አቶ መለስና ጓደኞቻቸው አምባገነን ስርአትን ለመቀየር ነፍጥ አንስተው፣
በጭቆና ላለመኖር ሲሉ በህይወታቸው ተወራርደዋል፤ አላማቸውን ለማሳካት ገድለዋል ሞተዋል፡፡ ድል ቀንቷቸው የዛሬ 21 አመት አምባገነኑን
የደርግ ስርአት አስወግደው ምኒሊክ ቤተመንግስት ሲገቡ ኢትዮጵያን በለውጥ ጎዳና ሊመሩ፣ ዴሞክራሲን በማስፈን በሀገሪቱ አዲስ ታሪክ
እንዲያኖሩ የሚያስችል ዕድል ነበራቸው ፡፡ አምባገነኑን የኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ደርግ ካስወገዱ በኋላ ግን አምባገነኑን
የአቶ መለስ ዜናዊን ስርአት ከማስቀመጥ ባለፈ በግንቦት 20 ድል ታሪክ ሊሰሩ አልቻሉም፡፡
ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት፣ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ዶጋ አመድ አድርጎ ግንቦት 20, 1983 ዓ.ም የተቋጨው ጦርነት አንድን ወታደራዊ አምባገነን መሪ በኃይል
በማስወገድ የይምሰል ዴሞክራሲያዊ ስርአትን(pseudo democracy) የገነባ ሲቪል አምባገነን መተካት የተወሰነ ቡድንን ወይም
ግለሰቦችን ፖለቲካዊ የበላይነት(hegemony) ለማረጋገጥ ያለመ እንዳልነበር በትጥቅ ትግሉ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች ያረጋግጣሉ፡፡
የህወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገብሩ አስራት ሰኔ 19,2002 ለወጣችው አዲስ ፕሬስ ጋዜጣ አሞራው
ስለተባለ የህወሓት ጀግና ታጋይ ሲያስረዱ ‹‹አሞራው ቀና ብሎ እየተደረገና እየሆነ ያለውን ነገር ቢያይ ይገርመው ነበር›› ካሉ
በኋላ የአቶ መለስ መንግስት በአሞራውና በሌሎች ታጋይ ሰማእታት መስዋዕትነት ስልጣን እየነገደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን የያዘበት ተመሳሳይ ወቅት አምባገነናዊ ኮሚኒስት ስርአቶችን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ
የጀመሩት የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ለውጥ ማምጣታቸውን Carleton
University፡ Institute of European and Russian
Studies አጥኚ የሆኑት ድራጎስ
ፖፓ (DRAGOS
POPA) ሮሜኒያንና ቡልጋሪያን ነቅሰው ያመላክታሉ፡፡ የባልካን ሀገራትም ሁለት አስርት
ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እምርታ ማምጣታቸውን The
democratic transformation of the Balkans በሚል ርዕስ የቀረበው የሮዛ ባልፈር እና ኮሪና ስትራቱላት (Rosa Balfour and Corina Stratulat) ጥናት ያመላክታል፡፡ ጥናቱ
የባልካን ሀገራት በአጭር ጊዜያት ውስጥ ሶስት መሰረታዊ ለውጦችን ማስመዝገባቸውን ያስረዳል‹‹ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ከኮሚኒዝም የእዝ
ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ እንዲሁም ከአንድ ፓርቲ አገዛዝ ወደ መድብለ ዴሞክራሲ ተለውጠዋል›› ይላል፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ባለፉት 21 አመታት የታየውና አሁንም ያለው ነባራዊ ሁኔታ ለግንቦት 20 ድል የወጣውን የህይወት ግብር እና በድሉ ማግስት የተገኘውን የግንቦት 20 ፍሬ ስናወራርድ
ውጤቱ ኪሳራን የሚያመላክት ነው፡፡
ይህ ጽሁፍ በህወሓት በስተመጨረሻም በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት ለ17
አመታት በተደረገው ፅኑ ትግል የተገኘው የግንቦት 20 ድል ሊያመጣ ያልቻላቸውን አስር አንኳር ነጥቦች ይፈትሻል፡፡