Pages

Monday, March 28, 2016

‘እስመ ሥሙ ይመርሖ ኀበ ግብሩ’

በፍቃዱ ኃይሉ

የሥም ነገር ሳልወድ በግዴ ያፈላስመኛል። ሥም ተራ መለያ መጠሪያ ብቻ ነው ብዬ አልቀበልም። ምናልባት መጀመሪያ ላይ እንዲያ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁን፣ ሥም በባሕልና የሥልጣኔ ዝግመተ ለውጥ ሒደት (evolution of civilizations) ውስጥ ብዙ ውስብስብ ነገሮችን እያነገበ በጊዜ ባቡር ተሳፍሮ ውስብስብ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሥም የባሕል መገለጫ፣ የፖለቲካ አመለካከት መንፀባረቂያ፣ የወላጆች ለልጆች ውርስ ነው። ለዚያም ይመስለኛል “ሥምና ማንነት” የሚለው ጉዳይ የመጽሐፍ ምዕራፍ እና የጥናት ርዕስ ለመሆን እየበቃ ያለው።  አባቶቻችን በፈረንጆች ‘የሊትሬቸር’ አጻጻፍ ደምብ ስላልጻፉልን ፍልስፍና መስለው ያልታዩን አፈላሳፊ አባባሎች አሏቸው። የሊቃውንቱ “ሥሙ ይመርሖ ኀበ ግብሩ” (ሥሙ ተግባሩን ይመራዋል) የምትለው አባባላቸው አሁን ምዕራባውያን እያጠኑት ያሉት ጉዳይ ላይ እነርሱ የደረሱበት ድምዳሜ ነው። በነገራችን ላይ በተቀራራቢ ሮማውያንም ‹nomen est omen› (ሥም ዕጣፈንታ ነው) የሚሉት አባባል አላቸው፡፡ ሳይንቲስቶች «ሰው ወደሥሙ ወይም ከሥሙ ወዲያ (እየተጎተተ ወይም እየተገፋ) የሚኖር ብኩን ፍጡር ነው» ወደማለቱ እየዳዳቸው ነው። ለመሆኑ አንድ ሰው ለመለያ ይሆነው ዘንድ የተሰጠው ሥም ማንነቱን ያሳብቃል? ባሕሪው ላይ ወይም ተግባሩስ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል?

የሥም ቅርፅ

ሥም ከአገር አገር ብቻ ሳይሆን ከዘመን ዘመን ቅርፁና ፀባዩን እየቀያየረ ይሄዳል። ለምሳሌ ምዕራባውያን ‘የቤተሰብ ሥም’ የሚሉት እኛ የለንም፤ አንዳንዶች የጎሳ ሥም እሱን ይተካል ይላሉ። በጊዜ መሥመር ደግሞ ለምሳሌ በኢትዮጵያ በ19ኛው ክ/ዘመን (ከ1900ቹ በፊት) የኢትዮጵያውያን ሥም የሚጻፈው (የሚገለጸው) ‘ከአያት ሥም➡ የአባት ሥም ➡ የልጅ ሥም’ በሚለው ቅደም ተከተል ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን (‘የእከሌ ልጅ’ ዘመን አልፎ፣ ‘የእከሌ አባት’ ዘመን ሲጠባ) በተቃራኒው ተደርጓል። በቱርክ እ.ኤ.አ. ከ1943 በፊት የቤተሰብ ሥም የሚባል ነገር አልነበረም። አንዱን ሰው ከሌላኛው ለመለየት ሲባል እስከ ሦስት ሥሞች ድረስ ይወጡለትና በዚያ መደዳ (በእኛ እስከ አያት ሥም በምንለው መንገድ) ይጠራ ነበር። በዚህ የአሰያየም ስርዓት የአባትና የልጅ ሥም ምንም የሚያዛምዳቸው ነገር የለም። ለምሳሌ የቱርክ አባት የሚባለው አታቱርክ (Atatürk) ሥሙ ሙስጠፋ ከማል ነበር። አታቱርክ የተጨመረው ኋላ ለክብሩ ሲባል ነው። የአባቱ ሥም ደግሞ አሊ ሪዛ ነበር። በቱርክ የተጠፋፉ ዘመዳሞች በሥም ተፈላልገው የመገናኘት አማራጭ አልነበራቸውም ማለት ነው። በሌላው ባሕል የልጅ ሥም፣ የአባት ሥም፣ የቤተሰብ ሥም… የምንለው ነገር ዝምድና መቁጠሪያም ጭምር ነው ማለት ነው፡፡

በአገራችን በተለያዩ ማኅበረሰቦች የተለያየ ዓይነት የሥም አወጣጥ አላቸው። ለምሳሌ በጋምቤላ የአኙዋክ ብሔረሰብ ሥም አወጣጥ ሥሙን ሰምቶ ስለሰውዬው ጥቂት ቤተሰባዊ መረጃ ማግኘት ይቻላል። በአኙዋክ፣ የመጀመሪያ ልጅ ኡመድ ይባላል፤ ሁለተኛ ኡጁሉ፣ ሦስተኛ ደግሞ ኦባንግ እያለ ይቀጥላል። አንዳንዴ አባትና ልጅ አንድ ዓይነት ሥም ሊኖራቸው ይችላል። ታላላቆቹ ሴቶች ሆነው መጀመሪያ የሚወለድ ወንድ ኦማን ይባላል። ለምሳሌ እኔ ከአኙዋክ ቢሆን የተወለድኩት ኦማን እባል ነበር እንደማለት ነው።…

በአማራ ተወላጆች ዘንድ ደግሞ ትንሽ ለየት ይላል። ለምሳሌ መንዞች “ርስትና ውትድርና ይወዳሉ” ይባልላቸዋል። ይህም በሥማቸው ሳይቀር ይስተዋላል። ለምሳሌ “ሸዋጉልቱ” የመንዜ ሥም ነው። አምበርብር፣ ደምሰው፣ ዳምጠው፣ አሸብር፣ የመሳሰሉትም የመንዜ ሥሞች ናቸው። ጎንደሬ ደሞ “ሹመት ይወዳል” ይባላል። የጎንደሬ ሥሞች ሹመቴ፣ መኳንንት ወይም መኮንን የመሳሰሉት ናቸው (ወይም ነበሩ)። ቀደም ብዬ እንዳልኩት የሥም አወጣጥ እንደጊዜው ይለዋወጣል። ጎጃም የሄድን እንደሆነ ደግሞ ከልጅ እስከ አባት (ወይም አያት) ያለው ሥም ተገጣጥሞ ዓረፍተ ነገር የሚሰጥበት ጊዜ አለ። በጣም ታዋቂ ከሆኑት መካከል ብንጠቅስ እንኳ ሐዲስ ዓለምአየሁ፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ፍቅር ይልቃል፣ እያደር አዲስን ማግኘት ይቻላል።

ሥም እና ፖለቲካ

ሥም የፖለቲካ መሣሪያም ነው። የአብዮቱ ሰሞን የተወለዱ ልጆች ‘አብዮት’፣ ‘ትቅደም’… የሚል ሥም ተሰጥቷቸው ዕድሜያቸውን እንኳ እንዳይደብቁ ሆነዋል። አሁንም ያ ባሕል ቀጥሎ “ሕዳሴ” ከሥም ዝርዝሮች ውስጥ ገብቷል። የኦሮሞ ብሔርተኞች ‘የአማራ’ ሥማቸውን እየቀየሩ ቢሊሱማ (ነፃነት)፣ ኒሞና (አሸናፊ) የመሳሰሉት የወጣት ‘አክቲቪስቶች’ ተመራጭ ሥሞች እየሆኑ ነው። ኦቦ ሌንጮ (“አንበሳው” እንደማለት) ለታ (ከዮሐንስ ለታ) እና ብዙዎቹ የኦነግ አንጋፋዎችም ሥሞቻቸውን በመቀየር ነው ትግላቸውን የጀመሩት። በዕውቀቱ ሥዩም የአያቱ ቀዳማይ ሥም በዻዻ መሆኑን መጥቀሱ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ለመተቸት እንደነፃ ፈቃድ ሆኖለታል (ወይም ተጠቅሞበታል)። ዮናታን ተስፋዬ ደግሞ የአባቱን ቀዳማይ ሥም (ቴሬሳ) ፈልጎ የተጠቀመው የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በአዎንታዊ መንገድ መረዳቱን ለማመልከት ነበር። በተመሳሳይ በ‘ያ ትውልድ’ ዘመን ሥምን ለፖለቲካ ዓላማ ራስን ለመደበቅ ሲባል መቀየር የተለመደ ነበር። ሕወሓቶች የሞቱ ጓዶቻቸውን ሥም ይወርሱ ነበር። ለገሰ ዜናዊ መለስ ዜናዊ እንደሆኑት ማለት ነው። በሕወሓት ለፖለቲካ ዓላማ ስዩም መስፍን ከአረቦች (ሶርያዎች) እርዳታ ለማግኘት ራሳቸውን ሙስሊም አስመስለው ለማቅረብ የአባታቸውን ሥም ሙሳ ነው ብለዋል። ብዙዎቹ የኦህዴድ ሰዎችም ከምርኮ ወደትግል ሲገቡ የ“አቢሲኒያ” ሥሞቻቸውን ወደ “ኦሮሞ” ቀይረዋል።

ሥምን ለፖለቲካ አገልግሎት መቀየር በዓለም ዙሪያ የተለመደ ነው። አምባገነኑ ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ‘የአውሮጳውያን’ ነው ያሉትን ሥማቸውን ቀይረው ነው ሴሴ ሴኮን በማስጨመር የትግል ሥም ያገኙት። በአገራቸው ዛየር (የአሁኗ ኮንጎ) የክርስቲያን ሥም (Middle Name የሚባለው) ‘የእብራይስጥን ሥም’ ለአፍሪካውያን ሲሰጥ የተገኘ ቄስ እስከ 5 ዓመት የሚደርስ እስር እንዲቀጣ የሚያደርግ ሕግ አውጥቷል። ጥቁር አሜሪካዊው ታጋይ ማልኮም ኤክስ የቤተሰቡን ሥም በ‘X’ የተካው እና ሌሎችም አጋሮቹ እንደዚያው ያደረጉት “የነጮች” ነው ያሉትን የክርስትና ሥም ለመቃወም ነበር።

ሥም እና ሃይማኖት

መጤ ሃይማኖት ነባር ባሕሎችን ሁሉ ደምስሶ የመተካት አቅሙ ኃያል ነው። ክርስትና እና እስልምና የዓለም ሥም አወጣጥ ቅርፅን የለወጡት በዚሁ ኃይላቸው ነው። በዓለማችን ላይ በብዛት ወንዶች የሚጠሩበት ሥም ‘መሐመድ’ ነው የሚል ነገር ማንበቤ ትዝ ይለኛል። በአገራችን ወላጆች ለልጆቻቸው ሥም ሲያወጡ ወይ አምላካቸውን መጥቀስ ወይም ከቅዱስ ባለታሪኮቻቸው የአንዱን ታሪክ መጥቀስ ይቀናቸዋል። በሱፍቃድ (በእግዜር ፍቃድ)፣ ዋቅጅራ (እግዜር አለ)፣ ገብረእግዚኣብሔር (የእግዜር ሥራ)… ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።

በቅዱሳን ባለታሪኮች ልጅን መሰየም በተለይ አሁን አሁን ፋሽን እየሆነ መጥቷል። አገር በቀል ሥሞችን ለልጆች ማውጣት ልጆቹን “ፋራ” (ወይም “አራዳ” ያልሆኑ) የሚያሰኝ ይመስላል።

በሌላ በኩል በቀድሞ ጊዜ ለንግሥና ሲባል ሥምን መቀየር የተለመደ ነበር። ብዙ ጊዜ ንግሥናን በጳጳሳት ተቀብቶ ለማፅደቅ ሲባል በክርስትና ሥም መጠራት ደንብ ነበር። (ነገሥታት ራሳቸውን ሥዩመ-እግዚአብሔር ይሉ ነበር። ስለዚህ ንግሥና ፖለቲካዊ ብቻም ሳይሆን ሃይማኖታዊም ነበር) ተፈሪ መኮንን [ቀዳማዊ] ኃይለሥላሴ የተባሉት በዚያ መንገድ ነው። “ቴዎድሮስ የተባለ ንጉሥ እስከ እስራኤል ይገዛል” የተባለውን ትንቢት ወይም ጥንቆላ ተከትሎ ነው ካሣ ኃይሉ ራሳቸውን [ዳግማዊ] ቴዎድሮስ ብለው ያነገሡት። ቀዳማዊ ቴዎድሮስም ሥማቸውን ያገኙት በትንቢቱ መሠረት እሰከ እስራኤል የመግዛት (ካልሆነም ትንቢቱን ሰምተው በሥም የሚግገዙላቸው እንዲያገኙ) ተመኝተው ነው። አውሮጳውያን አፍሪቃዊ ኃያል የክርስቲያን መንግሥት መሥርቷል ብለው በአንዲት ደብዳቤ መነሻ ብዙ ያወሩለት የነበረውን ቄስ ዮሐንስ (Prester John) ለመሆንም ሲባል ነው እስከ አራተኛ የተደረሰው። ዐፄ ዮሓንስ እና የወሎ ሙስሊሞች የገቡበት ቁርሾ መነሻም የዐፄው እንደሥማቸው የማደር ምኞት ይመስለኛል።

ሥም እና ስርዓተ—ፆታ

ሥም ስርዓተ-ፆታን የሚገልፅበት ሁኔታም ቀላል አይደለም። ወንዶች በአማራው ተወላጅ ዘንድ በጥቅሉ ምናባዊ ጀግንነትን የሚያጎናፅፍ ሥም ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ ወንዳፍራሽ፣ ናደው፣ ሺመክት፣ መኩሪያ፣ የመሳሰሉትን ሥሞች መጥቀስ ይቻላል። በኦሮምኛ ሌንጮ (አንበሳው)፣ ኬራንሶ (ነብሩ፣ ደፋሩ)፣ ዋንጎ (ቀበሮው) የሚሉ በኃይለኛ አራዊቶች ሥም ለወንዶች የሚሰጡ ስያሜዎች ጀግንነትን ለወንድ የማልበሱ ማኅበራዊ ትውፊት አካል ናቸው። ጫላ (ቀዳሚው)፣ ሁንዳራ/ኢራና (የበላይ)፣ ኩማራ (ሺመክት) የመሳሰሉትም የተጠቀሰውን ምናባዊ ጀግንነት አልባሽ ኦሮምኛ ስያሜዎች ናቸው። በሲዳምኛ አዳቶ (ደፋሩ)፣ ዳፉርሳ (የማይዳፈሩት) የመሳሰሉት ሥያሜዎች የላይኞቹ ዓይነት ሚና አላቸው። በሌሎቹም ቋንቋ እና ባሕሎች ውስጥ ተመሳሳይ አጠራሮች አሉ።

ለሴቶች ሲሆን ውበታቸውን፣ ወይም በቁስ የሚተመን ዋጋቸውን የሚገልፅ ሥም ይሰጣቸዋል፦ መድፈሪያሽ ወርቅ፣ ሺብሬ፣ ወርቂቱ፣ ብሪቱ፣ ሸጊቱ፣ ቆንጂት…የሴቶች ሥም አወጣጥ ሴቶችን በአትክልትና ፍራፍሬ የሚመስልበትም ጊዜ ቀላል አይደለም፤ አበባ፣ ወይኒቱ፣ ትርንጎ፣ ብርቱኳን፣ ሸዊት (በትግርኛ “እሸት” ማለት ነው) ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። በኦሮምኛ ቢፍቱ (ብሩህ፣ ፀሐይቱ/ጣይቱ)፣ ፋኖሴ (መብራቴ)፣ መጋሌ (ጠይም/ቆንጆ)፣ ዱንጉጄ (ሽንኩርት፣ አጭር ቆንጆ)፣ በከልቻ (ኮኮብ፣ ለዓይነ ቆንጆ) የመሳሰሉት ሥሞችና በሲዳምኛ ዳንቺሌ (ቆንጆ፣ ፀባየ ሸጋ)፣ ደራርቱ (አበባ፣ ፍካት (ኦሮምኛም ነው)) ሴትን በውበቷ የመግለፅ ትውፊታዊ ወግ ያሳያሉ።

ሥም እና የቤተሰብ ታሪክ

ሥም አንዳንዴ የሐዘን መግለጫ ነው። አባቱ (ተፀንሶ እያለ ወይም በልጅነቱ) ወይም ታላቅ ወንድሙ የሞተበት ልጅ ለምሳሌ በአማርኛ ምትኩ፣ ማስረሻ… ይባላል፤ በትግርኛ ካልኣዩ፤… ታላላቆቹ ሲወለዱ እየሞቱ እሱ ግን ያንን መሰናክል ያለፈ ልጅ ለምሳሌ በአኙዋክ ኞም ይባላል፤ በሲዳማ ሪቂዋ ይባላል።

ሥም አወጣጥ ልጁ በተወለደ ጊዜ ወላጆች የነበራቸውን ግንኙነት፣ የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ወዘተ የሚናገርበትም ሁኔታ አለ፤ ለምሳሌ አስማማው፣ አስታርቄ… የመሳሰሉት ሥሞች ብዙ ጊዜ የሚወጡት እየተጥጣሉ (በተለይ በልጅ እጦት) የነበሩ ጥንዶች የልጅ መገኘቱን ተከትሎ ሲስማሙ ነው። ወላጆች ልጅ ሲወልዱና የጥሩ ዕድል (በተለይ የሀብት) መምጣት ከተገጣጠመ ልጃቸውን ሀብታሙ፣ ጥጋቡ፣… ብለው ሊሰይሙት ይችላሉ። በተቃራኒው ከገጠማቸው ደግሞ ያንኑ የሚያንፀባርቅ ሥም ይሰጡታል፤ ለምሳሌ ‘በድሉ’ የሚለው ሥም በዕድሉ ይደግ ከሚለው የመጣ ነው፤ ወይም ሳይታቀድ ከመጣ ነው። በኦሮሞ ትውፊት ተጨማሪ ልጅ የማይፈልጉ መሆኑን ለመግለጽ ወላጆች ለ“መጨረሻ” ልጃቸው ጉታ የሚል ሥም ያወጣሉ።

«ሥምህን ንገረኝና ማንነትን እነግርሃለሁ»

የኒው ሳይንቲስት ጋዜጠኛ ጆን ሆይላንድ "nominative determinism" (ሥም አመጣሽ ቁርጠኝነት) የሚለው ነገር አለው። ‘ሥም አመጣሽ ቁርጠኝነት’ የሚወክለው በሥማቸው ተገፍተው ለስያሜያቸው የሚስማማ ሙያ ሲከተሉ ነው። ለምሳሌ በዕውቀቱ ሥዩም ኃይለኛ ቦክሰኛ ቢሆን ኖሮ ሥሙ ከሙያው ጋር አይሰምርም እንል ነበር። በቡጢው ሥዩም ይሆን ነበርና። ስለዚህ የበዕውቀቱ ‘ሥም አመጣሽ ቁርጠኝነት’ ኋላ ቀር የሚለውን ስርዓት (social order) በነውጥ/ነፍጥ ሳይሆን በዕውቀት በመሞገት መንገሥ/መሰየም ነው።

ብዙ መንግሥቱ፣ ንጉሡ የተባሉ ሰዎች መራኄ መንግሥትነት ማዕረግ ሳያገኙ አንድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ቦታውን መቆናጠጡ ብቻ መንግሥቱ የተባለ ሰው ሁሉ የመንግሥት ኃላፊ ይሆናል ማለት ባይቻልም ሥማቸው ግብራቸውን ቀድሞ እንዲመራው በማድረጉ ረገድ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል በሚለው ግን መስማማት እንችላለን፡፡

በአማራው ማኅበረሰብ ዘንድ ‹ደመላሽ› የሚለው ሥም የሚሰጠው “ደም የተቃቡ” ቤተሰቦች መካከል ከአንደኛው ወገን ተበቃይ ባልነበረበት ጊዜ ለተወለደ ልጅ ነው፡፡ የዚህ ልጅ ዕጣፈንታ ባስተዳደግ ይወሰናል፡፡ ሥሙን ያወጡለት ሰዎች ሥሙን ለምን እንዳወጡለት ብቻ ሳይሆን ምን እንዲያደርግላቸው እንደሚፈልጉም ጭምር እያስተማሩት ነው፡፡ ስለሆነም፣ አድጎ “ጠላት” የሚለውን ወገን ለመግደል መሠማራቱ ሰፊ ዕድል ያለው የሕይወቱ ምዕራፍ ነው የሚሆነው፡፡

ሥም እና ማንነት ግንኙነት አላቸው የሚሉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ “ሥማችን - ወይም ሰዎች ሥማችንን ሲሰሙ በሚያሳዩት ግብረ-መልስ ወይም የማንነት ግምት ላይ ተመሥርቶ ባሕሪያችንን ይወስናል፡፡” ወደድንም ጠላንም በሥማችን ብቻ ሰዎች ዘውጋዊ ማንነታችንን፣ የቤተሰባችንን ሁኔታ፣ እና ሌሎችም መሠረታዊ ግምቶችን ስለኛ ያሳልፋሉ፡፡ እኛም ይህንኑ ስለምንረዳ የሰዎቹን ግምት ለማጠናከር ወይም ለማስተባበል የበኩላችንን ጥረት በማወቅም፣ ባለማወቅም ማድረጋችን አይቀርም፡፡

ሥም በባለቤቱ ላይ የሚያመጣውን ማንኛወንም ዓይነት ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለመደ-ሥም (popular name) መስጠት እንደመፍትሔ ይጠቆማል፡፡ ልጆች በሥማቸው ማንነታቸው እየተገመተ፣ እነሱም በምላሹ በሥማቸው እና ሥማቸውን ሰምተው ሰዎች በሚያሳልፉት ግምት ተፅዕኖ ሥር እየወደቁ ‹የሥማቸው ፍሬ› እንዳይሆኑ ሲባል ለልጆች በሚያድጉበት አካባቢ የተለመደ የሚባለው ዓይነት ሥም ቢሰጣቸው የገዛ ሥማቸው ሰለባ ከመሆን ይድናሉ፡፡ 

---
እንደ ዋቢ:-
- የነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ድርሰቶች፣
- Atatürk (biography), by Andrew Mango
- Wax and Gold, by Donald Levine
- ፍቅር እስከ መቃብርን የጻፉት «ሐዲስ» ናቸው ወይስ «ዓለማየሁ»? (የሚከራዩ አማት እና ሌሎች)፣ በዳንኤል ክብረት
- ሉኣላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ፣ በገብሩ አሥራት
- ሥምና ማንነት (ከአሜን ባሻገር)፣ በበዕውቀቱ ሥዩም
- Typology of Oromo Personal Names, by Tesfaye Gudeta Gerba
- እና የተለያዩ ድረገጾች እና ሌሎችም...

Sunday, March 6, 2016

የ“ተቃራኒ” ወገን የትግል አጋርነት

በአፍሪካ አሜሪካውያን የሲቪል መብቶች ትግል ውስጥ እና በደቡብ አፍሪካ ነባር ጥቁሮች ከመጤ አፍሪካነሮች የተነጠቁትን የዕኩል ሰውነት መብት ለማስመለስ ሲታገሉ፣ ጥቂት የማይባሉ ነጮች (ወይም አፍሪካነሮች) የትግላቸው አጋር ሁነውላቸው ነበር። ሌሎች ጥቂቶች በደሎቹን ምክንያታዊና ተገቢ ለማድረግ (to justify) ተከራክረዋል። ብዙኃኑ ግን በገለልተኝነት እና በስጋት ተመልክተውታል። ከጥቁሮቹ ታጋዮች መካከልም ከፊሎቹ ለዕኩል የሰውነት ማዕረግ ታግለዋል። ከፊሎቹ ነጮቹን ለመበቀል ታግለዋል። ዞሮ፣ ዞሮ ግን ሁሉም ነባሩን ትርክት እና ተቀባይነት የነበረውን (mainstream) አስተሳሰብ ማፈራረስ ነበራቸው። በዚህ ግዜ ነጮቹ ቀድሞ የነበራቸውን የተለየ መብት ከጥቁሮች ጋር መጋራታቸው መብታቸውን እንደመነጠቅ ቆጥረውታል። ለምሳሌ ቅድሚያ ይሰጣቸው የነበረውን አገልግሎት ከጥቁሮች ዕኩል እንዳደራረሳቸው እየተሰለፉ እንዲያገኙ መገደዳቸውን እንደመብት ነጠቃ ይቆጥሩታል።

እነዚህ ተግዳሮቶች መገፋፋት ይፈጥሩ ነበር። በዚህ ሳቢያ ከነጮቹም፣ ከጥቁሮቹም ወገን አብረን መኖር አንችልም የሚል ሰውነትን የመጠራጠር ዝንባሌ ታይቷል። በአሜሪካ እነማልኮም ኤክስ ይመሩት የነበሩት እንቅስቃሴ የነጭ የሆነውን ሁሉ መጠየፍን እንደስትራቴጂ የቆጠረ ነው። የነሱ ተቃራኒ ዕኩያ የሚባለው ኬኬኬ የሚባሉት የነጮች ጥቁር ተጠያፊ ቡድን ነው። የማልኮሜክስ ‘ኔሽን ኦቭ ኢስላም’ እና ‘ኩ ክላክስ ክላን’ አንዴ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ጥቁሮቹም ነጭ የማያዩበት የጥቁር ዓለም፣ ነጮቹም ጥቁር የማያዩበት የነጭ ዓለም ሊመሠርቱ። አንዱ ሌላኛውን ለማግለል እንደመስማማት።

በቀድሞዋ አሜሪካ ሰሜኖቹ "ነጻ አገሮች" ሲሆኑ ደቡቦቹ "ባሪያ አሳዳሪ" ነበሩ። ሶሻሊስቶቹ በወቅቱ በሰሜን የነበረውን የጭሰኝነት ሁኔታ እያዩ በሰሜን ያለው የጭቁን ሠራተኞች ሁኔታ እና በደቡብ ያለው የባሪያዎች ሁኔታ አንድ ነው እስከማለት የሚደፍሩ ነበሩ – በመደብ ጭቆና ትንተና። ነገር ግን በወቅቱ ከደቡብ ባርነት ኮብልለው ወደሰሜን ጭሰኝነት የሚፈልሱ እልፍ ሰዎች ቢኖሩም፣ ከሰሜን ጭሰኝነት ወደደቡብ ባርነት የኮበለሉ ሰዎች አልነበሩም።

ሌላኛው ፈታኝ ነገር ያንን ጥቁሮችን የሚያንኳስስ ስርዓት የሚደግፉ ጥቁሮች መኖራቸው ለነጭ አስተባባዮች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ነበር። ማልኮም ኤክስ በባርነት የነበሩ ጥቁሮችን በሁለት ይከፍላቸው ነበር። የቤት እና የመስክ ኔግሮዎች (house and field negroes) ብሎ። የቤት ኔግሮዎቹ ጥቁር ቢሆኑም ከጌታው የሚተርፈውን ከስር ከስር የመቋደስ ዕድሉ ነበራቸው (they were privileged)። ተመችቷቸዋል። ስለዚህ፣ አብዛኛውን ፍዳ እንደሚቀምሱት የመስክ ኔግሮዎች ስርዓቱን አይቃወሙትም፣ እንዲያውም በደሉን በሰበብ ያለባብሱለታል።

እንዲህ ዓይነቱ የታሪክ ትርክት መገፋፋት ኋላ ላይ የዕኩል ሰውነት ማዕረግ ለማግኘት ይታገሉ ለነበሩት ለነማርቲን ሉተር ኪንግ ፈታኝ ነበር። በግለታሪኩ ላይ ኪንግ የሲቪል መብቶች ትግሉ አንዱ ፈተና ይህ እንደነበር ገልጿል። መጨረሻ ላይ ስኬታማ የሆነው ግን፣ የአግላዮቹ ሳይሆን የአካታቾቹ ትግል ነው። ጥቁሮቹ ዕኩል መብቱን ሲያገኙ ቀድሞ ነጮቹ ይፈሩት እንደነበረው ዓይነት ጥፋት አልደረሰም።

በደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲ ጥቁሮች ብቻ ሳይሆን ነጮችንም በአባልነት ይቀበል ነበር። የነማርቲን ሉተር ኪንግ እንቅስቃሴም በርካታ ነጭ አጋሮች ነበሩት። ማልኮም ኤክስ ከመገደሉ ጥቂት ቀደም ብሎ ስለሚፀፅተው ነገር ሲናገር አንዲት ታዳጊ ልጅ ጠቅሷል። ከዓመታት በፊት ማልኮም የአግላዩ ትግል ሊቀ ጳጳስ እይያለ አንዲት የ10 ዓመት ሕፃን ልጅ እቅፍ አበባ ይዛ ለጥቁሮች ትግል አጋርነቷን ለማሳየት ስትወጣ ‘ሂጅ ከዚህ፤ እኛ ከነጮች ጋር አጋርነት የለንም’ ብሎ አባሯት ነበር። ኋላ፣ እየበሰለ ሲመጣ ተፀፅቷል።

እኛ አገር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፆታን ጨምሮ፣ ከፊሉ በመደብ፣ ከፊሉ በማንነት፣ ከፊሉ በመደብ እና በማንነት ምክንያት በሚሉት መሠረት (መሠረቱን ባለሙያዎች በጥናት ሊበይኑልን ሲገባ እኛ ባላዋቂነት ጭቃ እየተለቃለቅንበት እንገኛለን፣ ለማንኛውም) ለዘመናት በገዢዎች እና በተገዢዎች መካከል (ወይም ዘመንና በሕል ባፈረጠማቸው እና ባንኳሰሳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች /ምሳሌ ወንዶች እና ሴቶች/) ለደረሱት በደሎች እና በዘለቄታው ላስከተሉት በማንነት ላይ የተመሠረተ የተጠቃሚነት ጉዳትን ለማስተካከል (undoing sustained system of repression) አንዱ የሌላው አጋር በመሆን አካታች የመብት ትግል በማድረግ ፈንታ አግላይ ትግል እያደረግን ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ አማራጭ እያለን፣ ሁሉንም ተሸናፊ የሚያደርገውን አማራጭ እየተከተልን እንገኛን።

ብዙ ጊዜ አጋርነትን አለመከተል ጦስ አለው። "ችግር የለም" በሚል በክህደት (denial) የተጀመረው፣ ወደፍረጃ ወይም መጥሌ (prejudice) ያድግና ውጤቱ የእርስበርስ እልቂት ይሆናል። ለዕኩል ዕድል እና መብት የሚታገሉት ቡድኖች በአግላይ ትርክት ጠላት የሚል ሥም የሚያወጡለት ቡድን ስለሚኖረው "ተቃራኒያችን" የሚሉትን ወገን ይገፋሉ። በሌላ በኩል ያንኛው ወገንም አንዳንድ ነባር ጥቅሞቼ ሊሸረሸሩብኝ ነው፣ ከሌሎች የዕኩል ባለመብቶች ጋር ልጋራው ነው በማለት የአፀፋ ግፊት ይገፋሉ።

የአንዱ እምነት ተከታይ ይሄ በደል ነበረብኝ፣ አለብኝ፣ በዘዴ እንዲቀጥል እየተደረገብኝ ነው ሲል፤ አንዱ ብሔርተኛ በማንነቴ ምክንያት እንዲህ ዓይነት በደል ይደርስብኝ ነበር፣ አሁንም አለብኝ፣ በዚህ አካሔድ ወደፊትም በደሉ ይቀጥልብኛል ሲል፤ አንዷ ሴት በመሆኔ ብቻ ወንዶች በቀላሉ የሚያገኙትን መብትና ዕድል ተነፈግኩ ስትል፣ «እኔ አለሁልህ/ሽ» በማለት ሰው ሠራሽ የእምነት እና የማንነት ድንበሮችን መስበር ካልቻልን ለሰውነት ማዕረግ ብቁ ነን ማለት አይቻልም። ተበዳይም በአርቲፊሻል ሰበቦች ላይ ተመሥርቶ ‘አንተማ በድለኸኛል፣ ወግድልኝ’ ካለ ትግሉ የሚገባውን የሰውነት ማዕረግ ለማግኘት ሳይሆን በተራው የሌሎችን ለመግፈፍ ነው ማለት ነው። ዳር ላይ ቁሞ ችግሩን ለመፍታት የሚፍጨረጨሩትን ፀጉር እየሰነጠቁ በማብጠልጠልም ግድግዳው አይፈርስም። የሚከፋፍለን ግድግዳ ፈርሶ፥ የሚያቀራርበን ድልድይ የሚሠራው እያንዳንዳችን ሌሎች በሚያደርጉት ትግል ውስጥ አጋርነታችንን በተግባር መግለጽ ስንችል ነው።

መጤ ሃይማኖት፣ ከመጤ ሃይማኖት በመምረጥ፣ (ግን በመሠረቱ ለገዢዎቹ ዋናው ሃይማኖቱ ሳይሆን በሥመ ሥዩመ–ፈጣሪነት የገዢነት ዕድል እና ተገዢ የማግኘት ጥረት ነው።) በወንዜ ማንነት ላይ በመመሥረት አገር ሲገዙ የነበሩ ሰዎች በነበሩበት አገር ውስጥ ያንን የሚያስተባብሉ (justify-ers) መኖራቸው አይገርምም። ይልቁን ከዚያ የአስተሳሰብ እስራት ወጥቶ ሰው ሆኖ መገኘት ነው ቁም ነገሩ።

ከገዢዎች እስራት ነጻ ከመውጣት በፊት ከገዛ ኋላ ቀር አስተሳሰባችን ነጻ መውጣት ይኖርብናል። መሬት የረገጠ ለውጥ ሊያመጡ እውነተኛውን ሥራ እየሠሩ ላሉት አጋር መሆን ካቃተን፣ ቢያንስ አደናቃፊ ላለመሆን መጣር ነው።