Monday, April 7, 2025

ውንብድና እና የአዲስ አበባ ዝምታ…

 (በፍቃዱ ኃይሉ) 


አዲስ አበባ ውስጥ ውንብድና ጨምሯል። ይህንን የምለው እንዲሁ በልምድ “ዛሬ ከትላንት ይከፋል” በሚል ዲስኩር ተጠልፌ አይደለም። በራሴ ደርሶ ስላየሁት ነው፤ ያውም በአንድ ዓመት ርቀት ውስጥ ሁለት ጊዜ የወንበዴዎች ጥቃት ሰለባ ሆኛለሁ፤ ገጠመኙ ከተማዬ ውስጥ በፍርሐት እና በድንጋጤ እንድንቀሳቀስ አስገድዶኛል (ዝርዝሩን ወደ በኋላ እነግራችኋለሁ)።


አዲስ አበባ ዕድሜ ልኬን የኖርኩባት እና ጓዳ ጎድጓዳዋን የማውቃት ከተማ ነች። አዲሳባ ውስጥ ያልሔድኩበት ሰፈር፣ አምሽቼ ያልገባሁበት ሰዓት አልነበረም። በፊት፣ በፊት ውንብድና አልነበረም እያልኳችሁ አይደለም። ድብን አድርጎ ነበር። ነገር ግን በጥቂት ጥንቃቄ ራሳችሁን ማዳን ትችሉ ነበር። አሁን ግን ዓይን ያወጣ፣ ጭካኔ የበዛበት፣ አልፎ ተርፎም ጥቂት ገንዘብ የሚያወጣ ስልክ ይዛችሁ እንደሁ ተስፋ በማድረግ፣ ሕይወታችሁን አደጋ ላይ የሚጥል “ጨቦ” (chokehold) ተደራጅተው በመኪና በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈፀምበት፣ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ውንብድና ነው።


ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ፣ ይኼ ቦሌ አካባቢ፣ ሁለት ሆነው የሚሔዱ ሰዎችን በመኪና የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከኋላቸው ሲያንቋቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ነው። ቪዲዮው እንደሚያሳየው ቪዲዮው ከሚቀረፅበት አቅጣጫ የመኪና ጡሩንባ ሲጮህ ይደመጣል። ቀራጩ መኪናው ውስጥ ያለ ይመስላል። በዚህ ጊዜ ከወንበዴዎቹ አንዱ ወደ መኪናው ድንጋይ ይወረውርበታል። ሌላ መኪናም እንዲሁ መንገድ ሊዘጋባቸው ሲሞክር ነገር ይታያል። ውንብድናው እየተፈፀመ ያለው ተመልካች ባለበት ሁኔታ ነው። ሁለቱን ተጠቂዎች ያነቋቸው ወንበዴዎች ግን ዘረፋቸውን በዚህ ሁሉ ግርግር ሳይረበሹ አጠናቅቀዋል። ይህን ዓይነት ቪዲዮ ሳይ የመጀመሪያዬ አይደለም። በጣም በርካታ ተመሳሳይ ትራጄዲዎች በየማኅበራዊ ሚዲያው ተለጥፈዋል። 


የመጀመሪያ ጊዜ የተዘረፍኩት በሲኤምሲ አጥር በኩል በዋናው ጎዳና ላይ፣ ከምሽቱ 2:05 ሰዓት ገደማ ነበር። የመንገድ መብራት ቢኖርም በዛፎቹ ተከልሎ የእግረኛው መንገድ ደንገዝገዝ ብሏል። መኪኖች ውር ውር ይላሉ። ድንገት ከኋላዬ የሆነ ሰው አንገቴ ላይ ተጠመጠመብኝ። መጀመሪያ የመሰለኝ የሆነ መላፋት የሚወድ የልጅነት ጓደኛዬ ድንገት ሲያየኝ ዘሎ የተጠመጠመብኝ ነበር። ከዛ ሌላኛውን ሰው ከፊት ለፊቴ አየሁት። ነገርዬው ዝርፊያ እንደሆነ በገባኝ በቅፅበት ውስጥ የለሁም። ስነቃ፣ መሬት ላይ ተጋድሜያለሁ። በሰመመን “መሬት ላይ ለምን ተኛሁ?” እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ከዛ በአጠገቤ ሽው ሽው የሚሉ መኪኖች አሉ። ደንግጬ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ። ሰውነቴ ትንሽ ተጋግጧል። ስልኬን እና ዋሌቴን ወስደውታል፤ ኪሴ ውስጥ የነበረው ትንሽ ገንዘብ ግን አልተወሰደም። በኋላ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የተናገሩትን ገጣጥሜ ስተነትነው ወንበዴዎቹ በመኪና የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እኔን ሲያንቁ አንድ ሚኒባስ ታክሲ ሲመጣባቸው ራሴን እንደሳትኩ በቁሜ ጥለውኝ በያዙት መኪና ሸሽተው እንደሔዱ ገምቻለሁ። ሰውነቴ የተፋፋቀው በዛ ምክንያት መሰለኝ። የኪስ ገንዘቤን ያልወሰዱትም በዚያ ምክንያት ተጣድፈው ይመስላል። 


ይኼንን ገጠመኜን ስናገር በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች በሙሉ ወይ በቅርቡ ደርሶባቸዋል አልያም የደረሰበት ሰው ያውቃሉ። የእኔም ታናሽ ወንድም ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶበት ነበር። እሱ ያውም ቀድሞ ነቅቶ ስለታገላቸው ትከሻው አካባቢ በጩቤ ወግተውታል። 


በጉዞ ገጠመኝ ከዚህ በፊት የጎበኘኋቸው አንዳንድ ከተሞች ውስጥ በጣም የሚያስፈሩ ታሪኮችን ስሰማ “አዲስ አበባ እኮ ገነት ናት” እያልኩ እናገር ነበር። ናይሮቢ እና ካምፓላ ውስጥ ትንንሽ የሰፈር ሱቆች መስኮታቸው በብረት ፍርግርግ ነው የሚጠበቀው። የመስታወት ሱቆች ያሉት ሞል ውስጥ ብቻ እንጂ መንገድ ዳር አይደለም። የኤቲኤም ማሽኖች በወታደር የሚጠበቁባቸው ቦታዎች አሉ። ጆሃንስበርግ ከተማ ዳር ዳሩ ላይ በእግር መንቀሳቀስ አይመከርም፤ ምክንያቱም የተደራጁ ወንበዴዎች ድንገተኛ የዘረፋ ጥቃት ሊፈፅሙባችሁ ይችላሉ። አዲስ አበባ እነዚህ ተርታ አልደረሰችም። ነገር ግን ወደዚያ እየተጓዘች ይመስለኛል። 


ሁለተኛውን ገጠመኜን ከማውራቴ በፊት ለምን ውንብድና እንዲህ ዓይን አወጣ የሚለው ላይ ጥቂት እንነጋገር። 

Friday, March 28, 2025

ግለሰብ፣ ፓርቲ፣ መንግሥት እና አገር

(በፍቃዱ . ኃይሉ)

አምባገነናዊ ስርዓቶች ግለሰብ፣ ፓርቲ፣ መንግሥት እና አገርን ለዜጎቻቸው እንደማይነጣጠሉ አስመስለው ያቀርባሉ። ግለሰቡን ከነካችሁ ፓርቲው ይፈርሳል፣ ፓርቲውን ከነካችሁ፣ መንግሥቱ ይፈርሳል፣ መንግሥቱን ከነካችሁ አገሩ ይፈርሳል። እውነት አላቸው። አምባገነኖች እና የአገዛዙ ጥቅመኞች ሕልውናቸውን ከአገሩ ሕልውና ጋር አስተሳስረው ነው የሚኖሩት። ኢሕአዴግ ከመውደቁ ትንሽ ሰሞን ቀደም ብሎ በአማርኛ ዝና ያገኘ አንድ የትግርኛ አባባል ነበርለምጣዱ ሲባል አይጧ ትትረፍ።በግለሰቦች እና አገዛዞች መተሳሰር ምክንያት ዜጎች አምባገነኖችን ለመጣል ሲታገሉ አገራቸውንም ራሳቸው ላይ ይማፍረስ ስጋት አላቸው። ስለዚህ አምባገነኖችን መታገል በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን የማይቻል አይደለም።

የማይሻር ግለሰብ እና የማይቀየር የፖለቲካ ፓርቲ ያለበት መንግሥት መጨረሻው ለአገሩ ጠንቅ መሆን ነው። ግለሰቡም፣ ፓርቲውም ዘላቂ ዕድሜ የላቸውም። በመሆኑም ዜጎች መፃዒ ዕጣ ፈንታቸውን በሰቀቀን እንዲጠብቁ ይገደዳሉ። ተወደደም ተጠላም በብዙኃን ይሁንታ የሚወጣ እና የሚወርድ መንግሥት ያለበት አገር የተሻለ ተስፋና ሰላም ለሕዝቡ ይሰጣል። ነገር ግን በብዙኃን ይሁንታ መውጣት እና መውረድ ብቻ በቂ አይደለም። ገዢዎች በሥልጣን ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ማድረግ የሚችሉት ነገር ካልተገደበ እያደር አውዳሚ ከመሆን አይመለሱም።

ይባስ ብሎ፣ በአምባገነናዊ ስርዓቶች ውስጥ ግን ሥልጣን ላይ መውጫ እና ሥልጣን ላይ መሰንበቻው መንገድ ነውጥ ብቻ ነው። ባለ ፍፁም ሥልጣኑ - አምባገነኑ - በወደቀ ቁጥር፣ ቢያንስ በየትውልዱ ትርምስ ይኖራል። አጥኚዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት፣ ትልቅ ጦርነት ያላየ ትውልድ የለም የሚሉት ለዚህ ነው።

መንግሥት በግለሰብ እጅ ተጠልፎ እንዳይወድቅ ለማድረግ የተፈጠረው ሞዴል ማዲሰኒያን ሞዴል ይባላል። ከአሜሪካ መንግሥት መሥራቾች መካከል ጄምስ ማዲሰን በጻፈው ጽሑፍ ላይ የተመሠረተ ሞዴል ነው። ሞዴሉ፣ ቢያንስ እስካሁን ለብዙ ዴሞክራሲያዊ አገሮች ሠርቷል።  የጀምስ ማዲሰን ጽሑፍ እንዲህ ይላል፤ሰዎች መልዓክ ቢሆኑ ኖሮ፥ መንግሥታት አያስፈልጉም ነበር። ሰዎችን የሚገዟቸው መላዕክት ቢሆኑም ኖሮ፥ መንግሥታት ላይ ቁጥጥር መጣል አያስፈልግም ነበር። ሰዎችን ሰዎች በሚያስተዳድሩበት ሁኔታ መንግሥትን መቅረፅ፥ ከባድ ፈተና አለበት። መጀመሪያ ገዢው ተገዢዎቹን መቆጣጠር መቻል አለበት፤ ከዚያ ገዢው ራሱን እንዲገዛ ማስገደድ ያስፈልጋል።” ("ፌዴራሊስት ፔፐርስ 51")

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም የማዲሰንያንን ሞዴል ለመኮረጅ ሞክሯል። በመነባነብ እንደሚነገረው ሕግ አውጪ አለ (ፓርላማው) ሕግ ተርጓሚ አለ (ፍርድ ቤቶችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ) እንዲሁም አስፈፃሚ አካል አለ (ጠቅላይ ሚኒስቴሩ፣ ካቢኔው፣ የፀጥታ ኃይሉ፣ ወዘተ።) ነገር ግን ሁለቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች የአስፈፃሚው አካል እስረኞች እንጂ ሚዛን ጠባቂዎች አይደሉም።

ውንብድና እና የአዲስ አበባ ዝምታ…

  (በፍቃዱ ኃይሉ)  አዲስ አበባ ውስጥ ውንብድና ጨምሯል። ይህንን የምለው እንዲሁ በልምድ “ዛሬ ከትላንት ይከፋል” በሚል ዲስኩር ተጠልፌ አይደለም። በራሴ ደርሶ ስላየሁት ነው፤ ያውም በአንድ ዓመት ርቀት ውስጥ ሁለት ጊዜ...