Pages

Friday, March 10, 2017

የፌሚኒዝም ሀሁ…

ፌሚኒዝምን በተመለከተ ሊያወዛግቡ የማይገባቸው ጥያቄዎች ሲያወዛግቡ እመለከታለሁ፡፡ ጥያቄዎቹን የማያነሷቸው ገና ውይይቱ ውስጥ ብዙም ያልቆዩ ሰዎች ናቸው እንዳልል አምናና ካቻምናም ይህንኑ ሲከራከሩ የነበሩ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በንባብ የበሰሉ ይመስላሉ፤ መጽሐፍ አሳትመው ፌሚኒዝምን ሊታገሉ የሞከሩም አልጠፉም፡፡ ስለዚህ እስኪ ምናልባት ‹በፌሚኒዝም ሀሁ› አልተግባባን እንደሆን በማለት ይህንን ጻፍኩ፣

ፌሚኒዝም ምንድን ነው?

ፌሚኒዝም "ሴቶች ከወንዶች ዕኩል መብት እና ዕኩል ዕድል እንዲያገኙ የሚጥር ንቅናቄ" ነው፡፡ ፌሚኒስት ማለትም (ሴትም ትሁን ወንድ) የዓለማችን ስርዓተ ማኅበር አባታዊ (patriarchal ወይም ለወንዶች የሚያደላ ወይም የወንዶች የበላይነት ያለበት) መሆኑን በማመን፣ እንዲለወጥ በየዘርፉ ወይም በአኗኗር የተደራጀ ወይም ያልተደራጀ ጥረት  የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው፡፡

ፌሚኒዝም ብዙዎች አንደሚፈሩት አባታዊውን ስርዓት አፍርሶ በሴት የበላይነት የሚተካ ንቅናቄ አይደለም፡፡ እርግጥ ስር የሰደደው አባታዊው ስርዓተ ማኅበር በሴቶች የበላይነት ልተካህ ቢሉት እንኳን በቀላሉ እና በቅርብ ጊዜ የሚተካ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ፌሚኒዝም ሴቶችን ወንድ የማድረግ ንቅናቄም አይደለም፡፡ ዕኩልነት ሲባል - የመብት፣ የትምህርት እና የሥራ - እንጂ የቁመት፣ የጡንቻ እና የመሳሰሉት አይደለም፡፡ ፌሚኒዝም ሴቶች በራሳቸው እና በዓለማቸው ዕጣ ፈንታ ላይ መወሰን የሚስችላቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ዕድል ሁሉ ከወንዶች ጋር እንዲጋሩ ለማስቻል የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ እርግጥ ነው ሴቶች ዕኩል መብት እና ዕኩል ዕድል ማግኘታቸው መብቱን እና ዕድሉን የተቀማ/የተካፈሉት የሚመስለው ወንድ መኖሩ የሚገመት ነው፡፡ ትግሉ ብዙ ተጉዟል፡፡ ሕጋዊ ጥያቄዎች በብዛት መልስ እያገኙ ነው፤ ማኅበራዊው ግን ገና ብዙ ግዜ ይወስዳል፡፡ ስርዓተ ማኅበሩ እንዳለ የሚመቻቸውን ሳያንገራግጭ የሚመጣ ለውጥም አይሆንም፡፡

ከዚህ ውጪ (ለምሳሌ ብዙ ባያሰጋም የአባታዊውን ስርዓት በሴቶች የበላይነት ለመተካት) የሚደረግ ንቅናቄ ከገጠማችሁ ፌሚኒዝም አይደለም፡፡ አነቃናቂዎቹም ፌሚኒስቶች አይደሉም፡፡ በዚህ መፍታት ይቻላል፡፡

ፌሚኒዝም ዘር አለው?

"ፌሚኒዝም አፍሪካዊ እሳቤ አይደለም፤ ምዕራባዊያን የጫኑብን አስተሳሰብ ነው" የሚሉ አስተያየቶች ደጋግመው ይደመጣሉ፡፡ ‹የአፍሪካ፣ የአሜሪካ የሚባል ሥልጣኔ ወይም እሳቤ የለም፤ የሰው ልጅ እንጂ› ብሎ ለሚያምን የኔ ብጤ አስተያየቱ በጣም የሚያናድድ ነው፡፡ ትልልቅ አገራዊ እሴቶቻችን ብለን የምንላቸው፣ ለምሳሌ ሃይማኖቶቻችን ሳይቀር (ክርስትና እና እስልምና ከመካከለኛው ምሥራቅ መጤ ናቸው) ከውጪ ተቀብለን እንደራሳችን፣ ከከባቢያዊ ሁነታችን ጋር አስማምተን እንዳልኖርን፣ አባታዊ ስርዓተ ማኅበር (patriarchy) ለማፍረስ ከምዕራባውያኑ ጋር በአንድ ሥም፣ አንድ ንቅናቄ ማድረግ መጤ እሳቤ እንደማስተናገድ ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ሴቶቹም የኛው፣ ጭቆናውም የኛው ነው፡፡ የዚህ አቤቱታ አቅራቢዎች፣ ከፌሚኒዝም የተሻለ የመፍትሔ ሐሳብ ካለ ቢጠቁሙ፣ ፌሚኒዝምን በደረቁ ከሚተቹ የተሻለ ይረቱ ነበር፡፡ ፀባቸው ከሥሙ ከሆነ በአማርኛ - ሴታዊነት - በሚል ለመተርጎም ተሞክሯል፡፡

አንዳንዶች፣ ‹የሴት ልጅ ጭቆና ከአፍሪካ ይልቅ ምዕራባውያን ጋር የከፋ እንደሆነ፣ እዚያ ሴት ልጅ እንደሸቀጥ እንምትታይ እየተከራከሩ፤ የኛውን በፈቃደኝነት ላይ እና ለተፈጥሮ ተስማሚ በሆነ መልኩ የተዘረጋ ስርዓተ ፆታ እንጂ ፆታዊ መድሎ አይደለም፡፡  የምዕራቡን መፍትሔ ስናመጣ ይህንን እሴት እናፈርሰዋለን› የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ስጋቱ ራሱ የተሳሳተ ስጋት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ችግሩ እኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያን ጋር መኖሩም ነው የጋራ መፍትሔ እንድንቀርፅ የሚያስገድደን፡፡ ሌላው ጉዳይ የምናሽሞነሙነው የእኛ የስርዓተ ፆታ ምድድቦሽ ራሱ ትግል የሚያስፈልገው ሌላ ዓይነት የጭቆና አካል እንጂ ለምዕራባውያኑ ሴትን እንደሸቀጥ የሚመለከት ስርዓት የመፍትሔ ትይዩ አማራጭ አይደለም፡፡

‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ከቀሪው ዓለም የተለየ ነው፤ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ለሴቶች የመምረጥ መብት ሳትሰጥ የኛ ሴቶች መንበረ ንግሥናውን ያሾሩት ነበር› የሚል መከራከሪያ አለን፡፡ እውነትም እንደሚመስለን የሴቶች መብትን አስቀድመን ማክበር ጀምረን ከሆነ መንገዱ ቀላል ነው ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው፣ ቢቢሲ ሴት ዜና አንባቢ ከመቅጠሩ በፊት፣ የኢትዮጵያ ሬድዮ ሴት አንባቢ ነበረው፡፡ የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመሠረት ብዙ ሴቶችን ባያገኝም፣ ሴት አባላት እንዳይኖሩት ግን በመከልከል አልጀመረም፡፡ የንግሥተ ሳባ ተረትም ኢትዮጵያውያን ሴትን ቁንጮ የማድረግ ፍርሐት እንዳይኖርባቸው ያደረገ ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክብረ ነገሥት ከንግሥተ ሳባ በኋላ ሴት ንግሥተ ነገሥት እንዳትሆን ያግዳል፡፡ (?) እነእቴጌ ጣይቱ ቤተ መንግሥቱን የመሩት በንጉሠ ነገሥቱ በኩል ባላቸው ተደማጭነት እንጂ በቀጥታ አይደለም፡፡ ንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ሲሾሙ፣ ሥራው ግን ይሠራ የነበረው በአልጋ ወራሻቸው ተፈሪ መኮንን ነበሩ፡፡ መንበሩ የተሰጣቸው የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል ነው፡፡ በሌሎች ትውፊታዊ ስርዓቶችም ቢሆን ሴቶች የተገለሉ ናቸው፡፡ በገዳ ስርዓት ለምሳሌ ሴቶች የሉበትም፡፡ ይልቁንም ወንዶች በአስተዳደሩ ሲተጉ፣ ሴቶቹ ተፈጥሮን (በአቴቴ) እንዲለማመኑ ነው የተተዉት፡፡ አሁን በ"ዘመናዊቷ" ኢትዮጵያ ደግሞ ችግሩ የተባባሰ ነው፡፡ የሴት መብት ማክበር ላይ ቀድመናቸዋል የምንላቸው አገሮች የትናየት ጥለውን ሲሔዱ እኛ ለምኒስትርነት እና ለአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊነት የምንሾማቸውን ሴቶች ማብቃት እንኳን አቅቶናል፡፡

(አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የፆታ መድልዖ የለም ብሎ የሚያምን ሰው ካለ የእሸቱ ድባቡን ‹ተባእታይ አገዛዝ በኢትዮጵያ› የሚል እና ፆታዊ መድልዖው ምን ያህል ማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር የሰደደ እንደሆነ የሚያሳይ፣ ጥልቅ ጥናት በ20 ብር ገዝቶ ማንበብ ይችላል፡፡)

ፌሚኒዝም ‹ጠላት› ብሎ የፈረጃቸው…

አንዱና ትልቁ ስጋት እየተባለ የሚወራው "ፌሚኒዝም ወንዶችን እንደጠላት ፈርጇል" የሚለው ስጋት ነው፡፡ እርግጥ የሴቶች የመብት እና የዕድል (opportunity) ዕኩልነት ጥያቄ የሚቀርበው ከወንዶች አንፃር ነው፡፡ ዕኩልነት እንዳይሰፍን እንቅፋት የሚፈጥረው ደግሞ አባታዊው ስርዓተ ማኅበር ነው፡፡ ስርዓተ ማኅበሩ ከወንዶች ባልተናነሰ በሴቶችም ነው የቆመው፡፡ ከብዙ ሺሕ ዓመታት ማኅበራዊ ዝግመተ ለውጥ በኋላ ሴቶችም ይሁኑ ወንዶች፣ ስርዓተ ማኅበሩ የወንድ የበላይነት እንዳለበት እንኳ እስከማይረዱበት ሁኔታ ድረስ ሥር ሰዷል፡፡ ፆተኝነት (sexism) ከቋንቋችን አንስቶ እስከ እያንዳንዷ የአኗኗር ዘይቤያችን ድረስ የበለያነትን ማፅኛ መሣሪያ ነው፡፡ የዚህ ሰለባዎች ደግሞ ወንዶችም ሴቶችም ናቸው፡፡ ስለዚህ የፌሚኒዝም የመጀመሪያው ጠላት ስርዓተ ማኅበሩ፣ በተለይምይህን የሚያፀናው ፆተኝነት ነው፡፡

አንድ ምሳሌ እጠቅሳለሁ፡፡ የምዕራባውያን እና የአገራችን የሥም አሰያየም ስርዓትን ስንመለከት ሁለቱም ሴቷን ከነመፈጠሯ ለመዘንጋት ወንዱን ዘላለም ለማኖር የሚተጉ ናቸው፡፡ ፈረንጆች የቤተሰብ ሥም በሚባል ይጠራሉ፣ ሴት ልጅ የአባቷን የቤተሰብ ሥም ትወርስና ትጠራበታለች፤ ትዳር ስትይዝ ደግሞ "አሳዳሪዋ" ባሏ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ በባሏ የቤተሰብ ሥም መጠራት ትጀምራለች፡፡ እንግዲህ ፆተኝነቱ ከመጠሪያ ሥሟ ይጀምራል ማለት ነው፡፡ በአገራችን ደግሞ ልጅ ባባቱ እና በወንድ አያቱ ሥም ይጠራል፡፡ እናቱ በልጇ ሥም ውስጥ ቦታ የላትም፡፡ ሃይማኖቶችም (ክርስትናን እንደምሳሌ ብንወስድ) ሴትን እስከነመፈጠሯ የሚዘነጉበት ግዜ ብዙ ነው፡፡ ኦሪት ዘ ፍጥረት ላይ እከሌ እከሌን ወለደ እያለ ሲዘረዝር ሰዎቹ ሴት ወልደው የማያውቁ ይመስላል፡፡ እስልምናን እንደምሳሌ ስንወስድ በቁርኣን ሥሟ የተጠቀሰችው ብቸኛዋ ሴት መርየም ብቻ ናት፡፡ በሃይማኖት፣ ልማድ እና ባሕል የተሰናሰሉት ፆተኝነቶች ሁሉ የፌሚኒዝም ጠላቶች ናቸው፡፡ ፌሚኒስቶች ጥያቄያቸው ቢለጠጥ ቢለጠጥ ምናልባት ልጅ በአባቱም፣ በእናቱም ሥም ይጠራ፤ ወይም ከሁለት በአንዱ (በልጁ ምርጫ) ይጠራ ሊሉ ይችላሉ፡፡ (ምሳሌ ነው እንጂ እንዲህ ዓይነት ንቅናቄ እስካሁን አልገጠመኝም) ይህ ለወንዱ የቀድሞ ዕድሉን ተሻሚ ስለሚሆን በጠላትነት የተፈረጀ ሊመስለው ይችላል፡፡ (ፌሚኒስቶቹ የቀድሞው በወንድ ሥም መጠራት ቀርቶ በሴት በምንጠራበት ስርዓት ይተካ ብለው ከተከራከሩ፣ ስለሴቶች የበላይነት መስበክ ጀምረዋል ማለት ነው - ይህ ወደፅንፈኛ ፌሚኒስትነት ያሻግረናል፡፡ ግን ‹ፅንፈኝነት› ያልነው አሁን አባታዊው ስርዓት የሚከተለው ስርዓተ ማኅበር ቀጥተኛ ግልባጭ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡)

‹ፅንፈኛ ፌሚኒዝም› አደጋው ምንድን ነው?

‹ፅንፈኛ ፌሚኒዝም› አንዳንዶች ‹የሴቶች የበላይነትን ለመፍጠር የሚደረግ ንቅናቄ ነው› ብለው ይላሉ፣ ሌሎች፣ ‹ፅንፈኛ ፌሚኒዝም ብሎ ነገር የለም፤ ቁርጠኛ ፌሚኒዝም ነው› ብለው ይከራከራሉ፡፡

ብዙዎቹን ፌሚኒስቶች የሚያስማማው ትርጉሙ ‹ፅንፈኛ ፌሚኒዝም› (radical feminism) የሚባለው ፖለቲካን እንደመሣሪያ በመጠቀም (የፖለቲካ ሥልጣን በመያዝ) አሁን ያለውን አባታዊ ስርዓት በሕግ በማስገደድ በፈጣን ሒደት በመቀልበስ የዓለም ስርዓተ ማኅበርን አናውጦ፣ የወንዶች የበላይነትን በማስቆም፣ ወንዶች እና ሴቶች ዕኩል የሚታዩበት ዓለም መፍጠርን ግብ ያደረገ ንቅናቄ ነው፡፡ በግብ ደረጃ ከተራው ፌሚኒዝም የሚለይበት መሥፈርት ባይኖርም አካሔዱ ላይ ልዩነት አለው፡፡ ስኬት ማስመዝገብ ይችላል ወይ የሚለው ምናልባት ያጠራጥራል፡፡

አንዳንድ ‹ፅንፈኛ ፌሚኒስቶች›፣ የፆታ መድልዖን ሲተረጉሙት በመደብ ይለዩታል፤ ‹ወንዶች ጨቋኝ መደብ፣ ሴቶች ተጨቋኝ መደብ ናቸው› በማለት፡፡ መፍትሔው ጨቋኙን መደብ መታገል ይሆናል፡፡ ሴቶች ወንዶችንም ሴቶችንም ጠቅልለው መግዛት ካልጀመሩ ለውጥ እንደማይመጣ የሚናገሩ አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሴትን ያሳንሳል ብለው ያሰቡትን አቀራረብ በመቀየር የሴቷን መጽሐፍ ቅዱስ (Woman's Bible) ያዘጋጁ ሴቶች አሉ፡፡ ባስ ሲል ከወንድ ዕኩል የማያየኝን ሃይማኖት አልቀበልም በሚል ሃይማኖታቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ አሉ፡፡ በወሲብም ላይ ወንድ ከላዬ አይሆንም ከሚሉ ጀምሮ ከወንድ ጋር አልተኛም እስከሚሉ ‹ፅንፈኛ ፌሚኒስቶች› አሉ፡፡

ትልቁ የፌሚኒዝም ተግዳሮት፣ እና ማንኛውንም ፌሚኒዝም በፅንፈኝነት እያስፈረጀ ያሰቸገረው አስተሳሰብ ሴትን እንደተፈጥሮ አሽከር የመመልከት አባዜ ነው፡፡ ሴት ልጅን ለማሞካሸት ሌላ ምክንያት የሌለ ይመስል "ዘጠኝ ወር ማርገዟ" እና "እናትነቷ" ብቻ ነው ሲጠቀስ የሚሰማው፡፡ ይህም ማለት የሴት ልጅ ተግባር ‹መውለድ› እና የሰው ዘርን ማስቀጠል ብቻ ነው የሚል መደምደሚያ በውስጡ አዝሏል፡፡ ተፈጥሮ የእናትነትን ፀጋ፣ ከመምረጥ መብቷ ጋር ነው ለሴት የሰጠቻት፡፡ አባታዊው ስርዓት ሴትን ያለፈቃዷ የተፈጥሮ አሽከር እንድትሆን ይደነግጋል፡፡ ውሎዋም ከልጆቿ ጋር ማጀት ውስጥ መወሰን እንዳለበት ያምናል፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ አንፃር መውለድን በራሷ ምርጫ እንድትወስን የሚታገለው ፌሚኒዝም ሁሌም ‹ፅንፈኛ› ነው፡፡

‹የፌሚኒዝምን ፅንፈኝነት› ጠለቅ ብሎ ላሰበው አስደንጋጭነቱ (ወይም ስጋትነቱ) ምንም ነው፡፡ የሚያስደነግጠው በአባታዊ ስርዓተ ማኅበር የሐሳብ አድማስ (mind-set) ውስጥ ቆመን ስለምናስበው ነው፡፡ ሲጀመር በትህትና ‹ወንድና ሴትን ዕኩል ማኖር እና ማየት› ከሚለው ንግግር ይልቅ ‹የወንዶች የበላይነትን ማፈራረስ› የሚለው ቃል ፅንፈኛ ቢመስልም፣ የሁለቱም ግብ የተንሰራፋውን ፆታዊ መድልዖን ማስቀረት ነው፡፡

የልኂቃን ፌሚኒስቶቹ ሥራ፣ ለገጠር ኮረዳ ምኗ ነው?

ፌሚኒዝምን ፍሬ አልባ እንደሆነ ለማስረዳት ከሚሰጡ ምሳሌዎች ዋነኛው ‹ከሥሙ ጋር ያልተዋወቁትን ሴቶች አልበጀም› የሚለው ትችት ነው፡፡ ሁሉም ፌሚኒስቶች እያንዳንዱን ጓዳ እያንኳኩ፣ እያንዳንዷን ሴት ነጻ ያወጣሉ ብሎ መመኘት የዋህነት ነው፡፡ እያንዳንዷ ፌሚኒስት ራሷን ነጻ ካወጣች፣ እያንዳንዱ ፌሚኒስት ራሱን ከፆተኝነት ነጻ ካወጣ ትልቅ ድል ነው፡፡ የተደራጁት ፌሚኒስቶች የውጤታማነት (effectiveness) ችግር እንዳለባቸው እና መሬት በረገጡ የብዙኃኑ ሴቶች ችግር ላይ ከማተኮር ይልቅ በምናባዊው ርዕየቶ-ዓለማዊ ክርክር ግዜያቸውን እና አቅማቸውን እንደሚያባክኑ ይነገራል፡፡ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን የፌሚኒስቶቹ ድክመት የፌሚኒዝምን አስፈላጊነት አያራክሰውም፡፡

የፌሚኒዝም ንቅናቄ ከገጠር ማጀት እስከ ከተማ ቤተ መንግሥት ድረስ መሆን አለበት፡፡ ልኂቃኑ ሴቶች ፓርላማ እንዲገቡ፣ ምኒስትር ሆነው እንዲሾሙ ጥረት ሲደረግ የገጠር ማጀት ውስጥ ላለች ኮረዳ ቀጥተኛም ባይሆን ተዘዋዋሪ ጥቅሞች አሉት፡፡ ካለችበት እርከን እስከላይኛው ጣሪያ እንደተምሳሌት የምታያት ሴት እና የሚበጃትን ሕግ እንዲወጣ የምትታገልላት ሴት ታገኛለች፡፡ እያንዳንዷ ፌሚኒስት ከሷ የሚጠበቀው ራሷን በአስተሳሰብ እና በኢኮኖሚ ነጻ ማውጣት ነው፡፡ የገጠር ኮረዳዋም ልኂቃኑ ሴቶች ከአባታዊው ስርዓተ ማኅበር ነጻ እያወጡ በመጡ ቀጥር ነጻ የመውጣት ዕድሏ እየሰፋ ይመጣል፡፡

ከዚህ በተረፈ፣ ፌሚኒዝም ሥሙ የሚጎድፈው ያለባሕሪው ነው፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት ሴቶች መጠጥ ቤት ሲያዘወትሩ ወይም በሱስ ሲጠመዱ ፌሚኒዝም ይወቀሳል፡፡ ሴት ልጅ ‹በማጀት መወሰን የለባቸውም› መባሉ ሴቶችን አበላሸ ይባላል፡፡ የነዚህ ችግሮች ሰለባ የሆኑ ብዙ ወንዶች ጉዳይ ግን ተድበስብሶ ያልፋል፡፡ ይህ ትችት በራሱ አባታዊው ስርዓት ፌሚኒዝምን መልሶ ከሚታገልባቸው ሰበብ አስባቦች አንዱ ነው፡፡ ሱሰኝነትን የመሳሰሉ ችግሮች ለወንዶችም ለሴቶችም ችግሮች ናቸው፡፡ "በሴት አያምርም" የሚለው አስተያየት በራሱ ፆተኝነት ነው፡፡

እንደመደምደሚያ፣ የፆታ መድልዖን ለማስቀረት ሴት ልጅ ስትደፈር መቅጣት በቂ አይደለም፤ ሴት ልጅን የመድፈር ሐሳብ የማይመጣለት ወንድ መፍጠርን ይጠይቃል፡፡ ሴት ልጅ ትምህርት ቤት እንደትሔድ መፍቀድ አይበቃም፤ ተመልሳ የቤት ሥራ የምትሠራበት ጊዜ መስጠት ብቻም አይበቃም፤ ከወንድሟ ያነሰች እንደሆነች በቃልም ይሁን በተግባር የምናሳይበትን ፆተኝነት ከቋንቋችንም ይሁን ከባሕላችን ነቅለን መጣል አለብን፡፡

No comments:

Post a Comment