ከዞን ዘጠኝ የተወሰደ
“ፒያሳ፤ መሐሙድጋ ጠብቂኝ” በመሐመድ ሰልማን የተጻፈ እና ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ኢ-ልቦለዳዊ
መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት አማካይነትመጽሐፉን የመገምገሚያ ዝግጅት አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም
ቀርቦ ነበር፡፡ በውይይቱ መሐል የመጽሐፉ ዝነኝነት ምንጮች ምን ምን ናቸው የሚል ውይይት የነበረ ሲሆን ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል
‹‹ደራሲው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ጸሐፊ የነበረ›› መሆኑን እና ‹‹ጽሑፎቹም በአዲስ ነገር ጋዜጣ እና ድረገጽ ላይ ወጥተው
የነበሩ›› መሆናቸውን ጠቀሰ፡፡ ውይይቱ የአዲስ ነገር ጋዜጣ መታሰቢያ ይመስል፣ የትዝታ ጫወታው ተጧጧፈ እናም ከውይይቱ ተሳታፊዎች
አንዱ የሚከተለውን ሲናገር ረዥም ጭብጨባ አዳራሹን አደመቀው ወጣቱ አስተያየት ሰጪ በንግግሩ መሃል የተጠቀመው እና ጢም ብሎ የሞላውን
አዳራሽ በጭብጨባ ያናጋው ንግግር የሚከተለው ነበር፡፡
‹‹ይህ ትውልድ በአዲስ ነገር ጋዜጣ የሚደራደር ትውልድ አይደለም፡፡››
ጉዳዩን አስገራሚ የሚደርገው ወጣቱ ይህንን የተናገረው አዲስ ነገር ጋዜጣ መታተም ካቆመች ከሁለት
ዓመታት በኋላ መሆኑ ሲሆን፣ አጋጣሚው የጋዜጣዋ መንፈስ በበርካቶች ልብ ውስጥ በትኩስነት መኖሩን የሚናገር ነበር፡፡
ዛሬ፣ ጥቅምት 5/2005 የዓለም የጡመራ የተግባር ቀን (Blog Action Day 2012) “የኛ ኃይል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
የጡመራ የተግባር ቀን በየዓመቱ የሚከበር፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦማሪዎች በሙሉ በአንድ ሐሳብ ዙሪያ የሚጽፉበት ቀን ነው፡፡ የተጀመረው
እ.ኤ.አ. በ2007 ሲሆን በተመሳሳይ ዓመት ‹‹አካባቢ››፣ በ2008
‹‹ድህነት››፣ በ2009 ‹‹አየር ለውጥ››፣ በ2010 ‹‹ውሃ››፣ በ2011 ‹‹ምግብ›› በሚል ሲካሄድ ዘንድሮ ደግሞ በ2012
‹‹የእኛ ኃይል›› በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው መሪ ቃል፣ ማኅበረሰብ፣ እኩልነት፣ ፀረ-ሙስና እና ነጻነትን በተመለከተ የኛ ኃይል
ምን እንደሆነ በመስበክ እንዲከበር ታስቦ የተመረጠ ነው፡፡ አከባበሩ ቀላል ነው፤ አስተባባሪዎቹ እንዳስቀመጡት ‹‹profile someone or a group who inspires you by the way they made a
positive influence… (ባመጡት አዎንታዊ ተጽዕኖ ያነቃቃችሁን የየሆነ ሰው ወይም ቡድን በመምረጥ ጻፉ…)›› የሚል ነው፡፡
እኛም ጮክ ብለን ስናስብበት እና በጭንቅላታችን ያቃጨለችው አዲስ ነገር ጋዜጣ ብቻ ሆነች፡፡
አዲስ ነገር ጋዜጣ ለሁለት ዓመታት (ከጥቅምት 2000 እስከ ታሕሳስ 2002) ብቻ በስርጭት የቆየች ነገር ግን መራኄ አዘጋጇ መስፍን
ነጋሽ የጋዜጣዋን ሁለተኛ ዓመት አስመልክቶ እንደገለፀው ‹‹አጭር ግን ረዥም ዓመት›› የኖረች ያክል የማትረሳ ጋዜጣ ናት፡፡