups are manipulating the platform for undeserved political gains. In Ethiopia’s social media sphere, almost all political figures and groups have their own propaganda teams who often use misinformation and incitement as a strategy. These social media warriors, if not fabricate total lies, exaggerate information, and narratives that support their advantages while ignore or suppress those that disfavors them. This is the new normal to the so-called post-truth era, but not acceptable.

The impact of social media narratives will not be easy in the next election of Ethiopia that is scheduled for June 5, 2021. As far as current trends are concerned, in this general election, it is most probable that voters will cast their ballots ill-informed than well-informed. The social media’s influence in dictating this misinformation of voters is higher as the mainstream media is largely influenced by the social media in Ethiopia.

The misinformation trend can be halted in the joint efforts of many stakeholders’ activities. This includes transparency and accountability (upon failure) of the government entities, the fact-checking effort of the media and journalists, the media literacy activities of civil societies, and an increased and quick moderation effort of the social media platform. Otherwise, laws such as the recently adopted “anti-hate speech and suppression of dissemination of false information” will only end up being instruments of the ruling party in Ethiopia. Moreover, laws are not effective ways of prevention of disinformation everywhere in the world.

Thursday, January 7, 2021

አሜሪካ እና ማኅበራዊ ሚዲያ

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ጉዳይ አሜሪካውያን የማይደራደሩበት ጉዳይ ነው። ሕገ መንግሥታቸውን መጀመሪያ ያሻሻሉትም በዚሁ ጉዳይ ነው። "ፈርስት አሜንድመንት" (አንደኛው ማሻሻያ) "ኮንግረስ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚገድብ ሕግ ማውጣት አይችልም" ይላል። ዛሬ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በአሜሪካውያኑ ኩባንያዎች ፌስቡክ እና ትዊተር ታግደዋል። አሜሪካውያንም ደንግጠዋል።  

ካፒቶል ሒል የሚሉት የፌዴራል መንግሥቱ ሕግ አውጪ (ኮንግረስ) በነውጠኞች የሰው መንጋ ተደፍሯል። አሜሪካውያኑ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ እንዲህ ዓይነት ቅሌት አይተው አያውቁም። ለዚህ የዳረጋቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ያገነነው የሴራ ትንተና እና የተዛባ መረጃ ልቅ ፍሰት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህ ድንገቴ መጣጥፍ የሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ፋይዳ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦስ እና የነውጥ መከላከል ጉዳይን በጨረፍታ እዳስሳለሁ። 

የንግግር ነጻነት ለምን? 

ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መከበር አለበት የምንለው ለአራት ወይም አምስት ዐቢይ ምክንያቶች ነው። 1ኛ) ተፈጥሯዊ ፍላጎት ስለሆነ፣ 2ኛ) እውነቱን በነጻነት ሳይነጋገሩ መረዳት ስለማይቻል፣ 3ኛ) የግለሰቦችን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማሳደግ፣ 4ኛ) አፈና የሚያስከትለውን ነውጥ ለማስቀረት፣ እና በቀደሙት ውስጥ ሊካተት ቢችልም፣ 5ኛ) ለሌሎች መብቶች መከበር አስፈላጊ ስለሆነ ነው። 

አመፅ ቀስቃሽ ንግግሮች እና የተዛቡ መረጃዎች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት መከበር አለበት የሚያስብሉ ምክንያቶችን ይቃረናሉ። ለዚህ ነው ዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች ሐሳብን የመግለጽ ነጻነቶች ስለሚገደቡባቸው ረገዶች (የጦርነት እና አመፅ ቅስቀሳ፣ የዘር ጥላቻ፣ ወዘተ…) እንዲሁም መርሖዎች (ሕጋዊነት፣ ቅቡልነት፣ አስፈላጊነት ላለው ዓላማ) ጥንቃቄ የተመላበት መዋቅር ለመዘርጋት የሞከሩት። ይሁንና የዘር ጭፍጨፋ አሰቃቂ ገጠመኝ ያላቸው አውሮጳውያን ሕጋዊ ጥንቃቄ ሲያበዙ፣ አሜሪካኖቹ ግን መፍትሔው ሁሌም ተጨማሪ ነጻነት ነው እያሉ ከርመዋል። 

በነገራችን ላይ የአውሮጳ እና የአሜሪካ ልዩነት በሕግ ረገድ ሰፊ ቢሆንም አውሮጳ (ለምሳሌ አክራሪዋ ጀርመን) ውስጥ ጋዜጠኞች በሙያቸው ይታሰራሉ ማለት አይደለም፤ ፖለቲካዊ ትችት ለመሰንዘርም ዜጎች አይፈሩም። አሜሪካውያንም ንግግሮችን በነጻነት ፈቅደው ለእያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር (micro aggression) ሳይቀር በመልስ ምት እያብጠለጠሉ የአደባባይ ንግግሮች በንግግር እንዲመከቱ የሚያደርግ ባሕል ፈጥረዋል። የሐሳብን የመግለጽ አፈናዎች ጋዜጠኞች ላይ የሚያርፈው፣ ወይም ንግግሮች ያለ ምንም ተጠያቂነት ሊቀሩ የሚችሉት በአምባገነናዊ ወይም ከፊል አምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ ነው። በርግጥ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር እና ሙያዊ ብቃትም ዝቅተኛ የሚሆነው በነዚሁ ከፊል/አምባገነን አገራት ነው። 

ሴራ መጎንጎን… 

ማኅበራዊ ሚዲያ ካመጣቸው ጦሶች መካከል ምንም ማስረጃ የሌላቸው መላምታዊ ሴራዎችን እንደ እውነት ማራገብ ማስቻሉ ነው። የተዛቡ መረጃዎች በመሠረቱ ጥንታዊ ናቸው። ቤንጃሚን ፍራንክሊን ከአሜሪካ "መሥራች አባቶች" ሁሉ አራቱም ቁልፍ የአሜሪካ ነጻነት እወጃ ሰነዶች ላይ የፈረሙ ሰው ናቸው። 'Like War' የተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ፖለቲካን የሚያትት መጽሐፍ ደራሲዎች ፍራንክሊንን "የአሜሪካ የተዛቡ መረጃዎች መሥራች አባት" ይሏቸዋል። ፍራንክሊን ለአሜሪካ ነጻነት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን በተዛቡ መረጃዎች እያዋዙ ሲጽፉ ከርመዋል። ብዙዎቹ የአገር ምሥረታ እና ሥልጣን ማደላደያ፣ እንዲሁም ሥልጣን መያዣ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ባይዋሹ እንኳ የማይሥማማቸውን እውነት ይገድፋሉ፣ የሚሥማማቸውን ያጋንናሉ። የትኛውም ፖለቲካዊ መዋቅር ወይም ማኅበራዊ ስርዓቶች በዚህ ዓይነት መንገድ ነው የተገነቡት። ሆኖም የሰው ልጅ ሥልጣኔም ይሁን ስርዓተ ማኅበሮች እየተሻሻሉ የሔዱት ቢያንስ ባለፉት ዘመናት ላይ ያሉ ቅራኔዎች ላይ በከፊል እየተሥማሙ እና የተሻለ ስርዓተ ማኅበር ለመመሥረት ያልተጻፈ ቃል ኪዳን ገብተው ነው። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ግን በሴራ ትንተና ተተብትበው አሻግሮ ማየት የተሳናቸውን ሰዎች እንዲደራጁ እና ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ዕድል በመስጠት የዓለምን ስርዓት ባፍጢሙ እንዲደፉት አቅም ሰጥቷቸዋል። 

ኪውኤኖን (QAnon) የሚባል የሴራ ወግ አለ። ነገርዬው በአሜሪካ ሰይጣን አምላኪ ዝነኛ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ድብቅ መንግሥት አላቸው ብሎ በማመን ላይ የተመሠረተ ነው። የዚህ ሴራ አማኞች ትራምፕ ከነዚህ ከሰይጣን አምላኪዎች ጋር ውጊያ ላይ ናቸው ብለው ያምናሉ። በስተመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ያሸንፉና ሰይጣን አምላኪዎቹ ይታሰራሉ ብለው ያምናሉ። ለዚህ ሴራ ትንተናቸው ምንም ማስረጃ አይፈልጉም። ከኪውኤኖን አማኞች ጋር ፖለቲካ፣ ርዕዮት ዓለም፣ ፖሊሲ አውርቶ መግባባት አይቻልም። ቁጥራቸው ደግሞ እየጨረመ ነው የሚሔደው። የትራምፕ ድጋፍ ሰልፎች ላይ ኪው (Q) የሚል ፊደል ያለበት ቲሸርት ወይም ኮፍያ ለብሰው ይወጣሉ። ትራምፕ እንዲህ ዓይነት ሰይጣን አምላኪ ማኅበር እንደሌለ እና እርሳቸውም ጦርነት ላይ እንዳልሆኑ እንዲናገሩ ቢጠየቁም ደጋፊዎቻቸውን ላለማጣት ሲሉ ("ይወዱኛል" ብለው) ሸፋፍነው አልፈውታል። ሕዳር ወር ላይ ከ70 በላይ የኪውኤኖን ንቅናቄ ደጋፊዎች ለኮንግረስ ተወዳድረው አንዷ ተመርጠዋል። በቅርቡ ፒው ሪሰርች እንደገመተው ከግማሽ በላይ አሜሪካውያን ስለንቅናቄው ቢያንስ ሰምተዋል። ይህ ሁሉ የጀመረው አንድ ራሱን የደበቀ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ባወራው ያልተረጋገጠ ወሬ ነው። 

ከሴራ ጉንጎና ባሻገር… 

የትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥም ሆነ የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት ያለ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚሆን ነገር አይመስልም። ነገር ግን የየአገራቱ ዜናዎች ሊያሳምኑን እንደሚፈልጉት የጠላቶቻቸው የእነ ራሺያ ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ክፍፍል ለመፍጠር መጣር [ብቻውን] የፈጠረው ችግር አይደለም። የተጠራቀሙ ማኅበራዊ ቅራኔዎች እና አድኃሪነት ሲጋጩ እና ሲፋለሙ፣ ያለምንም አርትኦት እና ይዘት ቁጥጥር (moderation) እንዳሻቸው እንዲፈነጩ መደረጉ ያመጣው ጦስ ነው። 

ሚዲያ የተነፈጋቸው የሴራ ንቅናቄ አራማጆች እና ያለማስረጃ ተሟጋቾች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የፈለጉትን የተዛባ መረጃ ጽፈው የፈለጉትን ያክል ተከታይ ያፈራሉ። የተዛባ መረጃቸው ሰለባ የሆኑ ተከታዮች የሚከፈለውን ሰብኣዊ መስዋዕትነት ከፍለው ለመሪዎቹ ግብ ይሰዋሉ። ትላንት ካፒቶል ሒል ገብታ በአስለቃሽ ጭስ እያለቀሰች ስትወጣ ሚዲያ የጠየቃት አንዲት ሴትዮ ለምን ወደ ሕንፃው እንደገባች ስትጠየቅ "ዐብዮት ላይ ነን" ("we are in revolution") ነበር ያለችው። ለነዚህ በተዛባ መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ የታወሩ ሰዎች የምርጫው ውጤት እነሱ የሚፈልጉትን ውጤት ካላመጣ በስተቀር ምርጫው ተአማኒ አይደለም። ምክንያቱም፣ ፕሮፓጋንዳው ከሌላ ወገን የሚመጣውን ነገር በሙሉ እንዲጠራጠሩ አድርጎ ሠርቷቸዋል። 

የእነቻይና ተቃራኒ ጥፋት… 

ቻይና የአሜሪካውያኑን ማኅበራዊ ሚዲያዎች አገሯ ላይ አግዳለች። የራሷን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በምትኩ አኑራለች። የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መንግሥትን ተቃውሞ መጻፍ አይቻልም። እንዲህ ያሉትን ይዘቶች የሚያነፈንፈው 'አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ' መጀመሪያውንም እንዳይለጠፍ ይከለክላል። አምልጦ ቢለጠፍ እንኳን ቆይቶ ያወርደዋል። ይህ ተሞክሮ አምባገነናዊ እና ተፈጥሯዊ ነጻነትን የሚጋፋ ነው። አምባገነኖች ቢያገኙት ለምን እንደሚያውሉት ስለሚታወቅ ተቀባይነት የለውም። ነገር ግን ቢያንስ መሆን የሌለበትን ነገር ለማወቅ እና ቴክኖለጂውን ከላየረ በጠቀስነው መርሕ (ሕጋዊነት፣ ተቀባይነትና አስፈላጊነት ላላው ዓላማ) ማዋል እንደሚቻል መማሪያ ይሆናል (የኮምፒዩተር ቫይረስን በአንቲቫይረስ እንደመመከት)። 

በሌላ በኩል ማኅበራዊ ሚዲያዎች የጥላቻ ንግግሮችን እና ነውጠኛ ፅንፈኝነትን (violent extremism) የሚኮተኩቱ ሴራዎችን የሚያጠልሉበት ስርዓት ያስፈልጋል። የማጥለል ሥራው ሐሳብ እንዳያፍን ስለሚያስፈልግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የተረጋገጡ ገጾች ሰማያዊ ባጅ እንደሚደረግባቸው ሁሉ፣ ተደጋጋሚ ሴራ ጉንጎናዎች እና ሴራ ተንታኞችን መለየት የሚያስችሉ፣ ቢጫ እና ቀይ ባጆችን እስከመለጠፍ እና ለተደራሲያኑ ማስጠንቀቂያ ደወል በመስጠት ተፅዕኗቸውን መቀነስ ያስፈልጋል። አለበለዚያ ከ'ሦስተኛው የዴሞክራሲ ሞገድ' ( 'Third Wave of Democracy') ወዲህ የታየው የዴሞክራሲ እመርታ በቀኝ ዘመም አክራሪነት፣ በሴራ ጉንጎና፣ በተዛቡ መረጃዎች፣ እና በጥላቻ ንቅናቄዎች ይቀለበሳል። 

ማኅበራዊ ሚዲያዎች አምባገነን መንግሥታትን ለመታገያ አቻ የሌላቸው መድረኮች ናቸው። ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግን አደገኛ ተግዳሮት ሆነዋል። 

የኢትዮጵያ ፈተና… 

የማኅበራዊ ሚዲያ ወጎች የኢትዮጵያ ፈተና አልሆኑም ማለት ክህደት ይሆናል። በርግጥ አምባገነናዊ አሠራሮችንም በመገዳደር አቻ የለውም። ሆኖም መሬት ላይ ግጭት ለመቆስቆስ የሚያበቁ ሴራዎችን በመፍጠር እና የተፈጠሩ ግጭቶችን በማባባስ በቀውስ ላይ ቀውስ እንዲፈጠር መድረክ ሆኗል። ሕዝበኝነት የፖለቲካው አዲስ ባሕሪይ እንዲሆን ያደረገውም ማኅበራዊ ሚዲያ ነው። ከገዢዎቹ እስከ ተቃዋሚዎቹ ድረስ በነፍስ ወከፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪዎች አሏቸው። የሥልጣን ሽኩቻዎች የሚራገቡት በፌስቡክ ነው። 

መጪው ምርጫ የፈለገውን ያክል ቢቀዘቅዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም። መራጮች ወደ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የሚሔዱት የተወዳዳሪዎችን አማራጮች ምንነት እና ልዩነት በቅጡ ተረድተው ከመሆኑ ይልቅ፥ በማኅበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳዎች የተፈጠሩ እውነትም፣ ውሸትም አዘል ማንነቶች እና ፍረጃዎች ተማምነው የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። በዚህ ረገድ ምርጫውን በቅጡ ተረድተው (well-informed ሆነው) ከሚመርጡ ሰዎች ይልቅ፣ በክፋት ተሳስተው (ill-informed ሆነው) የሚመርጡ ሰዎች ይበዙበታል ማለት ንፉግነት አይደለም። ይህ የሚሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ ምፅዓትን መመከት የሚችል የመንግሥት ግልጸኝነት፣ የሚዲያ ሐቅ አረጋጋጭነት፣ የብዙኃን የመረጃ ይዘት ተረጂነት እና የማኅበራዊ ሚዲያዎች በቂ አደገኛ ይዘት አጥላይነት በሌለበት በመሆኑ ችግሩ የከፋ ነው። በኢትዮጵያ የፍትሕ መከታ ሳይሆን የገዢዎች በትር የሆነው ሕግም ቢሆን የፖለቲካ ከመሆን አይተርፍም። ሕግ እንኳን በኢትዮጵያ፣ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ባላቸው አገራት ሳይቀር እንዲህ ዓይነቱን የተዛባ ወረርሽኝ ለመመከት ፍቱን መድኃኒት አይሆንም። 

ለዚህ ነው ስለአሜሪካ ሲወራ ለእኛ ብለን እንስማ የምለው!