Pages

Friday, August 25, 2017

መጽሐፍ የሚወጣው፣ የተዋነይ ዘ ጎንጅ 5 መሥመር ቅኔ

ጎንጅ ቅኔ ያጠናበት ደብር ሥም ነው። ደብረ ጥበብ ጎንጅ ቅዱስ ቴዎድሮስ ገዳም። ተዋነይ የባለቅኔው ሥም ነው። (የግዕዝ ትርጉሙ "ዋናተኛ" ማለት ነው።) ሊቁ ተዋነይ የልኅቀቱን ያክል እምብዛም አይወራለትም፤ ነገር ግን በዘመኑ ወደር የሌለው ልኂቅ ስለመሆኑ ሥራው ይናገራል። የሕይወት ተፈራ "Mine to Win" የተሰኘ ድርሰት መቼቱን በዐፄ ዮሓንስ ንግሥና ዘመን፣ በጎጃም/ጎንደር የቅኔ መማሪያ ደብሮች ያደረገ ልብወለድ ነው። ልቦለዱ የቅኔ ትምህርት ስርዓትን ያስተዋውቀናል፤ በበኩሌ የቅኔ ትምህርትን እና የቅኔ ሊቃውንት ታላቅነት ቀድሞ ከነበረኝ ግንዛቤ የበለጠ እንዲሆን አድርጎኛል። በተለይ የተዋነይ ዘ ጎንጅ (በውኑ ዓለም የነበረ ባለቅኔ) ተከታይዋ አምስት መሥመር ቅኔ መጽሐፍ የሚወጣት እንደሆነች ልቦለዱ አሳሰበኝ። ወይም በአጭሩ ብዙ ምዕራባውያን ስንት መጽሐፍ የጻፉለት ፍልስፍናን በአምስት መሥመር ይዟል። የቅኔው ትርጓሜ የመጽሐፍ ቅዱስን እና የመጽሐፍ ቅዱሱን ፈጣሪ ኅልውና ይሞግታል።
“የአምን ወይገኒ
ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ
ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ
ለነጽሮ ዝኒ ነገር እሥራኤል ከመይፍርሑ
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ
ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።”
(ተዋነይ ዘ ጎንጅ። ምንጭ፣ሕይወት ታደሰ ወደአማርኛ የተረጎመችው የሕይወት ተፈራ መጽሐፍ)
ትርጉሙን በኋላ እመለስበታለሁ። ስለተዋነይ መጀመሪያ የሰማሁት የበውቀቱ መጽሐፍ ላይ ነበር። እሱም በጨረፍታ - “የሌሊት ዜማዎች” የሚለው ግጥሙ ውስጥ። በውቀቱ ተዋነይን በግጥሙ ግርጌ ማስታወሻው አስተዋውቆን ያልፋል፣ “ተዋነይ በቅኔ ቤት አፈ ታሪክ ሞትን በግዝት ለሰባት ዓመታት ያቆመ ጀግና ነው"። ከዚያ በኋላ፣ አዲስ አድማስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ተዋነይ የተላከበትን መልአከ ሞት ደጃፉ ላይ በምትሐት 7 ዓመት አቁሞት በማርያም አማላጅነት ነው ገብቶ ነፍሱን እንዲወስድ የፈቀደለት የሚል አፈ ታሪክ አለ ይለናል። በሌላ በኩል ዕፀ ሕይወት አግኝቶ ነገር ግን በአጠቃቀም ስህተት ግማሽ ሰውነቱ ሞቶ ግማሹ ሲኖር፣ ፈጣሪውን ለምኖ ነው ሙሉ ለሙሉ የወሰደው የሚል ሌላ አፈ ታሪክም አለ። የኋላ ኋላ ቴዲ አፍሮም አንድ ዘፈኑ ላይ ሥሙን ጠቅሶት ያልፋል።

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተጻፈው የአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ "የኢትዮጵያ ታሪክ" (በሚል በሥርግው ገላው የተሰናዳው መጽሐፍ) ላይም ሥሙን እንዲሁ በአጭሩ ተጠቅሶ አገኘሁት። እንዲህ ይላል፣ “ዐፄ በካፋ በዘመኑ ከክፉ ሥራ በቀር ፩ ቀን በጎነት ሥራ አልሠራም። ያን ግዜ ተዋነይ የሚባል የጎንጅ ደብተራ ጠንቋይ ነበረው። ሙያው ከርሱ ጋራ ነበረ። በካፋም ፱ ዓመት ነግሦ [በ1723] በክፉ ሞት ሞተ።" ተዋነይን የቀድሞ ታሪክ የሚያስታውሰው እንዲህ ነው ማለት ነው? በርግጥም ይህን መሰል ቅኔ እየጻፈ መልካም ሥም ቢኖረው ነበር የሚገርመኝ። የፍቅር እስከመቃብሩ "ጉዱ ካሣ" የእውነተኛ ባለታሪክ ቢሆን ኖሮ (የእውነተኛ ሰው መነሻ ተደርጎ ነው የተጻፈው የሚሉ አሉ) በታሪክ የሚታወሰው እንደቀውስ ነበር። ከዚህ አንፃር የተዋነይ ዘ ጎንጅ እንደ ጠንቋይ መታወስ ላይገርም ይችላል። በነገራችን ላይ፣ ተዋነይ የዐፄ በካፋ አማካሪ ከመሆኑ በፊት የንጉሡን ምግብ ዕፀ መሰውር ለብሶ (እንዳይታይ ሆኖ) ይበላባቸው ነበር የሚባል አፈ ታሪክም አለ።

Sunday, August 20, 2017

የተዋሐደን ፆተኝነት

ይህ ጽሑፍ ስለ ፍትሕ ነው። አንባቢዎቼን በትህትና አስቀድሜ የምጠይቀው ነገር ቢኖር የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት መነፅሮቻችሁን አውልቃችሁ በፍትሕ መነፅራችሁ እንድታነቡኝ ነው።

የተዋሐደን ፆተኝነት ስንል ምን ማለታችን ነው? ምንጮቹ ምን ምን ናቸው? ውስጣችን ያለው ይህ ፆተኝነት ምን ያህል ችግር ይፈጥራል? የተዋሐደንን ፆተኝነትን እንዴት እንቅረፈው?

መግባቢያ ስለፆተኝነት

ፆተኝነት ማለት በአጭሩ ‘ፆታዊ መድልዖ’ ማለት ነው። በዓለማችን እጅግ የተንሰራፋው ለወንዶች የሚያደላው ወይም አባታዊው ስርዓተ ማኅበር ነው። (እርግጥ እጅግ ጥቂት ሆኑ እንጂ እናታዊ ስርዓተ ማኅበሮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ሕንድ አገር ሜጋላያ ስቴት ውስጥ የሚገኙት ጎሳዎች ሀብት የሚተላለፈው ከእናት ወደሴት ልጅ ነው፡፡ በዚህ ስርዓተ ማኅበር የትምህርትና መሰል ዕድሎች ከወንዶች ይልቅ ለሴቶች ይመቻቻሉ፡፡ ይህን ምሳሌ በዓለም ከተንሰራፋው አባታዊው ስርዓት አንፃር ከቁብ ሳልቆጥረው ላልፍ እችል ነበር። ነገር ግን የእነዚህ ጎሳዎች እናታዊ ስርዓት ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እዚህ መድረሱ አባታዊው ስርዓትም ሆነ እናታዊዋ በማኅበራዊ ብሒል የሚገኙ እንጂ ተፈጥሮ ያከፋፈለችን ሚና አለመሆኑን ስለሚያሳይ ነው።) የአገራችን ስርዓተ ማኅበር ከጥግ እስከ ጥግ አባታዊ ነው። ይህንን ስርዓተ ማኅበር ለመቀልበስ እና ፍትሐዊ ስርዓተ ማኅበር ለመመሥረት የሚደረጉ የተደራጁም ይሁን ያልተደራጁ ንቅናቄዎችን ሴታዊነት እንላቸዋለን። (‘እንስታዊነት’ የእንግሊዝኛውን ‘Feminism’ በቀጥታ የሚተካ ቢሆንም፣ አማርኛችን ስርዓተ ፆታ (gender) ያልተጫነው ‘ሴት’ የሚል ሥነ ተፈጥሯዊ (biological) ልዩነቱን ብቻ የሚገልጽ ቃል ስላለው ‘ሴታዊነት’ የሚለውን መርጫለሁ። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሴታዊነት ማለት “ፆታዊነትን መቃወም እንዲሁም ሴቶች ከወንዶች ዕኩል መብትና ዕኩል ዕድል እንዲያገኙ መታገል” የሚል ብያኔ ይኖረዋል።)

የተዋሐደን ፆተኝነት…

ስልካችንን የኋላ ኪሳችን አስቀምጠነው ብንሰረቅ ማነው ተወቃሹ? እንዝህላልነታችን ወይስ ሌብነቱ? በመርሕ ደረጃ ሌብነት በማንኛውም ሁኔታ ነውር ነው። ይህ ምሳሌ “ነውር ማለት ሁላችንም በራሳችን ላይ እንዲደረግብን የማንፈልገው ነገር ነው” የሚል ብያኔ እንድናገኝ ይረዳናል። ስለዚህ "ቤታቸውን ከፍተው ሰውን ሌባ ያሰኛሉ" የሚለው አባባል የሌብነትን ነውር አቃልሎ ያሳያል እንጂ አያስቀረውም። ልክ እንደዚህ ሁሉ የሴት ልጅ መደፈርን ነውርነትም እንዲህ በሰበብ ሊያስተባብሉ የሚሞክሩ ብዙ ናቸው። ነገር ግን በአገራችን ኢትዮጵያም ሆነ በአህጉራችን አፍሪካ ለሴቷ መደፈር እራሷኑ ተጠያቂ ማድረግ የተዋሐደን ፆተኝነት ማሳያ ነው። ዩጋንዳ በየካቲት 2006 አጭር ቀሚስ የሚከለክል ሕግ አውጥታ ነበር። ከዚያ ቀደም ብለው የወጣቶች ሚኒስትሩ "ጨዋነት የጎደለው አለባበስ የለበሱ ሴቶች ሲደፈሩ ከራሳቸው በቀር ማንም ተጠያቂ መሆን የለበትም" ብለው ተናግረው ነበር። ተመሳሳይ ንግግሮች በሁሉም የአፍሪካ አካባቢዎች የተለመዱ ናቸው። በአገራችንም፣ አንዲት ሴት በወንድ ጥቃት ደረሰባት የሚለው ዜና ሲሰማ ገና፥ “ምን አድርጋው?” የሚለው ምላሽ ይከተላል። ጥያቄው፣ ሴት ልጅ ምክንያታዊ ጥቃት ይገባታል ከሚል የተዋሐደን አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። ለጥቃቱ ከማዘናችን በፊት ቀድሞ የሚመጣብን ጥያቄ “ምን አድርጋው?” የሚለው ከሆነ የተዋሐደን ፆተኝነት ሥር የሰደደ ነው ማለት ነው፡፡

በቅርቡ ይፋ የሆነ (ነገር ግን ውጤቱ ከቀደምት ጥናቶች ጋር የሚመሳሰል) ጥናት እንደሚያስረዳን፣ በኢትዮጵያ 63% የሚሆኑት ሴቶች "ባል ሚስቱን ወጥ ካሳረረች፣ ከጨቀጨቀችው፣ ሳትነግረው ዙረት ከሔደች ወይም መሰል ጥፋት ካጠፋች… ቢመታት ምንም አይደል" ብለው ያምናሉ። ባንፃሩ አሳማኝ ምክንያት ካለ ሴት ልጅ መመታት አለባት ብለው የሚያምኑት 28% የሚሆኑት ወንዶች ብቻ ናቸው። ለምን ሴቶች የገዛ ራሳቸውን ጥቃት ተገቢ ነው አሉ። ለምን ከሴቶቹ ቁጥር ያነሱ ወንዶች መምታቱ ተገቢነት ላይ ተስማሙ? መልሱ ቀላል ነው። የተዋሐደን ፆተኝነት የገዛ ጥቃታችንን በራሱ ተቀባይነት እንዳለው ነገር እንድንቀበለው ያታልለናል። ወንዶች ከሴቶች የተሻለ፣ የትምህርትና የመረጃ ዕድል ስላላቸው የሴት ልጅ ጥቃት በማንኛውም ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን መረዳታቸውንም ውጤቱ ይጠቁመናል። በዚህም ፆተኝነት በትምህርት የሚቀረፍ ነገር መሆኑን በቀላሉ ማየት ይቻላል።

የተዋሐደን ፆተኝነት ከማኅበረሰቡ የተማርነው፣ የኑሮ ዘዬያችን የተገነባበት እና በየዕለቱ የምንከተለው ነገር ግን ጨርሶ የማናስተውለው ከመሆኑ የተነሳ "ትክክለኛ" የሚመስለን ነገር ነው። ሆስፒታል ሔደን ነጭ ጋዋን የለበሰች ሴት ስትገጥመን [ነርስ እንደሆነች እርግጠኛ በመሆን] "ሲስተር" የምንላት፣ ነጭ ጋዋን የለበሰ ሲገጥመን "ዶክተር" የምንለው የተዋሐደን ፆተኝነት አስገድዶን ነው። አንድ ቀን መሳሳታችንን ብናውቅ እንኳን ደግመን መሳሳታችንን እንቀጥላለን፡፡ በተመሳሳይ የቢሮው ሥራ አስኪያጅ እንዲሁ ስናስበው ወንድ አድርገን ነው፤ ጸሐፊዋን ደግሞ ሴት። "ማናጀሩ የታል?" ስንል ወንድ እንደሆነ አንጠራጠርም። የኩሽና ሥራ በጥቅሉ የሴት ነው ብለን ነው የምናስበው፡፡ ምግብ አብሳይ ስንባል በምናባችን ሴት እንስላለን፤ የትልቅ ሆቴል ሼፍ ስናስብ ግን ወንድ ነው በምናባችን የሚመጣው፡፡ ምክንያቱም ምግብ አብሳይነትም  ቢሆን ደረጃው እያደገ ሲመጣ ለሴት እንደማይገባ የተዋሐደን ፆተኝነት ሹክ ይለናል፡፡