Pages

Sunday, May 20, 2018

ሰው መሆን…

የሰው ልጆች ሰው ለመሆን ማለቂያ የሌለው አብዮታዊ ጉዞ ውስጥ ናቸው፡፡ እንደመታደል ሆኖ፣ የሰው ልጆች የላቀ እና እየላቀ የመጣ አእምሮ ባለቤት በመሆናቸው ምድርን እንደግል ንብረታቸው፣ ራሳቸውንም ተለይቶ እንደተመረጠ ፍጡር እየቆጠሩ፣ ምድርን ለራሳቸው ምቾት እያሾሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። የሰው ልጆች በሠለጠኑ ቁጥር ርሕራሔያቸው እየጨመረ፣ አውሬነታቸው እየቀነሰ መጥቷል። የራሳቸውን ነጻነት የሚያከብሩትን ያክል የሌሎችንም ለማክበር እየተጉ መጥተዋል። የሰው ልጆች ዛሬ ከራሳቸው አልፈው ስለአካባቢያቸው ብዝኃ ሕይወት እስከመጨነቅ ደርሰዋል። የሰው ልጆች ረዥም ጉዞ ገና አላለቀም። የሰው ልጆች ሰው የመሆን ጉዞ የት ተጀመረ? በየት በኩል አለፈ? ዛሬ የት ደረሰ? ነገስ ወዴት ይጓዝ ይሆን? የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የሰው መሆንን ጉዞ በወፍ በረር በመቃኘት የሰውነትን ዓላማ መገመት ነው።

ቶማስ ፍሬድማን ሉላዊነት 3ኛው ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጽፏል። የመጀመሪያው ደረጃ የአገረ-መንግሥታት እርስበርስ መተሳሰር ነው። ሁለተኛው ደረጃ የንግድ ኩባንያዎች ብዙ አገራት ላይ መሥራት መቻልና እርስ በርስ ግንኙነት ነው። የመጨረሻውና ሦስተኛው ደረጃ የሰዎች ድንበር ዘለል የአንድ ለአንድ ግንኙነት፣ የትብብር እና የውድድር ዕድል መጨመሩ እና መጠናከሩ ነው። እውነትም ዛሬ ሉላዊ ዜጋ (global citizen) መሆን ከመቼውም ግዜ በላይ ቀሏል። ይህ ክስተት የሰው መሆን ጉዞ አቅጣጫ ድንበር የለሽ የዓለም ዜጋ መሆን መሆኑን ይጠቁመን ይሆን?

በዓለማችን አሁን ላይ በአንድ ወቅት 7 ሺሕ ገደማ ቋንቋዎች ነበሩ። በአጥኚዎች ትንበያ መሠረት ከነዚህ ውስጥ በመጪዎቹ መቶ ዓመታት ውስጥ የሚቀሩት መቶዎቹ ብቻ ቢሆኑ ነው። በተረፈ ቀሪዎቹ ወይ ተናጋሪ በማጣት፣ ወይ ከሌላ ጋር ተዳቅለው አዲስ ቋንቋ ተወልዶ፣ ወይም ደግሞ በሌላ ምክንያት ይሞታሉ። በዚህ አካሔድ ስንገምተው ምናልባትም የሆነ ግዜ ዓለማችን ጥቂት ወይም አንድ ቋንቋ ብቻ የሚናገር የሰው ዘር መኖሪያ ትሆናለች። ይህ ምንን ያመለክታል? የሰው ልጅ ብዙ ሆኖ ጀምሮ አንድ ሆኖ እንደሚጨርስ? ወይስ፣ በሒደቱ ከአንድ ወደ ብዙ ከዚያ መልሶ ወደ አንድ-ነት እንደሚጓዝ? ሌላም፣ ሌላም…

ጥንት የሰው ልጆችን ከአንድ ሥፍራ ከመንቀሳቀስ የሚያግዳቸው ተፈጥሮ ብቻ ነበር። ዛሬ ዛሬ፣ ተፈጥሮ በሰው ልጆች ቁጥጥር ሥር እየዋለች በሔደች ቁጥር ሰው ሠራሽ ድንበሮች የሰውን ልጆች እንቅስቃሴ እየገደቡ ነው። ሆኖም አገረ-መንግሥታዊ ኅብረቶች፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ እነዚህን ሰው ሠራሽ ድንበሮች መልሰው እየሰበሯቸው ነው። ዛሬ የዓለም አገራት ድንበራቸውን አጥረው በአንድ ወቅት የሁሉም የነበረችውን ዓለም ተከፋፍለው የኔ እና የእናንተ ተባብለዋል። ጆርጅ ፍሬድማን መጪዎቹን መቶ ዓመታት በተነበየበት መጽሐፉ ይህ አይቀጥልም ይለናል። እሱ እንደሚለው 21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የዓለማችን ኃያላን አገራት እንደዛሬ ሳይሆን ስደተኞችን መፀየፍ አቁመው በገንዘብ ለመግዛት እስከ መሻማት ይደርሳሉ። ይህንን እውነት ይሆናል ብለን እንገምትና የሰው ልጅ የነገ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚመስል በምናባችን እንሳል። ግምታችን ለእውነቱ እንዲቀርብ ግን ያለፈውን ግዜ ከጥንስሱ ጀምሮ በጨረፍታ እናስታውሰው።