Monday, April 7, 2025

ውንብድና እና የአዲስ አበባ ዝምታ…

 (በፍቃዱ ኃይሉ) 


አዲስ አበባ ውስጥ ውንብድና ጨምሯል። ይህንን የምለው እንዲሁ በልምድ “ዛሬ ከትላንት ይከፋል” በሚል ዲስኩር ተጠልፌ አይደለም። በራሴ ደርሶ ስላየሁት ነው፤ ያውም በአንድ ዓመት ርቀት ውስጥ ሁለት ጊዜ የወንበዴዎች ጥቃት ሰለባ ሆኛለሁ፤ ገጠመኙ ከተማዬ ውስጥ በፍርሐት እና በድንጋጤ እንድንቀሳቀስ አስገድዶኛል (ዝርዝሩን ወደ በኋላ እነግራችኋለሁ)።


አዲስ አበባ ዕድሜ ልኬን የኖርኩባት እና ጓዳ ጎድጓዳዋን የማውቃት ከተማ ነች። አዲሳባ ውስጥ ያልሔድኩበት ሰፈር፣ አምሽቼ ያልገባሁበት ሰዓት አልነበረም። በፊት፣ በፊት ውንብድና አልነበረም እያልኳችሁ አይደለም። ድብን አድርጎ ነበር። ነገር ግን በጥቂት ጥንቃቄ ራሳችሁን ማዳን ትችሉ ነበር። አሁን ግን ዓይን ያወጣ፣ ጭካኔ የበዛበት፣ አልፎ ተርፎም ጥቂት ገንዘብ የሚያወጣ ስልክ ይዛችሁ እንደሁ ተስፋ በማድረግ፣ ሕይወታችሁን አደጋ ላይ የሚጥል “ጨቦ” (chokehold) ተደራጅተው በመኪና በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈፀምበት፣ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ውንብድና ነው።


ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ፣ ይኼ ቦሌ አካባቢ፣ ሁለት ሆነው የሚሔዱ ሰዎችን በመኪና የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከኋላቸው ሲያንቋቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ነው። ቪዲዮው እንደሚያሳየው ቪዲዮው ከሚቀረፅበት አቅጣጫ የመኪና ጡሩንባ ሲጮህ ይደመጣል። ቀራጩ መኪናው ውስጥ ያለ ይመስላል። በዚህ ጊዜ ከወንበዴዎቹ አንዱ ወደ መኪናው ድንጋይ ይወረውርበታል። ሌላ መኪናም እንዲሁ መንገድ ሊዘጋባቸው ሲሞክር ነገር ይታያል። ውንብድናው እየተፈፀመ ያለው ተመልካች ባለበት ሁኔታ ነው። ሁለቱን ተጠቂዎች ያነቋቸው ወንበዴዎች ግን ዘረፋቸውን በዚህ ሁሉ ግርግር ሳይረበሹ አጠናቅቀዋል። ይህን ዓይነት ቪዲዮ ሳይ የመጀመሪያዬ አይደለም። በጣም በርካታ ተመሳሳይ ትራጄዲዎች በየማኅበራዊ ሚዲያው ተለጥፈዋል። 


የመጀመሪያ ጊዜ የተዘረፍኩት በሲኤምሲ አጥር በኩል በዋናው ጎዳና ላይ፣ ከምሽቱ 2:05 ሰዓት ገደማ ነበር። የመንገድ መብራት ቢኖርም በዛፎቹ ተከልሎ የእግረኛው መንገድ ደንገዝገዝ ብሏል። መኪኖች ውር ውር ይላሉ። ድንገት ከኋላዬ የሆነ ሰው አንገቴ ላይ ተጠመጠመብኝ። መጀመሪያ የመሰለኝ የሆነ መላፋት የሚወድ የልጅነት ጓደኛዬ ድንገት ሲያየኝ ዘሎ የተጠመጠመብኝ ነበር። ከዛ ሌላኛውን ሰው ከፊት ለፊቴ አየሁት። ነገርዬው ዝርፊያ እንደሆነ በገባኝ በቅፅበት ውስጥ የለሁም። ስነቃ፣ መሬት ላይ ተጋድሜያለሁ። በሰመመን “መሬት ላይ ለምን ተኛሁ?” እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ከዛ በአጠገቤ ሽው ሽው የሚሉ መኪኖች አሉ። ደንግጬ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ። ሰውነቴ ትንሽ ተጋግጧል። ስልኬን እና ዋሌቴን ወስደውታል፤ ኪሴ ውስጥ የነበረው ትንሽ ገንዘብ ግን አልተወሰደም። በኋላ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የተናገሩትን ገጣጥሜ ስተነትነው ወንበዴዎቹ በመኪና የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እኔን ሲያንቁ አንድ ሚኒባስ ታክሲ ሲመጣባቸው ራሴን እንደሳትኩ በቁሜ ጥለውኝ በያዙት መኪና ሸሽተው እንደሔዱ ገምቻለሁ። ሰውነቴ የተፋፋቀው በዛ ምክንያት መሰለኝ። የኪስ ገንዘቤን ያልወሰዱትም በዚያ ምክንያት ተጣድፈው ይመስላል። 


ይኼንን ገጠመኜን ስናገር በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች በሙሉ ወይ በቅርቡ ደርሶባቸዋል አልያም የደረሰበት ሰው ያውቃሉ። የእኔም ታናሽ ወንድም ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶበት ነበር። እሱ ያውም ቀድሞ ነቅቶ ስለታገላቸው ትከሻው አካባቢ በጩቤ ወግተውታል። 


በጉዞ ገጠመኝ ከዚህ በፊት የጎበኘኋቸው አንዳንድ ከተሞች ውስጥ በጣም የሚያስፈሩ ታሪኮችን ስሰማ “አዲስ አበባ እኮ ገነት ናት” እያልኩ እናገር ነበር። ናይሮቢ እና ካምፓላ ውስጥ ትንንሽ የሰፈር ሱቆች መስኮታቸው በብረት ፍርግርግ ነው የሚጠበቀው። የመስታወት ሱቆች ያሉት ሞል ውስጥ ብቻ እንጂ መንገድ ዳር አይደለም። የኤቲኤም ማሽኖች በወታደር የሚጠበቁባቸው ቦታዎች አሉ። ጆሃንስበርግ ከተማ ዳር ዳሩ ላይ በእግር መንቀሳቀስ አይመከርም፤ ምክንያቱም የተደራጁ ወንበዴዎች ድንገተኛ የዘረፋ ጥቃት ሊፈፅሙባችሁ ይችላሉ። አዲስ አበባ እነዚህ ተርታ አልደረሰችም። ነገር ግን ወደዚያ እየተጓዘች ይመስለኛል። 


ሁለተኛውን ገጠመኜን ከማውራቴ በፊት ለምን ውንብድና እንዲህ ዓይን አወጣ የሚለው ላይ ጥቂት እንነጋገር። 

ያልታቀደ የሕዝብ ብዛት? 


አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ደሴት ሆናለች። ከተማይቱ የአገሪቱ ብቸኛዋ የሀብት እና ፖለቲካ ማዕከል ነች። ከጥቂት ዓመታት በፊት የሕዝብ ዕድገቷ ምጣኔ ከወሊድ በላይ፣ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ በሚደረግ ፍልሰት የበለጠ እንደሚጨምር ጥናቶች አመልክተው ነበር። ፍልሰቱ ሌሎች ከተሞች ያዲሳባን ያህል የኢኮኖሚ ዕድል ስለማያቀርቡ እንዲሁም ብዙ አካባቢዎች ሰላም ስላጡ፣ ቢጨምር እንጂ እንደማይቀንስ አያጠራጥርም። በቅርብ ጊዜ የሕዝብ ቆጠራ ስላልተደረገ፣ ሁሉም ነዋሪ የአዲስ አበባ ቀበሌዎች ነዋሪነት መታወቂያ ስላልያዘ፣ እንዲሁም ከተማይቱ የጎረቤት አገሮች ስደተኞችም መነኻሪያ ስለሆነች፣ የአዲሳባን ትክክለኛ ሕዝብ ቁጥር የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ሳይሆን “እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው።” ይህም ማለት ለነዋሪዎቿ በቂ ዕድል ለመስጠት እንኳ ከተማዋ ነዋሪዎቿን በቅጡ አታውቃቸውም ማለት ነው። እንኳን በቅጡ ሳይሰላ፣ ተሰልቶም ቢሆን ፈጣን የከተማ ሕዝብ ዕድገት ደግሞ ውንብድናን የመከላከል አቅም ያሳጣል


የተጋነነ የሀብት አለመመጣጠን? 


አዲስ አበባ የድሃይቱ ኢትዮጵያ የሀብት ማዕከል ነች። ኢትዮጵያ ካመረተችው ብዙውን የምታፈሰው ዋና ከተማዋ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ይህች ከተማ መልሳ የምትሰጠው (መስጠት የምትችለው?)፣ ምናልባትም ከሚጠበቅባት በታች ነው። ወይም ደግሞ ስትሰጥ ለአንዱ በኮንቴይነር፣ ለሌላኛዋ በማንኪያ ነው። አዲስ አበባ፣ በዓመት 365 ቀናት ቁርጥ እየበሉ፣ ውስኪ እየተራጩ የሚያድሩ ሰዎች እና በልተው ማደር አለማደራቸውን እርግጠኛ መሆን የማይችሉ ሰዎች ተጎራብተው የሚያድሩባት ከተማም ሆናለች። የሀብት አለመመጣጠኑ የትየለሌ ነው። ችግሩን የከፋ የሚያደርገው የሀብት አለመመጣጠኑ በከተማዋ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች መካከልም የሰፋ መሆኑ ነው። የአገሪቱ አንጡራ ሀብት በሙሉ በመግነጢሳዊ ሀይሏ እየተሳበ የበለጠ እያስፋፋው ይሄዳል እንጂ አይቀንስም። የሀብት አለመመጣጠን ደግሞ ለውንብድና ቅመም ነው።


“የወንበዴው መንግሥት”? 


አንዳንድ ውንብድናዎች በጠራራ ፀሐይ ነው የሚፈፀሙት። ለምሳሌ የመኪና ስፖኪዮ ተሰረቀባችሁ እንበል። የተሰረቀባችሁን ስፖኪዮ ራሱን የማግኘት አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች እንዳሉ፣ ስርቆቱ የደረሰባቸው ሾፌሮች በሙሉ የሚያውቁት ነገር ነው። እርግጥ ነው፣ ድሮ ጀምሮ ሶማሊ ተራ የሚታወቀው በዚህ ጉዳይ ነበር። አሁን ግን ነገሩ በቴክኖሎጂ ተቀላጥፎ፣ በስልክ የተሰረቀባችሁን የስፖኪዮ ዓይነት እና ቦታ ትናገራላችሁ፣ ክፈሉ የተባላችሁትን ገንዘብ በሞባይል ክፍያ ዘዴ ትፈፅማላችሁ፣ ከዛ ሞተረኛ እዚያው የተሰረቃችሁበት ቦታ ድረስ መጥቶ ስፖኪዮውን በነበረበት ሁኔታ ገጥሞት ይመለሳል። ይህ የትልቁ ምስል ትንሹ ማሳያ ነው። እነዚህ “የሚደወልላቸው ሰዎች” እንዴት ከሕግ ተጠያቂነት ራዳር ውጪ ሆኑ? ምን ዓይነት የወንበዴዎች መረብ ቢኖራቸው ነው ይህን ያህል የከተማዋን ምሥጢር በሙሉ የሚያውቁት? የፀጥታ መዋቅሩ ውስጥስ ተባባሪ ይኖራቸው ይሆን? 


የተዛባ የፀጥታ አካላት የትኩረት አቅጣጫ? 


የፀጥታ ኃይሎችን በተመለከተ ግራ የሚያጋባው በርካታ ፖሊሶች በየአውራ ጎዳናው የተሰማሩ መሆኑ ላይ ነው። በሰላሙ ጊዜ ስንቀሳቀስ የከተማ ፖሊሶችም ይሁኑ ፌዴራል ፖሊሶችን በመንገዴ ላይ እዚህም እዚያም አያለሁ። ውንብድናውን ግን በቅጡ መከላከል አልቻሉም።


ለሁለተኛ ጊዜ የተዘረፍኩት ቦሌ መንገድ ላይ ጌቱ ኮሜርሻል ፊት ፊት ለፊት ነው። ሰዓቱ ከምሽቱ 4:00 ሰዓት ገደማ ነበር። ከእህቴ ጋር በእግራችን እየተጓዝን ሳለ፣ አንዱ ድንገት ከእጄ ላይ ስልኬን መንትፎ ከኋላችን ቀስ እያለ ከጎናችን የሚሔድ ቶዮታ ኤክዚኩዩቲቭ መኪና ውስጥ ገብቶ እልም አለ። መኪናው ወዲያው ወደ ኦሎሚፒያ ድልድይ ገባ። ታርጋውን ለማየት ብሞክርም የኤንጅኦዎች የሚመስል ከመሆኑ በቀር ቁጥሩን ማንበብ አልቻልኩም። መኪናው ውስጥ ሌሎችም ጎረምሶች ነበሩ፤ አንዱ ተባባሪውን ሊረዳ በሩን ከፍቶ ሲወጣ፣ ነጣቂው እንዳመለጠኝ ሲመለከት ተመልሶ ገብቶ ተጠጋግተው ተቀምጠው ከነፉ። ይህ የሆነው በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ነው። ለወትሮው በቦሌ መንገድ የፖሊስ መኪና ወዲያ ወዲህ ሲመላለስ ስለሚያመሽ ይህ መንገድ እንዲህ ተጋላጭ ይሆናል ብዬ በፍፁም አልገመትኩም ነበር። ከዚያ፣ ከእነድንጋጤያችን ከደንበል ወደ መስቀል ፍላወር በሚወስደው መንገድ ስንሔድ፣ ፖሊሶች ተሰብስበው የሚያልፉ መኪኖቹን እያስቆሙ ሲፈትሹ ደረስን።  ምናልባት ሌቦቹ የፖሊስን ትኩረት እና አቅጣጫ ያውቁ ይሆናል ብለን ገመትን። የፖሊሶቹ ትኩረት እንዲህ ያሉ ወንበዴዎች መቆጣጠርም ይሁን መያዝ ላይሆን ይችላል። የአዲስ አበባ ፖሊስ አልፎ አልፎ እነዚህን የተደራጁ ሌቦች ያዝኩኝ የሚል ሪፖርት ሲያወጣ አያለሁ። ይሁን እንጂ የችግሩን ጥልቀት የሚመጥን ትኩረት የሰጠው አይመስለኝም።


አቅመ ቢስነት? 


የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ፋና “ለጥንቃቄ” እያሉ በመንገድ ላይ ካሜራ የተቀዱ የውንብድና ቪዲዮዎችን አልፎ አልፎ ያጋራሉ። በአንዱ ቪዲዮ ላይ፣ በመሐል የአዲስ አበባ፣ በተጨናነቀ የትራፊክ መንገድ ላይ ሌቦች፣ የመኪናውን በር ከፍተው የሆነ ነገር ይዘው ሲሯሯጡ ይታያል። ሹፌሩ መኪናውን ትቶ እየሮጠ ሲከተላቸው ግጭት ይፈጠራል። ብዙ ጊዜ ግን መኪናውም ሊሰረቅ ስለሚችል፣ የሚከተላቸው ሰው ጥቂት ነው። ሚዲያዎቹ ለጥንቃቄ ነገሩን ማጋራታቸው ጥሩ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት ወንጀል በአደባባይ እንደሚፈፀም ያወቀው መንግሥት አቅም አጥሮት ይሆን እያልኩ አንዳንዴ እጠራጠራለሁ። በፊት በፊት ኪስ አውላቂነት እና አጭበርባሪነት፣ ወይም ስልክ በአሳቻ ሰዓትና ቦታ መንትፎ መሮጥ የመሳሰሉ ውንብድናዎች እንጂ እንዲህ ወንበዴዎቹ በኩራት በየአደባባዩ የሚንጎማለሉበት ሁኔታ አልነበረም። 


እንግዲህ እኔ የታዘብኳቸውን ጠቃቀስኩ እንጂ የውንብድናው ዓይነት ብዙ ነው። ለምሳሌ ያክል አንድ ዘገባ የመኪና ስርቆት የኢንሽራንስ ኩባንያዎች ለከፍተኛ ጫና እስከመዳረግ የደረሰ ችግር እንደሆነ አስረድቷል። ከስልክ እስከ መኪና የሚደርሰው ዝርፊያ እና ውንብድና በየጊዜው እየተወሳሰበ እና ነዋሪዎችን እያስጨነቀ የመጣ ነገር ነው። ድሮ ድሮ ተኝተው የማያድሩት ደማቅ የከተማዋ አካባቢዎች ሳይቀሩ፣ አሁን አሁን በጊዜ ነው የሚያሸልቡት። ለዚህ ደግሞ በከተማው የተንሰራፋው ውንብድና ብቸኛው ባይሆንም አንዱ ምክንያት መሆኑ እምብዛም አያጠያይቅም። 


ነገር ግን ስለዚህ የውንብድና ቀውስ ብዙም አይነገርም። እርግጥ ነው አዲስ አበባ ሌሎች ብዙ ፈተናዎች አሉባት፤ ፋታ የማይሰጥ የኑሮ ዱብ ዱብ አለ፣ ከተማዋ እንዳዲስ ፈርሳ እየተሠራች ነው (ነዋሪዎች በመፈናቀል እና በአዲሲቷ አዲስ አበባ ውስጥ ራሳቸውን ለማግኘት የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ነው)፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ያሉ ግጭቶች ወላፈን ከተማዋንም ይደርሳታል፣ ወዘተርፈ። ቢሆንም ይህ የተደራጀ ውንብድና ካሁኑ ካልተገታ፣ እያደር ወጥቶ ወጥቶ መግባት ብርቅ ሊሆን ይችላል።  ከተማችን ከላይ የጠቀስኳቸውን ከተሞች ከመሆኗ በፊት ልንታደጋት ይገባል።



9 comments:

  1. ውድ በፍቃዱ የግል ገጠመኝህን ጨምሮ ከተማው ውስጥ ዕለት በዕለት የሚደረገውን የተደራጀ ውንብድና በትክክል ገልፀኸዋል፣አዲስ አበባ ውስጥ በቀን በጠራራ ፀሃይ በጎዳናዎች ላይ በግልፅ ዘረፋዎች ይፈፀማሉ፣መሸት ካለ በእግር ለመጓዝ አስጊ ነው ረዥም መንገዶች ላይ በመኪና ቅኝት የሚያደርጉ ወይም እግረኛ ፖሊሶችን መንገዱ ላይ ማየት አይቻልም ፣ሌላው ቀርቶ በቀን ሁለት ሶስት ሆነው መኪና ውስጥ ያለን ተሳፋሪ ወይም ሾፌር አዋክበው ሞባይል ወይም ቦርሳ ነጥቀው ሲሄዱ ምን እየሰሩ እንደሆነ ገብቶት ወይም ጠርጥሮ ለመከታተል ለመያዝ ብቃት ያለው የፖሊስ አባል ያለ አይመስለኝም፣ምናልባትም ፖሊሶቹ የከተማን የማጭበርበሪያ ስልት ለመረዳት የማይችሉ ከተሜነቱ የሚያንሳቸው ስለሆነም ይሁን አንዳንዴ በቅርብ ርቀት ባሉበትም እንደ ሁጳ፣ ሿሿ ፣ጥምጥም ፣ጨቡ፣ (ሀንግ) በመሳሰሉትን የሌብነት ስልቶች ሰዎች ሲዘረፉ ለመከላከል ምንም ሲያደርጉ አይታይም ነገሩን በቅጡ የሚረዱትም አይመስለኝም ።

    ReplyDelete
  2. ፍቄ ልቅም ያለ ሀቅ ነው የከተብከው አሁን ላይ አምሽቶ ለመግባት ትልቅ ስጋት ያለባት ከተማ ብትኖር አዲስ አበባ ነች፡፡
    የፀጥታ አካላት ወደ ቢት መግቢያ እዚህ ግባ የማይባሉ ለአደጋ የማትጋለጥባቸው ቦታዎች ላይ ፍተሻ ያደርጋሉ ስርቆት ሲፈፀም ግን የሉም፡፡
    እኔም ሰሚት 72 ፖሊስ በአምስት ሜትር ልዩነት ቁሞ እያየ ተደብድቤ ነገርግን ባደረኩት ጥረት ከመዘረፍ ድኛለሁ፡፡

    ReplyDelete
  3. በጣም የሚያሳቅቅ ጊዜ ላይ ተደርሷል ከልጆቼ ጋር ነው ሁሌ የምንቀሳቀሰው ግን ሰላም የሚሰማኝ የአዲስ አበባ ጎዳና እዛው ትምህርት ቤታቸው አካባቢ ከዛም ሰፈር ስንደርስና ያደኩበት ሰፈር ብቻ ነው። ሌላውን ጉዞ በሰቀቀን ነው የምንቀሳቀሰው አንድ ነገር ቢያደርጉኝ ምን ይሆናሉ ልጆቼ እያልኩ። ከምሽት አንድ ሰአት በዃላ ጭራሽ አልሞክረዉም። ደና ኑሮ ቢኖርህ በምንም ተአምር ግን በጥቂቱም ቢሆን እያጣጣምክ በሰላም መኖር አይታሰብም። ሰላሜ ቤቴ ውስጥ ብቻ ነው ያለው። ለሱም ኑሮ በዚ ከቀጠለ የጊዜ ጉዳይ ይመስለኛል።

    ReplyDelete
  4. ከሚበላው ፆሙን የሚያደረው ከተሜ በሚበዛበት ወንጀል እያደገ ቢሄድ ምንም አይገርምም። ፖሊሱስ ቢሆን በየትኛው ደሞዙ ኑሮውን አሸንፎ ይኖራል ብለን በስራው ጉድለት እንውቀሰው። ብቻ የወደፊቱን ያስፈራል።

    ReplyDelete
  5. የመንግስት ዉጤት ነዉ

    ReplyDelete
  6. ኤርታራዊያን ከካንፕ ወጥተዉ በከተማ እንዲኖሩ ከተፈቀደላቸዉ በሆላ ብዙ ጨቦዎች የተፈጠሩት ከእነሱ ነወ ሲያዙ ትግሬ ነኝ የአዲግራት ልጅ ነኝ ይላሉ ጨቦ ኤርትራዊ ነዉ ።

    ReplyDelete
  7. This happened to me around Adey Abeba, Saris. I was driving with my car door unlocked when a guy approached my side and hit my car hard. In that moment, another guy snatched my iPhone 14 Pro Max and ran off. This occurred at 7 AM, in front of the public and nearby traffic police.

    ReplyDelete
  8. ከተወለድኩበት ቤት በመቶ ሜትር ርቀት ላይ በገጀራ የታገዘ ዝርፊያ ከተፈፀመብኝ በኋላ ከመሸ ከኋላዬ ሰው እንዲሄድ አልፈቅድም

    ReplyDelete
  9. Dear B: thanks for writing on this timely topic and sharing your own unfortunate experiences too. Let me also add a few factor which I thought I missed in your analysis legal aspects contributing to this problem: 1) the probability of getting caught, 2) the severity of punishment for these criminals offences, 3) the certainty that those who are commit these crimes will actually receive the legal punishment. In other words these crimes might be increasing because criminals know that there is low probability that they will be caught, and that they do not fear the punishment they would receive, and that criminals know that that they can evade justice.

    ReplyDelete

My Public Appeal: Voice of America Matters to Ethiopia

To the Government of the United States of America and all concerned, As a friend of the free press from Ethiopia, I write this appeal with d...