(በፍቃዱ ኃይሉ)
አዲስ አበባ ውስጥ ውንብድና ጨምሯል። ይህንን የምለው እንዲሁ በልምድ “ዛሬ ከትላንት ይከፋል” በሚል ዲስኩር ተጠልፌ አይደለም። በራሴ ደርሶ ስላየሁት ነው፤ ያውም በአንድ ዓመት ርቀት ውስጥ ሁለት ጊዜ የወንበዴዎች ጥቃት ሰለባ ሆኛለሁ፤ ገጠመኙ ከተማዬ ውስጥ በፍርሐት እና በድንጋጤ እንድንቀሳቀስ አስገድዶኛል (ዝርዝሩን ወደ በኋላ እነግራችኋለሁ)።
አዲስ አበባ ዕድሜ ልኬን የኖርኩባት እና ጓዳ ጎድጓዳዋን የማውቃት ከተማ ነች። አዲሳባ ውስጥ ያልሔድኩበት ሰፈር፣ አምሽቼ ያልገባሁበት ሰዓት አልነበረም። በፊት፣ በፊት ውንብድና አልነበረም እያልኳችሁ አይደለም። ድብን አድርጎ ነበር። ነገር ግን በጥቂት ጥንቃቄ ራሳችሁን ማዳን ትችሉ ነበር። አሁን ግን ዓይን ያወጣ፣ ጭካኔ የበዛበት፣ አልፎ ተርፎም ጥቂት ገንዘብ የሚያወጣ ስልክ ይዛችሁ እንደሁ ተስፋ በማድረግ፣ ሕይወታችሁን አደጋ ላይ የሚጥል “ጨቦ” (chokehold) ተደራጅተው በመኪና በሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚፈፀምበት፣ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ውንብድና ነው።
ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ፣ ይኼ ቦሌ አካባቢ፣ ሁለት ሆነው የሚሔዱ ሰዎችን በመኪና የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከኋላቸው ሲያንቋቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ነው። ቪዲዮው እንደሚያሳየው ቪዲዮው ከሚቀረፅበት አቅጣጫ የመኪና ጡሩንባ ሲጮህ ይደመጣል። ቀራጩ መኪናው ውስጥ ያለ ይመስላል። በዚህ ጊዜ ከወንበዴዎቹ አንዱ ወደ መኪናው ድንጋይ ይወረውርበታል። ሌላ መኪናም እንዲሁ መንገድ ሊዘጋባቸው ሲሞክር ነገር ይታያል። ውንብድናው እየተፈፀመ ያለው ተመልካች ባለበት ሁኔታ ነው። ሁለቱን ተጠቂዎች ያነቋቸው ወንበዴዎች ግን ዘረፋቸውን በዚህ ሁሉ ግርግር ሳይረበሹ አጠናቅቀዋል። ይህን ዓይነት ቪዲዮ ሳይ የመጀመሪያዬ አይደለም። በጣም በርካታ ተመሳሳይ ትራጄዲዎች በየማኅበራዊ ሚዲያው ተለጥፈዋል።
የመጀመሪያ ጊዜ የተዘረፍኩት በሲኤምሲ አጥር በኩል በዋናው ጎዳና ላይ፣ ከምሽቱ 2:05 ሰዓት ገደማ ነበር። የመንገድ መብራት ቢኖርም በዛፎቹ ተከልሎ የእግረኛው መንገድ ደንገዝገዝ ብሏል። መኪኖች ውር ውር ይላሉ። ድንገት ከኋላዬ የሆነ ሰው አንገቴ ላይ ተጠመጠመብኝ። መጀመሪያ የመሰለኝ የሆነ መላፋት የሚወድ የልጅነት ጓደኛዬ ድንገት ሲያየኝ ዘሎ የተጠመጠመብኝ ነበር። ከዛ ሌላኛውን ሰው ከፊት ለፊቴ አየሁት። ነገርዬው ዝርፊያ እንደሆነ በገባኝ በቅፅበት ውስጥ የለሁም። ስነቃ፣ መሬት ላይ ተጋድሜያለሁ። በሰመመን “መሬት ላይ ለምን ተኛሁ?” እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ከዛ በአጠገቤ ሽው ሽው የሚሉ መኪኖች አሉ። ደንግጬ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ። ሰውነቴ ትንሽ ተጋግጧል። ስልኬን እና ዋሌቴን ወስደውታል፤ ኪሴ ውስጥ የነበረው ትንሽ ገንዘብ ግን አልተወሰደም። በኋላ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የተናገሩትን ገጣጥሜ ስተነትነው ወንበዴዎቹ በመኪና የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እኔን ሲያንቁ አንድ ሚኒባስ ታክሲ ሲመጣባቸው ራሴን እንደሳትኩ በቁሜ ጥለውኝ በያዙት መኪና ሸሽተው እንደሔዱ ገምቻለሁ። ሰውነቴ የተፋፋቀው በዛ ምክንያት መሰለኝ። የኪስ ገንዘቤን ያልወሰዱትም በዚያ ምክንያት ተጣድፈው ይመስላል።
ይኼንን ገጠመኜን ስናገር በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች በሙሉ ወይ በቅርቡ ደርሶባቸዋል አልያም የደረሰበት ሰው ያውቃሉ። የእኔም ታናሽ ወንድም ከጥቂት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶበት ነበር። እሱ ያውም ቀድሞ ነቅቶ ስለታገላቸው ትከሻው አካባቢ በጩቤ ወግተውታል።
በጉዞ ገጠመኝ ከዚህ በፊት የጎበኘኋቸው አንዳንድ ከተሞች ውስጥ በጣም የሚያስፈሩ ታሪኮችን ስሰማ “አዲስ አበባ እኮ ገነት ናት” እያልኩ እናገር ነበር። ናይሮቢ እና ካምፓላ ውስጥ ትንንሽ የሰፈር ሱቆች መስኮታቸው በብረት ፍርግርግ ነው የሚጠበቀው። የመስታወት ሱቆች ያሉት ሞል ውስጥ ብቻ እንጂ መንገድ ዳር አይደለም። የኤቲኤም ማሽኖች በወታደር የሚጠበቁባቸው ቦታዎች አሉ። ጆሃንስበርግ ከተማ ዳር ዳሩ ላይ በእግር መንቀሳቀስ አይመከርም፤ ምክንያቱም የተደራጁ ወንበዴዎች ድንገተኛ የዘረፋ ጥቃት ሊፈፅሙባችሁ ይችላሉ። አዲስ አበባ እነዚህ ተርታ አልደረሰችም። ነገር ግን ወደዚያ እየተጓዘች ይመስለኛል።
ሁለተኛውን ገጠመኜን ከማውራቴ በፊት ለምን ውንብድና እንዲህ ዓይን አወጣ የሚለው ላይ ጥቂት እንነጋገር።